05 NOVEMBER 2014 ተጻፈ በ 

ከሱዳን በመገንጠል የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችን ቁጥር በአንድ እንዲጨምር ያደረገችው ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ለማጣጣም አልታደለችም፡፡ የዚህ መንስዔ ደግሞ የሌላ ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት አይደለም፡፡

ነፃነቷን ባገኘች ማግስት አገሪቱን ወደ ነፃነት ለማድረስ ከፍተኛ ትግል ያደርጉ የነበሩት የቀድሞ የትግል አጋሮች ግጭት እንጂ፡፡ በፕሬዚዳንትነትና በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገሪቱን ሲመሩ የነበሩት ሳልቫ ኪርና ሪክ ማቻር (ዶክተር) በቀሰቀሱት ግጭት የተነሳ የአገሪቱ ዜጐች ለዘመናት ሲናፍቁት የኖሩትና ብዙዎች የሞቱለትን ነፃነት አሁንም መጎናፀፍ አልቻሉም፡፡

ከአሥር ወራት በፊት የተጀመረው የደቡብ ሱዳን ብጥብጥና ቀውስ ከሁለቱ ባላንጣ ግለሰቦች በኩል ያሉ ደጋፊዎች ኑዌርና ዲንቃ በተሰኙ ሁለት የአገሪቱ ዋነኛ ብሔሮች ጐራ ለይተው የብሔር ግጭት መልክ ሰጡ፡፡ ለዘመናት ለነፃነትና በጋራ ያደረጉትን ትግል ወደ ጐን በመተው እርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ መግባታቸው ብዙዎችን ያሳዘነ ከመሆኑም በላይ ባለፉት አሥር ወራት የአብዛኛዎቹ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን የዜና ሽፋን ሆኖ ሰንብቷል፡፡

ከቀውሱ መነሳት በመቀጠል የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ተቋም (ኢጋድ) ብጥብጡ ወደከፋ ደረጃ እንዳይሸጋገርና አገሪቱ የጀመረችውን የነፃነት ጉዞና የዜጐች የሰላምና የነፃነት አየር መተንፈስ ጉጉትና ምኞት እንደዳታጐል የበኩሉን ድርሻ ለመጫወት ሲሞክር ተስተውሏል፡፡

ምንም እንኳን ኢጋድ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ወደ ድርድር ጠረንጴዛ ቀርበው ያሉዋቸውን ልዩነቶች በሰላምና በድርድር እንዲፈቱ ለማድረግና ለማስቻል ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም፣ የተለያዩ የሰላም ስምምነቶች ቢፈረሙም፣ ፊርማዎቹም ሆነ ስምምነቶቹ ከወረቀት ነብርነትና ከመገናኛ ብዙኃን ፍጆታነት የዘለለ ተፈጻሚነት አልነበራቸውም፡፡

ስምምነቶች በተፈረሙ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ሁለቱም ታዋጊ ወገኖች አንዱ አንዱን እየወቀሰና እየከሰሰ መልሰው ወደ ጦርነት ያመራሉ፡፡ በብዙዎች ጥረትና ድካም የሚደረሱት ስምምነቶች የሚጣሱት በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ነው፡፡

በብጥብጡ ሳቢያ ብዙዎቹ ደቡብ ሱዳናውያን ለሞት፣ ለእንግልትና ለስደት የተዳረጉ ሲሆን ለዘመናት ሲጠብቁት የነበረው የነፃነት ውጤትም ቀቢፀ ተስፋ ሆኖባቸዋል፡፡

በአገሪቱ የተቀሰቀሰው ቀውስ ከቤት ንብረት ያፈናቀላቸው ደቡብ ሱዳናውያን በስደት ኑሮአቸውን ለመግፋት የተገደዱ ሲሆን በተለይ ወደ ጐረቤት አገር ኢትዮጵያ የገቡት ስደተኞች ቁጥር እጅግ በርካታ በመሆኑ ኢትዮጵያ በርካታ ስደተኞችን በመቀበልና በማስተናገድ ቀዳሚዋ አፍሪካዊት አገር እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ይህ ክስተት ደግሞ የተከሰተው ወደ አገሪቱ የገቡት የደቡብ ሱዳናውያን ቁጥር እጅግ በርካታ በመሆኑ ነው፡፡

በርካታ ድርድሮችና የሰላም ስምምነቶች እንዲፈረሙ ማድረግ የቻለው ኢጋድ የተፈረሙት የሰላም ስምምነቶች ለማስፈፀም ግን አልተሳካለትም፡፡ ኢጋድ ከተለያዩ አጋር ዓለም አቀፍ ተቋማትና አገሮች ጋር በመተባበር የተለያዩ ሥራዎችን ቢሠራም ከአሥር ወራት በኋላም ቢሆን የሚፈለገውን ሰላም በደቡብ ሱዳን ለማረጋገጥ አልተቻለውም በማለት የሚሞግቱ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች አሉ፡፡

