መንግስት ሁከቱን ለማስነሳት በሞከሩ ወገኖች ላይ የማያዳግም እርምጃ እወስዳለሁ አለ

 Tuesday, 29 December 2015 07:14
Written by  መታሰቢያ ካሳዬ

– “ድርቁ በ50 ዓመት ታሪካችን ያልታየ ነው ቢባልም ብዙ ጉዳት አላደረሰም”
– “ፀረ ሠላም ኃይሎችን መስመር ማስያዙን እናውቅበታለን፤ ልምዱም ችሎታውም አለን፤”
– “የሥራ ዕድል ባለመፈጠሩ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ያደረባቸው ወጣቶች በሁከቱ ተሳትፈዋል”
– “ህዝቡ ሳያምንበት ለደቡብ ሱዳን የሚሰጥ መሬት የለም”

ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎችና በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን የተከሰተውን ብጥብጥ በማስነሳትና በመቀስቀስ የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ይዘው ህዝቡን በማደናገር የሰው ህይወት እንዲጠፋ አድርገዋል ባላቸው ወገኖች ላይ መንግስት ህጋዊና የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ገለፁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትላንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠትና ሁለተኛውን የትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማፅደቅ በፓርላማ ተገኝተው እንደተናገሩት፤ በኦሮሚያ ክልል የተነሳውንና መንግስትም በቂና አጥጋቢ ማብራሪያ ያልሰጠበትን የማስተር ፕላን ጉዳይና በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በአማራና በቅማንት ማህበረሰብ መካከል የተነሳውን አለመግባባት መጠቀሚያ በማድረግ የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማስፈፀም የሚንቀሳቀሱ ወገኖች አሉ። እነዚህ በህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነት ሽፋን የሽብርተኛ ድርጅት ሴሎችን በውስጣቸው በመያዝ ሁከቱን ያባባሱና የመሩ እንዲሁም ከሻቢያ የሚሰጣቸውን መመሪያ ለማስፈፀም ሌት ተቀን የሚሰሩ አካላትን መንግስት በዝምታ እንደማይመለከታቸውና ፀረ ሰላም ኃይሎችን መስመር ማስያዝና አደብ ማስገዛቱን እንደሚያውቅበት፣ ልምዱና ችሎታውም እንዳለው ገልፀዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የተነሳው ጥያቄ አግባብነት ያለው ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በወቅቱ መንግስት በጉዳዩ ላይ በቂ ማብራሪያ ባለመስጠቱና ስለጉዳዩ ህዝቡ በግልፅ እንዲያውቅ ባለመደረጉ ችግሩ መከሰቱን ተናግረዋል። “በአንዳንድ የገጠር የከተማ አካባቢዎች ለወጣቶቻችን የሥራ ዕድል በመፍጠር የኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ባለመደረጉ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ያደረባቸው ወጣቶች የሁከቱ ተሳታፊ መሆናቸው አስገራሚ ጉዳይ አይደለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አርሶ አደሩም ልማታዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ የሚሆንበት ሥራ ላይ በበቂ ሁኔታ ባለመሰማራቱና ያልተፈቱ ጉዳዮች በመኖራቸው የሁከቱ ተሳታፊ ሆኗል ብለዋል።
