Saturday, 12 December 2015 11:09
አለማየሁ አንበሴ
– “ከህዝቡ ጋር መግባባት ሳይፈጠር ማስተር ፕላኑ አይተገበርም” የክልሉ ፕሬዚዳንት
ከማስተር ፕላኑ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጥያቄዎችን መንግስት እያስተናገደ ያለበው አግባብ ትክክል አለመሆኑን የገለፁ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ በኦሮሚያ ከተፈጠረው ተቃውሞ እንዲሁም፣ በጐንደር ማረሚያ ቤት ከተነሳው እሣት ጋር ተያይዞ ተፈፀመ ያሉት ግድያ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠይቀዋል፡፡
“በሰላማዊ ተቃዋሚዎች ላይ መተኮስ አግባብ አይደለም” ያለው ሰማያዊ ፓርቲ፤ መንግስት ለህዝብ ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲሰጥ ያሳሰበ ሲሆን ኢዴፓ በበኩሉ፤ የዜጐች የመብት ጥያቄዎች በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡ መንግስት በኦሮሚያና በጐንደር ከህዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን እያስተናገደ ያለበት መንገድ እንደሚያሳስበው የገለፀው ኢዴፓ፤ ከማስተር ፕላኑም ሆነ ከጐንደር ከተማ ማረሚያ ቤት ጋር በተያያዘ የተከሰተው ጉዳት በገለልተኛ አካል እንዲጣራና አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል፡፡
መንግስት የሚከተለው የፌደራሊዝም አወቃቀርና የፖሊሲ ክፍተት በኦሮሚያ ከማስተር ፕላኑ ጋር ተያይዞ ለተፈጠረው ችግር ሰበብ እንደሆነ ለአዲስ አድማስ የገለፁት የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ፤ የመሬት አጠቃቀም፣ የከተማ አከታተምና የህዝብ አሠፋፈር ፖሊሲ ችግር የተቃውሞው መንስኤ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በኦሮሚያ አካባቢ ለተፈጠረው ችግር ምክንያቱ ማስተር ፕላኑ ብቻ አይደለም፤ የዲሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብትና የመልካም አስተዳደር እጦትም ለተቃውሞው መነሻ እንደሆነ ፓርቲው ጠቁሟል፡፡
የማስተር ፕላኑን ጉዳይ ሰነዶችን ከመረመርን በኋላ አቋም እንወስዳለን ያሉት የመድረክ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው በበኩላቸው፤ ኦፌኮ በመድረክ ግንባር ስር ሆኖ መግለጫ እየሰጠ ያለው በተናጥል መግለጫ የመስጠት መብቱን ተጠቅሞ መሆኑን ጠቁመው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በተቃውሞ ምክንያት የሰው ህይወት መጥፋቱን መድረክ አጥብቆ ይቃወማል ያሉት አቶ ጥላሁን፤ መንግስት ለህዝብ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠት እንዳለበት ገልፆ የማስተር ፕላኑን ጉዳይም በህገመንግስቱ መሠረት መፍታት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል የሆኑት የኦሮሞ ኦቦ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሞ ነፃነት አንድነት ግንባር፣ የመላ ኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲና የኦሮሞ ብሄራዊ ኮንግረስ ፓርቲዎች በጉዳዩ ላይ ባለ 10 ነጥብ የጋራ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል፡፡
የፖለቲካ ድርጅቶቹ በፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ጉዳዩን ለውይይት አቅርበው ገዠው ፓርቲ ፕላኑን ለህዝብ በግልፅ እንዲያስረዳና የአንድም ዜጋ ህይወት እንዳይጠፋ ሲያሳስቡ መሰንበታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ለተቃውሞ መነሻ የሆነው የጨፌ ኦሮሚያ፣ የኦሮሚያ ከተሞችን በተመለከተ በቅርቡ ያፀደቀው አዋጅ መሆኑን የጠቆሙት ፓርቲዎቹ፤ አዋጁ በአስቸኳይ እንዲሻርና የህዝቡ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እንዲመለስ የጠየቁ ሲሆን ተቃውሞ በሚያሰሙ ተማሪዎች ላይ እየተወሰደ ያለውን የኃይል እርምጃም አጥብቀው እንደሚቃወሙ ገልፀዋል፡፡ የፌደራል ፖሊስ ኃይል በአስቸኳይ የዩኒቨርሲቲዎችን ቅጥር ለቆ እንዲወጣ፣ በምትኩም መሳሪያ ያልታጠቁ የፀጥታ ኃይሎች ጥበቃ እንዲያደርጉና የዜጎች ተቃውሞ የማቅረብ መብት እንዲከበር ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል፡፡
“በተማሪዎችና በወላጆቻቸው ላይ የግድያና የአካል ጉዳት ያደረሱ ኃይሎች በአስቸኳይ በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዲሁም፤ የታሰሩ ዜጎችም እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡
