በአገር ዉስጥም ሆነ ከአገር ዉጭ የሚገኘዉ ተቃዋሚ ኃይል የግል ፍላጎትን ተመርኩዞ የቅማንት ብሄረሰብ የራስ አስተዳደር ጎንደር ላይ ቢቋቋም የሰፊዉ አማራ ህዝብ ጥቅም በከፍተኛ ደረጃ እንደሚጎዳ በመጥቀስ ህዝቡን በተሳሳተ መንገድ እንዲያስብና ከቅማንት ህዝብ ጋር አላስፈላጊ ጦርነቶች እንዲካሄዱ የሚያደርጉ የዉሸት ቅስቀሳዎች (propagandas) ሌት ተቀን እያካሄዱ እንደሆነ እናዉቃለን፡፡ ስለሆነም ለእነዚህ የዉሸት ቅስቀሳዎች መልሳችን የሚከተለዉን ሊመስል ይገባዋል ባይ ነኝ፡-

  1. በመጀመሪያ ደረጃ የቅማንት ብሄረሰብ የጠየቀዉ የራስ አስተዳደር ጥያቄ ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚገዛበትን ወይም የሚተዳደርበትን ህገ-መንግስት (የህጎች ሁሉ የበላይ በሆነዉ ህግ) መሰረት የቀረበ እንጅ እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ በግለሰቦች ወይም በቡድኖች ፍላጎት ላይ ተመስርቶ አይደለም፡፡ የምንገዛበት ህገ-መንግስት ወይም ሌሎች ህጎች ሁሉ የሁሉንም ህዝቦች ጥቅም ባከበሩና ባቻቻሉ መንገድ የሚቀረፁና የሚተገበሩ እንጅ የአንዱን ህዝብ ጥቅም ብቻ በሚያስከብር ሁኔታ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለሆነም የቅማንት ብሄረሰብ የራስ አስተዳደር በሚቋቋምበት ወቅት የቅማንትና የአማራን ህዝቦች ጥቅሞች ባከበረ ወይም ባቻቻለ መንገድ መሆኑ የማይቀር ነዉ፡፡
  2. የቅማንት ብሄረሰብ የራስ አስተዳደር የሚዋቀረዉ የቅማንት ህዝብ በኩታ-ገጠም ሰፍሮ በሚገኝባቸዉ ቀበሌዎች እና ጎጦች እንጅ ተቃዋሚዎች እንደሚያስወሩት ቅማንት ያልሆነዉን አማራ ሁሉ በጉልበት በቅማንት አስተዳደር ዉስጥ እንዲገባ በማድረግ አካሄድ አይደለም፡፡ ካሁን በፊት የክልላችንና የፌዴራል መንግስቶቻችን የቅማንት ህዝብ ከጠየቃቸዉ 126 ቀበሌዎች መካከል ያፀደቋቸዉ 42 የቅማንት ቀበሌዎች ፍፁም ኩታ-ገጠም መሆናቸዉ ሃቅ ነዉ፡፡ ይሁን እንጅ ሌሎች በርካታ ቀበሌዎችና ጎጦች አሁንም ፍፁም ኩታ-ገጠም ሆነዉ ሳለ በቅማንት አስተዳደር ስር ሳይካተቱ መዘለላቸዉ እና የ42 ቀበሌዎች ብቻ ዉሳኔ አላስፈላጊ የሆነ ደም አፋሷል፡፡ ይህን ተከትሎም መንግስት የቅማንት የራስ አስተዳደር የሚፈታዉ በጠበንጃና በኃይል ሳይሆን በህዝብ ፍላጎትና ቀጥተኛ ተሳትፎ እንደሚሆን አቋም ወስዷል፡፡ የቅማንት ህዝብ ብቻ ሰፍሮ የሚገኝባቸዉና ፍፁም ኩታ-ገጠም የሆኑ ቀበሌዎችንና ጎጦች በተመለከተ በቅማንት ህዝብ ቀጥታ ተሳትፎ የሚወሰኑ ሲሆን ከአማራ ህዝብ ጋር እንደመጠኑ ብዛት ተቀላቅለዉ የሚገኙትን ቀበሌዎችና ጎጦች በሚመከለት ግን ሁለቱም ህዝቦች በነፃነት ይወስናሉ፡፡ በህዝበ-ዉሳኔ (referendum) ስርዓት ሁለቱም ህዝቦች ማንም ሳያስገድዳቸዉ ድምፅ በሚሰጡበት አካሄድ ተፈፃሚ ይሆናል ማለት ነዉ፡፡
  3. የሁለቱን ህዝቦች ፍላጎት ባጣጣመ መንገድ በቅማንት አስተዳደር ስር የሚካተቱት ቀበሌዎችና ጎጦች በግልፅ ከታወቁ በኋላ ቀጥሎ የሚመጣዉ ጉዳይ የቅማንትን አስተዳደር በልዩ ወረዳ ደረጃ ሳይሆን በዞን ደረጃ ማደራጀት ይሆናል፡፡ ምክኒያቱ ደግሞ ግልፅና ግልፅ ነዉ ፡ በቅማንት አስተዳደር ስር የሚካተቱት ቀበሌዎችና ጎጦች ቁጥር ብዙ ከመሆናቸዉ አንፃር የቅማንትን ህዝብ በልዩ ወረዳ አጭቆ ወይም ጨፍልቆ ማስተዳደር የባሰ የመልካም አስተዳደር ችግር መፍጠር ይሆናል፡፡ በአገሪቱም ሆነ በክልል 3 ዉስጥ ያሉት የአስተዳደር መዋቅሮችም በተሞክሮ የሚያሳዩት ይህንን ነዉ፡፡ ይህ ማለት የአሁኑ ሰ/ጎንደር ዞን በጥቅሉ ከሁለት ተከፍሎ ሁለት የዞን አስተዳደሮች ይኖሩታል፡-

