Thursday, 06 November 2014 08:39
ሻምበል ገ/መድህን ቢረጋ
የተዘጋ አጀንዳ መስሎ የነበረው ልውጥ ሕያው (Modified Organism) ቀስ በቀስ እግር እያወጣ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደርሷል።ልውጥ ሕያው፣ ሰው ሰራሽ የሆነ ወይም ከሌላ ሕያው የተወሰደ ወይም እንደአዲስ የተቀመመ ባይተዋር ዘረመል ወይም ሌላ ንጥረ ነገር ስለተከተተበት የዘረመሎች ይዘቱ ወይም ባሕርዩ ክስተት የተለወጠለት ሕያው ማለት ነው።
ዓለም ዓቀፍ ሕብረተሰብ በዘረመል ምህንድስና ውጤቶች ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እያቀረበ በሚገኝበት በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ፓርላማ በ2001 ዓ.ም የወጣውን የደህንነት ሕይወት አዋጅ ለማሻሻል ረቂቅ አዋጅ ቀርቦለታል። በአሜሪካ፣ በአውሮፓ እንዲሁም በኤዢያ አህጉሮች ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ ከሚያስተናግዱት ጉዳዮች አንዱ በዘረመል ምህንድስና ውጤቶች ጋር በተያያዘ በሚከሰቱ የተለያዩ ጠንቆች ምክንያቶች ነው።
ረቂቅ ሰነዱ በድፍኑ ብቻ ባለድርሻ አካላት ነባር አዋጁ አላሰራ አለን የሚል መከራከሪያ በማንሳታቸው አዋጁ እንዲሻሻል ተፈልጓል ይላል። ከሁሉ በላይ ረቂቅ ሰነዱ ላይ የሰፈረው “በሃገሪቱ ያለውን የልማት ፍላጎት ለመመለስ የሚያስችሉ ሆነው አለመገኘታው ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረጉ ውይይቶች በመረጋገጡ የካርታሄና የደህንነት ዓላማና ድንጋጌዎች መሰረት ባደረገ መልኩ በሕጉ አንቀፆች ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ ሃሳብ ቀርቧል” ይላል።
ረቂቅ አዋጁ በአጠቃላይ ትኩረት ያደረገው በምርትና ምርታማነት ላይ ያተኮረ ጽንሰ ሃሳብ ቢመስልም በሀገሪቷ ቀጣይ የግብርና ስርዓትና ነባር ዝርያዎችን ከመታደግ አንፃር ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ አያመላክትም። እንዲሁም ነባር ዝርያዎችን በልውጥ ሕያው በመተካት በቀጣይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ሊያሳርፍ የሚችለውን አደጋም ሊመለከት አልፈቀደም። ከዚህም በላይ ባለድርሻ አካላትን ከውይይት በማራቅ እንዲደመጡ አልተፈቀደም። እነዚህን እና ሌሎች ጥያቄዎችን በማንሳት የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ጥበቃ ሊቀመንበር የሆኑትን ሻምበል ገ/መድህን ቢረጋን ባልደረባችን ፋኑኤል ክንፉ አነጋግሮአቸዋል።
ሻምበል ገ/መድህን ቢረጋ የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ጥበቃ ማሕበር ሊቀመንበር ሲሆኑ፤ በፖለቲካ ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው።
ሰንደቅ፡- ከዚህ በፊት የደህንነት ሕይወት አዋጅ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግ መጠየቃችሁ የሚታወስ ነው። እንዲሻሻሉ ያቀረባችሁት የማሻሻያ ነጥቦች መካከል በመሠረታዊነት የሚነሱት የትኞቹ ናቸው?
