የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በታህሳስ ወር 2001 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ጉባዔው ከቀረቡለት አዋጆች መካከል ዋነኛ የዕለቱ መከራከሪያ የነበረው የፀረ ሽብር አዋጁ ነበር፡፡
ይሁን እንጂ በፀረ ሽብር አዋጁ ድንጋጌዎች ላይ እስኪደክሙ የተከራከሩት የሕዝብ ተወካዮች፣ በቀጣይ ለቀረበው አጀንዳ ትኩረት አልነበራቸውም፡፡ በመሆኑም ይህ ትኩረት ያላገኘው የደኅንነት ሕይወት አዋጅ በእንግሊዝኛው አጠራር ‹‹ባዮ ሴፍቲ ፕሮክላሜሽን›› ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ሳይመራ በመጀመሪያ ንባብ በአብላጫ ድምፅ ፀደቀ፡፡
ይህ አዋጅ በአገሪቱ ዕለታዊ የሥራ ማስፈጸም እንቅስቃሴ ላይ እክል ለመፍጠር የፈጀበት ጊዜ ግን አራት ወራት ብቻ ነው፡፡ ወቅቱ በአገሪቱ ከፍተኛ ድርቅ ተከስቶ ስድስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በድርቅ እየተሰቃዩ ነበር፡፡ በመሆኑም በወቅቱ የነበረው የአደጋ መከላከያና ዝግጁነት ኮሚሽን ለተባባሪ አገሮችና ድርጅቶች በቀረበው የትብብር ጥሪ በርካቶች ምላሽ መስጠት ቢጀምሩም፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ለዕርዳታ ያጓጓዘው በዘረ መል ምሕንድስና የተለወጠ የስንዴ ምርት ወደ አገር መግባት አልቻለም ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በዘረ መል ምሕንድስና የተለወጠ ዘር ወደ አገር ውስጥ መግባት የሚችለው በሕግ አግባብ ሥልጣን ከተሰጠው የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ፈቃድ ማግኘት ሲቻል ነው፡፡
በመሆኑም ጉዳዩ ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጽሕፈት ቤት መቅርቡ የግድ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በድርቅ የተጎዱ ኢትዮጵያውያን ጉዳይን ከግምት በማስገባት እንዲሁም የዕርዳታ እህሉ ከታቀደለት ዓላማ ውጪ ለዘርነት እንዳይውል የሚለውን ሥጋት በማመዛዘን የዕርዳታ እህሉ ተፈጭቶ በዱቄት መልክ እንዲገባ ወስነዋል፡፡
በዚሁም መሠረት ኢትዮጵያ ጥብቅ የአካባቢ ጥበቃ ሥርዓትና የዘረ መል ምሕንድስና ጠንቆችን በአግባቡ መገንዘብ የቻለች አስብሏታል፡፡ ነገር ግን አገሪቱ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ያስቀመጠችውን የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ግብ የዘርፉ ግብዓት በሆነው የጥጥ ምርት እጥረትና የጥራት ጉድለት የተነሳ ማሳካት ባለመቻሏ፣ የዘረ መል ምሕንድስና ላይ ጥብቅ የሆኑ ድንጋጌዎችን የያዘውን የደኅንነት አዋጅ (ባዮ ሴፍቲ አዋጅ) በድጋሚ ለማሻሻል እየተሞከረ ነው፡፡ ማሻሻያው በደንና አካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር፣ በግብርና ሚኒስቴር፣ በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እንዲሁም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በጋራ ትብብር የተረቀቀ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአካባቢ ጥበቃ ተከራካሪዎችና የዘረ መል ምሕንድስና ተቃዋሚ ቡድኖች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ ኢትዮጵያ በፖለቲካ ጫና በዘረ መል ምሕንድስና የተለወጠ ዘርን ወደ አገር ለማስገባት ሕጓን እያላላች ነው የሚሉ አሉ፡፡
