Wednesday, 09 December 2015 14:16

  • በ 
  • በአሁኑ ሰዓት ቀላል የማይባል የኢትዮጵያ አካባቢ ለድርቅ ተጋልጧል። በርካቶች የእርዳታ እህልን ለመጠበቅ ተገደዋል። የድርቁ መከሰት ሳይሆን ድርቅን ሊቋቋም የሚችል አርሶ አደርንና አርብቶ አደርን መፍጠር አለመቻሉ በራሱ አነጋጋሪ ነው። ድርቅ ኢትዮጵያን ሲያጠቃ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በየአስር አመቱ በድርቅ የምትጠቃ አገር ዛሬም ድርቅ ሲመጣ እጁን ለምፅዋት የሚዘረጋ ህዝብን ይዛለች።የኢትዮጵያ ገበሬ በድርቅ ምክንያት የረሀብ ተጋላጭነት እድሉ የሰፋ የሆነው ከመጀመሪያውም ኑሮው ከእጅ ወደ አፍ በመሆኑ ነው። ድርቅ ይመጣል ድርቅ ይሄዳል። ጥሎት የሚሄዳቸው አደገኛ ውጤቶች ግን በቀላሉ ተነቅለው የሚጣሉ አይደሉም። በዚህ የኢኮኖሚ አምዳችንም ከድርቁ ባሻገር ሊኖሩ የሚችሉትን ቀጣይ ፈተናዎች በተወሰነ ደረጃ ተመልክተናል።

የተረጂነት ሥነልቦና

በኢትዮጵያ ድርቅና ረሃብ በተደጋጋሚ ተከስቷል። ድርቅና ረሃቡ ከመነሳቱ ባሻገር ሌላኛው ፈተና የምግብ እህል እርዳታው በቀጣይነት እየፈጠረ የሚሄደው የተረጂነት ሥነ ልቦና ነው። በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የተከሰተው የድርቅ ፈተና በርካቶች የተረጂነት ሥነ ልቦናን እንዲያዳብሩ አድርጎ በመቆየቱ የድርቁ ሁኔታ መለስ እያለ ቢሄድም እንኳን የተረጂነት ስሜቱ ግን በቀላሉ የሚላቀቅ ሆኖ የሚታይ አይሆንም።

ከዚህ ቀደም በአገሪቱ በተከሰቱት ተከታታይ የድርቅ አደጋዎች እርዳታውን ከማቆም ይልቅ ህብረተሰቡ በምግብ ለስራ ፕሮግራም በአካባቢው የልማት እየተሳተፈና ከጉልበቱ ከሚገኝ የላብ ውጤት እየሰራ የግብረ ሠናይ ድርጅቶችን የእርዳታ ምግብ እህል እንዲያገኝ ሲደረግ ቆይቷል። በድርቅ የተጎዳን መርዳትና ማገዝ የመንግስትም ሆነ የቀሪው ህብረተሰብ የሞራልና የኃላፊነት ግዴታ መሆኑ ጥርጥር የለውም።  ችግሩን ለመቀልበስ ርብርብ ካልተደረገ ድርቅ ወደ ረሃብ ብሎም ረሃብ ወደ ህልፈተ ህይወት ማምራቱ የማይቀር ነው። ችግሩ መፍትሄ እያገኝ ሄደ ማለት የድርቁ ምዕራፍ ወደያውኑ ይዘጋል ማለት ግን አይደለም። አስከትሎት የሚመጣው ውጤት ከድርቁ የእድሜ ዘመን በላይ ይጓዛል። ከእነዚህ ቀጣይ ችግሮች መካከል አንዱ ይሄው ማህበረሰባዊ የተረጂነት ስነልቦናን ፈጥሮ የመሄዱ ውጤት ነው።

