Wednesday, 17 February 2016 14:43

በይርጋ አበበ

የኢትዮጵያ ፖለቲካ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ያለው የአገሪቱ ፖለቲካ ከመወነጃጀልና ከመወቃቀስ የጸዳበት ጊዜ አለ ማለት ይከብዳል። በተለይም የተቃውሞው ጎራ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ከመወቃቀስና ከመወነጃጀል ባለፈ አንዳንዴም መጠላለፍና መነቃቀፍ ውስጥ ሲገቡ ማየት የተለመደ ክስተት ሆኗል። ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረበት ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ጀምሮ ህጋዊ እውቅና አግኝተውና በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው ወደ ትግል ከገቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ግንባር ቀደሙ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ለመድብለ ፓርቲ ስርዓቱ ካከናወነው ትግል ይልቅ በውስጣዊ የእርስ በእርስ ሽኩቻው ተለይቶ ይታወቃል ቢባል ከእውነታው መራቅ አይሆንም። ካለፉት 24 ዓመታት የፓርቲው ምስረታ ጀምሮ ፓርቲውን በሊቀመናብርትነት መምራት የቻሉት ግለሰቦች ቁጥራቸው አራት ብቻ ቢሆንም (ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፣ ኢንጂነር ኃይሉ ሻወል፣ አቶ ማሙሸት አማረ እና አቶ አበባው መሃሪ) የፓርቲው የውስጥ ችግር ከዚህም ያለፈ ሆኖ ታይቷል።

ይህ የመኢአድ አመራሮች የውስጥ ሽኩቻ ካለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል በኋላ ደግሞ በድጋሚ ተነስቶበት ሰሞኑን አንደኛው ከሳሽ ሌላኛው መልስ ሰጭ አንደኛው አጋጅ ሌላው ታጋጅ ሆነው እየተወዛገቡ ይገኛሉ። የፓርቲውን ውዝግብ በተመለከተ ባለፈው ሳምንት እትማችን ከሁለቱም ወገን አንድ አንድ አመራሮችን ቃለ ምልልስ አድርገን ሀሳባቸውን ማቅረባችን ይታወሳል። በ2005 ዓ.ም ፓርቲው ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ከተመረጡት 19 የፓርቲው ስራ አስፈጻሚዎች መካከል የደቡብ ቀጠና ኃላፊ እና የሲዳማ ዞን የፓርቲው ሰብሳቢ አቶ ገለቱ ጀጀርሳ አንዱ ናቸው። የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ገለቱ እና የላዕላይ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ይርዳው ሽፈራው የፓርቲውን ወቅታዊ የውስጥ ቀውስ እና የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አበባው መሃሪ አካሂደውታል ያሏቸውን የስነ ምግባር ግድፈቶች ለዝግጅት ክፍላችን አቅርበዋል።

አቶ ገለቱ “ቀደም ሲል የፓርቲው የላዕላይ ምክር ቤት 1/3ኛ የምንሆን አባላት የጋፍ ፊርማ አሰባስበን ፕሬዚዳንቱ የምክር ቤት ስብሰባ እንዲጠሩን ብንጠይቅም አላውቃችሁም ብሎ አባረረን” ሲሉ ይናገራሉ። ሆኖም በዚህ ተደናግጠው እንዳልተቀመጡ የሚናገሩት አቶ ገለቱ “ህጋዊ መንገዱን ተከትለን ለምርጫ ቦርድ ሂደን ጉዳዩን ስናስረዳ ትክክለኛ የፓርቲው የምክር ቤት አባል መሆናችንን ካረጋገጠ በኋላም ቢሆን አቶ አበባው የምክር ቤት ስብሰባውን ላካሄድ ፈቃደኛ ሳይሆኑ በእምብተኝነታቸው ቀጠሉ” ይላሉ።