ሻምበል ገ/መድህን፡-ለማሻሻያ ያቀረብናቸው ነጥቦች ቀደም ተብሎ በአዋጁ መካተት የነበረባቸው ናቸው። ለምሳሌ ልውጥሕያውን ለማስፋፋት የሚተጉ ኃይሎች እንዳሉ ሁሉ ከልውጥ ሕያው ነፃ (GMO free zone) የሆነ አካባቢ ለሚፈልጉ ሰዎችም እንደመብት በአዋጅ ውስጥ መካተት ነበረባቸው። ይህ መብት አፍሪካ ሞዴል ተብሎ በሚታወቀው ቻርተር ላይ የተካተተ በመሆኑ በወቅቱ በቀረበው ረቂቅ ሰነዱ ውስጥ እንዲካተት የተደረገ ቢሆንም አዋጁ ሲጸድቅ ግን እንዲወጣ ተደርጓል።
ሌላው የክልል መንግስታት እንደአስፈላጊነቱ ከፌዴራል መንግስት አዋጅ በተለየ ጠንከር ያለ አዋጅ እንደአካባቢያቸው ሁኔታ ማውጣት እንዲችሉ መፈቀድ አለበት የሚል ነበር። ምክንያቱም ክልሎች ያላቸውን የብዘሀህ ህይወት (Biodiversity) ከግምት በማስገባት እንዲሁም ያላቸውን ስነ-ምህዳር (Ecology) ከግምት በመውሰድ በልውጥ ሕያው ላይ እንደአስፈላጊነቱ ጠንካራ አዋጅ የማውጣት ስልጣን ሊሰጣቸው ይገባል ተብሎ በረቂቅ አዋጁ የቀረበ ቢሆንም እንዲወጣ ተደርጓል።
ሌላው በእነዚህ ልውጥ ሕያው መነሻነት ጉዳት ቢከሰት ይህን ጉዳት የሚጠይቅ የመንግስት ተቋም መኖር አለበት የሚል ነበር።ይህም ሲባል የጉዳት ካሳና ተጠያቂነት (Liability and redress) የሚያሳይ አንቀጽ በአዋጁ ውስጥ እንዲካተት ጠይቀን ነበር። በረቂቁ ሰነድ ላይ ይህ በክፍል ስድስት ላይ ሰፍሮ የነበረ ነጥብ ቢሆንም አዋጅ ሲፀድቅ ግን ሙሉ ለሙሉ እንዲወጣ ተደርጓል። ይህ ማለት ሸማቹም፣ አርብቶ አደሩም፣ ገበሬውም፣ ተራ ዜጋውም በልውጥ ሕያው አማካኝነት አንድ ጉዳት ቢደርስበት በጉዳቱ መጠን ካሳ የመጠየቅ መብቱን የሚያረጋግጥለት አንቀጽ ይህ ነበር፣ ሆኖም ግን እንዲወጣ ተደርጓል። በዚህ ምክንያት አሁን ያለው አዋጅ ከጉዳት ካሳ እና ከተጠያቂነት ውጪ በሆነ መልኩ የጸደቀ ነው። በወቅቱ ከ2ሺ በላይ ሸማቾች እና የነባር ዝርያ አርሶ አደሮችን አስተባብረን አስፈርመን ለሚመለከታቸው አካሎች በ2003 ዓ.ም ልከን ነበር። በዚሁ መሰረት የማሻሻያ ነጥቦች እንዲካተቱም ጥያቄ አቅርበን ነበር።የእኛ ጥያቄዎች መልስ ሳያገኙ አሁን ሕጉ ሊሻሻል ነው የሚል ዜና ሰማን።
ሰንደቅ፡- ሕጉ የሚሻሻለው ከላይ በሰፈሩት ጥያቄዎች መነሻ ነው? ወይንስ በሌላ ወገን አቅራቢነት ነው?