ግሽበትን ማባባስ

ግሽበት ከባድ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፈተና ሆኖ ቆይቷል። በኢትዮጵያ ባለፉት ተከታታይ አመታት በተከሰተው ግሽበት ሰፊውን ድርሻ ይዞ የነበረው ምግብ ነክ የሆነው ሸቀጥ ነው። መንግስት ይህንን በመረዳትና በሸማቾች ዋጋ መናር የተከሰተውን የዋጋ መናር ለመከላከል መሰረታዊ የሚባሉትን ሸቀጦች ማለትም፤ እንደ ስንዴ ዘይትና ስኳር የመሳሰሉ ምርቶችን ከውጪ በማስመጣት ለህብረተሰቡ በማከፋፈል የሰራቸው ስራዎች የግሽበቱ መጠን ቀላል በማይባል መልኩ እየወረደ እንዲሄድ አድርጎታል።ይህ የድጎማ እህልና የዘይት አቅርቦት በዋነኝነት ይቀርብ የነበረው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኘው የከተማ ነዋሪ ነው። በዚህ መልኩ የነበረው መሰረታዊ ሸቀጦች የድጎማ ስርጭት ለህብረተቡ ለማድረስ መንግስት ወጪዎችን በሁለት መልኩ  ማውጣት ግድ ሆኖበታል። በአንድ መልኩ ለመሰረታዊ ሸቀጦች የሚያገለግል የውጪ ምንዛሪን መመደብ ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ በዚህ ደረጃ አገር ውስጥ የገባውን ሸቀጥ በተጨማሪ ገንዘብ ደጉሞ ለህብረተሰቡ ማቅረብ ነው። በዚህ መልኩ ከ 2001 ጀምሮ መንግስት ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ መድቦ በየዓመቱ በርካታ ቶን የውጪ የስንዴ ግዢን እያከናወነ ይገኛል።

ይህም በመሆኑ አሁን በገጠሩ የአገሪቱ ክፍል የተከሰተው መጠነ ሰፊ የድርቅ አደጋ ደግሞ መንግስት ቀላል የማይባል የገንዘብ መጠንን በመመደብ ከውጪ የስንዴና መሰል የእርዳታ አቅርቦቶችን በስፋት አጠናክሮ እንዲሸምት አስገዳጅ ሁኔታን ጥሎበታል። በሙከራ ላይ ያለው የኢትዮ ጅቡቲ የጭነት ባቡር ከውጪ በግዢ እየገባ ያለውን የእርዳታ እህል በማመላለስ ላይ መሆኑን በተለያዩ መገናኛ ብዙኋን ሲገለፅ ቆይቷል። ይህ በመንግስት የውጪ ምንዛሪ ወጪ ላይ የሚፈጥረው ጫና ቀላል አይደለም።

ሁኔታዎች በቀላሉ መሻሻል ካልቻሉና የድርቁ አድማስ እየሰፋ የሚሄድ ከሆነ በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረው አሉታዊ ጫና በዚያ መጠን እየሰፋ የሚሄድ መሆኑ ጥርጥር የለውም። ችግሩ ለምን ያህል ጊዜ ሊቆይ ይችላል የሚለው ጉዳይ በተፈጥሮ ችሮታ ላይ የተንጠለጠለ የመሆኑ ጉዳይ ደግሞ ፈተናውን ያከብደዋል። በመንግስት ባለስልጣናት በኩል ድርቁ እየተባባሰ የሚሄድ ከሆነ የተለያዩ የልማት በጀቶችን ሳይቀር ታጥፈው መንግስት እርዳታ የማቅረቡ ስራ ላይ ተኩረቱን አድርጎ የሚረባረብ መሆኑን በተደጋጋሚ ገልጿል። ይህ ደግሞ ሌላኛው ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ነው። የአንድ መንግስት በጀት በአመዛኙ ለፍጆታ እየዋለ ሲሄድ የኢኮኖሚውን መፃኢ እድገት እንደሚገታው ጥርጥር የለውም። መንግስት በአንድ በኩል ለዕህል ግዢ ከፍተኛ የሆነ የውጪ ምንዛሪን ያወጣል፤ በሌላ መልኩ አስገዳጅ ሁኔታዎች የሚፈጠሩበት ከሆነ ደግሞ የልማት ፕሮግራሞችን ለማጠፍ ይገደዳል።

