ወያኔ ለሥልጣን ከበቃበት ግዜ አንስቶ ከተቃውሞ ነጻ የሆነበት ግዜ የለም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ድርጅቱንም ሆነ በአመራር ላይ የነበሩና ያሉ ግለሰቦችን በመጥላት ሳይሆን ለዮሐንስ ቤተ መንግሥት ታግሎ ለምንይልህ ቤተ መንግሥት ሲበቃ፤ ከፋኖነት ወደ መንግስትነት ሲለወጥ የዓላማም ሆነ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማድረግ ባለመቻሉና ኢትዮጵያን በማጥፋት እቅዱ በመቀጠሉ ነው፡፡

የሚካሄደው ተቃውሞ ግን መልክና ቅርጽ የሌለው ቀጣይና ተደጋጋፊ ያልሆነ ውል አልባ በመሆኑ መስዋዕትነት የሚያስከፍል እንጂ የወያኔን ሥልጣን የሚነቀንቅ ለመሆን አልቻለም፡፡ በየትኛውም የህብረተሰብ ክፍልና በማናቸውም የሀገሪቱ አካባቢ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምክንያቱ ወያኔ ሆኖ እያለ ጥቃቱ የደረሰበት ወይንም ቀድሞ በመንቃት ጥቃቱን ለመከላከል አንዱ አካባቢ ወይንም የህብረተሰብ ክፍል ተቃውሞ ሲያሰማና የጥይት ምላሽ ሲለገሰው ሌላው አካባቢ ወይንም የህብረተስብ ክፍል በእኔ ካልደረሰ የሚል በሚመስል ሁኔታ በዝምታ ይመለከታል፡፡እሱ ተረኛ ሲሆን ደግሞ ሌላኛው ለእኔ ግዜ ልትረዳኝ ቀርቶ ቢያንስ መች ጮህክልኝ በሚል አይነት በል ብቻህን ተወጣው ብሎ በዝምታ ያያል ያዳምጣል፡፡ ይህ መልክ አልባ ተቃውሞም ወያኔ በየተራ በተናጠል ዜጎችን በማሰር በማሰደድ በመግደል ከጨዋታ ውጪ እያደረገ ተደላድሎ ለመኖር አስችሎታል፡፡

ሌላው ቢቀር የጥያቄው ምንነትና የጠያቂዎቹ ማንነት ሳይታይ ወያኔ ለጥያቄው የሚሰጠው ኢ- ሰብአዊ ኢ- ሕጋዊና ኢ- ዴሞክራሲያዊ ምላሽ የወያኔን አገዛዝ የማይቀበሉትን በሙሉ (የተደራጁም ሆኑ ያልተደራጁ) በአንድ ድምጽ እንዲጮሁና በአንድ መስመር እንዲሰለፉ ባበቃቸው ነበር፡፡አንድ የህብረተሰብ ክፍል የሚያነሳውን ጥያቄ ሌላው ላይደግፈው ይችላል፡፡ የአንድ አካባቢ ነዋሪዎች ጥያቄ በሌላ አካባቢ ለሚኖሩ የሚጎረብጥ ሊሆን ይችላል፤አንዱ የፖለቲካ ድርጅት የሚያራምደው አቋም ለሌላው የማይጥመው ሊሆን ይችላል፡፡ስለሆነም ለጥያቄው መልስ ማግኘት ለአቋሙ ግብ መምታት ላይተባበር ይችላል፡፡ እንደውም አለመተባበር ብቻ ሳይሆን ጥያቄውን ሊቃወም አቋሙን ሊያወግዝ ይችላል፡፡