ሻምበል ገ/መድህን፡-መጀመሪያ ሕጉ ለምን መሻሻል አስፈለገ ለሚለው ምላሽ ያለው እንዲሻሻል አሁን ጥያቄ አቀረበ የተባለው አካል ነው። ሕጉ መሻሻል አለበት ከተባለ ነባር አዋጅ ሲረቅ የነበርነው ባለድርሻ አካላት በሙሉ ለውይይት መጋበዝ አለብን።ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የተወጣጡ የባለሙያ ምክረ ሃሳቦች በማሻሻያ ነጥቦቹ ላይ መስማማት አለባቸው። እኛም እንደአንድ ባለድርሻ አካል ያቀረብናቸው የማሻሻያ ነጥቦችም መካተት አለባቸው ብለን እናምናለን። ስለዚህም በረቂቅ አዋጁ ወቅት የነበርን ባለሙያዎች በማሻሻያ ነጥቦች ላይ መወያየት እና መተማመን አለብን። አሁን የሆነው አዋጁ በአንድ ወገን በኩል በቀረበ የማሻሻያ ነጥቦች ላይ ተመስርቶ ሊሻሻል ነው ሲባል ሰማን። ይህ ፈጽሞ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው የሚሆነው። ሃሳባችን ይደመጥ ብሎ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን መደመጥም ሕገመንግስታዊ መብታችን ነው።
ሰንደቅ፡- ለሚመለከተው አካል በውይይት መሳተፍ እንደምትፈልጉ በደብዳቤ አታሳውቁም?
ሻምበል ገ/መድህን፡-ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት፣ ለጠ/ሚንስትር ጽ/ቤት፣ ለፕሬዝደንት ጽ/ቤት፣ ለሁሉም በደብዳቤ ጽፈን አሳውቀናል። እስካሁን የተሠጠን ምላሽ የለም።
ሰንደቅ፡- የማሻሻያ ነጥቦችን ያረቀቀው አካል፣ ሌሎች ባለድርሻ አካሎችን በማሻሻያ ነጥቦቹ ላይ ድምፃቸው እንዳይሰማ የፈለገበት አግባብ ከምን የምን የመነጨ ነው?
ሻምበል ገ/መድህን፡-በዚህ ላይ አሁን የምስጠው አስተያየት የለም።
ሰንደቅ፡- የማሻሻያ ነጥቦችን ያረቀቀው አካል ከዓለም ዓቀፍ የልውጥ ሕያው አምራቾች ጋር የተሞዳሞደ ቡድን ነው የሚል ሥጋትስ አላችሁ?
ሻምበል ገ/መድህን፡-በዚህ ላይ አሁን የምሰጠው አስተያየት የለም።
ሰንደቅ፡- ከዚህ በፊት የአሜሪካንን ኤምባሲዎች ኬብል የጠለፈው ዊኪሊክስ፣ የኢትዮጵያ የደህንነት አዋጅ በጣም አሳሪና ጥብቅ ነው ሲል አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ወደ አሜሪካ ደብዳቤ መፃፉን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። ይህን ተከትሎ ቀስ በቀስ እየተንከባለለ የመጣ ጫና አድርጎ መውሰድ ይቻል ይሆን?
ሻምበል ገ/መድህን፡- እንደማንም ሰው የዊክሊክስን መረጃዎችን በወቅቱ ተመልክቻለሁ። አሁን ከቀረበው የማሻሻያ ነጥቦች ጋር የአሜሪካ መንግስት ተፅዕኖ አለው፣ የለውም ለሚለው ጥያቄ በመረጃ ለማቅረብ ተጨባጭ ስራዎች ያስፈልጋሉ። አሁን ባለኝ መረጃ ግን ምንም ለማለት አልችልም። ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የአሜሪካ ኤምባሲ እና ዩኤስኤድ ልውጥ ሕያውን በተመለከተ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲስፋፋ ግፊት እንደሚያደርጉ ግን እናውቃለን።
ሰንደቅ፡- በቀረበው የማሻሻያ ረቂቅ ላይ መሰረታዊ ለውጥ በነባር አዋጁ ላይ ያመጣሉ የምትሏቸው ምንድን ናቸው?