የዘረ መል ምሕንድስናና ፖለቲካው
የዘረ መል ምሕንድስና በተፈጥሮ ሥርዓት ሊገኙ የማይችሉ በተለያዩ ዝርያዎች ውስጥ የሚገኙ ዘረ መሎችን ተፈጥሮዓዊ ባልሆነና ለየት ባለ የጥበበ ሕይወት ዘዴ በማቀናጀት አዲስ ባህሪን የመፍጠርያና ሕያዋንን የመለወጫ ዘዴ ነው፡፡ ይህ ዘዴም የዘረ መሉን መረጃ በመቀየር (Genetic Editing) ጠባዩን በመለወጥ፣ የዘረ መሉን ስፍራ በመቀየር፣ የማጣበቅና ፀረ ሕያው ኬሚካልን መጠቀም ያካትታል፡፡
በዚህ ሒደት አዲስ የዘረ መል ቅንብር በመሥራትና ዘረ መሉን በቫይረስ ወይም በባክቴሪያ አለዚያም አካላዊ በሆነ ግፊት አማካይነት ወደ የሚቀየረው ሰብል ዘር ወይም ሕዋስ እንዲገባ በማድረግ አዲስና ልዩ ለውጥ ሕያው የመፈብረክ ዘዴ ነው፡፡
በዚህም መሠረት የዘረ መል ምሕንድስና ውጤት በሰውና በአካባቢ ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል የዘርፉ ተመራማሪያንና ምሁራን ይናገራሉ፡፡
የኢትዮጵያ የደኅንነት ሕይወት (የባዮ ሴፍቲ) አዋጅ ቁጥር 655 መቅድም ሕግ መውጣት አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጽ ‹‹የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 44 እና 92 ድንጋጌዎች የአካባቢ ደኅንነት መብት የሰውና የእንስሳት ጤናን፣ የአካባቢ ደኅንነትን፣ በአጠቃላይም የአገሪቷን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን ልውጥ ሕያዋን ሊያስከትሉት ከሚችሉት ጠንቅ መጠበቅ አስፈላጊ ስለሚያደርገው ነው፤›› ይላል፡፡ የዚህ የባዮ ሴፍቲ አዋጅ ሌላ መነሻ የሆነው ካርታኼና ፕሮቶኮልም አገሮች በዘረ መል ምሕንድስና የተፈጠረ ዘር ዝውውርና አጠቃቀም በአካባቢና በሰው ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የሚደነግግ ነው፡፡
ይህንን ፕሮቶኮል በአሁኑ ወቅት 168 አገሮች ተቀብለው ያፀደቁት ቢሆንም፣ የዘረ መል ምሕንድስና ደጋፊና በስፋት ተጠቃሚ አሜሪካ ግን እስካሁን አላፀደቀችውም፡፡
በዘረ መል ምሕንድስና የሚፈጠር ዘር አዲስ የተለያዩ ዘረ መሎች ጥንቅርን የሚይዝ መሆኑና ይህ ጥንቅር ደግሞ በተፈጥሮ የማይገኝ መሆኑና አዲሱ ዘረ መል ውጤት በውል የማይታወቅ መሆኑን ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
‹‹መልካ ኢትዮጵያ›› የተባለ ሲቪክ ማኅበር መሥራችና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሚሊዮን በላይ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የዘረ መል ምሕንድስና ላይ እየሠሩ የሚገኙት ኩባንያዎች በዓለም ላይ ታላቅ ኃይል ባላቸው በአሜሪካና በአውሮፓ መንግሥታት ተቀማጭነት ያላቸው መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹በመሆኑም በገንዘብ፣ በማሳመንም፣ ሳይንስን በማዋደቅም ሊሆን ይችላል ቴክኖሎጂው ዓለም ላይ እንዲጫን እየተደረገ ነው፤›› በማለት ይከራከራሉ፡፡