የአገር ውስጥ ሸመታና የምግብ ዋጋ ግሽበት

መንግስት ለድርቅ ለተጋለጠው ህብረተሰብ የእርዳታ እህልን ለማቅረብ የአገር ውስጥ ግዢዎችን ጭምር ሳይቀር የሚጠቀም መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልፅ ቆይቷል።  ችግሩ የተፈጠረው በቤተሰብ ደረጃ እንጂ በአገር አቀፍ ደረጃ  ሲታይ የምግብ እህል ዋስትና ተረጋግጧል የሚሉ መረጃዎች በተደጋጋሚ የመሰማታቸውም ሚስጥር ይህ ነው።ይህ ማለት በድርቅ የተጠቃው የህብረተሰብ ክፍል በቂ ምርት ባይኖረውም በሌላ አካባቢ ግን በቂ ምርት አለ ማለት ነው። በመሆኑም መንግስት ትርፍ ምርት ያለውን ለማካካስ በጀት መድቦ ወደ አገር ውስጥ እህል ሸመታ መግባቱ አይቀሬ ነው። በዚህ በኩል ሰፊ ስራን እንዲሰራ ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ እህል ንግድ ድርጅት ነው። ድርጅቱ በአገር አቀፍ ደረጃ በተዋቀሩት የክልል ቅርንጫፍ ጣቢያዎቹ አማካኝነት በጀት መድቦ በየዓመቱ ሰፊ የእህል ግዢን ያከናውናል።

ከዚህ ቀደም በመንግስት በኩል የእህል ግዢ ሲፈፀም ሁለት መሰረታዊ ግቦችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ነበር። በአንድ መልኩ ገበሬው የእህል ዋጋ እንዳይወድቅ ለመከላከል ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ የመንግስትን የመጠባበቂያ ክምችት ከፍ ለማድረግ ነው። በአሁኑ ሁኔታ ሲታይ ከውጪ የእህል ምርትን መግዛት የውጪ ምንዛሪ ፈተና የመሆን ፈታኝ ደረጃ ላይ ከደረሰ፤ መንግስት ሁለት አማራጮችን በስፋት ለመጠቀም ይገደዳል።

በአንድ አቅጣጫ የአገር ውስጥ ግዢን በስፋት ማካሄድ ሲሆን በሌላ አቅጣጫ ደግሞ የውጪ ረድኤት ድርጅቶችን እገዛ መማፀን ይሆናል። ከተረጂው ቁጥር ስፋት አንፃር መንግስት የአገር ውስጥ ግዢን በስፋት የሚያከናውን ከሆነ በአገር ውስጥ የእህል ዋጋ ማሻቀብ ላይ የራሱን የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖን አያሳድርም ማለት አይቻልም። ለኢትዮጵያ ያለፉት አመታት የግሽበት ፈተና ዋነኛውን ድርሻ የወሰደው የመሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች ዋጋ ማሻቀብ መሆኑም ሊዘነጋ አይገባውም።

የድርቁ ደረጃዎችና ቀጣይ ፈተናዎች

ድርቁ በቀጣይ ምን አይነት ደረጃ እንደሚኖረው ከወዲሁ መተንበይና መወሰን አይቻልም። የክረምቱ ዝናብ እንዲሁ ያለፈ በመሆኑ በቀጣይ ሊጠበቅ የሚችለው የበልግ ዝናብ ነው። ይህም ካለሆነ የመጨረሻው አማራጭ የሚሆነው የቀጣዩን ዓመት የክረምት ዝናብ መጠበቅ ይሆናል። በአሁኑ ሰአት ለድርቅ ተጋልጦ የእርዳታ እህል የሚጠብቀው አርሶ አደር እስከ ክረምት መግቢያ ብሎም በቀጣይ ዝናብ ጠብቆ የሚዘራው እህል እስኪደርስ የረድኤት እጅን የሚጠብቅ መሆኑ ጥርጥር የለውም። ጥያቄው እርዳታን መጠበቁ ሳይሆን ቀጣዩ የበልግና የክረምት ዝናብስ ምን ያህል አስተማማኝ ነው? የሚለው ጉዳይ ይሆናል።

የዝናቡ ሁኔታ የተፈጥሮ ጉዳይ በመሆኑ በተጨባጭ እንዲህ ይሆናል ብሎ መናገር አስቸጋሪ ይሆናል። በቀጣይ ዝናብ ይዘንባል ተብሎ እንደሚጠበቀው ሁሉ ያለፈው አይነት የተዛባና የሳሳ የክረምት ወቅትም ሊፈጠርም ይችላል ብሎ መጠራጠርም አስፈላጊ ነው። በዚህ ከቀጠለ ቀጣዩን ፈተና የበለጠ የከበደ ያደርገዋል። ይህ ከሆነ አሁን ያለው የመንግስት የእርዳታ እህል የማቅረብ አቅም አሁን ባለበት ደረጃ ምን ያህል  ይቀጥላል? የሚለው ጥያቄም መጠየቅ አለበት።

