የማለዳ ወግ…. የዛሬው ደም የነገ እዳችሁ ሆኖ ይፋረዳችኋል ! =====================================
* ከጎንደር ባዕታ ወህኒ እሰከ ኦሮሚያ ተማሪዎች
የጎንደር የባዕታ ወህኒ ቤት መቃጠሉን ተከትሎ ሰው ቆስሏል ፣ ሰው ሞቷል … የጎንደር ከተማ ነዋሪ ባዕታ ወህኒ ቤት እያለ በሚጠራው ማረሚያ ቤት በተከሰተ የእሳት አደጋ ከ17 ሰዎች በላይ ሰዎች መሞታቸውን የነገሩን የመንግሥት የሚዲያ ተቋማት ከቀናት በፊት “አንድም ሰው የሞተ የለም !” ብለው አላግጠዋል ፣ ዛሬ ነገሩ ተቀያይሮ የሟቾቹን ቁጥር 17 ብለው ነግረውናል ። ፖሊስ ከ17ቱ መካከል 1 ታራሚ ለማምለጥ ሲል በፖሊስ መግደሉን ቢያምንም የቀሩት ” በመጨናነቅና በግፊት ሞቱ !” ብሎናል! ዳሩ ግን ሰው ውስጥ ውስጡን ከሰማ በኋላ የተሰጠው የመንግስት መግለጫ የተዋጠለት አለ ለማለት አልደፍርም !
ከእሳት አደጋው የተረፉት ታራሚ እስረኞች ከተቃጠለው የባዕታ ወህኒ ወደ አንገረብ ወንዝ አካባቢ ወዳለው አዲሱ እስር ቤት የተላለፉት መሆኑ ሲገለጽ ፣ በአዲሱ ማረሚያ ቤት በእሥረኞችም አካባቢ የተረጋጋ ነገር አይሰማም ! ቃጠሎው ተነስቶ ሁከት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በርካታ ታራሚዎች አድራሻ እንዳልተገኘ ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ ። በጎንደር የባዕታ ወህኒ ቃጠሎን ተከትሎ በተሰራው ስራ ሰው አዝኗል ፣ ተናዷል ፣ በግኗል …

በኦሮሚያ ክልልም በተማሪዎች በተቀሰቀሰውን አመጽ ከአንድ ጫፍ ተጀምሮ ወደ ሌላ ጫፍ እየተስፋፋ ሲሄድ ተቃውሞውን ለማብረድ የጸጥታ ኃይሎች ወሰዱት እየተባለ ባለው እርምጃ የሰው አካል ፣ ጎድሏል ፣ ንብረት ወድሟል ፣ የሰው ህይወት ተቀጥ ፏል ! ወሬው መሰማት ከተጀመረበት ቀን አንስቶ በማህበራዊ ድረ ገጾች በምስል ተደግፎ በመሰራጨት ላይ ያለው የተጎጅዎች ምስል እያሳቀቀን ይገኛል … አዝነናል
ሰው በድርቅ ባንዱ የሐገር ጫፍ ለከፋ አደጋ ተዳርጎ ባለበት በዚህ የከፋ ቀን ድርቅ ባልነካው ክፍል ፖለቲካዊ ከረሃቡ የበለጠ እየጎዳን ነው ! የሀገሬ ሰው በተፈጥሮም ህይዎቱ ከጉስቁልና ፈቀቅ አልል ብሏል ፣ ያንድ ሰሞንን ድርቅ በ25 ዓመት በተገነባው ሰላምና እድገት መግፋት ተስኖን ስንንከላዎስ ጉድ እየታየ ነው። ከፊውዳላዊ አስተዳደር እስከ ሸላሚ ደርግና ዲሞክራሲያዊው ባለመርህ ኢህአዴግ በዘባተሎ ፖለቲካ ተጠልፈን እንዲህ ሳይረጋ ዜጋውም ሳይደላው ፖለቲካው የንጹሃን ደም እየተገበረበት እነሆ እስከዛሬ ቀጥሏል ! ትናንትም ከጃንሆይ እስከ ደርግ ዛሬም ከህዎሃት ኢህአዴግ ያለው ረዥም ጌዜ አላስተምረን ብሎ እየሆነ ያለው በጣም ጠልቆ አሳዝኖኛል !
መንግሥት ማናቸውንም ዓይነት ሰላማዊ ተቃውሞን በኃይል ለመፍታት ሲሞክር የሚገፋው ወዳላስፈላጊ የከፋ አመጽና ቂም እንጅ የሚፈይደው ጠቀሜታ ፣ የሚያገኘው ጥቅም የለውም ። ከሚንቀለቀል እሳት ሊያመልጥ የሚሸሽን በህግ ጥላ ስር የነበረን ታራሚ በጥይት መቁላት ፍትሓዊነት አለው ማለት አይቻልም ፣ ያሻውን ምክንያት ይሰጠው ተማሪ ተቃውሞ አሰማ ተብሎ በባሩድ አረር የማቃጠል፣ የመቁላት ተገቢነት ምንም ምክንያት ይሰጠው ሕጋዊነቱ ተቀባይ የለውም !
ኢህአዴግ በርሃ ላይ በቁምጣ እያለ ሰላማዊ ተቃውሞ በኃይል ለመግታት ሲሞከር ደርግን ያወግዝ ነበረ ፣ ዛሬ እርሱ ሥልጣን ሲጨብጥ ግን በኃይል የነዋሪውን ድምጽ ለማፈን የተውሸከሸከ ምክንያት ይሰጥ ለምዷል ፣ የብዙዎችን ተቃውሞ ጥቂት ብሎ እያኮሰሰ ነገር መሸፋፈን ቀዳሚ ተግባር አድርጎታል! ይህ መሰሉ ያሰለቸን አካሄድ መቆም አለበት ፣ በንጹሃን ላይ የሚወስደውን የኃይል እርምጃ ማቆም አለብት ! መንግሥት ጉዳዩን በኃይል ለመፍታት ከመሞከር ነገሮችን በሆደ ሰፊነት ሊመለከታቸው ይገባል !
” ጉልበት አለኝ ” ተብሎ በመታበይ በዜጎች ላይ ግፍ መስራት ተገቢ አይደለም ። ይልቁንም ሃገራችን ወደ ለየለት የዘር ጥላቻ ማዕበል አንዳትግባ ጥንቃቄ ያለው ኃላፊነት የሚጠይቅ ስራ መሰራት አለበት! ጉዳዩ እንዲህ ከቀጠለ ወደ ሌላ የስቃይ ማዐጥ እንዳትጓዝ ስጋት አለኝ ! ጉልበተኞች ጉልበት የከዳቻው ቀን ከሰሩት ሁሉ ግፍ ወደ ፍትህ አካላት ቀርበው እንደሚጠየቁበት ልብ ሊሉ ይገኛል ! ግፈኞች ሆይ የዛሬው ደም የነገ እዳችሁ ሆኖ ይፋረዳችኋል !
ኢትዮጵያ ለዘልአለም ትኑር !
ነቢዩ ሲራክ
ህዳር 24 ቀን 2008 ዓም