ሻምበል ገ/መድህን፡- እንዲሻሻል ከተፈለገው አደገኛ ነጥብ አንዱ፣ አንድ ልውጥ ሕያው የሚያመርት ኩባንያ ከምን እንዳመረተው እና አደጋ እንደማያስከትል የሚሰጠው ማረጋገጫ ሰነድ አለ። ነባር አዋጅ ይህን መረጃ ከአምራች ኩባንያው ብቻ ሳይሆን ከሀገር ውስጥ መንግስታዊ ተቋምም ማረጋገጫ አብሮ ማቅረብ እንዳለበት ይደነግጋል። አሁን ይሻሻል ተብሎ የቀረበው ነጥብ ደግሞ፣ ስለልውጥ ሕያው ያመረተው ኩባንያ ብቻ ማረጋገጫ ከሰጠ ይበቃል ይላል። ሀገር ውስጥ ያለ ሌላ የመንግስት ተቋም ማረጋገጥ አያስፈልገውም ይላል።
ሰንደቅ፡- ምን ማለት ነው?
ሻምበል ገ/መድህን፡- ይህ ማለት ለምሳሌ በዓለም ላይ ትልቁን የልውጥ ሕያው አምራች የሆነው የአሜሪካው ሞሳንቶ ነው።በአዲሱ አዋጅ መሰረት፣ የአሜሪካኑ ሞሳንቶ እራሱ ለሚያመርተው ልውጥ ሕያው ከምን እንዳዘጋጀው እና አደጋ እንደማያስከትል የራሱ ማረጋገጫ ይዞ ይቀርባል ማለት ነው። በሀገር ውስጥ የሞሳንቶ የልውጥ ሕያው ዝርያዎች አደጋ ያድርሱ፣ አያድርሱ የሚመረምርም የሚጠይቅም ተቋም አይኖርም ማለት ነው። ወይም ከማንኛውም ወገን ነፃ የሆነ አካል የሞሳንቶን ልውጥ ሕያውን ምርቶችን አይመረምርም።
ሰንደቅ፡- ሞሳንቶ እንዴት ራሱ ባመረተው ልውጥ ሕያው ዝርያ ላይ አደጋ አለው የሚል መረጃ ሊያቀርብ ይችላል? ሌላውስ ቢሆን?
ሻምበል ገ/መድህን፡-የእኛም ስጋት ይህ ነው። አበውም እንደሚሉት “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” አይነት ነው። ስለሞሳንቶልውጥ ሕያው ዝርያዎች በዓለም ላይ እያስከተሉ ያለውን አደጋ በብዙ ማረጋገጫዎች ማሳየት፣ ማቅረብ ይቻላል። የሚታወቅም ነው።የሚያዘጋጅበትን መረጃዎችም በመደበቅ ይታወቃል። አሜሪካኖች የምንበላው የምግብ አይነት ከምን እንደሚዘጋጅ ይነገረን ብለው በርካታ ሰላማዊ ሰልፎችን ሞሳቶን በመቃወም አድርገዋል። ስለሚመገቡት ምግብ ግን የነገራቸው አካል የለም። ይህ የሆነው መረጃ ማግኘት መብት መሆኑ ሕገመንግስታዊ ጥበቃ ባለባት ሀገረ አሜሪካ ነው፡ የአሜሪካ ሕዝቡ የሚመገበውን ምግብ ከምን እንደሚዘጋጅ ለማወቅ ሞሳንቶን የማስገደድ አቅም እንኳን መፍጠር አልቻለም። ለገዛ ሕዝባቸው መረጃ የከለከሉ ኩባንያዎች ለእኛ በምን አግባብ ግልጽ መረጃ እንደሚሰጡን፣ ማሻሻያ ሃሳብ ያቀረቡ ወገኖች ብቻ ነው የሚያውቁት። አደጋው ግን የሁላችንም መሆኑ ያሳዝናል።
ሰንደቅ፡- የኩባንያው መረጃዎች በቂ ናቸው ተብሎ ቢወሰድ እንኳን፣ በልውጥ ሕያዊ ዝርያዎቹ አደጋዎች ቢፈጠሩ ኃላፊነት የሚወስደው አካል ማን ነው? የማሻሻያ ረቂቅ ሰነዱ በዚህ ላይ ምን ይላል?
