Wednesday, 09 December 2015 13:55

  • በ                                                         
  • – በምስራቅ በለሳ ት/ቤቶች የመዘጋት አደጋ አጋጥሟቸዋል

    “ከ25 አመታት ወዲህ አጋጥሞ የማያውቅ ድርቅ ተከስቷል”

    የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

    ገዱ አንዳርጋቸው

 በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በትግራይና በአማራ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የድርቅ አደጋ መከሰቱ ይታወቃል። ይህን ክስተት ተከትሎም የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ከመንግስትና ከግል ለተውጣጡ በርካታ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ቦታው ድረስ በመውሰድ ሁኔታውን እንዲዘግቡ አድርጓል። አስራ ሰባት ቀናትን በፈጀው በዚህ የጋዜጠኞቹ ቅኝት ላይ ተመስርተን፤ ዘንድሮ ዓለም አቀፉን የኤሊኖ የአየር መዛባት ክስተት ተከትሎ በኢትዮጵያ የተፈጠረውን የድርቅ ችግርና እየተወሰደ ያለውን እርምጃ ከክልሎቹና አመራሮች አንፃር በከፊል እንዳስሳለን።

መንግስት በተደጋጋሚ ጊዜ ድርቁ ስለመከሰቱ የእምነት ቃሉን ቢሰጥም፤ “ርሃብ” ይሉት ክስተት ግን ፈጽሞ የለም ብሏል። ይሁን እንጂ በትክክል የተረጂውን ቁጥር ባለመታወቁ፤ ከቀበሌ እስከ ዞን ባሉ አመራር አካላት መካከል የመናበብ ጉድለት በመከሰቱና የድሃ-ድሃ ተረጂዎችን መለየት በሚል መስፈርት በተፈጠረ ሰፊ የመረጃ ክፍተት ምክንያት በርካታ ዜጐች አሁንም የእርዳታው እህል እንዳልደረሳቸው ወይም ቢደርሳቸውም ከሚያስተዳድሩት ቤተሰብ ቁጥር አንፃር በቂ አለመሆኑና የተከታታይነት ችግሮች መኖራቸው ድርቁን ወደአስከፊ ደረጃ እንዳይወስደው ተሰግቷል።

ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሁሉ ቀዳሚው የህዝብ ጥያቄ የመጠጥ ውሃ፣ የምግብ እና የእንስሳት መኖ አቅርቦት ሲሆን፤ ለዚህም መንግስት የቻልኩትን እየሰራሁ ነው ይላል። በበርካታ አካባቢዎች ውሃን በመኪና የማመላለስ ስራ ሲሰራ የተመለከትን ቢሆንም፤ በቂ አለመሆኑ ግን ከህዝቡ ጩኸት በላይ ገዝፎ ይታያል። ከዚሁ ጐን ለጐን ደግሞ ምሳሌ መሆን የሚችሉ የውሃ ቁፋሮዎችና የመስኖ እንቅስቃሴዎች በተለይም በደቡብ፣ በትግራይና በአማራ አንዳንድ ወረዳዎች ውስጥ መመልከት ችለናል።

ኦሮሚያ

በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎችና ቀበሌዎችም ውስጥ የድርቁ ሁኔታ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል። ከ3 ነጥብ 3 ሚሊየን ህዝብ በላይ በሚኖርበት በዚህ ዞን የበልግ ምርት ከ20 እስከ 25 በመቶ የሚሆነው ሙሉ በሙሉ የጠፋ ሲሆን፤ በክረምቱም ምርት 11 በመቶ ለማግኘት የታቀደ ቢሆንም፤ የተገኘው ውጤት 27 በመቶ በዝናብ መዛባት ምክንያት ጠፍቷል ሲሉ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደምሴ ያቺሶ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል። ከመስከረም ወር በኋላ በህፃናትና እናቶች ላይ የምግብ እጥረት በመታየቱ እስከ ቀበሌ ድረስ የሚቀርብ የምግብና የአልሚ ምግብ አቅርቦት በክልሉ መንግስት ድጋፍ ስለመደረጉም ተናግረዋል።