በተለይ ሞንሳንቶ የተባለው ዘሮችን በተለይም በዘረ መል ምሕንድስና የተፈጠሩ ዘሮችን የሚያቀርበው የአሜሪካ ኩባንያ፣ በመላው ዓለም የአሜሪካን ፖሊቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉልበት በመጠቀም አገሮች ላይ ተፅዕኖ በማድረስ በዘረ መል ምሕንድስና የተለወጡ ዘሮችን እያስፋፋ ነው የሚል ክስ ይቀርብበታል፡፡
ይህን ግዙፍ የአሜሪካ ኩባንያ በጥርጣሬ የሚመለከቱ ብዙ ናቸው፡፡ እነዚህ ወገኖች ሥጋታቸውን ሲገልጹ፣ ሞንሳንቶ አሜሪካ ከቬትናም ጋር ባካሄደችው ጦርነት ውጊያውን ለመደምደም የተጠቀመችበትን ኮሬንጂ የተሰኘ ገዳይ ኬሚካል ያመረተ ኩባንያ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚያ በዘለለም ተርምኔተር ኪድን ያመረተ ኩባንያ ነው ይላሉ፡፡ እንዴት ዛሬ ላይ ሊታመን ይችላል?›› በማለት የሥጋታቸውን መነሻ የሚናገሩ ብዛት አላቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሞንሳንቶ የሚያቀርበውን ልውጥ ዘር ገዝቶ የተጠቀመ አገር በየዓመቱ ዘሩን በተጠቀመ ቁጥር የአገልግሎት ክፍያ መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ በመሆኑም የሞንሳንቶ ኩባንያ ጥገኛ የመሆን ዕድሉ የሰፋ ነው በማለት የኩባንያውን እንቅስቃሴ በመተቸት አገሮች እንዲጠነቀቁ ይመክራሉ፡፡
የአሜሪካ ኤምባሲዎች ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶቻቸው የሚልኳቸውን መረጃዎች ያጋለጠው ዊኪሊክስ የተባለው ድረ ገጽም፣ የአሜሪካ መንግሥት በዘረ መል ምሕንድስና የተለወጠ ዘርን በመላው ዓለም ለማድረስ የሚያደርገውን ግፊት አጋልጧል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2007 ፈረንሳይ የዘረ መል ምሕንድስና ውጤቶችን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኗ የተነሳ በወቅቱ በፈረንሳይ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ክሬግ ስታፕሌተን ለውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤታቸው ፈረንሳይን ጨምሮ ሌሎች የዘረ መል ምሕንድስናን ያልተቀበሉ የአውሮፓ አገሮችን አሜሪካ መቅጣት እንደሚገባት ያስተላለፉትን መልዕክት አጋልጧል፡፡
ይህ ግፊት ኢትዮጵያ ላይ ተሰንዝሯል ብቻ ሳይሆን ግፊቱ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ዶ/ር ሚሊዮን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ወደ ኢትዮጵያ ለውጭ ዘሮች እንዲገቡ ለምን ተፈለገ ተብሎ ሲታሰብ የሚታዩ ነገሮች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ የእርሻ ሥርዓቷን እንድትለውጥ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ተቋቁሟል፡፡ ይህ ተቋም ድጋፍ የሚያገኘው ከአሜሪካ ኤምባሲና ከአሊያንስ ፎር ግሪን ሪቮሊዩሽን ኦን አፍሪካ (አግራ) ከሚባል ተቋም ነው፡፡ ካልተሳሳትኩ አግራ ሞንሳንቶ በተባለው ድርጅት ውሰጥ 17 በመቶ የሚሆን የሀብት ድርሻ አለው፤›› በማለት የትስስር ሰንሰለቱን ዶ/ር ሚሊዮን ለማሳየት ሞክረዋል፡፡