ሻምበል ገ/መድህን፡-መሰረታዊ ችግሩ ይህ ነው። በተለይ ከእኛ ሸማቾች አንፃር ይህ ጥያቄ መሰረታዊ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ለሚደርሰው ጉዳቱ ኃላፊነት የሚወስደው ብቻ ሳይሆን የጉዳቱ መጠንም መረጋገጥ ያለበት በሶስተኛ ወገን ነው። በተከሰተው ጉዳት መጠን መጠየቅም ያለበት አምጪው ወገን ነው። ለምርምር አስገባለሁ የሚለው አካል ጉዳት ከተከሰተ ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት መደንገግ አለበት። ይህ ካልሆነ ግን አደጋው ምትክ አልባ ነው የሚሆነው።
ሰንደቅ፡- እየተባለ ያለው ለልውጥ ሕያው ዝርያዎች ፈቃድ ሰጪ የመንግስት ተቋም አያስፈልግም ነው?
ሻምበል ገ/መድህን፡- አዎ። የልውጥ ሕያው ኩባንያዎች ማረጋገጫ በቂ ነው። ይህ ነው አንዱ የማሻሻያ ረቂቅ ሰነዱ የሚለው። እኛ ደግሞ የምንለው ፈቃድ ሰጪ የመንግስት ተቋም አስፈላጊ ነው። ምንም ቢሆን የመንግስት ተቋም በሀገሩና በሕዝቡ ላይ ከሶስተኛ ወገን የበለጠ አስተማማኝ ስራዎች ይሰራል የሚል እምነት አለን። ስለዚህም ለልውጥ ሕያው ፈቃድ ሰጪ የመንግስት ተቋም የግድ ያስፈልጋል።
ሰንደቅ፡-ልውጥ ሕያው ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው ለምርምር ለማዋል ብቻ ነው ወይንስ ለምግብነት በግዢ ወደሀገር ውስጥ ለማስገባት ነው?
ሻምበል ገ/መድህን፡- በማንኛውም መልኩ ሊገባ ይችላል። ቁም ነገሩ በነባሩ ሕግ ላይ ወደ ሀገር ውስጥ ልውጥ ሕያው የሚያስገባ አካል በመጀመሪያ ከግንዛቤ የመነጨ ስምምነት ማግኘት አለበት። ይህ ማለት፣ በነባር አዋጁ መሰረት አንድ እንቅስቃሴ እንዲተገበር ከባለስልጣኑ የሚሰጥ አዎንታዊ ጽሁፍ ማግኘት አለበት። ይህም ሲባል፣ ልውጥ ሕያውን መሥራት ወይም ለትምህርት፣ ለምርምር፣ ለምርት፣ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት፣ ወደውጭ ለመላክ፣ በትራንዚት ለማስተላለፍ፣ ለተጤነ ልቀት፣ በዝግ ለማምረት፣ ለማጓጓዝ፣ በገበያ ለማቅረብ፣ ለሰው ወይም ለእንስሳት በመድሃኒትነት ለመጠበቅ፣ ለምግብነት፣ ለመኖነት ወይም ለፋብሪካ ጥሬ እቃነት ማዋልን ሁሉ ያካትታል። እነዚህ ሁሉ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ከግንዛቤ የመነጨ ስምምነት የግድ ነው።
ሰንደቅ፡- በቀረበው ረቂቅ የማሻሻያ ሰነድ ልውጥ ሕያውን ለምርምር መጠቀም በተመለከተ ብቻ ነው የሚባለውን አግባብ እንዴት ያዩታል?
