ሰሞኑን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ምክክር ያደረጉት የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮች፣ በኦሮሚያ ክልል የተከሰተውን ግጭት ለመፍታት ሁለገብ ውይይት እንዲደረግና የሕግ የበላይነት እንዲከበር መጠየቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ሚኒስቴሩ በርካታ የውጭ መልዕክተኞችን ያነጋገረ መሆኑን ገልጸው፣ በተለይ ደግሞ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ያነጋገሩዋቸው የአውሮፓ ኅብረት ተወካዮች በወቅታዊ የፖለቲካና የፀጥታ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አብራርተዋል፡፡

በአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ ልዑክ ኃላፊ ሚስስ ቻንታል ኸብረችት የተመራ የልዑካን ቡድን፣ በኦሮሚያ የተከሰተው ግጭት ሁለገብ ውይይት በማካሄድ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝና በአገሪቱ የሕግ የበላይነት እንዲከበር ለሚኒስትር ዴኤታው መግለጻቸውን ቃል አቀባዩ አስረድተዋል፡፡ የአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲጠበቅም ልዑካኑ መናገራቸውን ኃላፊው አክለው ገልጸዋል፡፡

ልዑካኑ ስደተኝነትን በመቀነስና ዘላቂ መፍትሔ በማፈላለግ ላይም ሐሳባቸውን ማካፈላቸውን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡ በኦሮሚያ አካባቢ በተከሰተው ግጭትና የመንግሥት ዕርምጃን በተመለከተ የተቀሩት ዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት ያሳዩት አቋም እንዳለ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ የአውሮፓ ኅብረት ልዑካን ካቀረቡት ሐሳብ ተመሳሳይ እንደሆነና ችግሩ በውይይት ይፈታ የሚል እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ስለተከሰተው ድርቅ፣ በደቡብ ሱዳን ስላለው ወቅታዊ ሁኔታና እንዲሁም ከጎረቤት አገሮች ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ቃል አቀባዩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በሌላ ዜና የአውሮፓ ኅብረት ከብራሰልስ ታኅሳስ 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በኦሮሚያና በአማራ ብሔራዊ ክልሎች የተከሰተውን አለመረጋጋት ለማርገብ አገሪቱ ገንቢ ውይይት በማድረግ ለግጭቶቹ ሰላማዊና ዘለቄታዊ የሆነ መፍትሔ እንድትሻ ጠይቋል፡፡ የሕገ መንግሥቱን ማዕቀፍ በመከተል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በውይይቱ እንዲሳተፉና ከብጥብጥና ግጭት ከሚያነሳሱ መግለጫዎች እንዲታቀቡ ጠይቋል፡፡

በተጨማሪም የአውሮፓ ኅብረት በግጭቱ ሕይወታቸውን ላጡ ቤተሰቦችና ወዳጆች የተሰማን ሐዘን ገልጾ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመወያየት ፈቃደኛ መሆኑ የሚበረታታ እንደሆነ አመልክቷል፡፡

Source     =   Ethiopian Reporter

 

 

Leave a Reply