ከሚርቃና ባሻገር…..!!

እናንተ የፌስቡክ ወስፈንጥረኞች አንድ የማይጥማችሁን ሐሳብ ስታነቡ ሐሳቡን በመሞገት ፋንታ “ጫታም፤ ጀዝባ፤ ሚርቃና” እያላችሁ የመዘባረቅ ልማድ እንዳለባችሁ ይታወቃል ፡፡ እኛ የምንለው! ጫት መቃም “ኸምር” እንደ መጠጣት ይመስላችኋል ልበል?… ለምሳሌ “የቃመ ሰው ይዘባርቃል፡፡ የሚሰራውን አያውቅም፡፡ የሚጽፈውንም አያውቅም”… እንደዚህ ነው የምታውቁት እንዴ?…. አያችሁ! ከቤት የተነገራችሁን በጥላቻ የተከደነ አባባል እንዳለ ይዛችሁ ስለምትወጡ ነው እንዲህ የሚምታታባችሁ፡፡ አባባሉ ሙስሊሙን ኢትዮጵያዊ፣ በተለይም የሀረርን ሰው ቅስም ለመስበር ነበር የተፈበረከው፡፡ አሁን ደግሞ ማንኛውንም የሀረርጌ ሰው (ክርስቲያኑንም ሆነ ሙስሊሙን) ለማሸማቀቅ የሚሞከርበት መሳሪያ ሆኗል፡፡ ደግነቱ የሚሸማቀቅ ሰው አለመኖሩ ነው፡፡ ምንም የለም !!
—-
ልንቆጣ ነበር፡፡ ግን ብዙ ወዳጆች ስላሉን ቁጣውን ረሳነው፡፡ እውነቱን ለማወቅ ለሚሹ ጓዶቻችንም እውነቱን ልንነግራቸው ወደድን!!

የጫት መቃም ውጤት የሚታየው እነዚያ “መርቅነህ ነው፤ ቅመህ ነው” የሚሉ ሰዎች ከሚናገሩት በተቃራኒው ነው፡፡ የሚቅም ሰው ቅጠሉን ሲጎርስ ነው ሐሳቡ የሚስተካከልለት፡፡ ሳይቃም ሲቀር ግን ሰውዬው በሐራራ ብዙ ነገር ሊቀባጥር ይችላል፡፡ ረብሻውም አይጣል ነው፡፡ በሐራራ ሰው የገደለም ሞልቷል፡፡ አንዱ በሜንጫ ሰው ገድሎ ፍርድ ቤት ቀረበ፡፡

ዳኛ፡ Maalif ajjeeste? (ለምንድነው የገደልከው)
ገዳይ: Sa’aan haraaraa (የሐራራ ሰዓት ነበር)
Manacaanis qara (ሜንጫውም የሳለ ነበር)
Xiqquman tuqe (ትንሽ ነው የነካሁት)
Liphuma je’e (ግን ወዲያኑ ሸኘሁት)

እንግዲህ ጫት እንዳትቅሙ የምንመክራችሁ እርሱን አጥታችሁ በሐራራ ሰዓት የሚመጣባችሁን አደገኛ ስሜት ለመቆጣጠር ያቅታችሁ ይሆናል በማለት ነው፡፡ በተለይ ቅጠሉ በማይበቅልበት ወረዳና ከሀገር ውጪ የምትኖሩ ከሆነ ቢቀርባችሁ ይሻላል (ሰበብ እንድትሆኑብን አንፈልግም)፡፡ ከዚያ በቀር እርሱን ቅማችሁ ትዘባርቃላችሁ ማለት ዘበት ነው፡፡ የቃመ ሰው ጭራሹኑ ይዘጋል፡፡ አይለፈልም! አያወራም!! አይዘባርቅም!! በአንድ ነገር ላይ concentrate አድርጎ እርሱን ከግብ ለማድረስ ይጥራል፡፡ በሌላ ወቅት የሰራቸው ስህተቶችም አንድ በአንድ ወለል ብለው ይታዩታል፡፡

