ይህ ሻማ የሚለኮስበት፣ ኬክ የሚቆረስበት ጊዜ አይደለም!!
.
ሰሞኑን ብአዲን 35ኛ የልደት በአሉን ያከብራል፡፡ ቁጥሩ እንጂ የጨመረው፣ አከባበሩ ያው እንደ ዱሮው ነው፣ እንደ 1984ቱ እና 85ቱ፤ ብቻቸውን፡፡ በነገራችን ላይ ህውሀትም ሆነ ብአዲን በአላቸውን፣ ድላቸውን የሚያከብሩት ብቻቸውን ነው፡፡ በደርግ ላይ የተቀዳጁት ድል የግል ሀብታቸው አድርገው፣ የዋሉበትን ግንባር፣ የከፈሉትን መስዋእትነት፣ የዛሬ ከፍተኛ ባለስልጣናትን የጦር ሜዳ ጀብድ፣ በፊልም አስደግፈው፣ ከወር ለዘለለ ጊዜ ያቀርቡልናል፤ በየአመቱ፡፡ በደርግ አምባገነናዊ የግፍ አገዛዝ የተንገፈገፈው ህዝብ ለድላቸው ቅንጣት አስተዋጽኦ ያደረገ አይመስላቸውም፡፡ ደርግን እንደአንባገነናዊ ስርአት በጦርነት አሸንፎ ማስወገድ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ማሸነፍ ይመስላቸዋል፡፡ በየከተማው በድል አድራጊነት ሲገቡ ታንካቸውን እያጀበ በዘፈን እንደተቀበላቸው ረስተውታል፡፡
.
በአንድ አንባገነናዊ መንግስት የተነሳ ወንድም ከወንድሙ የተጨራረሰበትን አሳፋሪ ጦርነትና የተገኘውን ጎምዛዛ ድል (መቼም ወገንህን ገድለህ ያገኘኸው ድል ጣፋጭ ሊሆን አይችልምና)፣ የጦር አውድማዎችንና የወንድሞቻችንን አስክሬን እያሳየን የምናከብረው እስከመቼ ነው? አንድ አመት፣ ሁለት አመት ይሁን…ሀያ አምስት አመት?! ለምንድነው የተገኘው ድል፣ የተከፈለው መስዋእትነት ባስገኘው መልካም እሴት አጅበን የማናከብረው? ባስከተለው መጥፎ አሰራር የማንገመግመው?
በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ የግንቦት ሀያ ድል፣ ኢትዮጵያውያን እስከዛሬ በጦርነት ከተቀዳጀናችው ድሎች ሁሉ የበላይና ብቸኛ እንደሆነ ሁሉ፣ ሌሎች ብሄራዊ ነጻነታችንንና ሉአላዊነታችንን አስጠብቀው ያቆዩ ብሄራዊ ድሎቻችንን ማሳነሱ ነው፡፡ የአድዋ ድል፣ የሰማእታት ቀን. . .ከዜና ዘገባ ካለፉ (ቀንቷቸው) የአንድ ሰአት ፕሮግራም ቢሰራላቸው ነው፡፡ የነአቡነ ጴጥሮስ ሀውልት የት ነው? አጼ ምኒልክ ማናቸው? አሉላ አባነጋ፣ ባልቻ አባነፍሶ፣ ዘርአይ ድረስ፣ አብዲሳ አጋ፣ በላይ ዘለቀ . . . እነማን ናቸው? ስንት ወጣቶች ያውቋቸዋል? ዛሬ በዘመነ ኢህአዴግ ድላችን ግንቦት ሀያ፣ ጀግኖቻንም የግንቦት ሀያ ጀግኖች ብቻ እንደሆኑ ተደርጎ ይቀርባል፡፡ ይህ ስህተት ነው! አንዱ ሌላውን ይደግፋል፣ ያጸናል እንጂ፣ አንዱ ሌላውን አይተካም፡፡ በታሪካችን፣ በነጻነታችንና በሉአላዊነታችን ውስጥ ሁሉም የራሳቸው ዋጋ አላቸው፡፡
.
ስለኢትጵያ ነጻነት ስናወራ፣ ተከብሮ ስለኖረው ድንበራችንና የባህርበራችን (ነበር እያልንም ቢሆን) ታሪክ ስናገላብጥ ኢህአዴግ የአንዲት አርፍተነገር ድርሻ እንኳን የለውም፡፡ በአንጻሩ የደርግን አንባገነናዊ አገዛዝ በማስወገድ ረገድ በሚጻፍ ታሪክ ውስጥ ኢህአዴግ አብዛኛውን ገጽ ይይዛል፤ ምናልባት ይህን ታሪክ ከኢህአዴግ የሚሻማው ቢኖር ድርጅቱ ከተጸነሰ ጀምሮ በእቅፉ ሸሽጎ ለድል ያበቃውና በድል አድራጊነት በገባበት ጉሮወሸባዬ እያለ የተቀበለው ህዝብ ነው፡፡
.
ኢህአዴግን ለድል ያበቃው የኢትዮጵያ ህዝቦች እንደሆኑ፣(ምንም እንኳን ለትግሉ ያበረከተቱት አስተዋጽኦና የተቀበሉት መከራ፣ እንዳሉበት መልከአምድራዊ ሁኔታ ቢለያይም) ከራሱ ከኢህአዴግ በላይ እማኝ አይገኝም፡፡ በተለይ የሰሜን ኢትዮጵያ ህዝቦች፣ ‹‹ለሀጥአን የመጣ፣ ለጻድቃን ይተርፋል››ን በተረተው ደርግ መከራን ተቀብለዋል፤ ለኢህአዴግ በተወረወረው ወድቀዋል፡፡
.
