Wednesday, 29 October 2014 14:23

በሳምሶን ደሳለኝ  

 

የፖለቲካ ጨዋታ መቼም ስጎና ፓስታን እንደመቀላቀል ቀላል አይሆንም። ከተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ቀርቶ በአንድ ወጥ ፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ለቁጥር የሚታክት የፖለቲካ ጥልፍልፎሽ መኖሩ አይካድም። ፖለቲካን በጥሬው ከተመለከትነው ደግሞ ይህን መሰል ሂደት ተፈጥሯያዊ መሆኑ አሻሚ አይደለም።

በፖለተካ ፓርቲዎች ውስጥ አንዱ ከሌላው ወይም አንዱ ቡድን ከሌላው ቡድን የተሻለ መሆኑን ለማሳየት የሶስተኛ ወገን ተለጣፊ አስተሳስብ ያለው አድርጎ ማቅረብ የተለመደ የፖለቲካ መጫወቻ ካርታ መሆኑ አዲስ አይደለም። በተለይ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ዓለም በሁለት ታላላቅ የፖለቲካ ርዕዮተዓለም ስትከፈል በፖለቲከኞች መካከል የመበላላት የፖለቲካ ጨዋታ ቀሎ የሚታይ፣ የሰው ልጅ ሂይወትም በቀላሉ የሚረግፍ የደረቀ የዛፍ ቅርፊት ይመስል በአስተሳሰቡ ብቻ በየቦታው መርገፉን ብዙ ማጣቀሻዎች ማንሳት ይቻላል።

በሶሻሊዝም ርዕዮተዓለም የተሰለፉት ኃይሎች፣ በፓርቲያቸው ውስጥ የሚፈጠሩ ተቀናቃኝ አስተሳሰሰብ የሚያራምዱ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖችን የካፒታሊዝም ርዝራዦች ናቸው የሚል ታፔላ በመለጠፍ በአደባባይ ይገድሏቸው ነበር። በካፒታሊዝም ጎራ የተሰለፍ ኃይሎችም በውስጣቸው የሚበቅሉ አስተሳሰቡ በዝባዥ መሆኑን ለማንፀባረቅ የሚሞክሩ ኃይሎችን የሶሻሊስት ርዕዮተዓለም አራማጅ ኃይሎች ናቸው በማለት በአደባባይ ብዙዎችን ፈጅተዋል።

ይህም ብቻ አይደለም፣ ነፃ ሀገሮች የራሳቸውን የፖለቲካ ዕጣ ፈንታ እንዳይወስኑ በአሜሪካ መራሹ ካፒታሊዝም እና በታሏቋ ሶቪዮት ሕብርት መሪነት ሲቀነቀን በነበረው የሶሻሊስት ርዕዮተዓለም መነሻነት ብዙ ንፅሃን የዓለም ዜጎች በግፍ ረግፈዋል። የእነሱን አስተሳሰብ አልቀበልም ያሉ መንግስታት ተወረዋል፣ ፈርሰዋል፣ ተገድለዋል። ዓለም ሕዝቦች ደም እንደጎርፍ አለጠያቂ ፈሷል።

በጊዜው ከሚጠቀሱት ታፔላዎች መካከል በሶሻሊስት ጎራው፤ ንዑስ ከበርቴ፣ አድኃሪ፣ አደርባይ፣ ሸፍጠኛ፣ ፀረ-ሕዝብ፣ አቋም አልባ፣ መደብ የለሽ፣ አናርኪ እና የመሳሰሉት ይገኛሉ። በካፒታሊስ ጎራ ውስጥ አንድ ተቀናቃኝ ኃይልን ለመብላት፣ ይህ ሰው ኮሚኒስት ነው። ወይም ይህ ቡድን የኮሚኒስት አስተሳሰብ የሚያራምድ ነው የሚል ታፔላ መለጠፍ ግለሰቡን ወይም ቡድኖችን ለማጥፋት ከበቂ በላይ ምክንያት ነበር።

ከቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ ዓለም ዓቀፉ ሕብረተሰብ በግልፅ በአሜረካ መራሹ የምዕራቡ ዓለም የነፃዊነት እና የኒዮ ነፃዊነት ፖለቲካ ኢኮኖሚ ውስጥ ወደቀ። መድብለ ፓርቲ ስርዓት በሚባል የፖለቲካ ፈሽን አለም ሁሉ ተሳታፊ ሆነ። የሕዝቦች የመንግስታት የፖለቲካ ቁመናቸው መለኪያ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት አንዱና ዋነኛው መሆኑ ዓለም ዓቀፍ ኢፔሪያሊዝም አዋጅ አስነገረ። መድብለ ፓርቲ ስርዓት የማይከተል ሀገር የምዕራቡ ዓለም ፖለቲካ ኢኮኖሚ አራማጅ መሳሪያ ከሆኑት አይ.ኤም.ኤፍ እና ዓለም ባንክ አንዳችም የገንዘብ ድጋፍ እንዳያገኙ ተደረገ። ምርጫ ያጣው የተቀረው የዓለም ሕብረተሰብ እና መንግስት ወደ መድብለ ፓርቲ ስርዓትን ተቀበለ።

የመድብለ ፓርቲ ስርዓት የተካው ሌላ ሳይሆን ዓለምን በሁለት ጎራ ወጥሮ መውጫ ቀዳዳ ያሳጣውን የሶሻሊስት ጎራን እና የካፒታሊስት ጎራን የፖለቲካ ፋሽንን ነበር። ጨዋታው ከዓለም ዓቀፍ የፖለቲካ መድረክ ወደ ሉዓላዊ ግዛት የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ተመለሰ። በሉዓላዊ ግዛት ውስጥ ያለው የፖለቲካ ጨዋታ አዲስ መልክ እያያዘ መጣ። ይህም ሲባል፣ ዓለም ዓቀፉ ገዢ አስተሳሰብ የሆነውን የነፃዊነት እና የኒዮ ነፃዊነት ፖለቲካ ኢኮኖሚ የተሸከሙ የተፈጠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሀገር በቀል የፖለቲካ አስተሳሰብ አራማጅ ፓርቲዎች የሚፋጠጡበት የፖለቲካ መድረክ አዲስ የፖለቲካ ፋሽን ሆኖ ብቅ አለ።

የነፃዊነት እና የኒዮ ነፃዊነት ፖለቲካ ኢኮኖሚ አራማጅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዓለም ዓቀፉ ኢምፔሪያሊዝም ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ሲቀርብላቸው፣ ሀገር በቀል የፖለቲካ ኢኮኖሚ የሚያራምዱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ግን ፈታኝ የፖለቲካ ከባቢያዊ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩባቸው ተደረገ። ይህም በመሆኑ በተለይ በሶስተኛው ሀገሮች ውስጥ ተቀራማች መንግስታት እንደአሸን ፈሉ። የተሻለ ተቀራማች መንግስት ሆኖ መገኘት የሚያስመሰግን ዓለም ዓቀፍ ከበሬታ የሚያስገኝ ሆኖ ናኘ። በዚህ ተቀራማች መንግስታት እና ሀገር በቀል አስተሳሰብ አራማጅ ኃይሎች መካከል ዓለም ለሁለት ተወጠረች። ከሕዝቦች ፈቃድ ውጪ የሚነግሱ ፖለቲከኞችን መመልከት አስገራሚነቱ እየቀረ፣ እየሟሸሸ መጣ።

ከሉዓላዊ ሕዝቦች ፈቃድ ውጪ በአንድም በሌላ መንገድ የአንድን ሀገር የፖለቲካ ኬሚስትሪ በውጭ ኃይሎች እየተቀመመ እንደወባ ኪኒን በማደግ ላይ ላሉ ሀገሮች ይታደል ጀመር። ይህን መርዘኛ ኪኒን ወባ ኖረ አልኖረ መወጥ አማራጭ የሌለው ምርጫ ሆነ። ኧረ እኔ ወባ አልያዘኝም ብሎ ኪኒኑን ለመዋጥ የሚያንገራግር አካል ከተገኘ፣ መታመምህን እኔ እንጂ አንተ እንዴት ታውቃለህ ተብሎ ይገፀስ ጀመር። ዓለም በዚህ መልኩ እስካሁን ድረስ የፖለቲካ ፋሽኑን የቀየረ የፖለቲካ ስርገት ውስጥ መሆኗን የሚክድ ፖለቲከኛ የለም።

የስርገት ፖለቲካ በእኛስ ሀገር ምን ይመስላል?

