በዚሁ ሰፊ አዳራሽ ባለው ጠባብ በር ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጋር ተጋፍቶ የወጣው ለምሳ ነበር፡፡ ርቦታልም፡፡ ደጃፍ ላይ ቆሞ ግን አጠገቡ ከሚታየው የምግብ ገበታ ይልቅ ዩኒቨርሲቲው በር ላይ የሆነ ነገር ቀልቡን የሳበው ይመስላል፡፡ እጃቸው ላይ ደብተርና ስክርቢቶ የያዙ በርከት ያሉ ተማሪዎችና ሌሎችም ተለቅ ተለቅ ያሉ ሻንጣዎች ያነገቡ (አስተማሪዎች ሳይሆኑ አይቀሩም) ሰብሰብ ሰብሰብ ብለው ይታያሉ፡፡ በሩ ተዘግቷል፡፡ የፀጥታ ኃይሎችም በብዛት ይታያሉ፡፡

ከበሩ ገባ ብሎም እዚህም እዚያም በቡድን በቡድን ሆነው የተሰባሰቡ ተማሪዎች ይታያሉ፡፡ የከነከናቸው ነገር ያለመሆኑ ያሳብቅባቸዋል፡፡ ከአዳራሹ የወጡ ሰዎች በእነዚህ ሰዎች ቀልብ የተሳቡ ያህል፣ እነሱም ለታዳሚዎች የማይታየው ከውጭ የሆነ የሚረብሽ ነገር ቀልባቸውን ገዝቶታል፡፡

ምሳውን በመያዝ መቀመጫውን የያዘው አምሐም በሁኔታው ግር ተሰኝቷል፡፡ የምሳ ኩፖኑን እያስረከበ ምግቡን የሚያነሳው ታዳሚ ምን እንደተፈጠረ እምብዛም ግድ ያለው አይመስልም፡፡ ከውጭ ግን መጠነኛ ጩኸት መሳይ ነገር ይሰማል፡፡

‹‹ሰምታችኋል? መውጣት አትችሉም እየተባልን ነው፡፡ በር ተዘግቷል፤›› አምሐ ስልኩን ከዘጋ በኋላ ፍርኃትና ድንጋጤ ፊቱ ላይ ተቀላቅለውበት ያወራ ነበር፡፡ ከታዳሚዎች መካከል ሌላ ወጣት ተማሪ ክፉኛ ደንግጣ ‹‹ምን ተፈጠረ?›› በማለት ጠየቀች፡፡ ‹‹ውጭ ግርግር አለ፡፡ በፌደራሎችና በተማሪዎች መካከል ግጭት ተፈጥሯል፤›› አለ፡፡

ይኼ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሰባት ዓመታት በፊት በተቋቋመው የሰብዓዊ መብቶች ማዕከል በተዘጋጀው ውይይት የተከሰተ አጋጣሚ ነው፡፡ በታዋቂው የሕገ መንግሥቱ አርቃቂ በአቶ ክፍሌ ወዳጆ የሰላምና የሰብዓዊ መብቶች ማስታወሻ ማዕከል ውስጥ የከተመው የሰብዓዊ መብቶች ተቋም፣ ከሌሎች የዩኒቨርሲቲው ማዕከላት ጋር በመተባበር ጭምር በሰብዓዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ምርምር የሚያካሂድ ሲሆን፣ የሁለተኛና የዶክትሬት ዲግሪ እየሰጠ የሚገኝ ነው፡፡

ተቋሙ ታኅሣሥ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ከኖርዌይ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውና በሰብዓዊ መብት ላይ ባተኮረው ውይይት ግብዣ የተደረገላቸው እንግዶችና ቁጥራቸው በርከት ያሉት የዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ አባላት ተገኝተውበት ነበር፡፡ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ውይይት የተደረገበት ይህ በተለይ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ማስተር ፕላኑን መነሻ በማድረግ የተነሳው ግጭት የመወያያ አጀንዳ የነበረበት ጊዜ ነበር፡፡

በመንግሥት ላይ የሚካሄድ ማናቸውንም ተቃውሞዎች ቀድሞ በመምራት የሚታወቀው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ደግሞ፣ የኦሮሞ ተወላጆች በማስተር ፕላኑና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ተቃውሞውን እንዲቀላቀል ተደጋጋሚ ጥሪዎች ቢደረጉለትም ሙከራ እንኳ ያደረገው ነገሮች መርገብ ከጀመሩ በኋላ ነው፡፡ በዋዜማው ታኅሣሥ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. የተቃውሞ መልዕክት የያዙ ወረቀቶች ከተበተኑ በኋላ፣ በዚሁ በርካታ ፕሮፌሰሮችና የውጭ ዲፕሎማቶች የተገኙበት የሰብዓዊ መብት ውይይት የተደረገበት ቀንና ተማሪዎቹ መጠነኛ እንቅስቃሴ አድርገው ከፌዴራል ፖሊስ ጋር  የተጋጩበት ዕለት ሊገጣጠም ችሏል፡፡ ቦታውም ተጋጥሟል፡፡