በ2005 ዓ.ም የወጣው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 9.2.18 “ከአቅም በላይ የሆኑ ጥፋቶችና ጉድለቶች ሲፈጠሩ 1/3ኛውን የማዕከላዊ ምክር ቤት አባላት በማስፈረም የማዕከላዊ ምክር ቤት ስብሰባ እንዲጠራ ለፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጥያቄ ማቅረብ ይችላል ሲል የሚደነግግ ቢሆንም አቶ አበባው መሃሪ ግን የማዕከላዊ ምክር ቤት ስብሰባውን ሳይጠሩ ቀሩ” ሲሉ ይናገራሉ።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሃሪ ግን የአቶ ገለቱን ሀሳብ “መሰረተ ቢስ ውንጄላ ነው” ሲሉ ይናገራሉ። አቶ አበባው ሃሳባቸውን ሲያጠናክሩ “የማዕከላዊ ምክር ቤት አባላት ስብሰባ አልጠራም የተባለው ፓርቲያችን በገጠመው የፋይናንስ ችግር እንጂ በሌላ በምንም ምክንያት አይደለም። እንዳልከው ወደ ምርጫ ቦርድ ሂደዋል ነገር ግን እናንተ ህገ ወጥ ናችሁ ብሎ አሰናብቷቸዋል” ሲሉ ነው የገለጹት።

አቶ አበባው አያይዘውም “በመጀመሪያ ደረጃ እናንተ ጋ መጥተው አስተያየት ከሰጡት መካከል ገለቱ ማን ነው ብለህ የጠየክ እንደሁ እሱ ቀደም ሲል የእነ አቶ ማሙሸት ስራ አስፈጻሚ የነበረ እና በመጨረሻም ምርጫ ቦርድ ውክልና የነሳው ሰው ነው። አሁን እየሰራ ያለው በማጭበርበር ፓርሪውን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ ትክክል አይደለም። በዚህ ሰዓት የመኢአድ ስራ አስፈጻሚም አይደለም” ይላሉ።

ቀደም ሲል አቶ ገለቱ እና ሌላው አስተያየታቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ የሰጡት አቶ ይርዳው ሽፈራው “የማዕከላዊ ምክር ቤት አባላት የ65 ሰዎችን የድጋፍ ፊርማ አሰባስበን ወደ ፓርቲው ጽ/ቤት ሂደን ልንሰባሰብ ስንሞክር አቶ አበባው አባረውናል” ሲሉ የገለጹ ቢሆንም አቶ አበባው ግን “የድጋፍ ፊርማ አሰባስበን የሚሉት ከፓርቲ የተባረሩትን ጨምሮ 14 ሰዎች ብቻ ናቸው። እነሱ ግን ለማወናበድ እንዲረዳቸው ከፓርቲው የሌለ ሰውም ጭምር አስፈርመው ነው የተሰባሰቡት። ይህንን ደግሞ ላሳይህ እችላለሁ” ሲሉ ይቃወማሉ።

ፓርቲው በሁለት ጎራ ተከፍሎ ሲወዛገብ የአባላት እና የደጋፊዎች እጣ ፈንታ ምንድን ነው? ለሚለው የዚህ ጋዜጣ ሪፖርተር ጥያቄ መልስ የሰጡት የሁለቱም ወገን አስተያየት ሰጭዎች መልስ ሰጥተውበታል። አቶ ገለቱ ጀጀሎ እና አቶ ይርዳው ሽፈራው “አሁን የማዕከላዊ ምክር ቤት አባላት ተሰብስበው የፓርቲውን ፕሬዚዳንት አግደናል። አቶ አበባው ስለታገዱ ፓርቲውን በጊዜያዊነት የሚመራው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ይሆናል። ይህንም ለሁሉም አባሎቻችንና የቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች አሳውቀናል። በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ በመጥራት የፓርቲውን ቋሚ አመራሮች መርጠን እስክናሳውቅ ድረስ ተረጋግታችሁ ተቀመጡ ብለን ነግረናል። ሁሉም ተቀብሎ የማዕከላዊ ምክር ቤቱን ውሳኔ ተቀብሎ ተረጋግተው በሰላማዊ መንገድ እየሰሩ ይገኛሉ” ብለዋል።

አቶ አበባው መሃሪ ከወራት በኋላ ማለትም መጋቢት 24 እና 25 ቀን 2008 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚጠሩ ተናግረዋል። ይህን እንዴት ታዩታላችሁ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው እነ አቶ ገለቱ “ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት በመጀመሪያ ማዕከላዊ ምክር ቤት መሰብሰብ አለበት። አሁን አቶ አበባው ያደረጉት የማስመሰል ስራ ነው። አሁን ማዕከላዊ ምክር ቤቱ ካገዳቸው በኋላ ሆን ብለው ለማወናበድ እንጂ ብቻቸውን ወስነው የሚያካሂዱት አይደለም። አቶ አበባው ብቻቸውን ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት አይችሉም ምክንያቱም በ2005 ዓ.ም በተካሄደ ጠቅላላ ጉባኤ የተመረጡትን የስራ አስፈጻሚዎች በሙሉ አሰናብተው በጠቅላላ ጉባኤ እና በማዕከላዊ ምክር ቤት እውቅና የሌላቸውን ሰዎች ይዘው ነው እየሰሩ ያሉት። የመጋቢቱ ጠቅላላ ጉባኤን በተመለከተ በእነ አቶ አበባው መዋቅር ስር አንድም የዞን እና የወረዳ ተጠሪ የለም። ይህ ማለት ደግሞ ዝም ብሎ ለማስመሰል ነው” ሲሉ መልሰዋል።

“ይህን ውሳኔያችሁን ማለትም አቶ አበባው መሃሪን ያገዳችሁበትን ሰነድ ምርጫ ቦርድ እውቅና ሰጥቷችኋል? ምርጫ ቦርድ እውቅና ካልሰጠው ያስተላለፋችሁት ውሳኔ ተቀባይነት አይኖረውምና” ተብለው የተጠየቁት እነ አቶ ገለቱ “ምርጫ ቦርድ እኛን እውቅና ለመስጠት ማህተማችሁን አምጡ ብሎን በማህተሙ ላይ እየተከራከርን ነው። ማህተሙ በአቶ አበባው መሃሪ እጅ ስር ነው ያለው። ይህን ደግሞ እኛ በፍርድ ቤት ከሰን እየተከራከርን ነው። ምክንያቱም ማህተሙ ሊቀመጥ የሚገባው በአስተዳደርና ፋይናንስ እጅ ቢሆንም አቶ አበባው ግን ወስደው ማህተሙን በእጃቸው ይዘውታል። ምርጫ ቦርድ ግን አካሄዳችሁ ትክክል ነው የራስጌና የግርጌ ማህተም አድርጋችሁ አምጡ ሲል ነው ያሰናበተን” በማለት ተናግረዋል።

የፓርቲውን ማህተም ከአቶ አበባው እጅ ወስዳችሁ ለመጠቀም በፍርድ ቤት ከሳችኋል። ፍርድ ቤት የከሰሳችሁት አቶ ደመላሽ ካሳዬ በተባሉ ግለሰብ ነው። አቶ ደመላሽ ፓርቲውን ወክለው ፕሬዚዳንቱን መክሰስ እንደማይችሉ ደግሞ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ አበበ ቀደም ሲል ተናግረው ነበር። ምክንያቱም የአቶ ደመላሽ ውክልና የተነሳ መሆኑን ገልጸዋል። ውክልና በተነሳ ሰው መክሰስ ይቻላል? ለሚለው ጥያቄ ደግሞ “በፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ 17.10 የህግና ስነ ስርዓት ኮሚቴ አባላት የሚመረጡት በማዕከላዊ ምክር ቤት ነው ይላል። አቶ ደመላሽ ደግሞ የሕግና ስነ ስርዓት ኮሚቴ አባል ነው። በዚህም ምክንያት የፓርቲውን መብቶች ለማስከበር አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ጠበቃ ቀጥሮ ወይም በራሱ ውክልና በማንኛውም ፍርድ ቤት መከራከር ይችላል” ያሉ ሲሆን አያይዘውም “ውክልና ሲነሳ በኢትዮጵያ ህግ መሰረት ውክልና ሰጭው አካል ውልና ማስረጃ ሂዶ ውክልና ማንሳቱን ማሳወቅ ይኖርበታል። ውክልና ለሰጠው ግለሰብ ደግሞ ውክልናዬን አንስቻለሁ ብሎ ደብዳቤ አስፈርሞ መስጠት ይኖርበታል። አቶ ደመላሽ ግን በዚህ መልኩ ውክልናው መነሳቱ አልተገለጸላቸውም። ፍርድ ቤት ክሱን ሲያቀርቡም የፓርቲውን ውክልና አሳይቷል። ፍርድ ቤቱም ይሁንታውን ሰጥቶታል” ሲሉ ተናግረዋል።