እ.ኤ.አ. በ1966 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተካሄደው አብዮት መሰረታዊ ምክንያቶቹ ሀገር በቀል መሆናቸው ቢታወቅም ለጥያቄዎቹ ግን ምላሽ ለመስጠት የተሄደበት አግባብ ውጫዊ ነበር። ይህም ሲባል፣ በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የፊውዳሊዝም ስርዓት ለመቀየር ሀገር በቀል አስተሳሰቦች በስለውና ነጥረው የተዘጋጁ ባለመሆናቸው ሌሎች ሀገሮች ከራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የቀመሩትን የፖለቲካ ኢኮኖሚ አስተሳስብ እኛም ተቀብለን ለማስተናገድ ተገደናል። ይሄውም፣ የታላቋን ሶቪየት ሕብረት ሶሻሊዝም ነበር።

የታላቋን ሶቪየት ሕብረት ሶሻሊዝም የመደብ ውክልናው የሚመነጨው ከአምራች ሠራተኞች ነበር። በተለይ ከፋብሪካ ሠራተኞች። ይህን መሰል የመደብ ውክልና በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ማግኘት አስቸጋሪ ነበር። የሠራተኛም መደብ አልነበረም ማለት ይቻላል። ይህን ውክልና አልባ የፖለቲካ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ ነበር የታጠቅነው። ይህን ክፍተት በመተቀም ነበር ሶሻሊዝም ሰርጎ ወደኢትዮጵያ የገባው። በወቅቱም ሶሻሊዝም አስተሳሰብ ከውክልናው ውጪ ሥርነቀል ለውጥን የሚፈቅድ በመሆኑ ለለውጥ የተነሱ የዩንቨርስቲ ተማሪዎችም ይህን ስርነቀል ለውጥ ለሚያመጣ ርዕዮተዓለም ድጋፋቸው ከመስጠት አልፎ፣ ተቀብለው ታግለዋል። በእምነታቸውም ተሰውተዋል። ደርግም በማያውቀው ሶሻሊዝም ነጥቆ ነግሶበታል።

ከደርግ ውድቀት በኋላ አዲስ ኃይል ሆኖ የመጣው አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባለው ርዕዮተዓለም ነው። ይህ አስተሳሰብ ውክልናው ከገበሬ የሚነጭ ነው። አከራካሪ ነጥቡ ግን፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ራሱን የቻለ ዓለምን ለማየት የሚያስችል ርዕዮት ነው? ወይንስ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመዘርጋት ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት አመቻች መሳሪያ ነው። ይህም ሲባል፣ ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ኢኮኖሚ ስርነቀል በሆነ መልኩ ከቀየረ በኋላ፣ የምከተለው ርዕዮተዓለም ወይም ገዢ የፖለቲካ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ ዴምክራሲያዊ ልማታዊ መንግስትን ነው ማለቱ ነው።

ከዚህ አንፃር አብዮታዊ ዴሞክራሲ ለዴሞክራሲያዊ ሂደት የስርነቀል መጥረጊያ መሳሪያ ሲሆን፣ ሂደቱን ሲጨርስ ግን የራሱን ርዕዮት የሚመርጥበት አግባብ መኖሩን ያሳያል። ይህም በመሆኑ ይመስላል፣ የነፃዊነት እና የኒዮ ነፃዊነት ፖለቲካ ኢኮኖሚ አንቀበል የሚል የከረረ አቋም የሚያራምዱት። በተለይ የቀድሞ የኢሕአዴግ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ በግልፅ በዚህ ሀገር በቀል አስተሳሰባቸው በዓለም አቀፍ መድረኮች በመቅረብ ሲሟገቱ አስተሳሰቡን በሌሎች አካሎችም ጭምር ተቀባይነት እንዲያገኝ ሲተጉ ነበር።