1)የቅማንት ብሄረሰብ ዞን አስተዳደር 2) ሰ/ጎንደር ዞን አስተዳደር፡፡ ለሁለቱም የዞን አስተዳደሮች የዞን መስሪያ ቤቶች (መምሪያዎች፣ የዞን ፍ/ቤቶች) መቀመጫ በታሪካዊቷ ከተማ ጎንደር ይሆናል፡፡ በእርግጥ ጎንደር ከተማ ልዩ አስተዳደር ሆና ከቋቋመች ቆይቷል፡፡ ስለሆነም ርዕሰ መዲና እንደመሆኗ መጠን የሁለቱ ህዝቦች የዞን አስተዳደሮች መቀመጫ ብቻ ሳይሆን የከተማዉ ልዩ አስተዳደር መቀመጫም ሆና ጎንደር ከተማ ማገልገሏ የማይቀር ነዉ፡፡

  1. ይህ ከሆነ በኋላ ቅማንቶችም ሆነ አማሮች የራሳቸዉን ክልል ያለማሉ፤ጎንደር ከተማን ከሌሎች ብሄር-ብሄረሰቦች ጋር በመሆን በጋራ ያለማሉ፤ ጎንደር ከተማ ከሚገኘዉ ጥቅምም እኩል ተጠቃሚ ይሆናሉ እንጅ ድሮዉንም ጎንደር ከተማ የተቋቋመበት መሬት የቅማንቶች ስለነበር አሁንም ከጎንደር ከተማ ዉጭ እንሆናለን የሚል ምክኒያታዊ ያልሆነ ስጋት ሊፈጠር አይገባዉም፡፡ የቅማንት ህዝብም የራሱን ጥቅም አስከብሮ የሌሎችን ህዝቦች ጥቅም ያለአግባብ ሳይነካ ጥቅምን አቻችሎ አብሮ እንዴት መኖር እንዳለበት ጠንቅቆ የሚያዉቅ አስተዋይ ህዝብ እንደሆነ ታሪክ የሚመሰክረዉ እዉነታ ስለሆነ በግለሰቦች ወይም ቡድኖች የግል ፍላጎት ብቻ አቅጣጫዉን ስቶ ደጉ የቅማትም ሆነ የአማራ ህዝብ በወሬ ተነድቶ ወደ አላስፈላጊ ጥልቻና ግጭት እንደማይገባ እርግጠበኛ መሆን ይገባናል፡፡
  2. ከዚህ በላይ በተገለፀዉ አግባብ የቅማንት አስተዳደር የህዝብን ፍላጎት መሰረት አድርጎ ቢቋቋም በጎረቤት አማራ ወንድሞች በኩል አንድም አይነት ጉዳት አያመጣም፡፡ ይልቁንስ በብዙ መንገዶች የጋራ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ጎጃም ዉስጥ የአዊ አገዎች ልማት ለሌሎች አማራ ወንድሞች እንዴት እንደጠቀመ ጠንቅቀን እናዉቃለን፡፡ በተመሳሳይ መንገድ የሰ/ጎንደር አማሮችና ቅማንቶች ማንነታቸዉን መሰረት አድርገዉ የራሳቸዉን የቤት ስራ ለመስራት የአስተዳደር ክልላቸዉን ተከፋፈሉ እንጅ ጭራሽ ላይገናኙ ሊፈራረሙ አይችሉም፡፡ አንዱ ካንዱ የሚወስደዉ መልካም ተሞክሮ ቀላል አይሆንም፡፡ ስለሆነም የቅማንት አስተዳደር ከተፈቀደ ቅማንት ብቻ ይለማል፤ አማራ በድህነት ይራቆታል የሚለዉ ከንቱ ወሬ ቦታ አይኖረዉም ማለት ነዉ፡፡