መንግስት ለተቃውሞ ምክንያት ነው የተባለውን ማስተር ፕላኑን ካልሠረዘ በአገር ውስጥ በውጭ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚጠራ ባለፈው ሳምንት ያስታወቀው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፤ በክልሉ የተፈጠረው ተቃውሞ መቀጠሉንና የመንግስት የሃይል እርምጃም መጠናከሩን ጠቅሶ መንግስት ለተቃውሞው ሃላፊነት ወስዶ፣ ችግሩን በህጋዊና ሠላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጠይቋል፡፡ ከማስተር ፕላኑ ጋር በተያያዘ ተቃውሞ ከተነሳ ጊዜ ጀምሮ 10 ሰዎች መገደላቸውን፣ ከ150 በላይ መቁሰላቸውንና ከ500 በላይ ሰዎች መታሠራቸውን የገለፀው ፓርቲው፤ ለሟች ቤተሰቦች ካሳ እንዲከፈልና የታሠሩ እንዲፈቱም ጠይቋል፡፡ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድር በበኩላቸው ትናንት በሰጡት መግለጫ “በሁከቱ ምክንያት ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የክልሉ መንግስት ጥልቅ ሀዘን እንደሚሰማው ገልፀዋል፡፡
ማስተርፕላኑና በቅርቡ በኦሮሚያ ም/ቤት ስለከተሞች የወጣውን አዋጅ የተቃወመው ኦፌኮ፤ በተለይ የማስተር ፕላኑ እቅድ እንዲሠረዝ አበክሮ ጠይቋል፡፡
“የመለስ መንደር” የሚባሉ ፕሮጀክቶች በአስቸኳይ ይቁሙ” ያለው ኦፌኮ፤ የፌደራል የመሬት ልማት ኮርፖሬሽን የተሰኘው ተቋም የክልሎችን መሬት የማስተዳደር መብት የሚነጥቅ በመሆኑ ተግባራዊ እንዳይሆንም አሳስቧል፡፡
ፓርቲው አያይዞም “በአማራና በቤኒሻንጉል ክልል፣ ከህዝቦች እውቅና ውጪ መሬት ለጐረቤት አገር ለመስጠት እየተደረገ ያለው ዝግጅት በአስቸኳይ ይቁም” ሲል ጠይቋል፡፡
ባለፈው ሳምንት በጐንደር ወህኒ ቤት የተነሳውን የእሣት ቃጠሎ ተከትሎ የሰው ህይወት በመጥፋቱ የተሰማውን ሀዘን የገለፀው ፓርቲው የሟቾች ጉዳይ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድም ጠይቋል፡፡
በኦሮሚያ ከማስተር ፕላኑ ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ተቃውሞና በጐንደር ማረሚያ ቤት በደረሰው አደጋ ዙሪያ የአቋም መግለጫ ያወጡት የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና ሰማያዊ ፓርቲም መንግስት ለችግሮቹ እየሰጠ ያለውን ምላሽ ኮንነዋል፡፡
ሰሞኑን የተማሪዎች ተቃውሞ ረገብ ያለ ቢመስልም በተለያዩ መንገዶች መቃወማቸውን ቀጥለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኦሮሞ ተወላጅ ተማሪዎችን ጨምሮ በተለያዩ የኦሮሚያ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎች ጥቁር ልብስ ለብሶ ሜዳ ላይ በመሰባሰብ በፀጥታ ለደቂቃዎች በመቀመጥና በመቆም እንዲሁም የተጣመረ ሁለት እጅን ወደ ላይ ከፍ አድርጐ በማሳየት ተቃውሞ ሲያሰሙ መሠንበታቸውን ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
የክልሉ መንግስት በበኩሉ፤ ቀደም ሲል ተማሪዎች በግንዛቤ እጥረት የተነሳ በቅርቡ በጨፌ ኦሮሚያ ውይይት ተደርጐበት የነበረው የኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች ህዝባቸው ፍቃደኛ ከሆነ ለጋራ ልማት ሊጣመሩ ይችላሉ የሚለው አዋጅ በተዛባ መልኩ ተተርጉሞ በመቅረቡ የተፈጠረ ችግር ነው ብሏል፡፡ በጨፌው ውይይት ተደርጐበት የነበረው አዋጅ በኦሮሚያ ውስጥ የሚገኙ ተዋሳኝ ከተሞች አብረው ለማደግ ከፈለጉ ተጣምረው ልማታቸውን ማከናወን የሚያስችላቸው መሆኑን የጠቆመው የክልሉ መንግስት፤ ይህ የሚሆነው የሁለቱ ከተማ ህዝቦች ሙሉ ፍቃደኛነት ሲኖር ብቻ ነው ብሏል፡፡
ትናንት በጉዳዩ ላይ መግለጫ የሰጡት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሙክታር ከድር፤ ማስተር ፕላኑ ህዝቡ ሳይስማማበት እንደማይተገበር ገልፀው ሁከት የተፈጠረው እቅዱን ግልፅ በማድረግ ረገድ ውስንነት በመኖሩ ነው ብለዋል፡፤
“ሁከቱ እንዲባባስ ያደረጉ ፀረ ሰላም ኃይሎች ከድርጊታቸው በአስቸኳይ የቆጠቡ” ያሉት አቶ ሙክታር ተማሪዎች ተረጋግተው ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በጨፌ የቀረበው አዋጅ ፈጽሞ ከማስተር ፕላኑ ጋር የማይገናኝ ነው ያሉት የኦሮሚያ ክልል ኃላፊዎች፤ ማስተር ፕላኑም ቢሆን ህዝብ ተወያይቶበት አምኖበት ሲፈቅድ ብቻ የሚተገበር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ሰሞኑን በአምቦ ማስተር ፕላኑን መነሻ አድርጎ በተከሰተው ተቃውሞ ዙሪያ በክልሉ መንግስት ኃላፊዎች ከነዋሪዎች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን ተቃውሞው የጥቂት ተማሪዎች እንጂ የህዝቡ አይደለም የሚሉ አስተያየቶች ተስተጋብተዋል፡፡ ሆኖም በጉዳዩ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ አለመሰራቱ ለተከሰተው ችግር ምክንያት መሆኑን የጠቀሱም አልጠፉም፡፡
ምንጭ አዲስ አድማስ