ውይይት

‹‹የሰብዓዊ መብት አተገባበር በኢትዮጵያ›› በሚለው ርዕስ ላይ የተደረገው ውይይት ከሰብዓዊ መብቶች ጽንሰ ሐሳብ ፍልስፍና ተነስቶ፣ ሴቶችና የፍትሕ አስተዳዳር አተገባበር ድረስ የአንድ ሙሉ ቀን ፕሮግራም ሆኖ፣ ስድስት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንዲደረግበት ታቅዶ የተያዘ ነበር፡፡ በማዕከሉ ኃላፊ ዶ/ር ይታየው ዓለማየሁ፣ በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ምትክ ዶ/ር ዮሴፍ መኮንን፣ እንዲሁም በኖርዌይ አምባሳደር ሚስተር እንድሪያስ ጋርደር የመክፈቻ ንግግሮች የተጀመረ ሲሆን፣ እንደታሰበው እስከ መጨረሻ ሰዓት የዘለቀ ውይይት አልነበረም፡፡

‹‹አገር በቀል የፍትሕ ሥርዓት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር እንቅፋት ይሆን ወይ?›› በዶ/ር አበራ ደገፋ፣ ‹‹የሰብዓዊ መብቶች የፍልስፍና መሠረት›› በዶ/ር በቀለ ጉተማ፣ ‹‹በመካከለኛው ምሥራቅ በዝቅተኛ የሥራ በቤት ሠራተኝነት የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርስ የሥነ ልቦና ችግር›› በዶ/ር ብርቄ አንበሴ፣ ‹‹ጫት ከሰብዓዊ መብቶች ጋር በተገናኘ›› በዶ/ር የራስ ወርቅ አድማሴ የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሑፎች በአቶ ዘካርያስ ቀንአ የመድረክ መሪነት ቀርበው መጠነኛ ውይይት ተደርጎባቸው ነበር፡፡ የተቀሩት ግን የወኃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል፡፡

ጫት ላይ የቀረበው ጥናት ከአብቃዮች ሰብዓዊ መብት ጀምሮ በቃሚዎች ላይ የሚያሳድረው የጤና እክል ላይ በቀረበው ሐሳብ ላይ ተንተርሶ ቀጣይና ሰፋ ያለ ጥናት እንዲደረግበት፣ እንዲሁም የጋምቤላና የትግራይ ክልሎች የክልከላ ፖሊሲ ሞክረው ለምን እንዳልተሳካላቸው ሲዳስስ፣ መንግሥት በአሁኑ ወቅት ከዘርፉ የሚያገኘውን ገቢ በመጪው ትውልድ ላይ ሊያሳድረው ከሚችለው ጉዳት አንፃር እንዲመዘንና በአገር አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ ፖሊሲ ቢወጣበት የሚሉ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡

እንዲሁም በቅርቡ በሕግ የተከለከለውና እስካሁንም መፍትሔ ያልተደረገለት ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ገቢ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ወጣት ሴቶች ወደ መካከለኛ ምሥራቅ መጉረፋቸው፣ ከዚያም አብዛኞቹ እዚያው ከሚገጥማቸው የባህል ግጭት፣ መደብደብና የሥራ መደራረብ በአዕምሮአቸው ላይ እያሳደረባቸው ያለው የጤና ችግር በዝርዝር የቀረበ ነበር፡፡ ‹‹ከስደትና የአዕምሮ ጤና›› የሚለው ይኼው ጥናታዊ ጽሑፍ በዘጠና የስደት ተመላሽ ወጣት ሴቶች ላይ በተሠራው ዳሰሳ፣ ብዙዎች የአዕምሮ ችግር እንዳለባቸው በጥናት አቅራቢዋ ዶ/ር ብርቄ አንበሴ ተረጋግጧል፡፡ የብዙዎቹን ቀልብ የሳበው ይኼው ጥናት ከሰብዓዊ መብት ጥሰት አንፃር የቀረበ ነው፡፡ ሴቶቹ በተሳሳተ መረጃ እንደሚጓዙ፣ አብዛኞቹ በሚደርስባቸው አካላዊና ወሲባዊ ጥቃት ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ችግሮች እንደሚጋለጡ ያስረዳል፡፡