መንግስት በማኛውም አጋጣሚ የእርዳታ እህል በድርቅ ለተጎዳው ህዝብ ማቅረብ እየተሳነው ከሄደ ሊፈጠሩ የሚችሉት ቀጣይ ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች እጅግ የከበዱ ይሆናሉ። አርሶ አደሩ ባለበት ቦታ እርዳታን ማግኘት ካልቻለ አካባቢውን ጥሎ ለመሰደድ ይገደዳል። ገበሬውና ቤተሰቡ ተሰዶ ወደ ከተማ እንዳይገባ ለመከላከል የመጨረሻው አማራጭ የሚሆነው የእርዳታ መቀበያ ማዕከላትን በማቋቋም የእለት ምግብን ማደል ነው። ይህ እጅግ ከባድ የሆነ ፈተና ነው።

ለድርቅ የተጋለጠው አርሶ አደር ወደዚህ  ደረጃ ከደረሰ  የእርዳታ አሰጣጡ ሁኔታ ከስንዴ ወደ ዱቄት እደላ ይለወጣል፣አልሚ ምግቦችንና ዘይትን ማደል ግድ ይላል፣ማብሰያ ብረድት ድስቶችንና መመገቢያ የፕላስቲክ ሳህኖችን ሳይቅር ማደልን ይጠይቃል። እነዚህ ሁሉ ሲታዩ  በቀጣይ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች እንደሚኖሩ ጥርጥር የለውም።

የዝናቡ ሁኔታ ተስተካክሎ ለድርቁ የተጋለጡት አርሶ አደሮችም ሆነ አርብቶ አደሮች ወደ ነበሩበት ሰብል የማምረት ስራ እንዲመለሱም የሚጠይቀው ቀጣይ የመቋቋም ስራም ቀላል አይሆንም። አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ ከብቶቹ  በተከሰተው ድርቅ ከሚሞቱ  የተወሰኑ የቁም እንስሳቱን ሸጦ በተወሰነ ደረጃ የእህል ሸመታን እንዲያካሄድ ምክረ ሀሳብ እየተሰጠው ይገኛል። ይህ ከሆነ በቀጣይም ቢሆን አርሶ አደሩንም ሆነ  አርብቶ አደሩን የማቋቋም ስራን የሚጠይቅ ይሆናል።  ይህ ቀጣዩ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ፈተና ይሆናል።

የግብርና ምርት መረጃ አሰባሰብ ጉዳይ

ማዕከላዊ ስታትስቲክስ የራሱን የሆነ ሳይንሳዊ ጥናት በማካሄድ በሰብል ምርት ያለውን አድገትም ሆነ መቀነስ በግልፅ ያስቀምጣል። ይህ ኤጀንሲው በስልጣን የተሰጠው ሀላፊነትና ተግባር ነው። ይህ መረጃ የህብረተሰቡ ግብአት እንደዚሁም የመንግስት የውሳኔ መነሻ ሀሳብም በመሆን ያገለግላል። አለም ባንክን ለመሳሰሉ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጋራ ለሚሰሩ አለም አቀፍ ተቋማትም ኦፊሴል የመረጃ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግለው ይሄው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ  ኤጀንሲ መረጃ ነው።

መረጃ የፖሊሲ ግብአት ነው፣ መረጃ የውሳኔ መሰረት ነው፣ በእጅ ላይ ያለ መረጃ ቀጣይ አካሄድ ምን ሊሆን እንደሚችል አቅጣጫን ይጠቁማል። ይህ ከሆነ የመረጃን ትክክለኛነትን ያህል የተዛባ መረጃም በዚያው መጠን ሊሰጥ የሚችለውን ውሳኔም የተዛባ ያደርገዋል።

በመንግስት አስፈፃሚ መስሪያቤቶች ባሉ መዋቅሮች ከታች ወደላይ እየተሰበሰቡ በመጨረሻ ለውሳኔ ግብአትና ለህዝብ መረጃ ፍጆታ የሚውሉ መረጃዎች አስተማማኝነታቸው ምን ያህል እርገጠኛ እንደሆኑ ብዙ ያነጋግራሉ።  “ብዙ ሰርተናል” ለማለት ያህል ለበላይ ተጠሪ መሰሪያቤቶች የሚቀርቡ የስኬት ሪፖርቶች የውሳኔ ግብአት ሆነው የሚያገለግሉ ከሆነ ተሳስቶ ማሳሳት ይሆናል።