የተፈጠረውን ቀውስ በሰላምና በድርድር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ለማድረግ በቀድሞው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአሁኑ በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ሥዩም መስፍን የሚመራው የኢጋድ ልዩ አደራዳሪዎች ቡድንም በአገሪቱ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ወደ አፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉዳዩን ለመምራት ማሰቡ እየተነገረ ይገኛል፡፡

ይህ ደግሞ የሁለቱ ተዋጊ ወገኖች በኢጋድ አደራዳሪ ቡድን አማካይነት የሚፈረሙትን የሰላም ስምምነቶች ተፈጻሚ ባለማድረጋቸው የመጨረሻው አማራጭ ተደርጐ የሚወሰድ ነው የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞችም አሉ፡፡

ጥላቻን ከማስወገድ አንስቶ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት እስከ ማቋቋም የሚሉ በርካታ ስምምነቶች የተፈረሙ ቢሆንም አንዳቸውም እስካሁን ድረስ ተፈጻሚ አልሆኑም፡፡ ሰኞ ዕለት በወጡ ዘገባዎች መሠረት፣ አገሪቱን በማስተዳደር ላይ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በቅርቡ በዩኒቲ ግዛት ባንቲዩ ከተማ ላይ የተፈጠረው ከፍተኛ ግጭትን በመቃወም አዲስ አበባ የሚገኘው የሰላም ተደራዳሪ ቡድናቸው ወደ ደቡብ ሱዳን እንዲመለስ ጥሪ አድርገዋል፡፡ ይህም የአገሪቱ ቀውስ ባለህበት ርገጥ ዓይነት ሆኖ ለወራት እየተካሄደ ያለውን የሰላም ድርድር ቀዝቃዛ ውኃ የሚደፋበት ነው፡፡

ምንም እንኳን ኢጋድ የወጠናቸውን በርካታ ዕቅዶች ከግብ ማድረስ የተሳነው ቢሆንም ሁለቱንም ተዋጊ ቡድኖች ወደ ድርድር ማምጣቱና በፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ታስረው የነበሩ የቀድሞ አመራር አባላትን ማስፈታት መቻሉ እንደ ዓብይ ስኬት የሚቆጥሩት በርካቶች ናቸው፡፡

እነዚህን ሁለት አበይት ክንዋኔዎች እንደ ስኬት የሚቆጥሩትና በድርድሩ ላይ ተስፋ ይጭራል ብለው የሚገልጹ ቡድኖች እንዳሉ ሁሉ ኢጋድ በደቡብ ሱዳን የተፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት በተገቢው ሁኔታ እንዳልተንቀሳቀሰና እንዲያውም የአመራር ብቃት ማነስ አለበት በማለት የሚተች ጐራም አለ፡፡

ኢጋድ አቅም አጥቷል?

የደቡብ ሱዳንን ቀውስ ለመፍታት ኢጋድ የአቅምም ሆነ የአመራር ብቃት ማነስ አለበት በማለት የሚተቹ ወገኖች እስካሁን ተፈርመውና ስምምነት ላይ ተደርሰው ተፈጻሚ ያልሆኑ ስምምነቶችን ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኢጋድ ውስጥ ያሉ አገሮች በደቡብ ሱዳን ኢኮኖሚም ሆነ ፖለቲካ ውስጥ የተለያየ ፍላጐት መኖር ኢጋድን ክፉኛ እንደጐዳው እና አቅም እንዳሳጣው ይገልጻሉ፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ለሪፖርተር ማብራሪያ የተሰጡ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የፖለቲካ ተንታኝ በእርግጥም ኢጋድ የአመራር ብቃት ማነስ አለበት የሚለውን ትችት ይቀበላሉ፡፡ ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ተቋሙ በአካባቢው አገሮች የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የመቅጫ መንገድም ሆነ አገሮች ከዚህ ዓይነት ችግሮች ቢታቀቡ ሊያገኙት የሚችሉት ማማለያ ጥቅም (Caroot & Stick) የሌለው መሆኑ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ የድርጅቱ የፋይናንስ መዋቅር አለመጠናከርና በአካባቢው ያሉ አገሮች የኢኮኖሚ አቋም ተመሳሳይ መሆን ሌላኛው የችግሩ ምንጭ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡

ከዚህ ሐሳብ ጋር በከፊል የሚስማሙት በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የልማትና የሰላም ተቋም ውስጥ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑ አቶ አቤል አባተ እንደሚገልጹት ደግሞ የችግሩ ምንጭ ኢጋድ በአገሮች መልካም ፍቃድ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በአካባቢው ያሉ አገሮች አብዛኛውን ጊዜ ችግሮቻቸውን ለመፍታት የሚሞክሩት በጋራ ስምምነት ላይ ተመሥርተው መሆኑም ሌላው ምክንያት ነው በማለት ያስቀምጣሉ፡፡

አንድ የኢጋድ መሪ ካፈነገጠ ያን መሪ በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ድርድር ወይም ወደ ቀድሞ አቋሙ ለመመለሰ የሚያስችል ማዕቀፍ ወይም መቅጫም ሆነ ማማለያ ማዕቀፍ አለመኖሩ ትልቅ ችግር መሆኑን እሳቸውም ያምናሉ፡፡

እንደ አቶ አቤል ገለጻ፣ ዋናው መቅጫ (Carrot) ፋይናንስ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ኢጋድ አስፈላጊው ፋይናንስ ስለሌላው የሚሰጠው ወይም የሚያደርቀው ነገር አይኖረውም፡፡ ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ስብስቡን በከፍተኛ ሁኔታ የሚረዱ አገሮች አለመኖር ነው፡፡ ‹‹ኢጋድ የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካና የመሳሰሉት ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና አገሮች ያላቸው ዓይነት የማማለያ (Carrot) አቅም የለውም፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ ማስፈራት አይችልም፤›› በማለት ይገልጻሉ፡፡

ኢጋድ ደቡብ ሱዳን ሰላም እንዲሰፍን ያካሄዳቸው በርካታ ድርድሮችና የሰላም ውይይቶች ከስኬት አለመድረስ ዋነኛው ምክንያት ከገንዘብ አቅም ጋር የሚያያዙት በርካታ ፖለቲካ ተንታኞችና ፀሐፊያን ቢኖሩም የስብስቡ አባል አገሮች የተለያየ ጥቅም በደቡብ ሱዳን ማዳበርና እነኚያን ጥቅሞች ተፈጻሚ ለማድረግ የሚደረግ እንቅስቃሴም ሌላ የችግሮች ምንጭ ነው በማለት የሚገልጹ አሉ፡፡

ከየአቅጣጫው የሚሰነዘሩ ጉዳዩን የተመለከቱ አስተያየቶች የተለያዩና በተናጠል መጠናት የሚያስፈልጋቸው ቢሆንም በአብዛኛዎቹ አስተያየት ሰጪዎችም ሆነ ፀሐፊያን ዘንድ የሚያስማማው ግን የገንዘብ እጥረት ነው፡፡

አቶ አቤል በደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድርን አስመልክቶ ኢጋድ ወሳኝ ምዕራፎችን መጓዝ ችሎ እንደነበር አስታውሰው፣ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈጠሩ የፖለቲካ ምስቅልቅሎች የተጀመረው ጥረት ፍሬ እንዳያፈራ እንቅፋት መፍጠሩን ይገልጻሉ፡፡

ምንም እንኳን ኢጋድ የመቅጫም ሆነ የማማለያ አቅም ባይኖረውም እነዚህን ነገሮች የያዙ አገሮችና ተቋማት አብረውት ነበሩ፡፡ ነገር ግን በቅርቡ በተከሰቱ ሁለት ዓበይት ዓለም አቀፍ ክስተቶች የተነሳ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዓይኑንና አትኩሮቱን ከደቡብ ሱዳን ላይ ማንሳቱን አቶ አቤል ይገልጻሉ፡፡

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አትኩሮትንና ዓይኑን ከደቡብ ሱዳን ላይ እንዲነቅል ያደረጉት ክስተቶች ደግሞ አንደኛው በዩክሬን የተከሰተው ቀውስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰተው የአይኤስ አሸባሪዎች ቡድን እንቅስቃሴ መሆናቸውን አቶ አቤል ይጠቅሳሉ፡፡

