ችግሩ ማስተር ፕላኑ ሳይሆን የመሬት ፖሊሲው ነው – ግርማ ካሳ
ቶኩማ ለቢሊሱማ
ስለ አዲስ አበባ ማስተር ፕላን ብዙ ይባላል። “SAY NO TO THE MASTER PLAN “ የሚል የተጻፈበት ፕሮፋይል ሰዎች ሲለጥፉ እያየን ነው። ሰዎች ማስተር ፕላኑ ለገበሬዎች መፈናቀል ምክንያት ነው ይላሉ። እኔ አልስማም። ማስተር ፕላኑ ጋር በመርህ ደረጃ ችግር አለ ብዬ አላስብም።
በመጀመሪያ ደረጃ ማስተር ፕላኑን ኖረም አልኖረም የአዲስ አበባ ድሆች እና በአዲስ አበበ ዙሪያ ያሉ ገበሬዎች ላለፉት 24 አመታት ብቻ ሳይሆን በደርግም ጊዜ ሲፈናቀሉ ነበር። የነዚህን ወገኖች መፈናቀል ያመጣው ማስተር ፕላኑ አይደለም። በአገሪቷ የተዘረጋው የመሬት ፖሊሲና የተበላሸው፣ ጥቂት ሰዎችን ብቻ እየጠቀመ ያለው፣ ግፈኛው የፖለቲካ ስርአት ነው። “ማስተር ፕላኑ ተሰርዟል” ቢባልም እንኳን ገበሬዎች መፈናቀላቸው አይቀርም። መሰረታዊ የፖለቲካ ለዉጥ እስካልመጣ ድረስ።
ይሄን ስል የፖለቲካና የመሬት ፖሊሲ ለዉጥ ከመጣ ገበሬዎች ከሚያርሱበት መሬት አይነሱም ማለት አይደለም። ይነሳሉ። ግን እነርሱን በጠቀመ መልኩ ነው የሚሆነው።
እንደሚታወቀው አዲስ አበባ አካባቢ ያሉ ቦታዎች በጣም ተፈላጊ ናችው። በዚያ ረገድ ችግር ሊኖረን አይገባም። ችግሩ ያለው ሌላ ቦታ ነው። ገበሬዉ በመሬቱ ላይ ያርሳል እንጂ የመሬቱ ባለቤት አይደለም። በመሆኑም የመንግስት ባለሥልጣናት፣ ለምሳሌ አንድ ሺህ ብር ካሳ ይሰጡትና መሬቱን በኃይል ይወስዱበታል። አንድ ሺህ ብሯ ወዲያው ታልቃለች። ገበሬው በከተማ ለማኝ ይሆናል። ባለስልጣናቱ የዚህን ገበሬ መሬት በ50 ሺህ ብር ሊዝ ያደርጉታል። በቀላሉ 49 ሺህ ብር አገኙ ማለት ነው። ትልቅ ዘረፍ!!!
ገበሬዉ የመሬት ባለቤት ቢሆን ኖሮ፣ በሌሎች የሰለጠኑ አገሮች እንዳለው፣ ለመንግስት እንበል 5 ሺህ ብር (10%) ግብር ቢከፈል፣ ወደ 45 ሺህ ብር ትርፍ ያገኛል። በዚህ ገንዘብ ከአዲስ አበባ ራቅ ብሎ ፣ ከሸጠው መሬት 4፣ 5 እጥፍ የሚሆን ሌላ መሬት ሊገዛ ይችላል። መሬቱን በመሸጡ የበለጠ ይከብራል።
እንግዲህ የችግሩ ዋና ምንጭ ላይ ማተኮር ይኖርብናል። በገበሬዎች ላይ የሚደርሰው ግፍ እንዲቆም ዜጎች የመሬት ባለቤት እንዲሆኑ ፣ የመሬት ፖሊሲው መለወጥ አለበት። “SAY NO TO THE MASTER PLAN “ የሚለው ሳይሆን “መሬት ላራሹ” የሚል መፈክር ነው ይዘን መነሳት ያለበት። የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን ለመቃወም ገበሬዎችን እንደ ሰበብ ማቅረቡ አይያስኬድም። ለገበሬው ካሰብን ገበሬው የሚያርስበት መሬት ብቸኛ ባለቤት እንዲሆን ትግል ይጀመር።
የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን፣ በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በትራንስፖርት ከአዲስ አበባ ዉጭ ያሉት እና አዲስ አበባ የሚያስተሳሰር ነው። ከአዲስ አበባ አልፎ ወደ ሌሎች ከተሞች የሚያደርሱ መንገዶች ይሰራሉ። በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞች ከምንም በላይ ለአዲስ አበባ ቅርብ በመሆናቸው ይጠቀማሉ እንጂ አይጎዱም።
እርግጥ ነው ይህን የንግድና የኢኮኖሚ መተሳሰር አክራሪዎችንና ዘረኞችን አያስደስትም። ሌሎች ወደ ሰበታ፣ ወደ ቡራዩ መጥተው ሲኖሩ ይክፋቸዋል። ተወረርን ይላሉ። እንግዲህ የበርሊንን ግድብ አይነት ሰርተው፣ ከነርሱ ብሄረሰብ ዉጭ ናቸው የሚሉትን ሰዉን ካላስቆሙት በቀር፣ በአዲስ አበባ አካባቢ ያሉ ቦታዎች ነዋሪዎቻቸው መጨመሩ አይቀሬ ነው።ይሄ ደግሞ ማስተር ፕላኑ ኖረም አልኖረም እየሆነ ያለ ክስተት ነው።
እንግዲህ ለኦሮሞ ተማሪዎችና ልሂቃንን ጥሪ አቀርባለሁ። የፖለቲካ ልዩነቶች አሉን። አሁን ያለውን በቋንቋ ላይ የተመሰረተ የፌዴራል አወቃቀር ብዙዎቻችን አጥብቀን እንቃወመዋለን። እነርሱ ይደግፉታል። የሐሳብ ልዩንት መኖሩ ችግር የለዉም። ግን ቢያንስ ልዩነቶቻችን እደተጠበቁ፣ ለምን ሁላችንም በሚያስማሙ ነጥቦች ዙሪያ ትግላችንን አናቀናጀም ? ለምን ኦፌኮ ከነ ሰማያዊ፣ መኢአድ ..ጋር ለነጻነት የሚደረግ የጋራ ግብረ ኃይል አቋቁሞ እንቅስቃሴ አያደረግም፣ በምርጫ ጊዜና ተማሪዎች ሲገደሉ መግለጫ ከማወጣት ?
