(ኢ.ኤም.ኤፍ) ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ምክንያት በጎንደር ማረሚያ ቤት ልላይ የእሳት አደጋ በደረሰበት ወቅት፤ እሳቱን ለማጥፋት የተደረገው ጥረት እምብዛም እንደሆነ የዓካባቢው ሠዎች ገልጸውልናል። በእሳት አደጋው ምክንያት የተቃጠሉ እስረኞች አሉ፤ ያመለጡ እና በጥይት ተደብድበው የተገደሉ ብዙ ናቸው።
የሰሜን ጎንደር አስተዳዳሪ የሆኑት ግዛት አብዩ (ግለሰቡ የብአዴን አባል እና የአካባቢው ፈላጭና ቆራጭ ነው) ከአዘዞ እና ከበለሳ የመከላከያ ሰራዊት እንዲመጣ አስደርገው፤ በእስረኞቹ ላይ ነጻ እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን የጎንደር አካባቢ ምንጮች ገልጸዋል። መትረየስ የተጠመደባቸው የመከላከያ መኪኖች በጎንደር ከተማ በብዛት ይታያሉ። በዋና ዋና መንገዶች ላይ የታጠቁ ወታደሮች ይታያሉ። ህዝቡ ከቦታ ወደ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ የማገድ ስራ ላይ ተሰማርተው እንደዋሉ ነው – ምንጮቻችን የገለጹት። አልፎ አልፎ ነዋሪው እና ታጣቂዎቹ የተጋጩበት አጋጣሚም ተከስቷል።
ምን ያህል ሰው ከእስር እንዳመለጠ፣ ምን ያህሉ እንደቆሰለ እና እንደሞተ በትክክል የተጣራ መረጃ አላገኘንም። ሆኖም በጎንደር ከተማ አልፎ አልፎ የተኩስ ድምጽ እየተሰማ እና መረጋጋት የሌለ መሆኑን ነው የአካባቢው ምንጮች በተለይ ለኢ.ኤም.ኤፍ የገለጹት።