የተረጂው ቁጥር ቀስ-በቀስ እያደገ መጥቶ በአሁኑ ወቅት 549 ሺህ 651 መድረሱን የሚናገሩት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ፤ ይህንንም ተረጂ በተቻለ የምግብ አቅርቦት ለማዳረስ እየተሰራ ነው ብለዋል። ከክልሉ መንግስትና ከፌዴራል መንግስት በተጨማሪ በክልሉ ያሉ የግብረሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ እንዳልተለያቸውም አስረድተዋል።

ከብቶቹን በተመለከተ የመኖ እጥረት በስፋት የገጠመው አካባቢ ሲሆን፤ የተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ ባለባቸው ስፍራዎች የተገኙ የግጦሽ መሬቶችን በመጠቀምና መንግስት ያቀረበውን መኖ በማድረስ ላይ እንደሚገኙ የዞኑ አስተዳዳሪ ቢናገሩም፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ግን በመኖ እጥረትና በውሃ ጥም በርካታ ከብቶች እንደሞቱባቸው ተናግረዋል። በዞኑ የውሃ እጥረቱን ለመቅረፍ የመንግስት ድጋፍ የተጠየቀ ሲሆን፤ 30 የውሃ ማመላለሻ መኪናዎች (ቦቴዎች) ተጠይቀው እስካሁን 17 ወደ ስራ መግባታቸውን ይናገራሉ። ይህ የውሃ ስርጭትም ለስምንቱ ወረዳዎች እንደሚከፋፈል ዋና አስተዳዳሪው አስረድተዋል። እስከ ታህሳስ ወርም መንግስት 10 ሚለዮን ብር መድቦ የውሃ ችግሩን ለዘለቄታው ለመፍታት እየሰራ ይገኛል። በተያያዘም የመስኖ ስራ እንቅስቃሴ የታየባቸው አካባቢዎች አሉ።

በድርቁ ምክንያት ከትምህርት ቤቶች የሚቀሩ ተማሪዎች ቁጥር ከቀን ወደቀን እየጨመረ ስለመምጣቱ በዞኑ የሚኖሩ ያነጋገርናቸው ሰዎች ቢያስረዱም፤ ዋና አስተዳዳሪው ግን አንድም ተማሪ ከትምህርት ገበታው አልቀረም ይላሉ። ለዚህም በየትምህርት ቤቱ የምናቀርበው ምግብ አስተዋፅኦ አድርጓል ሲሉ ይሞግታሉ። ለዚህም እንደ ጤና ኮማንድ ፖስት፣ እንደ አደጋ መከላከለ ኮማንድ ፖስት ሁሉ በትምህርት ቤቶችም አካባቢ የሚሰራ ጠንካራ ኮማንድ ፖስት አለን ሲሉ ይዘረዝራሉ። ምስራቅ ሐረርጌ ዞን 47 በመቶ በመስኖ የሚሰራ 155 ሺህ ሔክታር በላይ ለመስኖ እርሻ መዘጋጀቱን የገለፁት አስተዳዳሪው፤ ለወደፊቱም ይህንኑ አጠናክሮ የመስራት ዝግጁነት መኖሩን አስረድተዋል።