አገዛዙ እየገደለና እያረደ ያለው ሁሉንም ነው። ወለጋ ደም ሲፈስ፣ ጎንደርም ደም ፈሷል። እነ ኦልባና ለሌሳን ሽብርተኞች ብሎ በወህኒ ሲያንገላታ፣ እነ አንዱዋለም አራጌን ሽብርተኛ ብሎ አስሮ እያሰቃየ ነው። በወሎ ፣ በትግራይ ህዝቡ በድርቅና በረሃብ ሲመታ፣ በቦረና፣ በሃረርጌም እንደዚሁ ወገኖቻችን እየተሰቃዩ ነው። ሁላችንም፣ ያለብን ችግር ተመሳሳይ ነው። “እኛ እና እናንተ” የሚል ፖለቲካ. “የኦሮሞ መሬት፣ የአማራ መሬት …” የሚለው ዘረኛ አስተሳሰባችንን አስወግደን፣ “ሁሉም የኢትዮጵያ መሬት የሁሉም ነው። የሁላችንም ጥያቄ የመብትና የነጻነት ጥያቄ ነው” ብለን በጋር እንነሳ እላለሁ።
ማንኛውም ዜጋ ከቤቱ፣ ፤ ከእርሻው መፈናቀል የለበትም። በልማት ስም ጥቂቶችን ሃብታም ብዙሃኑን ድሃ የሚያደርገን የጭቆና ስርዓት ማብቃት አለበት ። የመሬት ፖሊሲው ተቀይሮ፣ የገበሬዉ የመሬቱ ባለቤት መረጋገጥ መረጋገጥ አለበት። ማንኛውም ዜጋ በፈለገው ጉዳይ ላይ ሰልፍ መዉጣት፣ ተቃዉሞ ማሰማት መቻል አለበት። የችግራችን ሁሉ ምንጭ የፖለቲክ ስርዓቱ ነው። ይህ ሥርዓት ደግሞ ትልቁ መሳሪያው እኛን በዘር መከፋፈሉ መቻሉ ነው።፡
በመሆኑም ቶኩማ(አንድነት) ለቢሊሱማ(ነጻነት) እላለሁ። ያለ ቶኩማ ቢሊሱማ የለም። ቶኩማ ደግሞ የኦሮሞዎች ቶኩማ ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያዊያን ሁሉ ቶኩማ ነው የሚያስፈልገው። መንዲ.፣ አምቦ የመሳሰሉት ትናንሽ ከተሞች ተቃዉሞ ቢነሳ አገዛዙ በቀላሉ ይቆጣጠረዋል። ተቃዉሞ ከተነሳ የግድ ወደ ትላልቅ ከተሞች መዞር አለበት። የባር ዳር፣ የአዲስ አበባ፣ የአዳማ ፣ የአዋሳ ፣ የድሬዳዋ ..ሕዝብ መነሳት አለበት።፡ የኦሮሞ ብሄረተኞች በትላልቅ ከተማ ቁጥራቸው እጅግ በጣም ትንሽ መሆኑም ደግሞ ይታወቃል። የኦሮሞ ልሂቃን፣ ይሄንን ተረድተው ፣ በኦሮሞ ብሄረተኝነት ስም የሚንቀሳቀሰውን ማህበረሰብ ከሌላው ጋር የማቀራረብ ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው። ሌላው ጥያቄ እንዲጠይቅማ ሌላው እንዲሸሽ የሚያደርጉ ዘረኛ ሬተሪካቸውን ማቆም አለባቸው። እነርሱ ናቸውና መጀመሪያዉኑ ያራራቁን።