የጫት ሚርቃና መጥፎ የሚሆንበት ወቅት ግን አለ፡፡ ይኸውም ከሌላ ነገር ጋር ተዳብሎ በሚወሰድበት ጊዜ ነው፡፡ የጫቱ ምርቃና ምንጊዜም የሚላችሁ “በዚህ መነቃቃት በቶሎ ስራህን ስራ” ነው፡፡ ሰውነታችሁን በምንም መልኩ አያስረሳችሁም፡፡ አዕምሮአችሁን አያስታችሁም፡፡ concentration ይሰበስብና በአንድ ወይንም በሁለት ነገር ላይ ብቻ እንድታተኩሩ ያደርጋችኋል፡፡ ሌሎቹ ግን በተፈጥሮ ያላችሁንና ነገር ግን በማህበረሰቡ የግብረ ገብ ልማድ ሳቢያ suppress የተደረጉትን ባህሪዎቻችሁን ያወጣሉ፡፡ ጫትን በዚህ ላይ ስትጨምሩበት ደግሞ ከውስጣችሁ “ስራህን ስራ” የሚላችሁ የሚርቃናው pressure ይስባችሁና በጤነኛ አዕምሮ የማይታሰቡ፤ ለህሊና የሚቀፉ ወንጀሎችን ልትሰሩ ትችላላችሁ፡፡ ለምሳሌ ጫት ከቃሙ በኋላ ጨብሲ እያሉ መጠጥ የሚጠጡ መደዴዎች ለእንዲህ ዓይነት ነውር በጣም የታገለጡ ናቸው (ከእህቱ ጋር የተኛው ሰውዬ ታሪክ ለዚህ አብነት ይሆናል)፡፡ እኛ የሀረርጌ ልጆች “ጨብሲ” ስንል ሚርቃናውን በወተት neutralize ማድረግ ማለታችን ነው፡፡ በተለይም እንቅልፍ በቶሎ መተኛት ከፈለግን በወተት ጨብሲ ማድረግ ደንባችን ነው፡፡ እነዚህኛዎቹ ግን ለፍየል ብቻ የሚታዘዘውን የቢርቃማ ጫት ይቅሙና በእርሱ ላይ አልኮል ይቀረቅሩበታል፡፡ ከዚያ በኋላ ፊፍ መሆን ነው እንግዲህ….!!

“ጫት እንቅልፍ ይከለክላል” ይባላል፡፡ ታዲያ እኛ የምንቅመው ለምን ሆነና?!! በሶስት ሰዓት በቁማችን እንዳናንኮራፋ ስንፈልግ እኮ ነው የምንቅመው፡፡ ስራዎች ሲበዙብን እርሱን እየቃምን በቶሎ ለመጨረስ እንጥራለን፡፡ በፈተና የተወጠረ ተማሪም እንቅልፉን ለማባረር መቃሙ የተለመደ ነገር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከቀን ይልቅ ሌሊት ተመራጭ ነው፡፡ ሌሊቱን በውስኪ መግፋት አንችልም መቼስ (ሀራም ነው!! ውድም ነው፡፡ በዚያ ላይ ውስኪ ያሰክራል እንጂ እንቅልፍ አያባርርም)፡፡ እኛ መቃምን ከድሮ ጀምሮ ያደግንበት በመሆኑ ምንም አያስፈራንም፡፡ አያሳፍረንም፡፡ ለኛ አሳፋሪው ነገር መጠጥ ጠጥቶ በቱቦ ውስጥ ተደፍቶ መገኘት ነው፡፡ በቃ!!

ጫት ይጎዳል!.. አዎን! በጥንቃቄ ካልተያዘ ይጎዳል፡፡ የምግብ ፍላጎት ይቀንሳል፡፡ እኛ ግን ቀን የምንቅመው በሆጃ፣ ማታም የምንጠጣው ወተትና እርጎ በመሆኑ የምግብ ፍላጎት የሚለውን ኬላ በቀላሉ እናልፈዋለን፡፡

የሚቃመው ጫትም በጥንቃቄ መመረጥ አለበት፡፡ “ቢርቃማ” እና “ወላህ” (ካረጀ ተክል የሚለቀም ነው) ከቃማችሁ ለአራት ቀናት እንቅልፍ የምታገኙ አይመስለኝም፡፡ እንዲሁም ከአንዳንድ አካባቢዎች የሚለቀሙት የጫት ዓይነቶች በአካባቢው መሬት የተነሳ ለሰው ልጅ አዕምሮ የሚበጁ አለመሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ ለምሳሌ ሃሜቲ ከሚባል መንደር የተለቀመ ጫት የቃመ ዐረብ እንዲህ ብሎ ነበር ይባላል፡፡

