ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረበት ጊዜ አንስቶ በአገሪቱ ውስጥ በርካታ ብሔር ተኮርና አገር አቀፍ ፓርቲዎች ተፈጥረው ለአገሪቱ የዲሞክራሲ ግንባታ የራሳቸውን የተለያዩ ገንቢ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
ድኅረ 83 የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በቁጥር መበራከትና በተለያዩ የርዕዮተ ዓለምና የፖሊሲ አቅጣጫዎች መደራጀት ማሳያ ይሆናል እንጂ ቀደም ባሉት የአገሪቱ የፖለቲካ ሒደት በድብቅ ወይም ውስጥ ለውስጥ ስለነፃነት መከበር የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች አልነበሩም ለማለት አይደለም፡፡
በአገሪቱ ውስጥ የተፈጠሩት በርካታ ፓርቲዎች የታገሉላቸውንና እናሳካዋለን የሚሉትን ዕቅድ ከግብ እንዳያደርሱ የተለያዩ ጋሬጣዎች እንደሚገጥሟቸው በተለያየ ወቅት በፓርቲዎቹ አመራሮች በሚሰጡ መግለጫዎችና በጉዳዩ ላይ ጥናት ያከናወኑ በርካታ ኢትዮጵያዊም ሆነ የውጭ አገር ተመራማሪዎች ይገልጻሉ፡፡
ፓርቲዎቹ በአብዛኛው ያሰቡትንና የወጠኑትን እንዳያሳቡ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል በዋነኛነት በእነዚህ ተመራማሪዎችም ሆነ በፓርቲው አመራሮች ከሚገለጹ አበይት ችግሮች መካከል የሚጠቀሱት ደግሞ፤ በአገሪቱ የተቃዋሚ ፓርቲ ባህል መፈጠር ገና በመጀመሪያዎቹ ደረጃዎች ላይ የሚገኝ ከመሆኑ አንፃር ፓርቲዎቹ የአመራር ብቃት ማነስ፣ የገንዘብና የቁሳቁስ እጥረት እንዲሁም ከገዥው ፓርቲ የሚደርስባቸው ተፅዕኖና አጠቃላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሚያግባቧቸው አገራዊ ጉዳዮችና አጀንዳዎች ላይ እንኳን በጋራ ከመሥራት ይልቅ የእርስ በእርስ ፉክክር ማድረጋቸው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ከእነዚህ አጠቃላይ ምክንያቶች መካከል ፓርቲዎቹ ከገዥው ፓርቲ ከሚደርስባቸው ተፅዕኖ፣ የገንዘብና የቁሳቁስ እጥረት እኩል ባይሆን እንኳን ከፍ ባለ ደረጃ የእርስ በእርስ መጠላለፍ ለብዙዎቹ ፓርቲዎች መፈረካከስና መዳከም እንዲሁም እንደ አንድ አማራጭ ኃይል ሆነው እንዳይታዩ ሚናውን መጫወቱም ይጠቀሳል፡፡
በአገሪቱ ውስጥ ያሉት በርካታ ፓርቲዎች ለቁጥር የሚያዳግቱ በርካታ ጥምረቶች፣ ኅብረቶችና ቅንጅቶች መስተዋላቸው ለፓርቲዎቹ አንድ ላይ ለመቆም መቸገራቸውንና በጋራ ለመሥራት በርካታ ደንቃራዎች መኖራቸውን ተንታኞች ይጠቁማሉ፡፡
በርካታ ኅብረቶችና ቅንጅቶች የመፈጠራቸውን ያህል የተጠበቀውን ያህል ውጤት ማስመዝገብ አለመቻሉ የአገሪቱን መራጭ ሕዝብና አጠቃላይ የአገሪቱ የተቃውሞ የፖለቲካ ጐራ ላይ እምነቱን እንዳይጥል ቀስ በቀስ እየሸረሸረው እንደሚገኝ የፓርቲዎቹ አመራሮች ራሳቸው ምስክሮች ናቸው፡፡
ለዚህም ይመስላል በቅርቡ የዘጠኝ ፓርቱዎች በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ‹‹የትብብር›› ምሥረታ ያካሄዱት እነዚህ ዘጠኝ ፓርቲዎች አገር አቀፍ ባህሪ ያላቸውና እንዲሁም ደግሞ ክልል አቀፍ ባህሪ ያላቸው ናቸው፡፡
እነዚህ ዘጠኝ ፓርቲዎች አካሂደናል ካሉት የኢትዮጵያ የተቃውሞ ጐራ አብሮ መሥራት አለመቻልንና መዳከምን ተከትሎ ወደፊት በተለይ የፊታችን ግንቦት ወር ላይ በሚደረገው አገር አቀፍ ምርጫ በጋራ ለመቆም የሚያስችል የጋራ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተመሠረተው የትብብር ስምምነት ከቦርዱ ዕውቅና ውጪ ነው ቢልም፣ የጋራ ስምምነቱን መመሥረት ተከትሎ የትብብር መሪዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ ግን ‹‹ለመተባበር የምርጫ ቦርድን ይሁንታም ሆነ ዕውቅና ማግኘት የለብንም፤›› ብለው ነበር፡፡
የቦርዱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ግን ‹‹በቦርዱ ደንብ ላይ ትብብር የሚል ማዕቀፍ የለም›› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹ስለዚህ በዚህ ትብብር አማካይነት ነገ ወደ ሥራ ሲገቡ ችግር ቢያጋጥማቸው ቦርዱ ሊቆምላቸው የሚችልበት የሥራ አገባብ የለም፤›› በማለት የትብብሩ ጉዞ ላይ በሚፈጠሩ ችግሮችም ሆነ ቅሬታዎች ቦርዱ ለትብብሩ ምንም ዓይነት ድጋፍ እንደማያደርግ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በትብብሩ አማካይነት ሲንቀሳቀሱ በሚፈጠር ችግር ተጠያቂ የሚሆኑት ‹‹እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ፓርቲ ራሳቸው ነው የሚሆኑት፤›› ብለዋል፡፡
ይፈጠራሉ ተብለው የሚሰጉት ችግሮች ምን ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ሪፖርተር ላቀረበው ጥያቄ ዳይሬክተሩ ሲመልሱ፣ በዚህ አካሄድ ላይ ሆነው የሕግ ጥሰት ቢፈጸም ቦርዱ የሕግ ከለላ እንደማይሰጥ በመግለጽ ሊፈጠር ይችላል ይሉት ሥጋት ከሕግ ማክበር ጋር ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
አጠቃላይ የሰነዱ ይዘት
‹‹የተቃዋሚ ፖለቲካ ጐራ የጋራ ትግል ውጤታማነት ላይ የተደረገ ግምገማና ዳሰሳ›› በሚል እነዚህ ትብብር የመሠረቱ ዘጠኝ ፓርቲዎች በጋራ ባወጡት ባለ 13 ገጽ ሰነድ ላይ የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ እንዳይሠሩ ስላደረጉዋቸው በርካታ ምክንያቶች በዝርዝር ነቅሶ አቅርቧል፡፡
በዋነኛነት የአገሪቱን የተቃዋሚ ጐራ በጋራ ለመሥራት ተግዳሮት ሆነዋል ተብለው ከተዘረዘሩት አበይት ምክንያቶች ውስጥ የሚከተሉት አበይት ነጥቦች ተካተዋል፡፡
እነዚህም ነጥቦች የተቃውሞ ጐራ ፓርቲዎች በጥምረት ለሚያደርጉት ጥረት የጠራ የጋራ ሐሳብ ችግር፣ የጋራ ዓላማ ግልጽ አለማድረግ፣ የጋራ ተግባራትን አለመመጠን፣ ከአቅም በላይ ማቀድና በፍላጐት መመራት የሚሉት ይገኙበታል፡፡
በዚህም መሠረት ወደ አብሮ መሥራት ወይም ትብብር ከመሄድ በፊት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አስመልክቶ ከፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች አንፃር በቂ ትንተናና ውይይት ሳያደርጉ በተቻኮለ መንገድ ወደ የጋራ ሥራ መግባት፣ ለሁለት ጽንፎች ትግል አመቺና አሳታፊ የአማካይ ፖለቲካ ሜዳ አለመስፋት፣ ለአገሪቱ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት በምንሄድበት መንገድ የገዥውን ፓርቲ የትግል ስልትና መንገድ መከተል፣ ካረጀውና ካፈጀው የፖለቲካ ሥልጣን ጥያቄና ለውጥ ታሪክና ልምድ የሐሳብ ልዩነቶችና በቅራኔዎች ላይ ሐሳብን አሟጦ በመወያየትና መከራከር ከመማማር ይልቅ መፈራረጅና መከፋፈል ወይም በይሉኝታ ታስሮ መቀመጥ የሚሉ ነጥቦች ላይ ገንቢ ውይይቶችን ማካሄዳቸውን ይገልጻል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሰነዱ የተቃውሞ ጐራ ፓርቲዎች አቅም ውስንነት፣ የገዥውን ፓርቲ የመከፋፈል ፖሊሲ ተግባራዊነትና ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ የሚመክት ተመጣጣኝ ዝግጅት አለማድረግ፣ ካለፈው ለመማር ለድክመቶችና ውስንነቶች የተቀመጡ የመፍትሔ ሐሳቦችን ተግባራዊ አለማድረግ፣ ለዳያስፖራ አሉታዊ ተፅዕኖ በሩን ክፍት ማድረግና የመሳሰሉትን ነጥቦች በአጠቃላይ የአገሮቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተጓዙበት በጋራ ያለመሥራት መንገድ አበይት ምክንያት አድርጐ ያቀርባል፡፡