አንድ ላብራቶሪ ውስጥ የሚሠራ ሳይንቲስት ሁለት ነገር ሊሠራ እንደሚችል የሚናገሩት ዶ/ር ሚሊዮን፣ ‹‹ስንዴን ከስንዴ ጋር ሊያቀላቅል ይችላል፡፡ ይህንን ደግሞ ገበሬውም ሆነ ተፈጥሮ የሚያደርጉት ነው፡፡ ስንዴን ከባክቴሪያ ጋር ሲቀላቅል ግን በተፈጥሮ የተገደበውን የዘረ መል ድንበር አልፏል ማለት ነው፡፡ የሰው ልጅ የማይመገባቸውና የማይጠቀማቸው ነገሮች ተቀላቅለው ጥሩ ባህሪ ለማግኘት እየተጣረ ነው፡፡ ሌላው ችግር ደግሞ ቴክኖሎጂው ተለያይነትን ማጥፋቱ ነው፡፡ ተለያይነት የሕይወት መሠረት በመሆኑ፣ ተለያይነት በጠፋ ቁጥር ሕይወት ይሞታል ማለት ነው፤›› በማለት ይከራከራሉ፡፡
በዘረ መል ምሕንድስና የተለወጠ ዘር እየተጠቀመች የምትገኘው ህንድ በርካታ ገበሬዎቿ በኢንፌክሽን አንዳንዶቹም በካንሰር እየተጠቁ መሆኑን ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ ታዲያ ይኼ ሁሉ ክርክርና በመረጃ ላይ የተመሠረተ የባለሙያዎች ግፊት በኢትዮጵያ እንዴት ጆሮ ሊያጣ ቻለ ብለው የሚጠይቁ አሉ፡፡
ቢቲ ኮተን
በጥጥ አምራችነቷ በዓለም አራተኛ ደረጃ እንደሆነች የሚነገርላት ፓኪስታን ብትሆንም፣ ኢትዮጵያ ከፓኪስታን ጋር የሚመጣጠን እምቅ አቅምና የሚለማ መሬት እንዳላት ይነገራል፡፡ ዘንድሮ በሚጠናቀቀው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይም ይህንን አቅም በመጠቀም ከጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ አንድ ቢሊዮን ዶላር የኤክስፖርት ገቢ ለማግኘት ውጥን ተይዟል፡፡ ይህም ማለት ከመቶ ሺሕ ሔክታር በታች ለምቶ የነበረውን ለጥጥ ምቹ የሆነ መሬት፣ በዕቅዱ ዘመን መጨረሻ ላይ ወደ 500 ሺሕ ሔክታር ማሳደግን ይጠይቃል፡፡
ይሁን እንጂ በ2007 ዓ.ም. መጀመሪያ ወራቶች ላይ በጥጥ መልማት የቻለው መሬት 110 ሺሕ ሔክታር ብቻ ሲሆን፣ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዋነኛ ችግሮች መካከል የጥጥ አቅርቦት ተጠቃሽ ነው፡፡ የዚህ ሁሉ ችግር ምክንያት በኢትዮጵያ የሚገኘው የጥጥ ዘር ጥራት የሌለው እንዲሁም በበርካታ ባክቴሪያዎች በተለይም በቦልሆርም የሚጠቃ በመሆኑ ነው፡፡ በአገሪቱ እየተመረተ የሚገኘው የጥጥ ምርት በተጠቀሱት ምክንያቶች በአገር ውስጥ ለሚገኙ ፋብሪካዎች የጀርባ አጥንት መሆን አልቻለም፡፡ በመሆኑም ከሌሎች አገሮች የጥጥ ምርት ማስገባትን የግድ ብሏል፡፡
በመሆኑም ችግሩን ለመፍታትና አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ ከፍ ማድረግ ካስፈለገ የግድ የጥጥ ዘርን መለወጥ ያስፈልጋል ወደሚል ድምዳሜ ተደርሷል፡፡ ይህ የጥጥ ዘር ደግሞ ‹‹ቢቲ ኮተን›› Bacillus Thuringiensis (BT) ነው፡፡ በተፈጥሮ አፈር ውስጥ ከሚገኘው ቢቲ ባክቴሪያ ጋር በዘረ መል ምሕንድስና የሚፈጠር የጥጥ ዓይነት ኬሚካሎች ውስጥም እንዲዋሃድ የሚደረግ ነው፡፡ እዚህ ባክቴሪያ ውስጥ የሚገኝ ‹‹ክራይፕሮቲን›› እንዲወጣ ይደረግና ጥጥ ውስጥ ካለ ዘረ መል ጋር ይቀላቀላል፡፡