ኸዘንና ቃት ሐቀል ሀሜቲ (የሃሜቲን ጫት ቅመን)
ማ ሹፍና ጠሪቀል በይቲ (የቤታችን መንገድ ማየት አቃተን)

ዐረቡ አደገኛ የሚባለውን የሃሜቲ ጫት ቅሞ ወደቤቱ የሚያደርሰውን መንገድ ብቻ ነው ያጣው፡፡ አረቄ ቢጠጣ ኖሮ ግን በሦሥት መለኪያ ብቻ እንዲህ ይሆን ነበር፡፡

ከጫት ጋር ተያይዘው የሚወሱት እንደ ሩሐኒያ ማናገር፣ ከወሊዮች ጋር መነጋገር፣ ከሽፍና ህልም ማየት የመሳሰሉት ተረቶች ግን የሉም፡፡ ቅጠሉ ስለተቃመ እንዲህ ይኮናል የሚሉትም አጭበርባሪዎች ናቸው፡፡ “ጀዝባ” የሚባሉትም እነርሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ሌላውን ነገር እርግፍ አድርገው ጫትን መቃም ብቻ እንደስራ የያዙ ናቸው፡፡ በተለይም ማታ ያለምንም ምክንያት እየቃሙ ያድሩና እስከ እኩለ ቀን ድረስ ይተኛሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ የሀረርጌ ኦሮሞ “Jazbaa fi sareen ganama rafti” የሚል ተረትና ምሳሌ ፈጥሮላቸዋል፡፡ “ጀዝባና ውሻ ጠዋት ይተኛል” እንደማለት ነው፡፡
——-
አዲስ አበባ ኖረናል፡፡ በጣም የሚገርመን ግን የዚያ ሀገር ሰው ወገኛነት ነው (እውነተኞችም እንዳሉ ሆነው)፡፡ ጫትን ከአደንዛዥ እጽ በእኩል ደረጃ እየኮነነ ወደ ጓሮው ስትገቡ ግን እኛ በውድ ዋጋ ይዘናት ለምናመጣት አንዲት ሐቃራ ሲንሰፈሰፍ ታገኙታላችሁ!! (ገንዘቡንስ አያውጣ! በርጫችን እያዳከመ በጀርባችን ላይ መተኮሱ ነው የሚያናድደው) ፡፡ አቤት መንሰፍሰፍ!! ስም ልጥራ እንዴ?…!! አያስፈልግም፡፡ ስማቸውን ብጠራ በጣም ነው የምታብዱት፡፡

እንግዲህ ዓይነቱ “ከቢር ጉሉሌ” የሆነ ሰውዬ ነው በሚዲያና በpublic አጋጣሚ ሁላ ከኛ የሚበልጥ እየመሰለው በስነ-ምግባር አስተማሪነት ራሱን የሚሰይመው፡፡ በተለይም በኤፍ ኤም ሬድዮኖች “ጫት… ሀገር አጥፊ፣ ባህል አጉዳፊ..” እያለ የሚሸልለው ሁሉ ወገኛ መሆኑን እወቁት፡፡ “እገሌ ሁለት ዙርባ ቡስጣኒ ጨረሰ” እያሉ የሚሳፈጡት ሁሉ ይቅማሉ፡፡ የግል ጋዜጦችም ያው ናቸው፡፡ መቃማቸውን በግልጽ ሲናገሩ የሰማኋቸውና ያነበብኳቸው እውቁ የድራማ ደራሲ ሃይሉ ጸጋዬ፣ ደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሄር እና ደራሲ ተስፋዬ ገብረ አብ ብቻ ናቸው፡፡ ሌላው ግን በልቡ የሌለውን የሚቀባጥር አስመሳይ ነው፡፡

