29 OCTOBER 2014 ተጻፈ በ 

በዳያስፖራ ካሉ ደጋፊዎች ጋር ባለመግባባታቸው ምክንያት የተነሳ ጥቅምት 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው በለቀቁት የቀድሞው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ፕሬዚዳንት አቶ ግዛቸው ሽፈራው (ኢንጂነር) ሥልጣን መልቀቃቸውን ተገቢ አይደለም የሚሉ የፓርቲው አባላት ለምርጫ ቦርድ የተቋውሞ ደብዳቤ አስገቡ፡፡

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአንድነት ፓርቲ የተለያዩ አካላት የራሳቸውን ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ ዳይሬክተሩ ‹‹ጉዳዩ በሰከነ መንገድ መፈታት ስላለበት እያየነው ነው፤›› ብለዋል፡፡

በዚህም መሠረት ‹‹የትኛው አካሄድ ነው ትክክለኛና ሕጋዊ የሚለውን በመመርመር በቅርብ ቀን ምላሸ ይሰጣል፤›› በማለት አክለው አብራርተዋል፡፡ ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁት የቀድሞው ፕሬዚዳንት በበኩላቸው፣ ‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ ለምርጫ ቦርድ የቀረበ ደብዳቤ ስለመኖሩ የማውቀው ነገር የለም፤›› በማለት ለሪፖርተር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የአንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አበበ አካሉ በበኩላቸው፣ ጉዳዩን አስመልከተው በሰጡት ማብራርያ ‹‹ባለን ደንብ መሠረት ብሔራዊ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔው በሌለበት ቦታ ፕሬዚዳንቱ ሥልጣኑን ሲያስረክብ ሌላ ፕሬዚዳንት መምረጥ የሚያስችል ሥልጣን ስላለው፣ ስለዚህ የተመረጡትን ፕሬዚዳንትና ቃለ ጉባዔውን አያይዘን አዲሱ ፕሬዚዳንት መመረጣቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ነው ያስገባነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አዲሱ ፕሬዚዳንት ያዋቀሩትን አዲስ የካቢኔ ዝርዝርም ለምርጫ ቦርዱ ማሳወቃቸውን ገልጸዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ሥልጣን የለቀቁበት መንገድ ተገቢ አይደለም የሚሉት ጥቂት ግለሰቦች በገዢው ፓርቲ አማካይነት የሚጠመዘዙ ግለሰቦች ናቸው ያሉ ሲሆን፣ በዚህም ጉዳይ ላይ ፓርቲው በቅርቡ የዲሲፒሊን ዕርምጃ  እንደሚወስድ አስታውቀዋል፡፡

Leave a Reply