ጥናቱ በተሰማሩበት የሥራ ቦታ ከአሠሪዎችና ከአገሮቹ መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ብቻ የተቃኘ ነበር፡፡ ከመጀመሪያው ጥናት አቅራቢዋ የሰውን ልጅ የመሥራትና ሠርቶ የመኖር መብት ላይ ጥያቄ ባለማቅረባቸው፣ ጥናቱ አካላዊ ጉዳት ላይ ከሚገደብ ቢሰፋ የሚል አስተያየት ግን ቀርቧል፡፡ ጥናቱ መንግሥት ሊወስደው የሚገባ ዕርምጃና ከአስቸኳይ የዜጎች መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ አንፃር ቀርቦ ቢሆን፣ ሙሉ ይሆን ነበር ተብሎም በመድረኩ አስተያየት ተሰጥቷል፡፡

‹‹አገር በቀል የፍትሕ ሥርዓቶች ለሰብዓዊ መብቶች መከበር እንቅፋት ይሆናሉ ወይ?›› በሚል በዶ/ር አበራ የቀረበው ጥናት በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶችን ከባህላዊ ሥርዓት አተገባበር አንፃር የሚዳሰስ ነው፡፡ የቦረናን ማኅበረሰብ በምሳሌነት በመወሰድ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ የሚታወቀው አገር በቀል የአስተዳደርና የዳኝነት ሥርዓት የሆነው የገዳ ሥርዓት ቢከበር ‹‹ሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተካተተ የሰብዓዊ መብት መርሆች የበለጠ ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳል እንጂ የሚፃረር አይደለም፤›› የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፡፡ አጥኚው እንደሚሉት፣ ገዳ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉት ባህላዊ የዕርቅ፣ የዳኝነትና የግጭት አፈታት ዘዴዎች ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና አግኝተው እኩል ተግባራዊ ቢደረጉ፣ በሰብዓዊ መብታቸው ላይ የሚፈጸሙ ጥሰቶች ይቀንሳሉ፡፡

በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን አገር በቀል የዳኝነት ሥርዓትን በመደፍጠጥ የተማከለና አንድ ወጥነት ያለው የፍትሕ ሥርዓት ለመፍጠር መሞከሩ፣ በደርግም ያው ሁኔታ እንደቀጠለ፣ በኢሕአዴግ ዘመን ግን በመርህ ደረጃ በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 34 እና በአንቀጽ 38 ዕውቅና የተሰጣቸው ቢሆንም፣ በተግባር ግን ወደ ንጉሡ የመመለስ አዝማሚያ እንዳለ በማስረዳት ሥጋታቸውንም ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የቦረና የዳኝነት ሥርዓትን ጨምሮ ለአገር በቀል አስተዳደራዊ ሥርዓቶች ዕውቅና አለመስጠት፣ ከሰብዓዊ መብት ጋር የሚፃረር አካሄድ መሆኑን ተከራክረዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ‹‹Legal Pluralism›› (የሕግ ብዝኃነት) አልተከበረም ማለት እንችላለን ወይ?›› የሚል ጥያቄ ቀርቧል፡፡ አማራጭ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውን በመጥቀስም አስተያየት ቀርቦ ነበር፡፡ ሌላም ‹‹በባህላዊ የዳኝነት ሥርዓትና በማዕከላዊ የፍትሕ ዳኝነት መካከል ግጭት አይፈጥርም ወይ?›› ‹‹የመጨረሻውስ የትኛው ይሁን ይላሉ?›› የሚሉ አስተያየት አዘል ጥያቄዎችም ቀርበው ነበር፡፡ ለቀረቡላቸው አስተያየቶችና ጥያቄዎች በስሜት መልስ የሰጡት ዶ/ር አበራ ደገፋ፣ ‹‹Why do you impose a law because you think it is good, but the Borena people think it is bad›› [የቦረና ሕዝብ የማይፈልገውን መንግሥት ብቻ ስለፈለገው የራሱ ያልሆነ ሕግ ከላይ ለምን ይጫንበታል?›› በሚል ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ አካሄዱ ከፌዴራል መንግሥት ሥርዓት የሚፃረር መሆኑንም ጭምር ተንትነውታል፡፡