ከላይ ለቀረቡት አራት ጥያቄዎች መልስ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው አቶ አበባው መሃሪ መልስ ሰጥተዋል። አቶ አበባው “ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ በትንሹ ከ250 ሺህ ብር ያላነሰ ገንዘብ ይጠይቃል። እኛንም የያዘን የፋይናንስ እጥረት ነው።  በዚህም ምክንያት የጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት ዘግይተን ነበር። በመጭው መጋቢት 24 እና 25 ቀን ጠቅላላ ጉባኤ ለዚህ ደግሞ ድጋፍ ከሚያደርጉልን ጋር እየተነጋገርን ነው” ሲሉ መልሰዋል። አቶ አበባው አያይዘውም “ምርጫ ቦርድ እነሱን ህጋዊ አይደላችሁም ብሎ ያሰናበተ ሲሆን እኛን ግን ጠርቶ አላነጋገረንም፣ ሊያነጋግረንም አይገባም። ምክንያቱም እነሱ ህገ ወጥ ሰዎች ስለሆኑ” በማለት ከእሳቸው እና ካቢያኔያቸው እውቅና ውጭ የሚንቀሳቀሱት ህገ ወጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የፓርቲው ማህተም በፕሬዚዳንቱ እጅ ስር በመሆኑ ፍርድ ቤት ቀርበው መልስ እንዲሰጡ ተደርጓል። ለመሆኑ ማህተሙን በእጅዎ መያዝ ይችላሉ? አቶ ደመላሽ ካሳዬ የተባሉት ግለሰብስ ውክልና እያላቸው ነው የከሰሱት? ለሚሉት ጥያቄዎች ደግሞ “አቶ ደመላሽ ከእነ ማሙሸት ጋር ሆኖ ምርጫ ቦርድ እውቅና ሲነሳው ተሰናበተ። ለመመለስ ጥያቄ ሲያቀርብ ስራ አስፈጻሚ በሙሉ ፓርቲውን እያፈረስክ ነው በሚል ጥያቄውን ሳይቀበለው ቀረ። ይህንን ውሳኔ እና ውክልናው መነሳቱን የሚገልጸውን ደብዳቤ መጥተህ ውሰድ ሲባል አሻፈረኝ በማለቱ ሳይቀበል ቀረ። አሁን ፍርድ ቤት ቀርቦ እኔን በመክሰስ ማህተሙን እንዳንጠቀም አሳግዷል። ነገር ግን የሄደበት መንገድ ፍርድ ቤቱን ያታለለ በመሆኑ ዳኛዋ የመጥሪያ ደብዳቤ እንዲደርሰው አድርገዋል” ሲሉ የተናገሩ ሲሆን ማኅተሙን በተመለከተ ደግሞ “ይህ የፓርቲው አሰራር ነው። በመሰረቱ ማኅተም መቀመጥ ያለበት መዝገብ ቤት ነበር። ነገር ግን መዝገብ ቤት ስለሌለን ለአሰራር እንዲመች በማለት ማኅተሙ በዋና ጸሀፊው እጅ እንዲቀመጥ ስራ አስፈጻሚ ወስኗል። የስራ አስፈጻሚውን ውሳኔ ማየት ትችላለህ” በማለት ተናግረዋል።

የሁለቱን ወገኖች የመከራከሪያ ሀሳብ በመያዝ ወደ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ ደውለን ነበር። የቦርዱ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ስልጠና ላይ መሆናቸውን ተናግረው በወቅቱ በጉዳዩ ላይ መረጃ  እንደሌላቸው ገልጸዋል። የተፈጠረ ነገር ካለ ደግሞ ቦርዱ ወደ ፊት የሚያስተላልፈው ውሳኔ ሊኖር እንደሚችል አስታውቀዋል።

ምንጭ ስንደቅ

Leave a Reply