በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት መስመር ዝርጋታ በመሬት ውስጥ ለማከናወን፣ ሲባል ከነባር ስፍራው ተነሥቶ የነበረው የሰማዕቱ ቅዱስ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልትን ከነበረበት ቦታ መልሶ ለመትከል የመሠረት ግንባታ ተጀመረ፡፡
የሐውልቱን መሠረት ግንባታ የሚያካሂደው አሰር ኮንስትራክሽን መሆኑን የተናገሩት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፈቃደ ኃይሌ፣ በጥር 2008 ዓ.ም. ሐውልቱ ወደነበረበት ይመለሳል ብለዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ለዚህ ፕሮጀክት የሚያስፈልገውን በጀት እንደመደበም ኢንጂነር ፈቃደ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ቀላል የከተማ ባቡሩ ፒያሳ ዳግማዊ ምኒልክ አደባባይን አልፎ በምድር ውስጥ የሚጓዝ በመሆኑ፣ ለዚህም 20 ሜትር ጥልቀት ወደታች በመቆፈሩ ነበር ግንባታውን ለማከናወን የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ሚያዝያ 24 ቀን 2005 ዓ.ም. የተነሣው፡፡ በወቅቱ በነበረው ዕቅድ ሐውልቱ ከዓመት በኋላ እንደሚመለስ ተነግሮ ነበር፡፡
አንዳንድ የሥነ ግንባታ ባለሙያዎች ባቡሩ ከሥር የሚያልፍ ሆኖ ሐውልቱ ደግሞ ከላይ በተገነባው አደባባይ ላይ ሲያርፍ ባቡሩ ከሥር በሚያልፍበት ወቅት የሚፈጠረው ንዝረት በሐውልቱ ላይ መሰንጠቅ ሊፈጥር ይችላል የሚል አስተያየት አንፀባርቀው የነበረ ቢሆንም፣ ግንባታው መርገብገብን (ቫይብሬሽንን) እንዲችል እንደሚደረግ መነገሩ ይታወሳል፡፡
የቀላል ባቡሩ ዋሻ ግንባታ ተጠናቆ ወደ አገልግሎት መግባቱን ተከትሎ ሐውልቱን ወደ ቦታው ለመመለስ እንደሚቻልና ሐውልቱ በሚቆምበት በኩል የሚያልፈውን መስመር እንቅስቃሴ ያገናዘበ ዲዛይን በቀላል ባቡር ሥራ ተቋራጭ መሠራቱን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ኅዳር 28 ቀን 2008 ዓ.ም. አስታውቋል፡፡
ከሰማንያ ዓመት በፊት በሐምሌ ወር ሰማዕት የሆኑት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የኢጣሊያ ፋሺስት በ1928 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ጦርነትን ባነሣ ጊዜ ከጦሩ ባለመለየት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ተከትለው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ዘምተዋል፡፡ ፋሺስቱ በማይጨው የመርዝ ጦርነት ከማድረጉ የተነሣ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሲበታተንም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የተመለሱት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሔደው ለአገርና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን ለሰላሌ አርበኞች በመስበክም ይታወቃሉ፡፡
ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የራሷን ጳጳሳት በ1921 ዓ.ም. በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ጊዜ ስታስሾም አንዱ አቡነ ጴጥሮስ ነበሩ፡፡ በ1875 ዓ.ም. የተወለዱት አቡነ ጴጥሮስ፣ ‹‹ጳጳስ ዘምሥራቀ ኢትዮጵያ” ተብለው፣ “ራሱ በሽሎ መለስ፣ እግሩ አቦክ ፈረንሳዊ ወሰን ድረስ (ጅቡቲ)›› 21 አካባቢዎችን ያስተዳድሩ ነበር፡፡
አርበኞች አዲስ አበባን በሁለት አቅጣጫዎች በሰሜናዊ ምዕራብና በደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ ለመቆጣጠር ውጊያ በከፈቱበት ጊዜ የተማረኩት አቡነ ጴጥሮስ፣ ለፋሺስት እንዲገዙ የኢጣሊያ መንግሥት ገዢነትንም አምነው አሜን ብለው እንዲቀበሉ ግፊት ቢያደርጉባቸውም፣ ሕዝቡም ሆነ አገሪቱ ለፋሺስት ጣሊያን እንዲገዙ እንዲቀሰቅሱ ቢያዛቸውም፣ ‹‹እምቢ ለአገሬና ለሃይማኖቴ›› ብለው፣ ሕዝቡ ለፋሽስት ጣሊያን እንዳይገዛ በማውገዛቸው ለሰማዕትነት ያበቃቸውን የሞት ጽዋ ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም. መቀበላቸው ይታወቃል፡፡ ለመታሰቢያቸውም ሐምሌ 16 ቀን 1938 ዓ.ም. ሐውልት እንደቆመላቸው ይታወቃል።
በፋሺስት ኢጣሊያ ከ80 ዓመታት በፊት ሰማዕት የሆኑት አቡነ ጴጥሮስ የተቀበሩበት ቦታ በአዲስ አበባ በስተደቡብ በለቡ አካባቢ ከአምስት ዓመት በፊት መገኘቱን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ማስታወቋ ይታወሳል፡፡ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፉሪ ምስካበ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ሃይማኖትና መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በወቅቱ ለሪፖርተር እንዳስታወቀችው፣ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕት ከሆኑ በኋላ የተቀበሩት ፋሺስቶች በመኖርያነትና በእስር ቤትነት ይጠቀሙበት በነበረው “ሙኒሳ ጉብታ” ላይ ነው፡፡
የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይል በሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም. ሰማዕቱን ገድሎ አስክሬናቸውን አደባባይ ላይ ጥሎ ከዋለ በኋላ፣ ቀብራቸው በምስጢር መፈጸሙን መዛግብት እንደሚያስረዱ ያስታወሰችው ቤተ ክርስቲያኗ፣ የእኚህ ታላቅ አባት ቀብር በምስጢር የተፈጸመበት ቦታ ለማግኘት የተለያዩ ምሁራን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የታሪክ ሰነዶችን ሲመረምሩ ቢቆዩም፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ “ከአዲስ አበባ በስተደቡብ በምስጢር ቀበሯቸው” ከሚል ጠቅላላ ፍንጭ ያለፈ ምንም ዓይነት የተረጋገጠ ማስረጃ ሳይገኝ ቆይቶ ነበር ፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም የቆመው  የሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ሁለተኛው ሐውልታቸው ሲሆን፣ የመጀመሪያው ሐውልት የኢትዮጵያ ጳጳሳት የአለባበስ ትውፊትን ያልተከተለ በመሆኑ ተነቅሎ በመናገሻ ደብረ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አፀድ እንዲገባ መደረጉ ይታወሳል፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በክብር የተቀመጠውን የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ወደ መንበሩ በአግባቡ ለመመለስ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮና የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን በጋራ ያቋቋሙት ኮሚቴ ሥራውን እየሠራ መሆኑ ታውቋል፡፡
የቅድስና ማዕረግ ለብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የሰጠችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉዳዩን እየተከታተለች ሲሆን፣ ሐውልቱ ወደ ስፍራው ሲመለስ ከ80ኛ ዓመት መታሰቢያ ጋር ልዩ መሰናዶ እንደሚኖር የቤተ ክርስቲያኒቷ የቅርስና የቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ቀሲስ ሰሎሞን ቶልቻ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ሚያዝያ 24 ቀን 2005 ዓ.ም. ከስፍራው ለጊዜው የተነቀለው ሐውልት የቀላል ባቡር ግንባታ ሥራው በተያዘለት ጊዜ ሲፈጸም፣ አዲስ በሚገነባው አደባባይ ላይ ሳይለወጥ በ2006 ዓ.ም. እንደሚመለስ መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

 

Leave a Reply