በእነዚህ ፓርቲዎች አማካይነት የቀረቡት ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ያብራራው ይህ ሰነድ፣ በአብዛኛው ያተኮረው እስካሁን ድረስ በተደረጉት የተቃውሞ ፖለቲካ ጉዞዎች የትብብርና አብሮ የመሥራት ችግሮች ላይ አበይት ትኩረት በመስጠት ነው፡፡ የተፈጠረውን ችግር በግልጽ ማወቅና መረዳት ወደ መፍትሔው ግማሽ መንገድ ያህል እንደመጓዝ ይቆጠራል ቢባልም፣ በዚህ ወቅት ስለፓርቲዎች አብሮ አለመሥራት ችግሮች ምክንያቶችን ብቻ መዘርዘር በቂ እንዳልሆነ በመጥቀስ የሚተቹም አሉ፡፡
እርግጥ ነው ሰነዱ ወደፊት በውይይት የሚዳብር መሆኑን በመግለጽ ያሰፈራቸው አንዳንድ የመፍትሔ ስትራቴጂዎች ቢኖሩም፣ ስለመፍትሔዎቹም አጠቃላይ ግንዛቤ ለመያዝና ለመወያየት እንደ ችግሮቹ ሁሉ በዝርዝር መፍትሔዎቹም ቢቀመጡ የተሻለ የውይይት ሐሳብ ሊፈጥሩ ይችሉ ነበር ሲሉ ተቺዎቹ ያክላሉ፡፡
እነዚህ በጋራ ለመተባበር የወሰኑት ፓርቲዎች ዘጠኝ ይሁኑ እንጂ በሒደቱ ወቅት የተለያዩ ፓርቲዎች አብረው ተጉዘዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንድነትና በመድረክ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ፓርቲዎች ተጠቅሰዋል፡፡
አንድነትና መድረክ ባላቸው ልዩነት የተነሳ ጉዳዩ ላይ ወስነው ትብብሩን ያለመፈረማቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ትብብሩ ችግሮችን ለመቅረፍ የተጓዘውን ጉዞና ችግሮቹን ነቅሶ ማውጣት ጥያቄ ውስጥ እንደሚከተው ተጠቅሷል፡፡ ለዚህም ምንም እንኳን የትብብሩ ኃላፊዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ ወቅት ሁለቱም ያሉባቸውን አንዳንድ ቴክኒካዊ ጉዳዮች አሟልተው በቅርቡ ይፈርማሉ ቢሉም፣ አሁንም ግን አብዛኛዎቹ ፓርቲዎች በአገሪቱ የሰፈነው የተቃዋሚ ፓርቲዎች የመጠላለፍና የመፈራረጅ የፖለቲካ ባህል ሰለባዎች ማሳያ መሆናቸውን ያመላክታሉ፡፡
ሌላው በዚህ ሰነድ ላይ ከአቅም ውስንነት ጋር በተያያዘ የተነሳው ጉዳይ አሁንም ፓርቲዎች አቅማቸውን ለመገንባት ዳያስፖራውን እንደ አንድ አማራጭነት መውሰዳቸውን ነው፡፡ ‹‹ከገዥው ፓርቲ የመከፋፈል ሴራ በተጨማሪ በእኛ ላይ ከተጠቀሱት ድክመቶች የተነሳ አቅማችንን በመከፋፈሉ ከሚመጣው ውስንነት በተጨማሪ የሕዝቡን የተባበሩ ጥያቄዎች ባለመመለሳችንም በየጊዜው ከአገር ቤትም ሆነ ከውጭ (ዳያስፖራ) በቂ ድጋፍ ለማግኘት አልተቻለም፡፡ የሚገኘውም ወጥነትና ቀጣይነት እንዳይኖረው ሆኗል፤›› በማለት የገቢ ምንጭን በተመለከተ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚጠበቅባቸውን ያህል እንቅስቃሴ አለማድረጋቸውንና ያሉትን ውስንነቶች ሰነዱ ያትታል፡፡
ምርጫና ትብብር
በተለያዩ ወቅት ከታተሙና የአገሪቱን የተቃውሞ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ከሚያጠኑ ተመራማሪዎች አካባቢም ሆነ አሁን አሁን ከአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ የሚደመጠው ጥያቄ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምን ምርጫ ሲደርስ ብቻ በጋራ ለመሥራት ይነሳሳሉ የሚል ነው፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች እስካሁን ከተፈጠሩት ትብብሮችም ሆነ ቅንጅት መሪዎች ዘንድ ሁነኛ መልስ ባይገኝም፣ አብዛኛው ምላሽ ግን ከመራጩ የሚገኘውን ድምፅ እርስ በእርስ ላለመቀራመትና ለገዥው ፓርቲ አሸናፊነት ዕድል ለመንፈግ የሚሉ ናቸው፡፡