በዚህ ረገድ ሙሉ ስልጣንና ኃላፊነት በህግ አግኝቶ መረጃዎች በመስክ ሰብስቦና ሳይንሳዊ በሆኑ ልዩ ልዩ ዘዴዎች ተንትኖ ለሚመለከታቸው አካላት ማቅረብ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ኃላፊነት ነው። የሚወስዳቸው የናሙና ምርቶች በምን መልኩ አገራዊ ውክልና ይዘው እንደሚተነተኑና ትንበያም እንደሚሰጥባቸው አሰራሩ ያለው በዚሁ መስሪያ ቤት እጅ ነው።

ይህ በበርካታ አገራት ያለ ማዕከላዊ አሰራር ነው። ለምሳሌ በአሜሪካ ግብርናን በተመለከተ ሙያዊ ትንተና ስራዎችን የመስራት ኃላፊነት የተሰጠው ለአገሪቱ የግብርና ስታትስቲክስ አልግሎት(National Agricultural statistics Service) ነው። መስሪያቤቱ የግብርና ምርቶችን ናሙና በመሰብሰብ መረጃዎችን ያሰራጫል፣ የአምራቾችን የዋጋ ጥናት ያካሂዳል፣ በሰብል የተያዘ የመሬት ስፋትንና የምርት መጠንንም በመሰብሰብ የራሱን የሆነ ስታቲስቲክሳዊ መረጃዎችን ይፋ ያደርጋል።

ይህ መረጃ ለገበሬዎች፣ ለመንግስት ለሸማቾች፣ ለኢንዱስትሪ ባለቤቶችና ለመሳሰሉት ዋነኛ ኢንዱስትሪ ግብአት በመሆን ያገለግላል። መረጃው ዋነኛ የመረጃ ምንጭ (Authorized report) ሆኖ ያገለግላል።የአገሪቱ ኦፊሴላዊ የመረጃ ሪፖርት ሆኖ በማናቸውም አካላት እየተጠቀሰ የሚሰራቸው የዚሁ ድርጅት መረጃ ነው። በኢትዮጵያ ረገድ በተለያዩ የመንግስት መገናኛ ብዙኋን በተደጋጋሚ እንደሚሰማውና እንደሚታየው አርሶ አደሩ ማሳ ድረስ እየገቡ “ገበሬው በግብርና ባለሙያዎች እየታገዘ ምርቱን በሶስትን በአራት እጥፍ እያሳደገ ነው። በዚህ ዓመት በዚህ ዞንና ክልል ይሄንን ያህል ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል፣ አርሶ አደሩ በእቅድ ዘመኑ መጀመሪያ ተይዞ ከነበረው የምርት መጠን በዚህን ያህል እጥፍ ብልጫ ምርትን አመረተ።

ገበሬው አዳዲስ አሰራሮችንና የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አምና ካመረተው በላይ ይሄንን ያህል ኩንታል ምርትን ማምረት ቻለ፤ አርሶ አደሩ የግብርና ባለሙያዎች በሚሰጡት ስልጠና በመታገዙ፤ የዚህ ክልል  አመታዊ የምርት መጠን በዚህን ያህል ፐርሰንት ማደጉን የእገሌ የቢሮ ኃላፊ ገለፁ፤ አርሶ አደሩ ለአንድ ሄክታር መሬት ይጠቀም የነበረውን አንድ ኩንታል የማዳበሪያ ግብአት ወደ አራት ኩንታል ከፍ ማድረግ በመቻሉ ቀደም ሲል በሄክታር ሲያገኝ የነበረው የምርት መጠን በዚህን ያህል እጥፍ  ማደጉን ገለፀ።” የሚሉትና የመሳሰሉት የግብርና ምርታማነት መረጃዎችና ትንበያዎች አሁን ድርቅ ሲከሰት ምስክር ሆነው መቅረብ አልቻሉም። መረጃ አሰባሰቡም ሆነ ትንበያው ከአንድ ኦፊሴል ከሆነ አካል መወሰድ እንዳለበት የሌሎች አገራት ልምድ ያሳያል።

ምንጭ ስንደቅ

 

Leave a Reply