-የሃይማኖት ተቋማት በፀሎት እንዲያስቡት ጥሪ አስተላልፏል
በቅርቡ የተመሠረተው የዘጠኝ ፓርቲዎች ትብብር ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሰላማዊ ሠልፍ ጠራ፡፡ ጥሪው የተደረገው ፓርቲዎቹ በኅዳር ወር የሚያካሄዱትን እንቅስቃሴ በተመለከተ ያዘጋጁትን የድርጊት መርሐ ግብር ጥቅምት 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ይፋ ሲያደርጉ ነው፡፡
ጥቅምት 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ትብብር የመሠረቱት ዘጠኝ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኃላፊዎች በሰማያዊ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በጋራ በሰጡት ‹‹በምርጫ ስም የነፃነት ትግሉን ማዘናጋት አይቻልም›› በሚል መግለጫ ላይ እንደገለጹት፣ በኅዳር ሙሉ ወር የ‹‹ነፃነት ለፍትሐዊ ምርጫ›› በሚል ርዕስ ሕዝባዊ የትግል መርሐ ግብር አዘጋጅተዋል፡፡
የስብስቡ ሰብሳቢ አቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) እንደገለጹት፣ ከኅዳር 27 እስከ 28 የሚቆይ የተቃውሞ ሠልፍ የሚካሄድ ቢሆንም፣ የት እንደሚደረግ ወደፊት እንደሚገለጽ አሳውቀዋል፡፡ ይህ የተቃውሞ ሠልፍ በወሩ ውስጥ የሚካሄዱ አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች መዝጊያ ፕሮግራም እንደሚሆን አቶ ይልቃል ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኅዳር ወር ውስጥ ባሉ ሦስት እሑዶች በተመረጡና አማካይ በሆኑ ሥፍራዎች ሕዝባዊ ስብሰባዎች እንደሚካሄዱም ተብራርቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የታላላቅ ሃይማኖት አገር ናት ያሉት አቶ ይልቃል፣ በየቤተ እምነቱ የፀሎት ፕሮግራም እንዲደረግ ጥሪ ማድረግና አባላት እንደየእምነታቸው ተሳትፎ የሚያደርጉባቸው እንቅስቃሴዎች ይኖራሉ ብለዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ እንዴት ልታስታርቁት ነው? የሚል ጥያቄ ከሪፖርተር የቀረበላቸው አቶ ይልቃል፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱ የሚለው ሌላ ነው፡፡ ከዚህ ጋር አይገናኝም፡፡ አገራችን አስገቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነች፡፡ ጭንቅ ላይ ነው ያለነው፣ ረሃብ በዝቷል፣ ጦርነት በዝቷል፣ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለው ልዩነት በዝቷል፡፡ አባቶቻችንና የሃይማኖት ተቋሞቻችን በፀሎት አግዙን ብሎ ማለት ፖለቲካና ሃይማኖትን መቀላቀል አይደለም፡፡ ለአገራችን ሃይማኖቶች ክብር መስጠት ነው፤›› በማለት መልሰዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ኅዳር ውስጥ ባሉ የጁምዓ ቀኖች ውስጥ ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዝርዝር መግለጫ የሚሰጥ ሲሆን፣ ለሌሎች ሃይማኖቶችም እንደየእምነታቸው እንደሚገለጽ አቶ ይልቃል አመልክተዋል፡፡
‹‹ነፃነት ለፍትሐዊ ምርጫ›› በሚል ርዕስ የሚካሄደው ሕዝባዊ ትግል በዚህ ላይ የሚያተኩርባቸው ዋና ዋና ተግባራትም ተገልጸዋል፡፡ በየቤተ እምነቱ ፀሎት ፕሮግራም እንዲደረግ ጥሪ ማድረግና አባላት የእምነታቸው ተሳትፎ ማድረግ፣ በምርጫ ዙሪያ የፓናል ውይይቶች ማድረግ፣ የአደባባይ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ማድረግ፣ ለመንግሥታዊ ተቋማት ደብዳቤ ማስገባት፣ የተቃውሞ ድምፅ ማሰማትና የሕዝብ ተሳትፎ ማበረታታትና ድጋፍ ማሰባሰብ የተካተቱ ዋና ተግባራት ናቸው፡፡