(ዋሽንግተን ፥ ዲሲ) –

የበዕውቀቱ ሥዩም አዲስ መጽሐፍ “ከአሜን ባሻገር” በሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ አዳራሽ እሁድ ጃንዋሪ 24 ቀን 2016 ከ4:00pm-7:00pm ይመረቃል።

ታዋቂው ገጣሚ እና ደራሲ በዕውቀቱ ሥዩም በዛ ያሉ ግጥሞችን፥ ቤሳ ልብወለዶችን፥ የዘፈን ድርሰቶችን፥ ወጐችን፥ ዋዘኛ ፖለቲካዊ እና ታሪካዊ መጣጥፎችን በተባ ብዕሩ ላለፉት ዐሥራ ዐምስት ዓመታት ከትቧል። ቀዳሚው የበዕውቀቱ ሥዩም የግጥም መድበል “ኗሪ ዐልባ ጎጆዎች” በ1993 ዓ.ም የታተመ ሲኾን፥ የበዕውቀቱ ሁለተኛው መጽሐፉ “በራሪ ቅጠሎች” ከደርዘን በላይ ታሪኮች ያካተተ የቤሳ ልብወለዶች ስብስብ ነበር።

የበዕውቀቱ ሦስተኛው መጽሐፉ የግጥም መድበል “የሣት ዳር ሐሳቦች” ሲኾን በርካታ ቅኔዎችን አካቷል። ከሌሎች ጸሐፍት ጋራ በመተባበርም “ክንፋም ሕልሞች” እና “ወንዞች እስኪሞሉ” በተሰኙ የቤሳ ልብወለዶች መድበል ውስጥ ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎቹን አሳትሟል። በዕውቀቱ ሥዩም በዐራተኛ እና ዐምስተኛ ድርሰቶቹም “እንቅልፍ እና ዕድሜ” እና “መውጣት እና መግባት” የተሰኙ ረጃጅም የልብወለድ መጻሕፍቶቹን ለተደራሲያን አቅርቧል። በዕውቀቱ ሥዩም አጫጭር ልብወለድ ታሪኮቹን በሁለት የሲዲ ተራኪ አልበሞች አሳትሞ አሰራጭቷል። በዕውቀቱ ዓለም አቀፍ ሽልማት የተቀዳጀ “ለዛሬ” የተሰኘ አጭር ፊልም ደርሷል። በዛ ላሉ ኢትዮጵያውያን አቀንቃኞች የዘፈን ድርሰትም ጽፏል።

በዕውቀቱ ወጎችን፥ ተረኮቹን፥ መጣጥፎቹን፥ ቤሳ ልብ ወለዶቹን ለታዳሚዎች በመድረክ አሳምሮ በማቅረብም ይታወቃል። በማኅበራዊ ሚዲያ (በተለይም በFacebook) በሚገባ ከሚገለገሉት ጥቂት ታዋቂ ሰዎቻችን ፊተኛ የኾነው በዕውቀቱ ባለፉት ዐምስት ዓመታትም ቁጥራቸው የበዙ ወጎችን፥ ተረኮችን፥ መጣጥፎችን፥ ቤሳ ልብወለዶችን በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ የበዕውቀቱ ሥዩም ወዳጆች የፌስቡክ ገፅ የብዕሩን ትሩፋት በማቅመስ ላይ ይገኛል። በ2001 ዓ.ም በብሔራዊ ደረጃ የዐመቱ ምርጥ ኢትዮጵያዊ ወጣት ጸሐፊ በመኾን ከፕሬዘዳንቱ እጅ ሽልማት ተቀብሏል።

በ2000 የለንደን ኦሊምፒክ ተጋባዥ ባለቅኔ ተብሎ፥ ኢትዮጵያን ወክሎ በሥፍራው ተገኝቷል። የተመረጡ የግጥም ሥራዎቹም በ2001 ና በ2004 ዓ.ም በዓለም አቀፍ የግጥም መድብሎች ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉመው ታትመዋል። በአሁኑ ወቅት በዝነኛው Brown ዩኒቨርሲቲ ተቀማጭ ጸሐፊ እና ተመራማሪ የኾነው በዕውቀቱ፥ በ2008 ዓመተ ምህረትም እነኾ “ከአሜን ባሻገር” የተሰኘ መጽሐፍ ደርሷል። የበዕውቀቱ ሥዩም አዲሱ መጽሐፍ “ከአሜን ባሻገር” ሃያ ምናብ አሳሽ፥ልብ ዳሳሽ፥ አዕምሮ ፈታሽ፥ ዋዘኛ እና ምፀታዊ ድርሰቶችን ያካተተ ሲኾን፤ የጽሑፎቹ ማጠንጠኛም ጉዞ ቀመስ፥ ፖለቲካ ቀመስ፥እና ታሪክ ቀመስ ተብለው ሊሰደሩ ይችላሉ። በዕውቀቱ በመጽሐፉ መቅድም ላይ አዋውቦ እንደገለጠው ጉዞ ቀመስ ተረኮቹ “…ሥዕላዊ ዘገባ ከማቅረብ ይልቅ ዕይታው የቀሰቀሰበትን ሐሳብ ማውጋት መምረጡን…”፤ ፖለቲካ ቀመስ መጣጥፎቹ “…የእንጉርጉሮ እና የልግጫ ድብልቅ…” መኾናቸውን፥ በዚህ ሁሉ ውስጥ የሐሳብ አርዐያዎቹ “…አንጎራጓሪ ሴቶች እንጂ ፖለቲከኞች አይደሉም” ይለናል ደራሲ በዕውቀቱ። በተጨማሪም በታሪክ ቀመስ መጣጥፎቹ በዕውቀቱ “በግለሰብ ብቃታቸው የሚያደንቃቸውን እና ኢትዮጵያን የሚያክል አገር መሥርተዋል” ሲል ገድላቸውን ያወሳል። የመጽሐፉ ምረቃ አዘጋጆች ሐሳብ ከሰመረ በቀጣዮቹ ሦስት ወራት ደራሲ በዕውቀቱ ሥዩም በተለያዩ የአሜሪካን ግዛቶች እና የአውሮፓ ከተሞች የመጽሐፍ ፊርማ ጉዞዎች እንዲያደርግ አቅደዋል።

የመጽሐፉ ምረቃ አስተናባሪዎች “የምረቃ በዐሉ በግሩም ኮሜዲ ቡፌ የተመላ፥ ከደራሲው ጋራ መጽሐፉ እንዴት እንደተጻፈ ቃለምልልስ የሚደረግበት፥ ሙዚቃ እንደ ጅረት የሚፈስበት” እንደሚኾን አስታውቀዋል። በተጨማሪም የምረቃ በዐሉ በዲሲ፥ በሜሪላንድ፥ እና በሰሜን ቨርጂኒያ አካባቢ የሚኖሩ የነቁ እና የበቁ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት የሚሳተፉበት ይኾናል። የምረቃ በዐሉ የተጋባዥ እንግዶች ዝርዝርም ታዋቂዎችን፥ አዋቂዎችን፥መሪዎችን፥ ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን፥ አርቲስቶችን፥ ወዘተ ያካተተ ይኾናል።

Leave a Reply