“ሽፈራው…ሞሪንጋ”
አጭር የመጽሐፍ ግምገማ፦ “ሽፈራው…ሞሪንጋ”
በፈቃዱ ፉላስ ደራሲው
አበራ ለማ ርዕስ፦ ሽፈራው…ሞሪንጋ፣ ታምረኛው ዕጽ የሽፋን ዓይነት፦ ስስ አሳታሚ፦ ማንኩሳ አሳታሚ አከፋፋይ፦ ዓይናለም የመጻሕፍት መደብር፣ አዲስ አበባ የታተመበት ዘመን፦ 2006 (አ.ኢ.አ)፣ 2014 (እ.ኤ.አ) የገጾች ብዛት፦ 160 ይህ በአቶ አበራ ለማ የተደረሰው ቀጭንና ጠቃሚ መጽሐፍ በሶስት ዋና ዋና ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን በውስጡም በርካታ የሞሪንጋ ዕፅ ምስሎችንና ሌሎችንም የተክሉን ገጽታዎች በዝርዝር ያካተተ ነው፡፡ ምስሎቹ፣ በተለይም የዕፅዋቱ፣ ቀለም (ከለር) ቢኖራቸው ይመረጥ ነበር፤ ምክንያቱም ተክሎቹን በተፈጥሮ ቀለማቸው ማየት ያስችል ነበርና ነው፡፡ ምዕራፍ 1 (ገፅ 7-37) የሞሪንጋ ዕፅ ዓይነቶችን (species)፣ በዓለም ዙሪያ ያለውን ሥርጭትና ሳይንሳዊ ስሞቹን፣ እንዲሁም በብዙ ሃገሮች የተሰጡትን አካባቢያዊ ስሞችን ይዘግባል፡፡ ቀጥሎም፣ ሰፋ ያለው የመጽሐፉ ክፍል፣ ምዕራፍ 2 (ገፅ 38-91)፣ የዕፁን ልዩ ልዩ ጥቅሞች ይዘረዝራል፡፡ በምግብነት፣ በመድሃኒትነት፣ የደፈረሰ ውሃን ለማጥራት ዕፁ ያለውን ጥቅምና ሌሎች ግልጋሎቶቹን ሲተነትን፣ የምዕራፉ ዋናው ትኩረት ግን በመድሃኒትነት ጥቅሞቹ ላይ ነው፡፡ ምዕራፍ 3 (ገፅ 123-155) ስለ ሞሪንጋ አተካከል፣ እንክብካቤ፣ አመራረት፣ ምርት አሰባሰብ፣ የምርት ውጤቶችን ለገበያ የማቅረብን ዝግጅት አብራርቶ፣ ቀጥሎም በኒካራጓ፣ በኢትዮጵያ (ሰፋ ያለው ክፍል)፣ እንዲሁም በኤርትራ የተገኙትን ተሞክሮዎች ይዘግባል፡፡ በመጽሐፉ የመጨረሻ ክፍል (ገፅ 156-160) ደራሲው መጽሐፉን ለማዘጋጀት የተጠቀመባቸው ማጣቀሻዎች ተዘርዝረዋል፡፡ በጠቅላላው፣ በዓለም ዙሪያ 13 የሞሪንጋ ዝርያዎች (species) ሲኖሩ፣ ከነኚህ መሃል 6 ቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ይበቅላሉ (ገፅ 13-29)፡፡ ዋናው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘው ዓይነት፣ ሞሪንጋ ስቴኖፔታላ መሆኑን መግለፅ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ሞሪንጋ (ሽፈራው) ከ 40 በላይ ለሚሆኑ የጤና እክሎች እንንደሚጠቅም ተወስቷል (ገፅ 43-47)፡፡ እነኚህም አስም፣ የደም ግፊት፣ ጉንፋን፣ ኮሌራ፣ የአንጀት ህመም፣ ሣል፣ የስኳር በሽታ፣ ጨብጥ፣ የደም ማነስ፣ ብጉርና የመሳሰሉትን በሽታዎች ያጠቃልላሉ፡፡ እዚህ ላይ ሁለት ችግሮች ይታያሉ፡፡ ይኧውም የዕፁ ስም አጠራርና ከዚያም የሚከተለው