ህብረተሰቡ ጥያቄዎቹን ሰላማዊና ህጋዊ በሆነ መንገድ አቅርቦ ተገቢ ምላሽ ማግኘት ሲገባው በአንዳንድ ፀረ ሰላም ኃይሎች አደናጋሪነት ወዳልተገባ ብጥብጥና ረብሻ ማምራቱ አግባብነት የለውም ያሉት አቶ ኃ/ማርያም፤ ለብጥብጡ መነሳት ምክንያት የሆኑ ሰዎች ተጠያቂ የሚደረጉበት አሰራር ተግባራዊ እንደሚደረግና በጉዳዩ ተደናግረው የገቡ አካላትንና ሆነ ብለው አቅደው የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ኃይሎችን የመለየቱ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህንን የማጣራቱ ሂደት ሲጠናቀቅም ለህዝቡ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን መሬት ቆርሳ ሰጠች መባሉንና በቋራ ወረዳ የሱዳን መከላከያ ሰራዊት መስፈሩን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄም ጠ/ሚኒስትሩ ሲመልሱ፤ “የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን ድንበር አለመካለሉ የሚታወቅ ጉዳይ ነው፤ ጉዳዩ በጋራ ድንበር ኮሚሽን በድርድር ላይ ነው፤ ይሄ ህዝቡ ተወያይቶ ድምዳሜ ላይ የሚደርስበት ጉዳይ ነው ተቆርሶ የተሰጠ መሬት የለም፡፡” ብለዋል፡፡
ህዝቡ ሳያምንበትና ሳይወያይበት የሚሰጥ መሬት እንደሌለና በደቡብ ሱዳን መንግስት በኩል ግን ጥያቄው መኖሩን ተናግረዋል፡፡ “ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር ባለን ጥሩ መግባባትና ወዳጅነት፣ ሱዳን ውስጥ በርካታ ኪሎሜትሮችን ገብተው የሚያርሱ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶችና አርሶ አደሮች አሉ፡፡ እነዚህንም የሱዳን መንግስት ምንም አይነት እርምጃ ሳይወስድ እስከ አሁን በዛው ይገኛሉ፡፡
ይህም የሚሆነው ድንበሩን እስከምናካልል ድረስ ነው፡፡” ብለዋል፡፡ በድንበር አካባቢ አሉ ስለተባሉት የደቡብ ሱዳን የመከላከያ ሠራዊት አባላት ሲናገሩም፤ ሰራዊቱ መኖሩን አምነው ዋንኛ ሥራውም ሻዕቢያ እያሰለጠነ የሚልካቸውን ኃይሎች መከላከል እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በጐረቤት አገሮች በተለይም በደቡብ ሱዳን ባለው ጦርነትና አለመረጋጋት ሳቢያ በርካታ የጦር መሳሪያዎች ወደ አገራችን መግባታቸውን የጠቆሙት ጠ/ሚኒስትሩ፤ እነዚህን ህገወጥ መሳሪያዎች ለመቆጣጠር በኬላ አካባቢ ጥብቅ ቁጥጥር ለማድረግ እየተሞከረ መሆኑንና ይህንን አልፈው ወደአገር የሚገቡ መሳሪያዎች በህጉና በመመሪያው መሰረት በአግባቡ የሚያዙበትን አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ማድረጉ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሰሞኑን በአንዋር መስገድ የተከሰተው ጉዳይም ከዚሁ ጋር የሚያያዝ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ድርቁን አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ ድርቁ በአገራችን የ50 ዓመት ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ መሆኑን አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚናገሩ ጠቅሰው፤ በድርቁ የተጐዳው የህብረተሰብ ክፍል ግን ጥቂት ነው ብለዋል፡፡
ድርቁ በአንድ ጊዜ የተከሰተ ሳይሆን ከካቻምናው የበልግ ወራት የዝናብ እጥረት ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡ ያለውን ጥሪትና ሀብት በመሸጥ ምግብ እየሸመተ እዚህ መድረስ መቻሉንም ገልፀዋል፡፡
በድርቅ ለተጐዱ ወገኖች የሚሆን እርዳታ ከውጭ እየመጣ እንደሆነና መንግስትም በድርቅ የተጐዱ ወገኖችን በመደገፉ ረገድ ከፍተኛ ሥራ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ድርቁ ይህንን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ አለመድረሱንና በዚህ ሳቢያ የተጐዱ ህፃናትና ነፍሰጡር ሴቶች አለመኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከታህሳስ 8 ቀን ጀምሮ ለአራት ቀናት በምክር ቤቱ ውይይት ሲደረግበት የሰነበተውና ከ2008 ዓ.ም እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ ተግባራዊ ይሆናል የተባለው የሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድም በዚሁ ጉባዔ ላይ ፀድቋል፡፡

ምንጭ ስንደቅ

Leave a Reply