‹‹የጋን መብራት››

የኢሕአዴግ መንግሥት ሥልጣን ከተቆጣጠረበት ከሽግግሩ ጊዜ ጀምሮ፣ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ለመከላከል የተለያዩ የቃልኪዳን ሰነዶች ተቀብሏል፡፡ በ1987 ዓ.ም. በፀደቀውና ሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥትም አሉ የተባሉትን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዩኒቨርሳል ዶክላሬሽን ኦፍ ሂውማን ራይትስ ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ቃል ኪዳን (UIDHR) ጨምሮ፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች ተቀብሎ ያፀደቀና የፈረመ መንግሥት ነው፡፡ በተግባር ግን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች እንደሚሉት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የፈረማቸውን የሰብዓዊ መብት ቃል ኪዳኖች ለመተግበር የሚያደርገው እንቅስቃሴ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በተለይ በኑሮ ዝቅተኛ የሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ሰብዓዊ መብት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማትና ግለሰቦች ሲጣስ፣ ፍትሕ ሲያጣና አቤት የሚልበት አካል ሲጠፋ ይስተዋላል ተብሎ ትችት ይቀርባል፡፡

መንግሥት የአገሪቱን ዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ለማስከበር የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አቋቁሞ ለመብቶቹ ጥበቃ እያደረገ እንደሆነ ቢገልጽም፣ በተግባር የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የዜጎች ሳይሆን የመንግሥት ስም እንዳይጠፋ ሲከላከልና ሲጠበቅ የሚውል ነው በሚል እየተወቀሰ ነው፡፡ ለዓመታት የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች መርሐ ግብር በማውጣትና በመወያየት ሲዘልቅም ይስተዋላል፡፡ የሰብዓዊ መብቶችን መርሆዎች በማስተማር ላይ መጠነኛ ሥራ ይሠራ እንደሆነ እንጂ፣ ዋናው ሥራው የሆነው ተፈጥሮዓዊ የሆነ የዜጎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሲያጋልጥ፣ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ላይ ሪፖርት ሲያወጣና ለዜጎች ሲከራከር አይስተዋልም ተብሎም ይወቀሳል፡፡

በዕለቱ አንድ የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት፣ ‹‹ስለሰብዓዊ መብት ስናወራ ይገርመኛል፡፡ ሰው እየተገደለ ‹አልተገደለም› የሚል የሰብዓዊ መብት ተቋም ባለበት፣ ሰው እየጠፋ ‹አልጠፋም› የሚል የመንግሥት ሚዲያ ባለበት ማን ከማን ጋር ነው የምንወያየው? ሚዲያው የማን ነው?›› የሚል ጥያቄ አንስቶ ነበር፡፡ ወጣቱ ከአዲስ አበባ ወደ ክልል ከዚያም ወደ ገጠር በተወረደ ቁጥር ሰዎች በየቀኑ የሚጨቆኑበት ሁኔታ እንዳለ፣ የዜጎች ሰብዓዊ መብት ጭራሽኑ እንደሌለ ተናግሯል፡፡ ‹‹እስቲ ወርዳችሁ ተመልከቱ፣ እስቱ ወደ ሕዝቡ ሂዳችሁ ጠይቁ፣ ይነግሯችኋል፤›› ሲል የሰብሰባው ተሳታፊዎች አዳራሹን በጭብጨባ አድምቀውት ነበር፡፡

ወጣቱ አስተያየት ሰጪ ጉዳዩን ከወቅታዊው በኦሮሚያ ክልል ከተነሳው ግጭትና ከመንግሥት ምላሽ ጋርም ለማገናኘት ሞክሮ ነበር፡፡ ለምሳ የወጡ ተጋባዥ እንግዶች ተመልሰው ውይይቱን መቀጠል አልቻሉም፡፡ አምሐ ጌታቸው እንዳለው፣ በአዳራሹ ውስጥ በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ውይይት እየተደረገ ከግቢው ውጪ ግን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጥያቄ ሲነሳ ነበር፡፡ በዋናው ስድስት ኪሎ ግቢ በተነሳው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ግጭት የተፈጠረ ሲሆን፣ ፌዴራል ፖሊስ የተቃውሞ ሙከራውን በኃይል አቁሞታል፡፡ ለተወሰኑ ሰዓታት ከግቢው መውጣት አትችሉም ተብሎ የስብሰባው ታዳሚዎችም ቆይተው ነው የተለቀቁት፡፡ በሰብዓዊ መብት ላይ የተጠራው ውይይት የቀትር በኋላ መርሐ ግብር ከአዳራሹ ውጪ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ በተነሳው ተቃውሞ ሳቢያ ተቋርጦ ቀርቷል፡፡