የመንግሥት ባለስልጣናትስ?…. ስንትና ስንቱ በጫት ገቢ ሚሊዮነር እንደሆነ ከነ ማስረጃው ልንዘረዝርላችሁ እንችላለን፡፡ ይህ ሁሉ እየታወቀ ነው ወገኞች አርቲስት ለመሆን የሚሞክሩት፡፡ ብዙ ጊዜ ደግሞ “ጫት መቃም” ሰዎችን ለማጥቃት የሚጠቀሙበት መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ጊዜ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሙስሊም በመሆናቸው ብቻ አንዱ ዘረኛ ጋዜጣ “የኦሮሚያ ክልል ውሳኔ የሚወስነው በበርጫ መጅሊስ ላይ ነው” ብሎ መጻፉን እናስታውሳለን፡፡ የሚገርመው እኮ ሁለቱም ሰዎች ሙስሊም ከመሆናቸው በስተቀር አይቅሙም፡፡ አንደኛው እንዲያውም ጫት መቃም ሐራም ነው ሲል እንደነበረ አስታውሳለሁ (ሰዎቹ ጁኔይዲ ሳዶ እና ዶ/ር ሙሐመድ አደም ይባላሉ)፡፡ እነዚህን ሰዎች በፖለቲካ አቋማቸውና በስራ አፈጻጸማቸው መተቸት ልክ ነው፡፡ ሙስሊም ስለሆኑ ብቻ “ውሳኔ የሚወስኑት በመጅሊስ ላይ ነው” እያሉ መጻፍ ግን ዐይን ያወጣ ዘረኝነት ነው፡፡

ቅጠሉን ከአደንዛዥ እጽ ጋር ማወዳደርስ?…..ቂቂቂቂቂ.. ያስቃል፡፡ ያሳፍራል፡፡ አውስትራሊያ ብትሄዱ እኮ ከሶማሊያ እና ከምሥራቅ ኢትዮጵያ የተሰደደው ህዝባችን በህግ ተፈቅዶለት በግቢው ውስጥ ተክሉን ሲያሳድገው ትመለከታላችሁ፡፡ በተለይም ምዕራባዊቷ የፔርዝ ከተማ በዚህ በደንብ ትታወቃለች፡፡ እዚያ ሀገር የሚከለከለው ከውጪ በዱቄት መልክ እየተዘጋጀ የሚገባው ጫት ነው፡፡ ይህኛው ጫት እጅግ በጣም concentrated ከመሆኑ የተነሳ በማንኪያ ሲወስዱት ጭንቅላት ሊነካ ይችላል፡፡ ጫት ውሃው ከወጣለት በጣም ምንም ጥቅም የለውም፡፡ ደግሞም ዱቄቱን ከሌላ ድራግ ጋር የሚቀላቅሉት እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ የዱቄቱ ጫት መከልከሉ አግባብ ነው (መድኃኒትም በመጠን ካልተወሰደ ይገድላል)፡፡

እዚህ ምሥራቅ ኢትዮጵያ ቅጠሉ ከሰባት መቶ ዓመታት በፊትም ይታወቃል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለጫት የጻፈው ግብፃዊው ምሁር ኢብን ፈድሉላህ አል-ዑመሪ ሲሆን ዘመኑም በ1349 ነው፡፡ ቅጠሉ ወደ የመን የሄደውም ከዚህ ነው፡፡ ስለዚህ “ጫት ከየመን ተገኘ” የሚባለው ስህተት ነው፡፡ ሁሉም ዶክመንቶች ቅጠሉ ከዚሁ የምሥራቅ ኢትዮጵያ ክልል እንደተገኘ ያረጋግጣሉ፡፡ “ኃይለ ሥላሤ ሀረሮችን ለማዳከም ያመጣው ነው” የሚለውን ተረት ለጊዜው እርሱት፡፡ ተረትና ታሪክ እየተደባለቀ ነው ሀገር የጠፋው፡፡
——
በአጠቃላይ ግን መልዕክታችን “አትቃሙ” የሚል ነው፡፡ አያያዙን ስለማታውቁት ሰበብ እንድትሆኑብን አንፈልግም!! ዋናው ነገር ደግሞ ከኦክሲጂን በስተቀር ደባል ነገር ለመልመድ አለመሞከር ነው፡፡ ጫት ብቻ ሳይሆን ቡናና ሻይ እንኳ ሱስ ከሆነ መጥፎ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ይቅርባችሁ!!

በማንኛውም ነገር addict መሆን በፍጹም አይመከርም፡፡ ስለዚህ የማትቅሙ ሆነ እንዳትለምዱት ምክራችንን እናስተላልፋለን፡፡ በወገኝነት የሚዋሹትን ግን አትስሟቸው፡፡ ጫትን በተመለከተ ያለው ሐቅ ከላይ የተገለጸው ነው፡፡

አፈንዲ ሙቱቂ

Leave a Reply