ችግር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘውና በስፋት ግልጋሎት ላይ የሚውለው ዝርያ ሞሪንጋ ስቴኖፔታላ (‘ሽፈራው’የሚለው ብዙውን ጊዜ ለዚህ ዕፅ – species – የተሰጠ ስም ነው) የተባለው ሲሆን በመጽሐፉ የተዘረዘሩት ጥቅሞች አብዛኛዎቹ የሞሪንጋ ኦሌይፌራ ጥቅሞች ናቸው፡፡ በ October 30፣ 2015 በኢትዮሚዲያ ይህ ገምጋሚ በከተበው ጦማር፣ ሁኔታው ሊያስከትል የሚችለውን የመረጃ መዛባት ችግር ለማመልከት ሞክሯል፡፡ በሌላ በኩል፣ ሞሪንጋ ኦሌይፌራ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም ሥርጭቱና ግልጋሎቱ እንደ ሞሪንጋ ስቴኖፔታላ የሰፋ አይደለም፡፡ ደራሲው በገፅ 50-57 ላይ የሞሪንጋን ምግብ ጠቃሚነት ይገልጻል፡፡ እነኚህ ጥቅሞች ዕፁ ካዘላቸው የምግብ ንጥረ ነገሮች (ፕሮቲኖች፣ አሚኖ አሲዶች፣ ማዕድናት፣ የተለያዩ ቫይታሚኖች) የሚመነጩ ናቸው፡፡ እንደገና ለማስታወስ ያህል፣ የምግብ ይዘቶቹ (ንጥረ ነገሮች) የተጠኑት ሞ. ኦሌይፌራና ሞ. ስቴኖፔታላን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ ሌላው የሽፈራው አገልግሎት የቆሸሸ ውሃን ለማጣራት ነው (ገጽ 79-80)፡፡ ይህ ውሃን የማጥራት ንብረቱ (ሞ. ስቴኖፔታላ) ኢትዮጵያ ውስጥ በተደረገ ጥናት ተረጋግጧል፡፡ ባንጻሩም በደፈረሰ ውሃ ውስጥ የሚገኙ ጥቃቅን ተህዋስያን (ባክቴሪያ) መጠን ይቀንሳል፡፡ ደራሲው በጥናት ጽሑፎች ማሰባሰብ ብቻ ሳይከለል እራሱ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በመዘዋወር መረጃዎችን ሰብስቧል (ገፅ 136147)፡፡ በጣም የሚያስመሰግን ነው፡፡ ይህን ገምጋሚ በጣም የገረመው ነገር ቢኖር፣ 15 የሚሆኑ የንግድ ድርጅቶች ለሃገር ውስጥ ፍጆታና ለውጭ ገበያ ሽፈራውን በማከፋፈል ሥራ ላይ የተሰማሩ መሆናቸው ነው፡፡ ነገር ግን፣ በገበያ ላይ የሞሪንጋ ውጤቶችን ጥራት፣ መጠንና አጠቃቀም ማን እንደሚከታተልና እንደሚቆጣጠር በመጽሐፉ ውስጥ አልተገለጸም፡፡ ደራሲው አዲስ አበባ ውስጥ በርካታ መደብሮች ሞሪንጋ እንደሚሸጡም ዘግቧል፡፡ ማጠቃለያ፤ ይህ ትችታዊ ግምገማ በተወሰኑ የመጽሐፉ ክፍሎች ያተኰረ ቢሆንም፤ ቅጹ ብዙ ጠቃሚ መረጃዎችን የያዘ መሆኑን መግለጽ አስፈላጊ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን፣ በተለይ የተጠቀሱት የመድሃኒትነት ጥቅሞች በጥንቃቄ መታየት ያለባቸው መሆናቸውን በአጽንኦት መግለጽ ተገቢ ይሆናል፡፡ የተወሰኑቱ ጥናቶች በእንስሳት ላይ፣ ወይም በመስታዬት (ኢን ቪትሮ) ሙከራ ላይ ብቻ የተመሰረቱ ናