Thursday, 24 December 2015 11:48

“የሱዳንን ወዳጅነት ለማግኘት የጎንደርን መሬት ቆርሶ መስጠት ተገቢ አይደለም”

አቶ አበባው መሀሪ

         የመኢአድ ፕሬዝደንት

– ለታህሳስ 24 ህዝባዊ ውይይት ጠርቷል

 

በይርጋ አበበ

ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረበት ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት 24 ዓመታት ከግማሽ ጊዜ ውስጥ እንደ ዘንድሮው በአገሪቱ ውጥረት የተስተዋለበት ዘመን አልነበረም ማለት ይቻላል። ፓርቲው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ተካሂዶ በነበረው አምስተኛው ዙር አገር አቀፍ ምርጫ 547 ወንበሮች ያሉትን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአጋር ድርጅቶቹ ጋር ሙሉ በሙሉ በተቆጣጠረበትና ፓርላማውም ስራ በጀመረበት በዚህ ወቅት አገሪቱ በውስጥ እና በውጭ ጉዳዮች ተወጥራ ትገኛለች።

ከአገር ውጭ ያሉ ፈታኝ ጉዳዮች የህዳሴውን ግድብ ተከትሎ የግብጽ አቋም ግድቡ ቢቻል እንዳይገደብ ካልተቻለ ደግሞ ግንባታው ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ ውትወታ መጀመሯ፤ ላለፉት 100 ዓመታት በሁለቱም አገራት ተቀባይነት ያልነበረው የኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር ጉዳይ በዚህ ዓመት እንደገና መነሳቱ እና ኢህአዴግም የሱዳንን ጥያቄ ለመመለስ የተዘጋጀ መሆኑ የሚሉት ቀጥተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ሲሆኑ የደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት እልባት አለማግኘቱ እና ላለፉት 17 ዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር ሰላም ያልሆነው የኤርትራ መንግስት ደግሞ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያ ላይ ተጽእኖ እየፈጠሩ ይገኛሉ።

በአገር ውስጥ ደግሞ የተለያዩ የደቡብ ክልል ብሔሮች ራሳችንን በራሳችን እንድናስተዳድር የዞንነት መብት ይሰጠን ከሚሉት ጀምሮ የቅማንት እና የአማራ ብሔረሰብ ውዝግብ፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን የኖኖ ወረዳ አስተዳዳሪዎችና የወረዳው ፖሊስ አዛዥ በናኖ አሌ ቀበሌ ነዋሪ በሆኑት የአማራ ብሔር ተወላጆች በንብረታቸውና በቤታቸው ላይ በፈጸሙት ቃጠሎ ምክንያት የብሔሩ ተወላጆች መፈናቀል፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያለው አለመረጋጋት እና በቅርቡ ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማን ማስተር ፕላን አንቀበልም ከመሬታችንም አንፈናቀልም ሲሉ ተቃውሞ ያነሱ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች እና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ኢህአዴግን እንዳለፉት ዓመታት ነገሮችን በእርጋታ እንዲያስብ ሳይሆን አፋጣኝ መልስ እንዲሰጥ የሚያስገድዱ ሁነቶች ናቸው።

ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በቅርቡ ጉምቱ የኢህአዴግ ባለስልጣናትን ሰብስበው የመልካም አስተዳደር ችግር እስከ ዶቃ ማሰሪያችን አንቆ ይዞናል ይህንን ችግር መቅረፍ ደግሞ የህልውናችን ጉዳይ ነው ሲሉ የተናገሩበት ኢህአዴግ ራሱ ያመነው የመልካም አስተዳደር ችግር ሌላው የመንግስት ራስ ምታት ሆኖ የቀረበ ጉዳይ ነው። እነዚህ ጉዳዮች በውስጥም በውጭም ወጥረው የያዙትን ኢህአዴግ መራሹን መንግስት በአገር ቤት እና ከአገር ውጭ ያሉ ተቃዋሚዎች የተለያዩ ሀሳቦችን በማቅረብ ችግሮች ሁሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ እየጠየቁ ይገኛሉ። ከእነዚህ ፓርቲዎች መካከል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) አንዱ ነው። ፓርቲው ባሳለፍነው እሁድ በጽ/ቤቱ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከፓርቲው አባላት እና ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ውይይት አካሂዶ ነበር።