ሆኖም ግን በምርጫ 97 ወቅት በጥቂት ወራት መደራጀትና እንቅስቃሴ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ የቻለውን ቅንጅት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ (ቅንጅትን) ጨምሮ በርካታዎቹ ትብብሮች በምርጫው ማግስት ሲፈረካከሱና መሪዎቹም ወደ የእርስ በርስ ዘለፋና መጠላለፍ ሲገቡ ተስተውሏል፡፡
በዚህ ረገድም ሰነዱ የነበረውን ችግር ‹‹ባለፉት 23 ዓመታት ለሕዝብ ከጥርጣሬና ጥያቄ ውጪ በሙሉ ልብ የሚቀበለውና አስፈላጊውን መስዋዕትነት ሊከፍልለት የሚችል መሪ ፓርቲ አላቀረብንለትም፤ በአንፃራዊነት ለ‹‹መንፈሱ›› ሽሚያ የተገባበት የ97 ቅንጅትም ቢሆን እምነት ቢጣልበትም በቃሉ አልተገኘም፤›› በማለት የፓርቲዎችን ችግር በግልጽ ያስቀመጠ ሲሆን፣ አሁንም ፓርቲዎች በጋራ ተነስተው የሕዝቡን ተስፋ ለመመለስና የገቧቸውን ቃል ኪዳኖች ለመመለስ ይህ አዲስ የትብብር ማዕቀፍ መነሳቱን ያወሳል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሁሉም ፓርቲዎች ‹‹በእስከዛሬው የጥላቻ ፖለቲካና አፍራሽ መንገድ ለደረሰው ጥፋት ንስሀ አድርገን የመቻቻል፣ የአንድነትና የፍቅር አቅጣጫ ለመከተል ሱባዔ መግባት ይኖርብናል፤›› በማለት በአገሪቱ ውስጥ ተፈጥረው ለከሰሙት ትብብሮች አለመሳካት የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም ፓርቲዎቹ ራሳቸው በጋራ ለመሥራት በንስሀ ታጥበው መነሳት እንዳልባቸው ይገልጻል፡፡
ምን መሠራት አለበት?
ይህ በዘጠኝ ፓርቲዎች በጋራ የተዘጋጀው ሰነድ በዝርዝር የተቀመጡት ዓላማዎችን ለማሳካት የተዘጋጀና ለቀጣይ የጋራ የፓርቲዎች ትግል እንደ አቅጣጫ አመላካች ሰነድ ሆኖ እንደሚያገለግል ተጠቅሷል፡፡
በዚህም መሠረት ‹‹ከተከባበርን፣ ከተደማመጥን፣ ከተስማማንና ከተባበርን ማለትም ለመለወጥ ፈቃደኝነቱና ቆራጥነቱ ካለን የጋራ ዓላማ በግልጽ እንቀርጻለን፣ በጋራ እንቆምለታለን፣ በጋራ ከምንፈልገው ግብ አብረን እንደርሳለን፣ አገርን ከጥፋትና አደጋ፣ ሕዝብን ከስቃይና መከራ እንታደጋለን፤›› በማለት በጋራና በአብሮነት የመሥራትን ጥቅም ይዘረዝራል፡፡ ሰነዱ ይህን ቢልም የተዘረዘሩትን ዓላማዎች ለማሳካት የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮችን በዝርዝር አያስቀምጥም፡፡
ከዚህ በተቃራኒው ሰነዱ ‹‹ኢሕአዴግን ጨምሮ ላለንበት ተጨባጭ ሁኔታ የሚመጥን ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጥና የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት የሚችል አንድም ፓርቲ የለም፤›› በማለት ለዚህ መፍትሔው ‹‹ሁሉን አቀፍ የብሔራዊ መግባባትና እርቅ ጉባዔ መጥራትና ማዘጋጀት›› እንደሆነ ይገልጻል፡፡
ይህም ከላይ በጥናቱ የተዳሰሱና በሰነዱ የተቀመጡ ችግሮችን ለመፍታት ኢሕአዴግም ሆነ ተቃዋሚዎች መፍትሔ የማይሰጡት ከሆነ በሰነዱ የተዘረዘሩትን ችግሮች መዘርዘርና መንቀስ በማን ይፈታ የሚለውን ጥያቄ የሚያጭር ከመሆኑም በላይ በትብብር ውስጥ ያሉት ፓርቲዎችስ ለለውጡ መፈጠር ያላቸው ድርሻ ምንድን ነው የሚል ጥያቄ ያጭራል፡፡