ዛሬ ብአዴን – ኢህአዴግ በዚህ ህዝብ ጉያ የተፈጠረበትን ሰላሳ አምስተኛ አመት አክብሯል፤ ያከበረው ግን ከፈጠረው፣ አብሮት ከተዋደቀው ህዝብ ጋር አይደለም፤ የባህርዳርና የአዲስ አበባ ህዝብ አይደለም፣ ‹‹ወፌ ቆመች›› ብሎ አሳድጎ፣ ጡንቻ ሆኖ ለድል ያበቃው፡፡ ለድል ያበቃው ህዝብ አንድም ተርቧል፤ አልያም ስለተራቡ ወገኖቹ አዝኗል፤ በአሉን ለማክበር ሀይማኖታዊውም ሆነ ማህበራዊው እሴቱ አልፈቀደለትም፡፡ ይህ አይገርምም፤ የሚገርመውና ግራ የሚያጋባው፣ ከ15 ሚሊየን ህዝብ በላይ በተራበበት ሀገር የድርጅቱ ይህንን በአል ማክበር ነው፡፡ አንድ የዚህ ድርጅት አባል የሆነ ጓደኛዬ ስለሁኔታው አንስተን ስንነጋገር፣ ድርጅቱ ልደቱን ማክበሩ ረሀቡን ለመቋቋም አቅም እንደሚፈጥርለት፣ የድርጅቱን መሪ የተከበሩ አቶ ደመቀን ንግግር ጠቅሶ ተሟገተኝ፡፡
.
የጓደኛኛዬን የመሟገቻ ጭብጥ ለመረዳት ከጭንቅላቴ በላይ ሆነብኝ፡፡ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎቻቸው በድግስ መንበሽበሽ፣ በካነቴራና ኮፍያ መድመቅ፣ በስብሰባ መታከት ረሀቡን ለመግታት አቅም የሚሆነው እንዴት ነው? የተራቡት እነሱ አይደሉ! መሪው በበላ ህዝብ የሚጠግብ በሆነማ የሚራብ አንድም ኢትዮጵያዊ አይኖርም ነበር፡፡ ይኸው ከላይ የጠቀስኩት ጓደኛዬ፣ ‹‹ለበአሉ የወጣው ገንዘብ ከአባላት የተዋጣና ከተለያዩ ድርጅቶች የተለገሰ ነው›› አለና አስገረመኝ፡፡ እነዚህ ሰዎችና ድርጅቶች እውነት ስለመስጠት፣ መርዳት የሚያውቁ ከሆነ፣ ለተራቡ መለገስ አይቀድምም? ወይስ የሰጡት በልግስና ሳይሆን ነገ ከድርጅቱ ለሚጠብቁት ውለታ ቀብድ ማስገባታቸው ነው? እኔ ይህንን ሀሳብ መቀበሉ ይቀለኛል፡፡
.
ኢህአዴግ መንግስት ነው፡፡ መንግስት ደግሞ የሀገር አስተዳዳሪ፣ የህዝቦች አባት ነው፡፡ ኢትዮጵያን እንደእናት፣ ልጆችን እንደህዝብ፣ አባትን እንደመንግስት ስንወስድ፣ ሀገር አንድ ትልቅ ቤተሰብ ማለት ነው፡፡ ታዲያ የትኛው አባት ነው ከልጆቹ መካከል አንዱ በህመም እየተሰቃየ፣ በጠኔ እየሰለሰለ የሌላኛውን ልጁን ልደት የሚያከብር? ‹‹ገንዘብ እሰጥሀለሁ፤ ግን የታመመውን ልጅህን ለማሳከም፣ የተራበውን ለማብላት ሳይሆን፣ የጤነኛውን ልደት ታከብርበት ዘንድ ነው››፣ ብንለው የትኛው አባት ነው (ማክበሩ ይቅር) ይሁን ብሎ ችሮታውን የሚቀበል? እንደአባት ይህ ስድብ ነው፤ ለጋሹም ደመኛ እንጂ ለጋሽ አይደለም፡፡
.
እና እንዴት ነው ብአዴን የተራበ ህዝብ ባለበት ሀገር፣ ይህን ያህል ገንዘብ ለበአል የሚያወጣው? ገንዘቡ ከየትም ይምጣ ከየት፣ ለአንድ ሰው ከአዲስ አበባ ባህር ዳር ደርሶ መልስ ለአየር የሚከፈለው ስንት ዳቦ ይገዛል? ስንት ጀሪካን ውሀ ይገዛል? በርግጥ ዛሬ ረሀቡ መግደል አልጀመረ ይሆናል፤ ግን በችጋር እየተሰቃዩ ያሉ ወገኞቻችን በሚሊየን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ እና አንድ ሰው ላንድ ቀን እንዲለብሰው ካኔተራና ኮፍያ ከማሰራት፣ ለአንድ ቀን የተራበ መመገብ አይበልጥም? በአልንስ ለማክበር ቢሆን፣ ከዚህ የተሸለ አስደሳች መንፈስ የሚፈጥር ተግባር አለ? ምን አይነት አባት ነው ልጁ በችጋር እየተጥወለወለ ፍሪዳ የሚቆርጥ፣ ውስኪ የሚቀዳ? እኔ በበኩሌ የተራቡ ወገኖቼን ሳስብ፣ ከዛሬ ተርፎ በመሶቤ ያደረ እንጀራ መኖሩ ይቆጠቁጠኛል፡፡
.
እና ብአዴን – ኢህአዴግን አዘንኩበት፤ ከቀደመው በላይ ተስፋ አጣሁበት፡፡ በምንም ሚዛን ይህ ሻማ የሚለኮስበት፣ ኬክ የሚኮረስበት፣ ልደት የሚከበርበት ጊዜ አይደለም፡፡
Source = EthioReference