በውይይት መድረኩ ላይም በተለይ ከሱዳን ጋር ስላለው የድንበር ማካለል ጉዳይ እና በአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ ተወያይቷል። በውይይቱም የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አበባው መሃሪ ከጋዜጠኞች እና ከፓርቲው አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። በቅርቡ የአዲስ አበባ ከተማን ማስተር ፕላን በመቃወም እና በቅማንት እና በጎንደር መካከል በተነሳው ግጭት የተሰው ዜጎችን በጧፍ ማብራት አስቧል።

የችግሮቹ መጀመሪያ

አቶ አበባው በመግለጫቸው “ደርግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 41 ዓመታት የኢትዮጵያ ህዝብ እና ኢትዮጵያ በስቃይ እና በማዕበል ውስጥ ይገኛሉ” በማለት ንግግር የጀመሩ ሲሆን አቶ አበባው ለንግግራቸው አስረጂ ምክንያታቸውን ሲያቀርቡም “ደርግ አገሪቱን በሚገዛበት ወቅት በፖለቲካ አመለካከት እየፈረጀ ህዝቧን ጨረሰ ምሁራኖቿን ገደለ ኢህአዴግ ደግሞ በጎሳ በመከፋፈል አገሪቱን ወደኋላ ጎትቷታል። ዜጎች በእኩልነት እንዳይንቀሳቀሱ እያደረገ በመሆኑ መንግስት በአገሪቱ ዜጎች እንዳይፈለግ አድርጎታል” ብለዋል።

ዶ/ር በዛብህ ኢትዮጵያዊያን ኢህአዴግን ድጋፋቸውን ስለነፈጉት ኢህአዴግም ፊቱን ከአገር ቤት ወደ ውጭ በማዞር አገሪቱን በባዕዳን ዜጎች አስወርሯታል ሲል ይገልጻል። ለዚህም በርካታ ኢትዮጵያዊያን በተማሩበት ሙያ መስራት እንዳይችሉ በማድረግ ሁሉንም ስራዎች ለውጭ ዜጎች በመስጠት ላይ ይገኛል። ይህን የሚያደርገውም በአገር ቤት ያለበትን ተቃውሞ በውጭ አገራት መንግስታት ድጋፍ በማግኘት የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም ነው ሲል አስታውቋል። እነዚህ ሁሉ ተሰባስበውም አሁን አገሪቱ ያለችበት አስከፊ ደረጃ እንድትደርስ አድርጓታል ሲል ይገልጻል።

በአገሪቱ ስለተከሰተው ድርቅ እና ርሀብ

“በአሁኑ ሰዓት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቻችን በርሃብ እንዲወድቁ ያደረጋቸው በኤል ኒኖ ምክንያት የተፈጠረው ድርቅ ሳይሆን የኢህአዴግ አገዛዝ ነው” ሲሉ የመኢአድ ፕሬዝደንት ገልፀዋል። ፕሬዝደንቱ አያይዘውም፤ “ድርቁ መከሰቱ እውነትነቱ እንዳለ ሆኖ ነገር ግን አርሶ አደሩ መሬቱን በአግባቡ አርሶ ጥሪት እንዳይሰበስብ በሰነፍ የአገዛዙ ካድሬዎች ተጠርንፎ ይውላል። ይህ እንዳለ ሆኖ ደግሞ መሬቱን በመንግስት እየተቀማ ለባለሀብት ተሰጥቶበት የአበባ እርሻ ስለሆነበት ድርቁን እንዳይቋቋም አድርጎታል” ብሏል። በድርቁ ምክንያት የደረሰው የምግብ እጥረት እንዲህ የከፋውም (በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ያመነው የተረጂው ዜጋ ቁጥር ከአስር ሚሊዮን ልቋል) በመንግስት ችግር ነው ሲል ሃሳባቸውን አጠናክረዋል።

ስለ ኢትዮ ሱዳን የድንበር አከላለል ጉዳይ

ቀደም ባሉት ዓመታት ከአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የአማርኛው ፕሮግራም ጋር ቃለ ምልልስ አካሂደው የነበሩት የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም “የሁለቱ አገራት የድንበር አወሳሰን ጉዳይ በየአስር ዓመቱ እየተነሳ በዚያው የሚመለስ ጉዳይ እንጂ አዲስ አይደለም። ከዚህ በፊትም በኃይለሥላሴ እና በደርግ መንግስታት ዘመንም ተነስቶ እንደነበር ይታወሳል። የሰሞኑም (ከዓመታት በፊት ነው) ካለፉት ጊዜያት የተለየ አይደለም” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