ደቡብ

የኤሊኖ ክስተት መኖሩን አስቀድሞ በማወቅና በማሳወቅ ይጠባበቁ እንደነበር በተግባር ከታየባቸው ክልሎች አንደኛው የደቡብ ብሄር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አንዱ ነው። በዚህም ጠንካራ ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም የክልሉ ፕሬዝደንት አቶ ደሴ ዳልኬ በጽ/ቤታቸው ለተገኙ ጋዜጠኞች ተናግረዋል። በክልሉ ወቅቱን ያልጠበቀ፣ የተቆራረጠና አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ በመጣሉ የተዘራው ማሳ ሙሉ በሙሉ ውጤታማ ሳይሆን ለመቅረቱ ዋነኛ ምክንያት እንደነበር ይናገራሉ። በተለይም ችግሩ የከፋባቸው በክልሉ ውስጥ በሚገኙና ስምጥ ሸለቆ በሚያልፍባቸው ምስራቅ ጉራጌ ወረዳዎች፣ ሶዶ፣ ምስቃንና ማረቆ ወረዳዎች እንዲሁም በስልጤ ዞን በከንባታ ጠንባሮ፣ ዳሎቻ፣ ሀዲያና ሲዳማ ውስጥ ባሉ ወረዳዎች በድምሩም ወደ 61 ወረዳዎች ላይ ድርቁ ታይቷል። በዚህም በዝናብ መዛባቱ ምክንያት ወደ 200 ሺህ ሔክታር ማሳ ሳይዘራ መቅረቱን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል። ይህም በመሆኑ ከተዘራው ውስጥ ወደ 96 ሺህ ሔክታር የሚገመት ሰብል በከፍተኛ ሁኔታ መጐዳቱን አምነዋል። ይህም የምግብ እጥረት ችግር ፈጥሯል ብለዋል። በዚህም ወደ 278 ሺ ተረጂ የዕለት እርዳታ እንዲያገኝ ሲደረግ፤ ከመስከረም ወር በኋላ ቁጥሩ በመጨመሩ ወደ 349 ሺህ ተረጂ የተደመረ ሲሆን፤ በድምሩም ወደ 671 ሺህ ህዝብ የምግብ እርዳታ ጠባቂ ሆኗል ብለዋል። ለዚህም የሚሆን የእርዳታ እህል መቅረቡን አስረድተዋል። የተረጂው ቁጥር እንደሚጨምር ይጠበቃል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ወደ 756 ሺህ ይሆናል ተብሎ ለሚጠበቅ ተረጂ በቂ ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።

ከእንስሳት አንፃርም በመኖ አቅርቦት፣ በውሃና በመድሐኒት በርካታ ስራዎችን ክልሉ ያከናወነ ሲሆን፤ አለፎ-አልፎም ቢሆን ግን የእንስሳት ሞት በክልሉ ሰለመከሰቱ አላስተባበሉም። በተለይም ውሃን በተመለከተ ችግሩ ባጋጠማቸው ወረዳዎች ላይ እስከ 5 ሺህ ሊትር መያዝ የሚችሉ ኩሬዎች በመቆፈር የተሰራ ሲሆን፤ በተጨማሪም በህዝብ ተሳትፎ ወደ 500 ሜትር ኪዩብ የሚይዝ ጉድጓድ ለማዘጋጀት እየተሰራ ነው ብለዋል። ይህም የውሃ ማሰባሰብ በቀጣይ ለመስኖ አገልግሎት ይውላል ሲሉ አክለዋል።

አማራ

በአማራ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል 69 ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ በድርቁ የተጐዱ ሲሆን፤ በእነዚህ ወረዳዎችም ውሰጥ 3 ሺህ 400 ቀበሌዎች እንዳሉና ከእነዚህም ውስጥ ወደ 800 ያህሉ ድርቅ የተከሰተባቸው ናቸው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ይናገራሉ። 300 ቀበሌዎች የጠና የውሃ ችግር ያለባቸው ሲሆን፤ በመኪናና በጉድጓድ ቁፋሮ አማካኝነት የውሃውን ችግር ለመፍታት በ168 ቀበሌዎች እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። ድርቁን ተከትሎ ለተከሰተው የምግብ እጥረት የክልሉ መንግስት 200 ሚሊየን ብር ድጋፍ በመስጠት መመደቡን ተናግረዋል። ያም ሆኖ የክልሉ ትልቁ ችግር የውሃ እጥረት እንደሆነም ተነግሯል።

በአንዳንድ ወረዳዎች የምግብ እርዳታ አለመድረስና ክፍፍሉም ላይ የመረጃ ክፍተት ተከትሎ የመጣ ችግር መኖሩን ያመኑት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በአፋጣኝ የሚታረምና ምላሽ የሚሰጥበት ተግባር ነው ብለዋል። ከከብቶች የመኖ እጥረት ጋርም በተያያዘ ከ200 ሺህ ያላነሱ ከብቶች ወደተጐራባች ወረዳዎች ስለመዘዋወራቸውና በቀጣይም የከብት ቁጥር ቅነሳን ለማበረታታት የገበያ ማፈላለግ ስራ እንደሚሰሩ አስረድተዋል። እስከ አሁንም 130 ሺህ ከብቶች ስለመሸጣቸው አስታውቀዋል።