በሰው ሰራሽ መንገድ የጥጥ ዘረ መል አካል እንዲሆን የተደረገው ክራይፕሮቲን የጥጥ ዋነኛ ጠንቅ የሆነውን አፍሪካን ቦል ዎርም የተባለ ተባይ የመግደል አቅም አለው፡፡ ስለሆነም ይህ ተባይ በዘረ መል የተፈጠረውን ቢቲ ኮተን ማጥቃት አይችልም ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ዘር ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ይፈለጋል፡፡
ነገር ግን ይህ ቢቲ ኮተን የተባለ ዘር ወደ አገር ውስጥ መግባት እንደሌለበት ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ቢቲ ኮተን የተባለው የጥጥ ዘር ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ቢፈቀድ፣ የኢትዮጵያ የጥጥ ዝርያዎችን ባህሪ ይቀይራል የሚል መከራከሪያ አላቸው፡፡ በተጨማሪም ቢቲ ኮተን ጥቅም ላይ ሲውል የሚፈጥረው ችግር ጥጥ ላይ ብቻ ለውጥ የሚያመጣ ላይሆን ይችላል፡፡ በተክሉ ዙሪያ ያሉ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ላይ የሚፈጠረውም አይታወቅም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የጥጥ ፍሬ የምግብ ዘይት ለማምረት ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን፣ ተረፈ ምርቱም ለከብቶች መኖ ይውላል፡፡ ኢትዮጵያ ከዘረ መል ምሕንድስና ነፃ ዞን የምትባል አገር ስትሆን፣ ለዚህ ለጥጥ ብቻ ተብሎ ይህንን የሚቀይር ነው የሚል አስተያየት ይሰጣል፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በዓመት 4.2 ሚሊዮን ሊትር ኬሚካል ለጥጥ ተባይ ማጥፊያ እንደምትጠቀም የሚናገሩ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ቢቲ ኮተን ጥጥ ኢትዮጵያ ላይ ለጥቅም ቢውል ይህንን መጠን ኬሚካል ማስቀረት ይቻላል ተብሎ ይታሰባል የሚሉት ዶ/ር ሚሊዮን፣ ይህ ሙሉ ለሙሉ እውነት እንዳልሆነ ይከራከራሉ፡፡ ህንድ የቢቲ ኮተንን ዘር እንደምትጠቀም ነገር ግን የምትጠቀመው የተባይ ማጥፊያ ኬሚካል መጠን ከዚህ በፊት ትጠቀም ከነበረው በ13 እጥፍ እንደጨመረ ይናገራሉ፡፡
በቻይናም ያለው ልምድ ተመሳሳይ እንደሆነ ገልጸው፣ የኬሚካል መጠኑ የሚጨምረው ቢቲ ኮተን የሚያጠፋው አፍሪካ ቦል ዋርምን ብቻ በመሆኑና ሌሎች ተባዮች በመጨመራቸው ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በርካታ የኢትዮጵያ የግብርና ባለሙያዎች ግን በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ አንደኛ ቢቲ ኮተን ተግባር ላይ የሚውለው ምርታማነቱና ተባይ ተቋቋሚነቱ በኢትዮጵያ መሬት ላይ ተፈትሾ ሲረጋገጥ ነው የሚሉት የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የባዮ ቴክኖሎጂ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር በላይነህ አድማሱ ናቸው፡፡
