December 2, 2015
(ኢ.ኤም.ኤፍ) የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስተር ፕላን በሚል የሚታወቀው አወዛጋቢ እቅድ በኦሮሚያ የሚገኙ ተማሪዎች ዳግም ለአመጽ እንዲነሳሱ አድርጓል። በአምቦ ዩኒቨርስቲ የተጀመረው ተቃውሞ፣ ወደ ነቀምት ወለጋ ዩኒቨርስቲ፣ ወደ መቱ ኢሉ አባቦር እና ሐረማያ ዩኒቨርስቲ ድረስ ተዛምቷል። በውጤቱም በርካታ ተማሪዎች ተደብድበዋል፤ የታሰሩም አሉ። ተቃውሞ በሚደረግባቸው ቦታዎች ለምሳሌ በአምቦ እና በነቀምት የኔትወርክ መቋረጥ ተስተውሏል።
ማስተር ፕላኑ አዲስ አበባ እና በዙሪያዋ የሚገኙ የኦሮሚያ ዞኖችን በትራንስፖርት እና ንግድ ዘርፍ ለማገናኘት የታቀደ ሲሆን፤ የኦሮሚያ ተማሪዎች ግን፤ “በልማት ሰበብ የኦሮሞ ገበሬዎችን የሚያፈናቅል እቅድ ነው” በማለት ይቃወሙታል። ባለፈው ሳምንት ከህዝቡ ጋር ውይይት ለማድረግ በቡራዩ የተጠራው ስብሰባ በጸጥታ ችግር ምክንያት ተሰርዟል። በሰበታ ተመሳሳይ ስብሰባ ለማድረግ ታቅዶ የነበረውን ህዝባዊ ስብሰባ ለግዜው እንዳይደረግ ተብሏል።
ይህ እቅድ ኦሮሚያን በሚያስተዳድረው ኦህዴድ ውስጥ ጭምር መከፋፈልን ፈጥሯል። ባለፈው ወር የኦህዴድ ማዕከላዊ አባላት በሙሉ እቅዱን መደገፍ ወይም መቃወማቸውን ወይም ማብራሪያ የሚፈልጉ ከሆነ እንዲጠይቁ ከፌዴራል መንግስት ማሳሰቢያ ቀርቦላቸው ነበር። ሆኖም አስተዳዳሪዎቹ ጭምር ማስተር ፕላኑን ሙሉ ለሙሉ የሚቀበሉት አልሆኑም። ገበሬው ከመሬቱ መፈናቀሉ ብቻ ሳይሆን፤ ባህሉ እና ቋንቋውን ጭምር በዚህ አይነት መንገድ ለማጥፋት የሚደረግ ጥረት ነው – በማለት ውስጥ ውስጡን የሚከራከሩ የኦሮሚያ ባለስልጣናት ጭምር መኖራቸውን ውስጥዊ ፍጭቱን የሚያውቁ የቅርብ ምንጮች ለኢ.ኤም.ኤፍ ገልጸዋል።
በፌዴራል መንግስት በኩል አባይ ጸሃዬ ስለማስተር ፕላኑ፤ “ተወደደም ተጠላም ማስተር ፕላኑ ስራ ላይ ይውላል፣ የተገበራል!” ሲሉ በተቃራኒው ደግሞ ኦቦ ለማ መገርሳ፣ የኦሮሚያ ክልል ምክርቤት አፈጉባኤ “ይህ ማስተር ፕላን ጥቅም ቢሰጥም ባይሰጥም ወርቅ የሚታፈስበት እንኳን ቢሆን የኦሮሞ ሕዝብ አልፈልግም ካለ አልፈልግም ማለት ነው።” በማለት ንግግር ሲያደርጉ የኦሮሚያ ምክር ቤት አባላት በጭብጨባ ጭምር ነው ሃሳባቸውን የደገፉት።
ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ልክ እንደ አቶ ለማ መገርሳ የኦሮሚያ ከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው። ትርፉ ግን በኦሮሚያ ፖሊስ መደብደብ ሆኗል።
አሁን “አሸባሪ” ተብሎ በእስር ላይ የሚገኘው በትግራይ የአረና ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ፤ አብርሃ ደስታ በአንድ ወቅት ይሄን በተመለከተ እንዲህ ብሎ ነበር።
“ኢህአዴግ ብሄር መሰረት ባደረገው ፌደራሊዝሙ “ይሄ መሬት የኦሮምያ ነው፣ ነፍጠኞች እንዳይወስዱባቹ ተጠንቀቁ!” እያለ ጥላቻ ሲሰብክ ከርሞ አሁን የኦሮሞ ተወላጆች “የኦሮምያ መሬት የኛ ነው። ለማንም አሳልፈን አንሰጥም!” ሲሉት ግዜ ለምን የኃይል እርምጃ መውሰድ መረጠ? ኢህአዴግ ራሱ የዘራውን ነው እያጨደ ያለው።
የኦሮምያ ጉዳይ አሳሳቢ ነው። መንግስት የኃይል እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥቦ መፍትሔ ቢያፈላልግ መልካም ነው። ጉዳዩ መፍትሔ ካልተበጀለት የብሄር ፈንጂ በተቀበረበት ሀገር ፈንጂው ይፈነዳና ህዝቦችን ሊጎዳ፣ ሀገርን ሊበታትን ይችላል። ከዓመፅ የሚጠቀም የለም፤ በግድያ የቆመ ዓመፅም የለም። ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ምድር የዘራውን የብሄር ፈንጂ በጥንቃቄ ማምከን ካልቻልን ረግጠን፣ አፈንድተን ራሳችንን እንጨርሳለን። በሀገራችን ጉዳይ ሁላችንን ያገባናል። የኃይል እርምጃ ይቁም፤ ነፃነት ይስፈን።” በማለት ሰፊ ትንታኔ አድርጎ ጽፎ እንደነበር ይታወሳል።
ባሌ ሮቤን መደወላቡ ዩንቨርስቲ ውጥረት ላይ ናቸው::የመዳወላቡ ዩንቨርስቲን ከከተማዋ የሚያገናኘው መስመር ታጥሯል::
በባሌ ሮቤ የፌዴራል ፖሊስ እና የአግኣዚ ጦር አባላት በከተማው ደርሰው በመፍሰስ እንዲሁም ከገጠሩ ወደ ከተማው የሚያስገቡ መንገዶችን በመዝጋት ከተማዋን ውጥረት ውስጥ ከተዋታል::የሮቤ መምህራን ኮሌጅን የሁለተኛ ደረጃ እና የመጀመሪያ ደረጃ ትምሕርት ቤቶችን ከበዋል::የመዳወላቡ ዩንቨርስቲ ከከተማው የሚያገናኘው መስመር በወታደሮችኡ ተቆርጦ የታጠረ ሲሆን ወደ ሮቤ ከተማ የሚመጡ የገጠር ነዋሪዎች ክመንገድ እንዲመለሱ ተደርጓል::
በመደወላቡ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች እና በወያኔ ሃይሎች መካከል ግጭት እንደተፈጠረ እየተነገረ ቢገም መረጃዎች እንዳይወጡ ወታደሮቹ አከባቢው በመክበብ ከፍተኛ ችግር እና ውጥረት እንደፈጠሩ የአከባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ::ከሁለት ቀ በፊት የመዳ ውላቡ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች በእራት ከተመገቡ በኋላ ተቃውሞ ያሰሙ የነበረ ቢሆንም በአከባቢው የአገዛዙ የታጠቁ ሃይሎች ስላልነበሩ ተቃውሞው በሰላም ተጀምሮ መጠናአቀቁ ይታወሳል::