ሻምበል ገ/መድህን፡- ረቂቅ ሰነዱ ለምርምር ለሚውሉ ልውጥ ሕያው ልዩ ፈቃድ በሚል እንዲገቡ የሚጠይቅ ነው። ይህ ማለት ልዩ ፈቃድ የሚያስፈልገውን የነባሩን አዋጅ ሳታሟላ በአቋራጭ መንገድ ወደሀገር ውስጥ የማስገባት ፍላጎትን ለማስፈጸም የሚያበረታታ ረቂቅ ነው። መከራከሪያ ነጥቦችን ስንመለከት ምርምር የምናደርገው ዝግ በሆነ ቦታ ላይ ነው ይላሉ። የሚገርመው በኢትዮጵያ አቅምና ዝግጁነት ቀርቶ፣ በሌሎች በበለጸጉ ሀገሮች ልውጥ ሕያው አፈትልከው እየወጡ ከፍተኛ ጉዳት እየፈጠሩ ነው የሚገኙት። ለምሳሌ ለሙከራ የመረጡት ቦታ ሆለታ አካባቢ ነው። ከዚህ የምርምር መዓከል ልውጥ ሕያው አምልጦ ቢወጣና የሆለታ አካባቢ ላይ አደጋ ቢደርስ ማንነው ተጠያቂ ማድረግ የሚቻለው? እንዴትስ አደጋውን መከላከል ይቻላል? ይህን መመለስ የሚችል አቅምም ሆነ ዝግጁነት እንደሌለን በግልፅ የሚታወቅ ነው። ለዚህም ነው፣ ሁሉም ሀገር ዓለም በሚከተለው መርህ ልውጥ ሕያው ወደሀገር ውስጥ መግባት አለበት እንጂ በተለየ ሁኔታ በሚል ተቀጽላ መፈጸም የለበትም።
ሰንደቅ፡- ነባሩ አዋጅ ልውጥ ሕያው ወደሀገር ውስጥ እንዳይገቡ አይከለክልም። ይህ በሆነበት ሁኔታ ልዩ ፈቃድ የሚል ማሻሻያ በአዋጁ ማቅረብ ለምን ተፈለገ?
ሻምበል ገ/መድህን፡- መጀመሪያ ላይ አዋጁ ለምን መሻሻል አስፈለገ የሚለውን ጥያቄ ያነሳሁት ለዚሁ ነው። አዋጁ ልውጥሕያው የሚገቡበትን መንገድ ዘርዝሮ አስቀምጦ እያለ ልዩ ፈቃድ ሳያገኝ መግባት አይችልም የሚለው ማሻሻያ ለማንም የሚገባ ነጥብ አይደለም።
ሰንደቅ፡- እንደነዚህ አይነት ነገሮችን ማስፈር ለሞሳንቶ ኩባንያ አይነቶች የሙስና በር መክፈት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል?
ሻምበል ገ/መድህን፡- ይቻላል፣ አይቻልም ሌላ ነገር ነው። እነሞሳንቶ ግን በተለያዩ ሀገሮች ከፍተኛ ባለስልጣናትና ተመራማሪዎችን በመደለል በአንድ ሀገር ውስጥ ፍላጎታቸውን ማስፈጸም የሚችል ሕግ እንዲወጣ እንደሚያደርጉ ብዙ መረጃዎች ማቅረብ ይቻላል።
ሰንደቅ፡- ማሻሻያ አዋጁ ላይ ነባሩ አዋጅ “በሃገሪቱ ያለውን የልማት ፍላጎት ለመመለስ የሚያስችሉ ሆነው አለመገኘታው” ይላል። በዚህስ ነጥብ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?