ነገር ግን የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ መብት በሆነውና ወያኔም በህገ መንስቱ ውስጥ ባሰፈረው ሀሳብን የመግለጽ፤ተቃውሞን በሰላማዊ መንገድ የመግለጽ፤ ያለማንም ጣልቃ ገብነት በነጻነት የመደራጀት ወዘተ መብቶቹን ተጠቅሞ ግለሰብም ይሁን ህብረተሰብ በነጠላም ይሁን በቡድን ጥያቄዎችን ሲያቀርብ አቋሙን ሲያራምድ ተቃውሞውን ሲያሰማ የሚሰጠው ምላሽና ጥይትና ዱላ ሲሆን ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆንና ለሰብአዊ መብቶች መከበር እታገላለሁ የሚል ድርጅትም ሆነ ግለሰብ በእኔ ካደረሰ ብሎ የዳር ተመልካች በመሆን በዝምታ ሊያልፈው የሚገባ አይደለም፡፡
የእኛ የሀያ አራት አመታት ተቃውሞ ግን መልክ የለሽ ውል አልባ በመሆኑ ሁሉ በየራሱ አጥር ዙሪያ የእኔ በሚላቸው ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ በመመርኮዝ በተናጠል ከመጮህ ሊያልፍ አልቻለም፡፡ እንዲህም በመሆኑ በየጊዜው የሚነሱ ተቃውሞዎች እስር ድብደባና ሞት ከማስከተል አልፈው ውጤት ማስመዝገብ አልቻሉም፡፡ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በወያኔ ላይ የሚያካሂዱዋቸው ተቃውሞዎች በእውቀት ላይ ተመስርተው ዘላቂ ዓላማ አንግበው በእቅድ የሚመሩ ሳይሆን በወቅታዊ ትኩሳት የሚቀሰቀሱና በስሜት የሚካሄዱ ነው የሚመስለው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጸሙ ህገ ወጥ ድርጊቶች ቢያንስ በሁለት ምክንያት ከፈጻሚው ወገን ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ የሚመለከቱና በአንድ ድምጽ እንዲጮህ የሚያደርጉት ነበሩ፡፡ ግን ትናንትም አልሆነም ዛሬም የለም፤ወደፊትም የሚሆን አይመስልም፡፡አንደኛ ድርጊቱ ህገወጥና ኢሰብአዊ በመሆኑ፤ሁለት ወያኔ ሌሎችን ለመወንጀያነት የሚጠቀምበትን ሕገ መንግሥት የሚጥስ በመሆኑ ሶስተኛ እንጨምር ካልን የድርጊቱ ፈጻሚ ሁሉም የሚቃወሙት ወያኔ በመሆኑና ጥቃቱ አይነትና ዘዴውን እየቀያየረ በሁሉም ላይ የሚፈጸም በመሆኑ ነግ በእኔ በማለት በየትኛውም አካባቢ በማናቸውም ዜጋ ላይ ሲፈጸም የፖለቲካ አመለካከት የአደረጃት ልዩነት ሀይማኖትም ሆነ ጎሳ ሳይለይ ሁሉም መቃወም ነበረበት፣ ግን የለም፡፡

በርግጥ የተቃውሞአችን መሰረቱ የህግ የበላይነት መረጋገጥ፣የሰብአዊት መብት መከበር በጥቅሉ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን ከሆነ ኢሰብአዊና ሕገ ወጥ ድርጊት የተፈጸመበት ግለሰብም ይሁን ቡድን የምንወደወው ይሁን የማንወደው ዓላማ ድርጊቱን የምንደግፈው ይሁን የምንቃወመው የተፈጸመበትን ድርጊት ከማውገዝና ከመቃወም የሚያግደን ሊሆን አይገባም፡፡ ለድርጊቱ መፈጸም ሰበብ/ ምክንያት የሆነው ጉዳይ ምንነትም ጥያቄ ባነሱና ተቃውሞ ባሰሙ ግለሰቦችም ይሁን ቡድኖች ላይ የተፈጸመን ህገ ወጥና ኢ-ሰብአዊና ድርጊት ከማውገዝና ከመቃወም ለመቆጠብ ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ ትግላችን ትናናሽ ፍጎቶቻንን ለማሳካት ካልሆነ በስተቀር ማንም ይፈጽመው በማንም ላይም ይፈጸም ሕገ ወጥ የሆኑ ኢ-ሰበአዊና ኢ- ዴሞክራሲያዊ ድርጊቶችን ልናወግዝና ልንቃወም ዳግም እንዳይፈጸምም በተባበረ ኃይል ልንታገለው ነው የሚገባው፡፡

በህብረተሰብ ደረጃ ቀርቶ ፕሮግራም ነድፈው ድርጅት መስርተው መንግስት መሆንን አልመው የሚታገሉት ፖለቲከኞችም (ብዙዎቹ በቁጥር ብቻ ነው ያሉት)አንዳቸው በሌላው ላይ የሚፈጸምን ሕገ ወጥ ድርጊት ሲያወግዙም ሲቃወሙም አይሰሙ፡፡ ከተግባራቸው አንደምናየው እነርሱን ለተቃውሞ የሚያነሳሳቸው የተፈጸመው ድርጊት ሕገ ወጥነትና ኢሰብአዊነት ሳይሆን የተፈጸመበት ግለሰብ፣ ቡድን ወይንም አካባቢ ለእነርሱ ያለው ቅርበት ወይንም ግንኑነት ነው፡፡ የአንደኛው ፓርቲ አባል ሲገደል ሌሎቹ ዝም፤የአንደኛው ፓርቲ አመራር ሲታሰር ሌሎቹ ዝም፣ ጥቃቱ ግን ሁሉንም በየተራ ያዳርሳል፡፡( ለወያኔ ካደሩት በስተቀር፡)

