(ዘ-ሐበሻ) ትናንት አርብ በኢትዮጵያ ፓርላማ ቀርበው ስለኢትዮ-ሱዳን አወዛጋቢ የድንበር ማካለል ጉዳይ መግለጫ የሰጡት ሕወሓት የሚመራው መንግስት ጠቅላይ ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ በድንበሩ ጉዳይ ያደረጉት ንግግር አነጋጋሪነቱ እንደቀጠለ ነው:: በርሳቸው ንግግር ዙሪያ የቀድሞው ኢህዲን (ብአዴን) ታጋይ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት በሜሪላንድ አሜሪካ የሚገኙት ያሬድ ጥበቡ በፌስቡክ ገፃቸው ኃይለማርያም ዛሬ ካሰሙት ንግግር በኋላ ገስጸዋቸዋል::
“እንኳን እርሳቸው፣ ነባሮቹ የብአዴን መሪዎች እነበረከትና አዲሱ እንኳ ከኤርትራና ሱዳን ጉዳይ የተገለሉ ነበሩ” ያሉት አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ከዚህ ጉዳይ እጃቸውን እንዲያወጡ መክረዋል::

የያሬድ ጥበቡ አስተያየት እንደወረደ ይኸው:-

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሱዳን ኢትዮጵያን ወሰን ጉዳይ በታላቅ ጥንቃቄ ቢያዩትና፣ ምክርቤቱ ውስጥ የሰጡት አይነት የኢትዮጵያን አራሾች በድንበር ገፊነትና፣ በሽፍትነት የመሳል ምስክርነት ቢቆጠቡ ተመራጭ ነው ። አለመግባባቱ ወደፊት ወደአለምአቀፍ አርቢትሬሽን ቢላክ ይህ ቪዲዮ የሱዳኖችን የይገባኛል ጥያቄ የሚያጠናክርና ኢትዮጵያን የሚጎዳ በመሆኑ፣ ከዚህ መሰል ምስክርነት ቢቆጠቡ ተገቢ ነው ። በሁለተኛ ደረጃ፣ አቶ ኃይለማርያም ለኢህአዴግ መጤ መሆናቸውን መረዳት አለባቸው ። እንኳን እርሳቸው፣ ነባሮቹ የብአዴን መሪዎች እነበረከትና አዲሱ እንኳ ከኤርትራና ሱዳን ጉዳይ የተገለሉ ነበሩ። በወያኔ ፖሊትቢሮ ብቻ የተያዘ የውስጥ ጉዳይ ነበር ። በወያኔ 40ኛ አመት በአል ላይ መቀሌ ላይ ንግግር ያደረገው ሱዳናዊ፣ ” እኔም ወያኔ ነኝ” ብሎ ከፈከረ በኋላ፣ መለሰ ለመጨረሻው ከደርግ ጋር ድርድር ወደ ለንደን ከማቅናቱ በፊት፣ ካርቱም ላይ ፕሬዚደንቱ ቢሮ መሬት ላይ ፈርሸው ስላደረጓቸው ውይይቶች የነበረውን ትዝታ አካፍሏል ። በዚያ ወቅት፣ የጋራ ጠላታቸው የሆነውን የአማራ ህዝብ ለማዳከም መለስ የገባው ቃል ሊኖር ይችላል ። ምናልባትም አዲሱን መንግስት በማቋቋም ስም ወያኔ ከሱዳን የበላው መሃያ ሊኖርም ይችላል። ብዙ ያልተፈተሹና የማናውቃቸው ጉዳዮች ስላሉ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለኝ ምክር፣ እጃቸውን ከዚህ ጉዳይ ውስጥ ማውጣትና፣ የወሰን ድርድር ለማድረግ የሚያሰገድድ ሁኔታ ፈፅሞ ባለመኖሩ፣ ጉዳዩ ባለበት እንዲቀጥል መተው የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ ። ሃገራቸውን የሚጎዳ ነገር ውስጥ እጃቸውን ባያስገቡ ይመረጣል ።Screen Shot 2015-12-25 at 8.55.10 PM

 

Leave a Reply