በክልሉም ሆነ በፌዴራል መንግስት በኩል የሚቀርቡ የእርዳታ እህል እየተዳረሰ ነው የሚል ምላሽ ቢሰጡም፤ በአንዳንድ ቦታዎች ግን ከቅድመ-መረጃው ጋር ያልተጣጣመ ተረጂ ቁጥር በመድረሱ ምክንያት የእርዳታ አሰጣጣቸው ላይ ችግር መፍጠሩን አልሸሸጉም። በዚህ አካሄድ ድርቁ በተከሰተባቸው በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ውስጥ የድሃ-ድሃ የመለየቱ ተግባርውስብስብና አስከፊ ችግርን የሚጋብዝ የመንግስትንም አቅም የሚፈታተን ይሆናል። ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሁሉ ድርቁን ተቋቁሞ ቤተሰቡን ማስተዳደር ይችላል በሚል “ከድሃ-ድሃ” መዝገብ የተሰረዘ አርሶ አደር “አለሽ መስሎሻል ተበልተሽ አልቀሻል” የሚተረትበት ችግረኛ እየሆነ ስለመምጣቱ ያነጋገርናቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች አቤት ይላሉ።

በቂ ምግብና ውሃ በሌለበት ሁኔታ ተላላፊ በሽታዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ታሳቢ በማድረግ ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የገለፁት ርዕሰ-መስተዳድሩ፤ የእከክ በሽታ ምልክት በአንዳንድ ቀበሌዎች በመከሰታቸው በመድሃኒት አቅርቦት እየሰጠን ነው ብለዋል።

በአማራ ክልል በድርቅ ከተጠቁ አካባቢዎች መካከል በተለየ ትኩረት መታየት ያለበት ምስራቅ በለሳ ሲሆን፤ 135 ሺህ ሰዎችን በያዘው በዚህ ወረዳ ውስጥ 32 ሺህ 154 ተረጂዎች እንዳሉ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጀንበር አያልነህ ይናገራሉ። ከፍተኛ የውሃ ችግር ያለበት ይህ ወረዳ በእከክ ምክንያት 11ሺህ ሰዎች ለበሽታ የተጋለጡ ሲሆን፤ ለ9 ሺህ 700 ሰዎች በቻ ህክምና መድረሱም ተሰምቷል። በወረዳው ከ200 ሺህ በላይ እንስሳት ሲኖሩ፤ 3ሺህ መሞታቸውን ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል። ከትምህርት አንፃርም ወረዳው 67 በመቶ ብቻ ያሳካ ሲሆን፤ በተለይም እንደማሳያ የሚቀርበው በጠርጣሯ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው የበረከተ ተማሪዎች በድርቁ ምክንያት ትምህርት በማቋረጣቸው 527 ተማሪዎችንና ሦስት መምህራንን ብቻ ይዞ ይገኛል። በዚህም ትምህርት ቤቱ የመዘጋት አደጋ አንዳንዣበበበት የትምህርት በቱ ርዕሰ መምህር አቶ ገላጋይ አሻግሬ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንድሚሉት በ48 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉ ተማሪዎች ለከፋ የምግብ እጥረት የተጋለጡ ሲሆን፤ የክልሉ መንግስት ተማሪዎቹን ለይቶ ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሚገኝ ገልጿል።

ከሁሉም በላይ ለተቸገሩ ወገኖች እርዳታን ለማድረስ ለክልሉ መንግስት ትልቅ ፈተና የሆነው የመንገድ ችግር ስለመሆኑ የተናገሩት አቶ ገዱ፤ ይህንንም ለመፍታት በዕቅድ ከተያዙ የመንገድ ፕሮጀክቶች በማዟዟር ችግሩ ባለባቸው አካባቢዎች በመስራት የውሃና የምግብ አቅርባቱን ለማሳለጥ እየሰራን ነው ብለዋል። የተከሰተው ድርቅ ምናልባትም ካለፉት 25 ዓመታት ወዲህ በእጅጉ የከፋ ነው ያሉት ርዕሰ-መስተዳድሩ፤ በክልልም በፌዴራልም ደረጃ ተስተካካይ ምላሽ በመስጠት ተግባራዊ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ትግራይ