ከእነዚህ ሁለት አቅጣጫ አስቀያሪ ዓለም አቀፍ ክስተቶች በፊት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የደቡብ ሱዳንን ጉዳይ በቅርብ ይከታተለው እንደነበር በምሳሌ የሚያስረዱት አቶ አቤል የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጆን ኬሪ አዲስ አበባ ላይ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ሦስት አገሮችን ማዕቀብ እንዲጥሉ አነጋግረው እንደነበር ያስታወሱ ሲሆን፣ ነገር ግን የደቡብ ሱዳንን ችግር ለመፍታት እየሠሩ የነበሩ ትሮይካ (የአሜሪካ፣ የእንግሊዝና የኖርዌይ መንግሥታት) እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ወደ ሁለቱ ዓለም አቀፍ ክስተቶች መሳብ ለችግሩ መፍትሔ ማጣትና ኢጋድ እንቅስቃሴ ውስንነት ምክንያት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ይህም ቢሆን ግን የኢጋድ አደራዳሪ ቡድን ሥራውን ከጀመረበት ካለፉት ስድስት ወራት በኋላ ምን ተጨባጭ የሆነ ውጤት አምጥቷል ብሎ ጉዳዩን በጥልቀት መመርመር አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ አቶ አቤል በእርሶቸው አተያይ አደራዳሪ ቡድኑ ቢያንስ ቢያንስ ሁለት ውጤት አምጥቷል፡፡ እነርሱም ይብዛም ይነስም ሁለቱ ተዋጊ ቡድኖች ወደ ድርድር እንዲገቡ ከማድረጉም በተጨማሪ የተወሰኑ ስምምነቶች እንዲኖሩ አድርጓል፡፡

ለዚህም እንደማጠናከሪያ የሚያነሱት የመጨረሻዎቹ ስምምነቶች በሥልጣን ላይ የሚገኙት ሳልቫ ኪር በግልጽ የተቀናቃኛቸው ሪክ ማቻር ቡድንን ጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመቀበል መስማማታቸውን ነው፡፡ የኢጋድ አደራዳሪ ቡድን ያመጣቸው መሰል ውጤቶች እንዳሉም ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም ግን በአብዛኛው የሚፈለገውን ያህል ውጤት እስካሁን ተገኝቷል ለማለት እንደማይቻል ግን ያክላሉ፡፡

ማዕቀብ እንደ አማራጭ?

በደቡብ ሱዳንን የተፈጠረውን ቀውስ በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች ሁለቱም ወገኖች በሰላም ድርድሩ ላይ የሚስማሙባቸውን ነጥቦች ማስፈጸም ካልቻሉ ማዕቀብ መጣልን እንደ አማራጭ ያቀርቡታል፡፡

ለዚህም ይመስላል ኢጋድም ቢሆን ሁለቱ ተደራዳሪ ወገኖች ለሚፈጽሙት የሰላም ስምምነት ተገዥ ካልሆኑ ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት በመምራት ማዕቀብ እንዲጣልባቸው ሊያደርግ ይችላል የሚሉ ዜናዎች መሠራጨት የጀመሩት፡፡

ቢያንስ የኢጋድ አባል አገሮች የኢኮኖሚ ማዕቀብ ቢጥሉ ለውጥ ሊመጣ ይችላል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ‹‹የኢኮኖሚ ማዕቀብ መጣል ይቻላል ነገር ግን እንኳን በኢጋድ የሚጣል የኢኮኖሚ ማዕቀብ ይቅርና በታላላቅ ተቋማትና አገሮች አማካይነት የሚጣሉ ማዕቀቦች እንኳን በአብዛኛው ውጤት አያስገኙም፤›› በማለት አቶ አቤል ይሞግታሉ፡፡

ለዚህም እንደ ምሳሌ ኤርትራንና ኢራንን ያነሱ ሲሆን ምንም እንኳን ኤርትራ ላይ በ2009 እና 2011 ላይ ማዕቀብ ቢጣልም ኤርትራ ላይ ለውጥ አለመታየቱን ይገልጻሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ‹‹ደቡብ ሱዳን ላይ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ቢጣል አብዛኛው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ትስስር ድንበር አካባቢ ባሉ ማኅበረሰቦች አማካይነት የሚካሄድ ኢ-መደበኛ ዓይነት ንግድ በመሆኑ እርሱን መገደብ በጣም ከባድ ነው›› በማለት ይገልጻሉ፡፡ በዚህ የተነሳ ማዕቀብ መጣል የደቡብ ሱዳንን ችግር የበለጠ ያከረዋል እንጂ ይፈታዋል የሚል እምነት እንደሌላቸው የገለጹት አቶ አቤል የማዕቀብ ፋይዳ ያን ያህል የጐላ ለውጥ እንደማያመጣ ገልጸዋል፡፡

ላለፉት አሥር ወራት በደቡብ ሱዳን በመካሄድ ላይ ያለው የርስ በርስ ጦርነት መነሻው ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ከቀድሞ የትግል አጋራቸውና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሪክ ማቻር ተቃጣብኝ ያሉት የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው፡፡

በአገሪቱ የተከሰተውን የእርስ በእርስ ግጭት ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም አንዱም የረባ ውጤት ማምጣት አልቻለም፡፡ መፍትሔው ማዕቀብም ይሁን ድርድር አልያም ውይይት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናውያን ግን ለዘመናት ሲመኙት የኖሩትንና የናፈቁትን ነፃነትና ሰላም ለማየት በጉጉት እየጠበቁ ነው፡፡

Leave a Reply