‹‹ጥጥ ላይ የምናስገባው ዘረ መል የሚፈጥረውን ባህርይ ስለምናውቅ ዘሩ ውስጥ የተጋባው ዘረ መል ተባይን የመቋቋም ባህርይ ብቻ እንዲኖረው ነው የሚደረገው፡፡ ከዚህ ውጭ ሌላ ሥጋትም ሆነ ችግር ሊያመጣ የሚችል ባህርይ ሊፈጠር አይችልም፡፡ ስለዚህ ከቁጥጥር ውጭ ሊወጣ የሚችል ችግር ይፈጠራል የሚል ሥጋት ሊኖር አይገባም፤›› ይላሉ፡፡
ይህንን ዘር ቀድሞ በነበረው አዋጅ ማስገባት የሚቻል ቢሆንም፣ የቀድሞው አዋጅ ዘሩን ያስገቡ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች እንዲሁም ተባባሪዎች ዘሩ በሰውና በአካባቢ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የማስገባት ሒደቱን ጥብቅ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በመሆኑም ዘሩ ወደ አገር የሚገባበትን ሁኔታ በመጠኑ ማቅለል የሚችል ረቂቅ ማሻሻያ ተዘጋጅቶ በአሁኑ ወቅት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዘንድ ለውይይት ቀርቧል፡፡ ይሁን እንጂ አዋጁ እንዲሻሻል የተፈለገበት ከቢቲ ኮተን ያለፈ ምክንያት እንዳለው አስረግጠው የሚናገሩ አሉ፡፡
የደኅንነት ሕይወት ማሻሻያ አዋጅ
በዘረ መል ምሕንድስና የተለወጡ ዘሮችን ወደ አገር ለማስገባት ቀድሞ የነበረው ሕግ አንዳንድ አንቀጾች ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችሉ ሆነው እንዳልተገኙና አሁን በአገሪቱ ያለውን የልማት ፍላጎት ለመመለስ የሚያስችሉ ሆነው ባለመገኘታቸው የደኅንነት ሕይወት አንዳንድ አንቀጾች እንዲሻሻሉ ሐሳብ ቀርቧል ሲል የማሻሻያ ረቂቁ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡
በተለይ የነባሩ ሕግ ሁለት አንቀጾች ላይ የተደረገው ማሻሻያ በዘረ መል ምሕንድስና የተለወጡ ዘሮች ላይ ኢትዮጵያ የአቋም ለውጥ እንዳደረገች ያሳያል በማለት ባለሙያዎች ይከራከራሉ፡፡
ከተደረጉት ማሻሻያዎች መካከል አንዱ የአዋጁን ዓላማ የሚደነግገው አንቀጽ ይገኝበታል፡፡ የቀድሞው አዋጅ ዓላማ ‹‹በሰውና በእንስሳት ጤና፣ በብዝኃ ሕይወት፣ በአካባቢ፣ በማኅበረሰቦችና በአጠቃላይ በአገር ላይ በልውጥ ሕያዋን ሊደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ማስቀረት ወይም ቢያንስ እስከ ኢምንታዊነት ደረጃ ማሳነስ፤›› መሆኑን ይገልጻል፡፡
ነገር ግን በማሻሻያ ረቂቁ ላይ ቀድሞ ከተጠቀሰው የአዋጁ ዓላማ በተጨማሪ ሌላ አንቀጽ እንዲካተት ቀርቧል፡፡ ‹‹ዘመናዊ ጥበበ ሕይወትን (ዘረ መል ምሕንድስናን) ጨምሮ ለብዝኃ ሕይወት ጥበቃና ዘላቂ አጠቃቀም የሚያገለግል ቴክኖሎጂ ተደራሽነትንና በቴክኖሎጂ ዝውውር መጠቀምን ማሻሻል፤›› የሚል ሌላ አዲስ ዓላማ እንዲካተት ቀርቧል፡፡
በተረቀቀው ማሻሻያ ላይ ተቃውሟቸውን በማሰማት ላይ የሚገኙት ዶ/ር ሚሊዮን፣ ‹‹በማንኛውም መልኩ አንድ ሕግ አንድን ጉዳይ እንዳይስፋፋ ለመቆጣጠር እንዲሁም በሌላ በኩል ለማበረታታትና ወይም ለማስተዋወቅ ሊረቀቅ አይችልም፤›› ሲሉ የሕግ አወጣጥ መሠረታዊ ዓላማ ተዛብቷል ይላሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የማሻሻያ አዋጁ ቀደም ሲል በዘረ መል ምሕንድስና የተለወጠ ዘርን ወደ አገር ለማስገባት የላኪው አገር የሚመለከተው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ባለሥልጣን ስለዘሩ የሚሰጠው መረጃ ትክክለኛ ስለመሆኑ ኃላፊነቱን እንዲወስድ ያስገድድ የነበረ ቢሆንም፣ ማሻሻያው ግን ዘሩን የለወጠው ኩባንያ ብቻ ኃላፊነቱን እንዲወስድ በማለት ማስተካከያ ያደርጋል፡፡ ይህ በመሆኑም ተጠያቂነት ከመንግሥት ወደ ግለሰብ ኩባንያዎች እንዲወርድ በማድረግ የተጠያቂነቱን ክብደት መቀነሱ አግባብ አለመሆኑን ባለሙያዎች ይከራከራሉ፡፡