ፖለቲከኞቻችን የሚታገሉት ቢሳካላቸው ቤተ መንግሥት ለመግባት ብቻ ሳይሆን ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ ለሰብአዊ መብት መከበር ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት እውን መሆን ካልሆነ ነገራችን ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጡ ይሉት ይሆናል፡፡ ከሆነ ደግሞ የሚቃወሙት ኃይል በሌላ ተቀዋሚ ላይ፣እነርሱ እንወክለዋለን ከሚሉት የሀገሪቱ ክፍል ውጪ በሚኖሩ ዜጎች ላይ በጥቅሉ በሀገሪቱ ውስጥ የሚፈጽማቸውን ሕገ ወጥ ተግባራት በሙሉ መቃወም ብሎም መታገል ይኖርባቸዋል፡፡ እንደውም ይህ ብቻ አይደለም ወያኔ በራሱ አባሎችም ላይ ሕገ ወጥና ኢ-ሰብአዊ የሆነ ድርጊት ከፈጸመ መቃወምና ማውገዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምክንያቱም የተቃውሞአቸው መሰረት የማውገዛቸውም ምክንያት የሚሆነው የፈጻሚውም ሆነ የተፈጸመበት ግለሰብ ወይንም ቡድን ማንነት ሳይሆን የተፈጸመው ድርጊት ህገ ወጥነትና ኢሰብአዊነት ነውና፡፡
ሰሞኑን ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ ኦሮምያን እያጥለቀለቀ ያለ የተማሪዎች ተቃውሞ እያየን እየሰማን ነው፡፡ ለተማሪዎቹ እንቅስቃሴ ከወያኔ በኩል የተሰጠው ምላሽ ያው የሚታወቀው የወያኔ ተግባር የሆነው በየግቢያቸው ውስጥ አያፈኑ መደብደብ ማሰርና መግደል ነው፡፡ ይህን የተማሪዎች ተቃውሞና የተሰጣቸውን ምላሽ ልዩ የሚያደርገው ጠቅላይ ምኒስትር ሀይለማሪያምደሳለኝ ኢትዮጵያ ሀሳብን በነጻነት መግለጽ ተቃውሞን በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ የሚቻልባት ሀገር በመሆኗ ብረት ያነሱ ሀይሎች ብረታውን ጥለው ተቃውሞአቸውን በሰላማዊ መንገድ ቢያራምዱ ይበጃቸዋል በማለት ምክር መለገሳቸውን በሰማን ማግስት መሆኑ ነው፡፡

ፈጣሪ ያሳያችሁ፣አዲስ አበባን ለማስፋፋት የታለመውን ማስተር ፕላን ተቃውመው ሰለፍ ለማድረግ ባሰቡ ተማሪዎች ላይ ጥይት የሚተኩሰውና የሚገድለው የህውኃት አገዛዝ ስልጣን የሚቀናቀኑትን ፖለቲከኞች በሰላማዊ መንገድ ሲያስተናግድ ፡፡ (በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ሀምሳ ምናን ፓርዎች አሉ አይደለም ወይ እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ) አቶ ሀይለማሪም በወያኔዎች እየተገፉ ያልሆነና የማይሆን ነገር ይናገራሉ፣ ውሉ ሳያድር ይጋለጣሉ፣ አንዴ ገብተውበታልና ከአፈርኩ አይመልሰኝ በማለትም ደግሞ ሌላ ውሸት ይናገራሉ፡አይ አለመታደል፡ነገ ደግሞ ምን ይሉን ይሆን!
ለመሆኑ የኦሮምያ መስተዳድር መቀመጫ አዲስ አበባ ይሁን ብለው የጠየቁ ሰዎችን ያሰረ ያንገላታ፣ (የሚጫና ቱለማ ማህበር አመራሮችን ያስታውሷል) በምርጫ 97 ቅንጅት አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ ሲያሸንፍ ተጣድፎ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ነች የሚል ሕግ ያወጣ፣ ቅንጅቶችን ለተመረጡበት መንግሥትነት ሳይሆን ለቃሊቲ ወህኒ ቤት ከዳረገ በኋላ ሕጉን ሽሮ ኦህዴድን ከአዲስ አበባ ያባረረ፣ ወያኔ ለአዲስ አበባም ሆነ ለኦሮምያ የሚጠቅም ነገር ያስባል ማለት አዙሮ ማየት አለመቻል ነው፡፡
ነገርን ነገር ያነሳዋል አንዲሉ ሆኖ ሌላ ጉዳይ ውስጥ ገባሁ፡፡ተማሪዎቹ ያነሱትን ተቃውሞ መደገፍ አለመደገፍ ብሎም መቃወም አንድ ነገር ነው፡፡ በተማሪዎቹ ላይ የተፈጸመውን ህገ ወጥና ኢሰብአዊ ድርጊት በዝምታ ማለፍ ግን ከማንም ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ አይደለም፡ ድርጊቱን በማውገዝ መግለጫ ያወጣው በፕ/ር መረራ የሚመራው ፓርቲ ብቻ ነው፡፡ ፓርቲው ስሙም ዓላማውም በኦሮምያ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ጉዳዩ በቀጥታ ያገባዋልና በተማሪዎቹ ላይ የተፈጸመውን ሕገ ወጥ ድርጊት በማውገዝ ብቻ ሳይወሰን ማስተር ፕላኑንም በመቃወም ነው መግለጫ ያወጣው፡፡
ሌሎች ግን ኦፌኮ አባል የሆነበትን መድረክ ጨምሮ ማስተር ፕላኑን ማውገዝ ባይጠበቅባቸውም ተቃውሞአቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመግለጽ የተነሱ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ህገ ወጥና ኢሰብአዊ ድርጊት ማውገዝ ነበረባቸው፡፡ በየግዜው ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ህይወት ሰዋዊ ባህርይ በራቃቸው አረመኔዎች እንደ አልባሌ በየሜዳው ሲወድቅ ለጉዳዩ ቅርበት አለን የሚሉ ወገኖች/ ድርጅቶች ድምጽ ብቻ ነው የሚሰማው፡፡ ኢትዮጵያውያን ላይ በተፈጸመ ድርጊት ኢትዮጵያውያን ዝም ብለው አኣለም አቀፍ ድርጅቶች ተቃውሞ ሲያሰሙ መስማት አያሳፍርም ጥያቄ ላይስ አይጥልም፤ ምን ጉዶች ነን፡፡ የእስካሁኑ አልፏል አሁን ግን በዚህ አንድ ተብሎ ሕገ ወጥና ኢሰብአዊ ድርጊትን ሁሉም የማውገዝና የመታገል ጅማሮ ቢያሳዩ አንድ ርምጃ ነበር ፡፡ ይህን የሚያደርጉት ደግሞ ለይስሙላ ታውመናል አውግዘናል ለማለት ሳይሆን ከልብ አምነውበት ሊሆን ይገባል፡፡

በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም ማስተር ፕላኑን በሚመለከት ያላቸው የሀሳብ አንድነትም ሆነ ልዩነት ጥያቄ ውስጥ ሳይገባ በመሰሎቻቸው ላይ የተፈጸመውን ኢሰብአዊና ሕገ ወጥ ድርጊት ማውገዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ነገ እነርሱም ለተቃውሞ የሚያስወጣ የእኔ የሚሉት ጉዳይ ገጥሞአቸው ( የምግብ ጉዳይ፤የመማር ማስተማሩ ጉዳይ ወዘተ ሊሆን ይችላል) ለተቃውሞ ቢንቀሳቀሱ የሚገጥማቸው በተመሳሳይ ዱላና ጥይት መሆኑን በማሰብ ሌላ ሌላው ቢቀር ነግ በእኔ በሚል መንፈስ ዛሬ በኦሮምያ ክልል በሚገኙ ዮኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን ሕገ ወጥ ድርጊት ማውገዝና የታሰሩ እንዲፈቱ፤ የተገደሉ እንዲታወቁና ገዳዮች ለፍርድ አንዲቀርቡ መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡፡

ተቃውሞው እንዲህ መደጋገፍ መልክ መያዝና ውል ማበጀት ካልቻለ ሁሉም የእኔ የሚለውን ጉዳይ አንጠልጥሎ ለተቃውሞ ሲነሳ ድብደባ እስርና ሞትን እያሰተናገደ ይቀጥላል፡፡ይህ ደግሞ የወያኔ የከፋፍሎ መግዛት እቅድ ውጤት በመሆኑ በወያኔ መበለጣችንንና ለግዞት የተመቻችን መሆናችንን ያሳያል፡፡ በአንዱ የሀገራችን ክፍል ወያኔ ያሻውን ሲፈጽም ሌላው የእኔ ጉዳይ አይደልም ካለ፤በአንድ ብሄረሰብ ላይ ጥቃት ሲፈጸም ሌሎች ብሄረሰቦች የሱ ጉዳይ ለእኛ ምናችን ነው ካሉ፤የኦሮምያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ግድያ ለሌላው ኢትዮጵያዊ የማያስቆጣ ከሆነ፤ጎንደር ላይ የተፈጸመው እስረኞች ከእሳት ሲሸሹ በጥይት መፍጀት የሚያስቆጣው አማራውን ብቻ ከሆነ፤ ወዘተ የመከፋፈሉ ሊቅ አቶ መለስ የአክሱም ሀውልት ለወላይታው ምኑ ነው በማለት የዘሩት ፍሬ በሚገባ አፍርቷል ማለት ነው፡፡

Leave a Reply