የድርቁ የከፋ ጉዳት ከታየባቸው አካባቢዎች መካከል በትግራይ ክልል የሚገኘውና በምስራቃዊ ትግራይ ዞን፣ አፅቢ ወንበርታ ወረዳ ውስጥ የሚገኘው ከሊሻአምኒ ቀበሌ ዋነኛው ነው። የሚላስ የሚቀመስ በጠፋበት በዚህ ቀበሌ የወረዳውና የዞኑ አመራሮች የእርዳታ አቅርቦት እንዳላደረሷቸው ኪሮስ ሃለፎም የተሰኙ የአካባቢው አርሶ አደር ይናገራሉ። ምንም አይነት ድጋፍ እንዳልተደረገላቸውና ቤተሰባቸውን ለመቀለብ ሲሉ ከብታቸውን በዝቅተኛ ዋጋ ገበያ ያወጡት እኚህ አርሶ አደር የወረዳው ሰዎች አንድም ቀን አነጋግረዋቸው እንደማያውቁ ይናገራሉ። በክልሉ በዚህ ቀበሌ ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች በድርቁ ምክንያት ትምህርት ያቋረጡ ሲሆን፤ ይህንንም ሉግዳ ከተሰኘው ት/ቤት ተገኝተን አረጋግጠናል። ይሁን እንጂ የወረዳው የግብርናና ገጠር ልማት ኃላፊ በበኩላቸው “ይህ ሁሉ ውሸት ነው” ሲሉ የአርሶ አደሩን ቅሬታ ያጣጥላሉ።

የክልሉ የውሃ ሀብት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አብርሃ አዱኛ፤ በበኩላቸው እንደ ክልል ከፍተኛ የውሃ ችግር መኖሩን አምነው፤ መንግስት ግን ተጨባጭ ስራዎችን በመስራትና ኅብረተሰቡን በመደገፍ ላይ ነው ብለዋል። የውሃ ችግርን ለመቅረፍ ከ20 ዓመታት በላይ የወሰደው የራያ አላማጣ የውሃ ፕሮጀክት አሁንም አለመጠናቀቁ የአካባቢው ነዋሪዎችን አማሯል። 200 የውሃ ጉድጓዶች ሲኖሩ፤ 15ቱ የኢንቨስተሮች ናቸው ብለዋል። ራያ አዘቦ ላይ 105 ጉድጓድ ያለ ሲሆን፤ 50ዎቹ ብቻ እንደሚሰሩ ገልፀዋል። የማሽነሪ ችግሮች የብዙዎቹን ጉድጓድ አሰሪር አስተጓጉሏል ብለዋል።

በትግራይ ክልል ምሳሌ መሆን የሚችሉ የመስኖ ስራዎች ቢኖሩም፤ የመረጃ አለመናበብና የአፋጣኝ ምላሽ አለመኖር በተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ በሚኖሩ አርሶአደሮች ላይ ጫና ፈጥሯል። 10 ወረዳዎችን በመስኖ ውሃ ማስተሳሰራቸውን የሚናገሩት የክልሉ ውሃ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብርሃ አዱኛ፤ የጉድጓድ ውሃዎችን ለመጠቀም የሚያስችል የትራንስፎርመር ግዢ ለመፈፀም የፌዴራል መንግስት 23 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርጐልናል ብለዋል።

እንደማጠቃለያ

በአጠቃላይ ግን በቀጣይ ሁሉም ክልሎችና ድርቁ ያጋጠማቸው አካባቢዎች በዘለቄታው መሰረት ያለባቸው የውሃ ማቆር፤ የመስኖና የጉድጓድ ውሃ አቅርቦትን ማስፋፋት እንደሆነ የሚናገሩት የየክልሎቹ የግብርና ባለሙያዎች፤ አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ ከሰማይ የሚንጠባጠበውን ሳይሆን፤ ከምድር የሚፈልቀውን ውሃ ስራዬ ብሎ መያዝ እንዳለበት ይመክራሉ። ለዚህም የየክልሎቹና የፌዴራል መንግስት ድጋፍና ቁርጠኛ አመራር እንደሚያስፈልግ አልሸሸጉም።

ምንጭ ስንደቅ

Leave a Reply