ሻምበል ገ/መድህን፡- የሚገርመው ኢትዮጵያ ባለፉት አስርት አመታት በሁለት አሃዝ የማያቋርጥ እድገት ማስመዝገብ የቻለች ሀገር ነች። ለዚህ እድገት ወሳኙ የግብርናው ዘርፍ መሆኑ አሻሚ አይደለም። ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት የአፈር ጥበቃ ስራዎች፣ የግብርና ስርዓቱ መስተካከል፣ የነባር ዝርያዎችን አጠቃቀም፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያዎችና ኮምፖስት በማዘጋጀት እንዲሁም ገበሬውን አመለካከት በመቀየር የተስተካከለ የአመራራት ሂደቶችን በመዘርጋት የተገኘ ውጤት ነው።
ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ የልውጥ ሕያው ዝርያዎችን ቅድሚያ በምትሰጥበት ሁኔታ ላይ አይደለችም። እነዚህ ምርታማነት እንጨምራለን የሚሉ ወገኖች በገበያ ውስጥ ያለውን የዝርያ አይነት ነባርና ልውጥ ህያው መሆኑን እንኳን ለመለየት የሚያስችል አደረጃጀት የሌላቸው ናቸው። እነሞሳንቶ በመሳሪያት የሚጠቀሙት ተመራማሪ ተብለው ምንአልባትም በእነሱ ተቋሞች ውስጥ የዘረመል ምህድስና የተማሩም ሊሆኑ ይችላሉ። አደጋው አሁን አይታያቸውም፤ ወደፊት ግን አደጋ ሲከሰት ምን እንደሚሉ መጠበቅ ነው። እነሱ የባዮ-ኢንጂነሪንግ ባለሙያዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ጥያቄው የባዮሴፊቲ ባለሙያዎችን ስንት ናቸው የሚለው ነው።
ሰንደቅ፡- የዓለም ዓቀፍ ግንኙነት መምህር መሆንዎት ይታወቃል። ልውጥ ሕያው በነባር ዝርያዎች የመተካት ሂደቱ በቀጣይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ያለው ተፅዕኖ እንዴት ይገልፁታል?
ሻምበል ገ/መድህን፡- በቀጣይ የፖለቲካ ሂደታችን ላይ ተፅዕኖ እንደሚያመጣ ምን ጥርጥር አለው። ምክንያቱም ከዊክሊክስ መረጃ መረብ የምትረዳው የኢትዮጵያ የደህንነት አዋጅ በጣም አሳሪ ነው። አያሰራም። ለተመራማሪዎች መንገድ አይከፍትም። እና ሌሎች ነገሮችን አካቶ አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ለመንግስታቸው ሪፖርት ማድረጉን አስነብቧል። የልውጥ ሕያው የመጨረሻ ግብ የአንድ ሀገር ግብርና ስርዓት እና ነባር ዝርያዎችን መቆጣጠር ነው። ይህ የረጅም ጊዜ እቅዳቸው ነው። ይህን እቅዳቸውን ማሳካት ከቻሉ አንድን ሀገር በልውጥ ሕያው ዝርያዎች ላይ ጥገኛ ያደርጋሉ። በመጨረሻም በሚቆጣጠሩት ዝርያዎች አማካኝነት ሀገሮች ለእነሱ ፍላጎት ተገዢና ተንበርካኪ ያደርጓቸዋል። በተዘዋዋሪ በአንድ ሀገር ያለውን ፖለቲካ ኢኮኖሚ እነሱ ወሳኝ ሆነው ይገኛሉ።
ተመራማሪ ነን የሚሉት የሚመለከቱት ምርታማነት ይጨምራል የሚለውን የሞሳንቶን ማደናገሪያ ነው። የሚያስከትለውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማሕበራዊ ቀውሶችን ግን አሁን ላይ መመልከት አልቻሉም። የፖለቲካ አመራሩም ልውጥ ሕያውን ከምርታማነት አንፃር እንጂ በቀጣይ ሊያስከፍል የሚችለውን የፖለቲካ ዋጋ መገንዘብ የቻለ አልመሰለኝም። ቢያንስ ደግሞ በሁለት አሃዝ በማደግ ላይ ያለችን ሀገር ልውጥ ሕያውን በምንም መመዘኛ ቅድሚያ ልትሰጠው አትችልም። የዚህ ጉዳይ ዋና ፈላጊዎች የአሜሪካ መንግስት እና ሞሳንቶ ናቸው። መጠቀሚያ ያደረጓቸው ደግሞ የእኛ ተመራማሪዎችን ናቸው። ይህን እውነት ፖለቲካ አመራሩ ደጋግሞ ሊፈትሸው ይገባል።