ሰሞኑን ግን የሁለቱ አገራት ድንበር የማካለል ጉዳይ እንደ አዲስ የተነሳ ሲሆን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያምም የድንበሩ ጉዳይ በቅርቡ እልባት እንደሚያገኝ መናገራቸውን አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። ሱዳናዊያን ደግሞ ድንበር ማካለሉ የሚከናወነው አሁን በኢትዮጵያ ግዛት ስር ከሚገኙ የሰሜን ጎንደር ግዛቶች መካከል የተወሰነ መሬት እንዲያገኙ ከተደረገ ብቻ ነው የሚል አቋም ያራምዳሉ። በዚህ የተነሳም ኢህአዴግን ተቃውሞ ገጥሞታል። ተቃውሟቸውንም እያሰሙ ይገኛሉ።

የመኢአድ ከፍተኛ አመራሮች በበኩላቸው፤ “እንደሚታወቀው መተማ ከቱርክ ከግብጽ እና ከድርቡሾች ጋር በርካታ ጦርነት የተካሄደበትና ኢትዮጵያዊያን አባቶቻችን ህይወታቸውን ሰውተው ያቆዩት የኢትዮጵያ መሬት ነው። ነገር ግን ኢህአዴግ ከሱዳን መንግስት ጋር ወዳጅነት ለመፍጠር በመፈለጉ ብቻ ሁለቱ አገራት ድንበራቸውን ሲያካልሉ እስከ መተማ ዮሐንስ እንዲሆን ኢህአዴግ ፍላጎቱን እያሳየ ይገኛል። ይህ ደግሞ ለሱዳንም ሆነ ለኢህአዴግ ስለማይበጀው ሁለቱም ወገኖች ቢያስቡበት መልካም ነው” ሲል ይገልጻል።

“የሱዳንን ወዳጅነት ለማግኘት የጎንደርን መሬት ቆርሶ መስጠት ተገቢ አይደለም” የሚሉት የመኢአድ ፕሬዝደንት “ጉዳዩን የጎንደር ጉዳይ ብቻ አድርጎ ማየት ስህተት ነው። ይህ የአገራችን ጉዳይ ስለሆነ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለሚመለከተው ዝም ሊባል አይገባም” ብለዋል። የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች አያይዞም ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን የሱዳን መንግስትም ጉዳዩን ቆም ብሎ ሊያስብበት ይገባል ያለ ሲሆን ሀሳባቸውን ሲገልጽም “የሱዳን መንግስት ሊገነዘበው የሚገባው ዛሬ በዚህ መንግስት ችሮታ (በኢህአዴግ) የኢትዮጵያን መሬት መውሰድ ቢችልም መሬቱ ተወስዶበት ዝም የሚል ኢትዮጵያዊ ባለመኖሩ ነገ በሁለቱ አገራት መካከል ሰላም እንዳይኖር የሚያደርግ ጦርነት የሚያስከትል ውሳኔ መሆኑን ከወዲሁ ሊገነዘበው ይገባል” ብሏል። መንግስታት ግንኙነታቸውን ሊመሰርቱ የሚገባቸው ከመንግስታት ጋር ብቻ ሳይሆን ከህዝብ ጋርም መሆኑን ያሰመሩበት አመራሮቹ አያይዘውም፤ “የሱዳን መንግስትም ኢትዮጵያዊያን ምን ይላሉ ብሎ ሊጠይቅ ይገባል እንጂ ዝም ብሎ ከኢህአዴግ ጋር ባለው ወዳጅነት ተነስቶ የአገሪቱን ድንበር ሊደፍር አይገባውም። ኢህአዴግም ቢሆን ከሱዳን ጋር ከሚመሰርተው ወዳጅነት ይልቅ ከኢትዮጵያዊያን የሚያገኘውን ወዳጅነት ሊያስቀድም ይገባል” ሲሉ አሳስቧል።

ስለ አዲስ አበባ ከተማ የተቀናጀ መሪ እቅ (ማስተር ፕላን)