የቀረበውን ማሻሻያ የሚቃወሙ የሲቪል ማኅበራት በጋራ ለመንግሥት ባቀረቡት ደብዳቤ አገሮች የሚሰጡትን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ኩባንያዎች ኃላፊነቱን እንዲወስዱ ማድረግ በምርምርና በትምህርት ሳቢያ ኢትዮጵያ ለድንበር ዘለል የዘረ መል ኩባንያዎች የሙከራ መስክ ለማድረግ የመግቢያ በር ይሆናል በማለት ቅራኔያቸውን በጽሑፍ አስገብተዋል፡፡
ሌላው ማሻሻያ አንቀጽ ማንኛውም ሰው ልዩ ፈቃድ ሳይሰጠው የዘረ መል ምሕንድስና አጠቃቀም እንቅስቃሴ ሊያከናውን አይችልም ይላል፡፡ በሥራ ላይ የሚገኘው አዋጅ ግን በዝግ ለሚካሄድም ሆነ ለውጥ ዘርን ወደ አካባቢ ለመልቀቅ ከግንዛቤ የመነጨ የስምምነት ፈቃድን ይጠይቃል፡፡
ይህንን ልዩነት የተገነዘቡት የዘረ መል ምሕንድስና ተቃዋሚ ሲቪክ ማኅበራትና ሌሎች ባለሙያዎች ልዩ ፈቃድን ለዝግ አጠቃቀም መስጠት የዝግ አጠቃቀምን ከጠንቅ ነፃ ወይም አነስተኛ ውጤት እንዳይኖረው አያደርገውም፡፡
ልዩ ፈቃድ ዞሮ ዞሮ የዝግ አጠቃቀምን ከግንዛቤ ከመነጨ ስምምነት ሥርዓት የማስወጣት ሒደትን የማጠናከሪያ አደገኛ መሣሪያና ስልታዊ አካሄድ ነው በማለት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሌላው እየተፈጠረ ያለው ብዥታ የዝግ አጠቃቀም ኢትዮጵያን ከዘረ መል ምሕንድስና ምርምር ተጠቃሚ እንደምትሆን ተደርጎ የመውሰድ አዝማሚያን፣ ዋጋውም ርካሽ፣ የሚሠራውም በአገር በቀል ዘረ መል ዕውቀትና ልምድ አስመስሎ ማቅረብ ነው፡፡ ምርምሩ ዘረ መሉ፣ ሙከራው ሁሉ በውጭ ኩባንያዎች የተቀነባበረ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ነው፤›› በማለት መንግሥትን አሳስበዋል፡፡
ይህ ረቂቅ ባለፈው ሳምንት የቀረበለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከቀድሞው በተሻለ መልኩ በዝርዝር እንዲታይ ለቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡ በመሆኑም ከመጀመሪያ ንባብ ያለፈ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ ይሁን እንጂ ረቂቁ ምን ያህል የአገሪቱን ጥቅም ያስከብራል የሚለው ብዙዎች የሚጠብቁት ነው፡፡
በመጀመሪያው የደኅንነት ሕይወት አዋጅ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባይወያዩበትም፣ የሚመለከታቸው አካላት ማለትም የአካባቢ ተሟጋቾችን ጨምሮ ረዥም ውይይት እንደተደረገበት ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የአዋጅ ማሻሻያ ቀደም ሲል የተወያዩ የአካባቢ ተሟጋቾችን ያሳተፈ እንዳልሆነ እየተገለጸ ይገኛል፡፡ አዋጁ አገሪቱን የመጥቀምም የመጉዳትም ባህሪ ያለው በመሆኑ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቂ ጊዜ ወስዶ ሊያየው ይገባል፡፡