Wednesday, 05 November 2014 12:00

የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) ወይንም የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በጋምቤላ ክልል በመዥንገር ዞን በቅርቡ በተከሰተው ግጭት 60 ያህል ሰዎች መሞታቸውን፣ 23 ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን፣ 36 መፈናቀላቸውንና አራት ያህሉ የደረሱበት እንዳልታወቀ ትላንት ለሰንደቅ ጋዜጣ በላከው 132ኛ ልዩ መግለጫው አስታወቀ።

ማንኛውም ሰው ሰብአዊ በመሆኑ ብቻ በህይወት የመኖር፤ የአካል ደህንነትና ነጻነቱ እንዳይገሰስ መብት እንዳለው እና በህጋዊ መንገድ በሀገሪቱ ውስጥ በመረጠው አካባቢ የመዘዋወር እንዲሁም የመኖሪያ ቦታ የመመስረት በኢፌዲሪ ህገ መንግሥት በአንቀጽ 14 እና 32 መደንገጉን ያስታወሰው የሰመጉ መግለጫ በተመሳሳይ መልኩ በአፍሪካ ሕብረት ቻርተር አንቀጽ 4 እና 12 መደንግጉን አስታውሷል። ሆኖም እነዚህ የሕግ ከለላዎች ቢኖሩም በጋምቤላ ክልል በመዠንገር ዞን በቅርቡ በተከሰተው የጎሳ ግጭት የብዙ ዜጎች ሕይወት ሊያልፍ መቻሉን አመልክቷል።

“በመሠረቱ መንግሥት የዜጎችን ሠላምና ፀጥታ የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መሆኑ ይታወቃል፤ ዜጎችም በሠላም ሠርተው ያለምንም ሥጋት ወጥተው መግባት፣ የላባቸውን ውጤት የሆነውን ምርትም የመሰብሰብና የመጠቀም ሕገ መንግሥታዊና ተፈጥሮአዊ መብት አላቸው። የዜጎች መብትና ነጻነቶች ተጥሰው ሲገኙ መንግሥት አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃዎች የመውሰድ ኃላፊነት አለበት። ሆኖም ግን አሁን በተለያዩ አከባቢዎች የብሔረሰቦች ግጭት እየተስፋፉ መጥቶአል። መንግሥትም ይህን አሳሳቢ ጉዳይ በዘላቂነት ለመፍታት እያደረገው ያለው ጥረት ከችግሩ ክብደት እና እየደረሰ ካለው ጉዳት አንጻር ሲታይ ጨርሶ የሚመጣጠን ሆኖ አልተገኘም። በመሆኑ መንግሥት ተመሳሳይ ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት ለነገ የማይባል አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። በቅርቡ በመዠንገር ዞን ለተፈጠረው ሰብአዊ እልቂት መንስኤ የሆኑ ምክንያቶችንና ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ግለሰቦችንና ቡድኖችን አጣርቶ አፋጣኝ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ያሳስባል” ሲል ሰመጉ በመግለጫው ጠቅሷል።

ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በፓርላማ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር በጋምቤላ ክልል በተከሰተው ግጭት እጃቸው አለበት የተባሉ ባለሥልጣናትና ሌሎች ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መግለፃቸው ይታወሳል።

Leave a Reply