ለእሳቸውና ለፓርቲያቸው ሀገር በቀል አስተሳሰብ ሁሉም ነገር ግን አልጋ በአልጋ ነበረ ለማለት አይቻልም። አሁንም አይደለም። በተለይ ግን በምርጫ ዘጠና ሰባት የነፃዊነት እና የኒዮ ነፃዊነት ፖለቲካ ኢኮኖሚ አራማጅ ፖለቲካ ፓርቲዎች የደቀኑባቸው ፈተና ቀላል አልነበረም። የተለመደውን የተቀራማች መንግስታትን ባሕሪ በዚህች ሀገር ውስጥ ለመትከል ከፍተኛ ሩጫ እንደነበር የፓርቲው ከፍተኛ የፖለቲካ አመራር የሆኑት አቶ በረከት ስምዖን “የሁለቱ ምርጫ ወጎች” በሚል መፃህፋቸው በስፋት አስፍረውታል። የመፃሃፉም ጭብጥ፣ የነፃዊነት እና የኒዮ ነፃዊነት ፖለቲካ ኢኮኖሚ የስርገት ፖለቲካ ላይ ያነጣጠረ ነበር።

በፖለቲካ ፓርቲዎች ስርገትና የታፔላ ፖለቲካ እንዴት ይታያል?

በየትም ዓለም የሚገኙ ተቀናቃን የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ የሌላውን ድክመት እና ጥንካሬ በመለየት የኃይል አሰላለፉን ያስተካክላል። ድክመቱን ያርማል። ጠንካራ ጎኑን የበለጠ አጠናክሮ ይዞ ይቀጥላል። በቀናቃኝ ወገን ያለውን ደካማ ጎን በመጠቀም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ይሰራል። በተቀናቃኝ ጎን ያለውን ጥንካሬ በመለየት ጥንካሬውን ለመሸርሸር ይሰራል። ምክንያቱም በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ውስጥ ምርጫ የግድ በመሆኑ የተሻለ ሆኖ መገኘት ግድ ስለሚሆን ነው።

ፖለቲካ ይሁንታ የለውም። ፖለቲካ በግልፅ ቋንቋ ስልጣን መፈለግ ነው። ስልጣን የሚፈለገው፣ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ አስተሳሰቡን እምነቱን በሕዝብ ላይ ለማስረጽ የግድ ከሕዝብ የመነጨ የፖለቲካ ስልጣን ስለሚያስፈልገው ነው። የፖለቲካ ስልጣን ለማግኘት የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። አንዱ በሌላው ፓርቲ ውስጥ የራሱን ሰዎች አስርጎ ያስገባል። በእነዚህ ሰዎች አማካኝነት የተቀናቃኝ ወገኖችን መረጃ በቀላሉ ማግኘት ያስችለዋል። በሚያገኛቸው መረጃዎች መነሻነት የተቀናቃኝ ፓርቲውን ስራዎች ቀድሞ በመሄድ ያከሽፋቸዋል። ይህን በማድረጉ የሚያገኘው የፖለቲካ ትርፍ ብዙ ነው።

የፖለቲካ መጫወቻ መድረክ ውስጥ ከተገባ በኋላ እንዴት የእኔ ፓርቲ ውስጥ የራሱን ሰዎች አስርጎ ያስገባል? ይሰልላል? እንድንፈርስ እየሰራ ነው? የሚባል ክስ የሚያቀርብ የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ፖለቲከኛ የፖለቲካ ሀ..ሁ … ያልገባው መሆኑ አሻሚ አይደለም። በጥሬ የፖለቲካ ቋንቋ ከተረጎምነው ደግሞ፣ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በተቀናቃኙ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ ሰርጎ መግባት ከቻለ የፓርቲውን ጥንካሬ የሚያሳይ እንጂ የሚያስወነጅል ተግባር አይደለም። ምክንያቱም የፖለቲካ ተፈጥሮያዊ ሂደት ይህን ስለሚፈቅድ ነው።

የፖለቲካ ሴራ መቋቋም የማይችሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሰርጎ የገባባቸውን ኃይል ጠርገው ከማስወጣት ይልቅ በፓርቲያቸው ውስጥ ለሚፈጠሩ ልዩነቶች አንዱ ሌላኛውን ለማጥቃት በሰርጎ ገብነትን በመለጠፍ ሲወነጃጀሉ ይስተዋላል። ፓርቲውም የራሱን ትልቅ ስዕል በመተው ወደታች ወርዶ ግለሰቦች ላይ ታፔላ ሲለጥፍ ይገኛል። ይህም በመሆኑ፣ ፓርቲው ብዙም ርቀት ሳይጓዝ ተጠልፎ ይወድቃል። የታፔላ ፖለቲካ መጨረሻውም ይህ ነው። እየታዘብን ያለነውም፣ ይህን የታፔላ ፖለቲካ ነው። ይሰውረን።

Leave a Reply