አዲስ አበባን እና በዙሪያ የሚገኙትን የኦሮሚያ ከተሞች በልማት ያስተሳስራል ተብሎ በመንግስት የተቀረጸውና በኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጬፌ ኦሮሚያ) አዋጅ እንደወጣለት የተነገረው የአዲስ አበባ ከተማ የተቀናጀ ማስተር ፕላን በበርካታ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ተቃውሞን የቀሰቀሰ ጉዳይ ነው። በተቃውሞው ምክንያትም እስካሁን ከ40 በላይ የኦሮሞ ተማሪዎችና ሌሎች ሰዎች መሞታቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እየገለጹ ሲሆን መንግስት በበኩሉ የሟቾች ቁጥር ተጋንኗል የተነሳው ብጥብጥም የኦሮሞ ተወላጆች ያነሱት ሳይሆን ከብጥብጡ ጀርባ ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት በሚያስቡ ጸረ ልማት እና ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ባላቸው ድርጅቶች አነሳሽነት ነው ሲል ገልጿል። እንዲሁም የኦሮሞ ተወላጆች ማስተር ፕላኑን አንቀበልም ካሉ ፕላኑ እንዳይተገበር እንደሚያደርግ የኦህዴድ ጽ/ቤት ማስታወቁ ይታወሳል።

በአንፃሩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ግን ይህን የመንግስት መግለጫ አይቀበሉትም “አዋጅ የሚሻረው በአዋጅ እንጂ በባለስልጣናት መግለጫ አይደለም” ሲሉ መቃወማቸው ይታወሳል። ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡም፤ “ተቃውሞው የተነሳውም መንግስት ዜጎችን ሳያማክር በራሱ መንገድ ወደ ተግባር በመግባቱ ሲሆን ብጥብጡ የተነሳውም የመንግስት ሰላም አስከባሪዎች ተቃውሟቸውን ባነሱ ዜጎች ላይ የወሰዱት የሀይል እርምጃ ነው” ሲሉ አስረድተዋል። መኢአድም “በኦሮሚያ የተጀመረው ብጥብጥ የተነሳው በኢህአዴግ በተፈጠረ ችግር ነው” ያለ ሲሆን “ዜጎች መብታችን ይከበር ከመሬታችን አንነሳም በማለታቸው ተቃውሟቸውን በጥይት ለማብረድ መንግስት በወሰደው እርምጃ ምክንያት የተነሳ ብጥብጥ ነው። ተቃውሞዎችን በሙሉ በሀይል እመልሳለሁ ብሎ መነሳት አገሪቱን ወደባሰ ብጥብጥ ይወስዳታል እንጂ መፍትሔ ሊሆን ስለማይችል መንግስት ሊያስብበት ይገባል” ሲል አሳስቧል። መኢአድ “የማስተር ፕላኑ ጥያቄ የኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጥያቄ መሆኑን መንግስት ሊያውቅ ይገባል” ሲል አቋሙን ግልፅ አድርጓል።

የመኢአድ የወደፊት እቅድ

ለአገራችን ዳር ድንበር መከበር እና ለአንድነቷ እስከ ደም ጠብታ እንታገላለን የሚለው መኢአድ “እስከ ደም ጠብታ እንታገላለን ስንል ነፍጥ አንስተን እንዋጋለን ማለት አይደለም። መኢአድ በኮንጎ የተፈጠረው አይነት የእር በእርስ ጦርነት በኢትዮጵያ እንዲደገም አይፈልግም። እኛ እስከ ደም ጠብታ የምንታገለው ሰላማዊ እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ብቻ ነው” ሲል የትግል ስልቱን ይፋ አድርጓል። ነገር ግን የፓርቲው የትግል ስልት በመግለጫ እና ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ደብዳቤ ከመጻፍ በዘለለ የጎዳና ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ከመጥራት እና ህዝባዊ ውይይትችን በማካሄድ እንደሚያዘጋጅ አስታውቋል። በዚህም መሰረት የመጀመሪያውን ህዝባዊ ውይይት የፊታችን ታህሳስ 24 ቀን በፓርቲው ጽ/ቤት እንደሚያካሂድ ገልጿል።

ኢህአዴግ በሩን ለውይይት እና ራሱን ደግሞ ለብሔራዊ እርቅ ማዘጋጀት አለበት የሚለው መኢአድ “ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎችም ሆነ ከሌሎች ችግር ከሚፈጥሩ ነገሮች መውጣት ከፈለገ ቁጭ ብሎ መነጋገር አለበት። መወንጀል እና ጥይት መተኮሱ የትም አያደርሰውም። አሁንም ሰላማዊ ትግል የሚቀጥል ከሆነ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ያሉ ታጋዮች የሚሰጡትን አስተያየት ተቀብሎ ተግባራዊ ቢያደርግ ለችግሩ ሁሉ መፍትሔ ያገኛል” ሲሉ ምክትል ፕሬዝደንቱ ዶ/ር በዛብህ አሳስበዋል።

ምንጭ ስንደቅ

Leave a Reply