  3. ሌላዉ ትልቁ ቅማንትና አማራ አብረዉ እንዳይሄዱ እንደስጋት የሚነዛዉ ወሬ ወደፊት ደንበር ለይተዉ ካንዱ አካባቢ ወደ ሌላዉ አካባቢ ሄደዉ መስራት ስለማይችሉ ፍፁም በኢኮኖሚም፣በማህበራዊና በሌሎች ጉዳዮች ይለያያሉ የሚለዉ ጉዳይ ነዉ፡፡ ይህ ስጋት ከከንቱ ስጋትነት ያመልጥም፡፡ ምክኒያቱም በክልል 3 ዉስጥ የስራ ቋንቋ አማርኛ እንደሆነ የክልሉ ህገ-መንግስት ደንግጓልና፡፡ ቅማንትኛ ቋንቋ አደገም አላደገም የክልሉ ህገ-መንግስት እስካልተሻሻለ ድረስ የሁለቱም ህዝቦች የመግባቢያና የስራ ቋንቋ አማርኛ ሆኖ መቀጠሉ የማይቀር ጉዳይ ነዉ፡፡ ስለሆነም ቅማንትም ሆነ አማራ በማንነቱ ሳይገለልና ሳይጨቆን በየትኛዉም ክልል ዉስጥ ተንቀሳቅሶ መስራትና መኖር እንደሚችል የፌዴራሉ ህገ-መንግስት በአንቀፅ 41 ስር ጭምር ደንግጎት የሚገኝ ጉዳይ ነዉ፡፡ ነገሩ የሚሆነዉ የእዉቀትና አመለካከት ጉዳይ ብቻ ይሆናል፡፡ ቀጥሎም የአፈፃፀም ጉዳይ ይሆናል እንጅ የስጋት ምንጭ ሆኖ አገር የሚያናጋ ጉዳይ በፍፁም ሊሆን አይችልም፡፡
  4. በመጨረሻም፡-
    7.1. ቅማንትና አማራ በማንነታቸዉ ምክኒያት ማለትም አማራ በመሆናቸዉ ብቻ ወይም ቅማንት በመሆናቸዉ ብቻ እስካልተጨቆኑ ድረስ፣
    7.2. የጋራ መግባቢያና የስራ ቋንቋ (አማርኛ) እስካላቸዉ ድረስ፣
    7.3. ከቅማንት ህዝብና ሰ/ጎንደር አማራዎች ዉጭ ሌላ ሶስተኛ ወገን በጉዳያችን ዉስጥ ገብቶ እንዳይፈተፍት ማድረግ እስከቻልን ድረስ፣
    7.4. በቅማንትም ሆነ አማራ በኩል ፅንፈኛ የሆነ አቋም ይዘዉ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን ወይም ቡድኖችን (Like ESAT journalist Messay Mekonnen) ማስተካከል እስከቻልን ድረስና፣
    7.5. የቅማንት ህዝብና ሰ/ጎንደር አማራዎች ጎንደር ከተማን በጋራ እስከተጠቀሙ ድረስ አብረዉ በልማት ጎዳና የማይገሰግሱበት ምክኒያት ምንድነዉ?

ህዳር 23፣2008

Source    =   Zehabesha

Leave a Reply