Thursday, 24 December 2015 11:27

– አቶ በቀለ ነጋ ከመንግስት ማስጠንቀቂያ ደርሶብኛል አሉ

በይርጋ አበበ

 

የአዲስ አበባና ዙሪያዋ የኦሮሚያ ልዩ ዞን እና የተቀናጀ ማስተር ፕላን እና በጎንደር ማረሚያ ቤት የተፈጠረውን ቃጠሎ ተከትሎ መንግስት የወሰደውን እርምጃ ለማውገዝ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) የፊታችን እሁድ በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ጥያቄ አቅርቦ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ፈቃድ መከልከሉን አስታወቀ።

የመድረክ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዓለሙ ኰይራ ለዝግጅት ክፍላችን እንዳስታወቁት “የሰልፉ ዓላማ በጎንደር እና በኦሮሚያ ክልል የሞቱ ሰዎችን ሀዘን ለመግለጽ እና ድርጊቱን ለማውገዝ ነው። ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ‘አሁን አገራችን ባለችበት ሁኔታ ጥያቄያችሁን ተቀብለን ሰላማዊ ሰልፉን እንድታካሂዱ ለመፍቀድ እንቸገራለን’ ሲል በደብዳቤ ገልጾልናል” ብለዋል። አቶ ዓለሙ አክለውም “የከንቲባ ጽ/ቤቱ ድርጊት የሚያመለክተው በአሁኑ ወቅት ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ መከልከሉን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ዓለሙ “በመጀመሪያ ሰልፍ የምታካሂዱበትን አቅጣጫ ቀይሩ ሲሉ ነበር የገለጹልን። እኛም በመጀመሪያ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ከመረጥነው ቦታ በመቀየር ከጽ/ቤታችን በመነሳት (በተለምዶ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ አምስተኛ በር አካባቢ እየተባለ ከሚጠራው) በራስ መኮንን ድልድይ አድርገን በቸርችል ጎዳና ወርደን መረሻችንን ድላችን ሀውልት ለማድረግ ወሰንን። ሆኖም ግን ይህንንም ከለከሉን” ሲሉ ገልጸዋል።

የመድረክ ዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዓለሙ ፓርቲያቸው ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ እንደሚሰጥ ገልጸዋል። “ፓርቲያችን ባደረገው ማጣራትያ በኦሮሚያ ክልል በማስተር ፕላኑ ጉዳይ በተነሳ ተቃውሞ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 85 ደርሷል። የሟቾቹን ማንነት እና አካባቢያቸውንም በዝርዝር ይዘናል” ሲሉ ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ዋና ጸሀፊ አቶ በቀለ ነጋ ከመንግስት ማስጠንቀቂያ እንደደረሳቸው ተናገሩ። አቶ በቀለ ለዝግጅት ክፍላችን በስልክ እንዳስታወቁት “ከቤቴ ስወጣ ሲቪል የለበሱ ሰዎች ጠሩኝና እንፈልግሃለን ብለው አነጋገሩኝ። ብጥብጡን እየቀሰቀስክ ነው፣ አርፈህ ተቀመጥ አሉኝ” ብለዋል። አቶ በቀለ አያይዘውም “ዴሞክራሲያዊ ባልነበረው ምርጫ ተወዳድረን ከኢህአዴግ ቀጥሎ ከፍተኛ ድምጽ ያገኘን ፓርቲ ብንሆንም እንደወንጀለኛ እየተቆጠርን እየታሰርን እንገኛለን። ባለፈው ምርጫ ተወዳዳሪ የነበሩ በርካታ የፓርቲያችን አባላትም በአሁኑ ሰዓት በእስር ላይ ይገኛሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

ምንጭ ስንደቅ

Leave a Reply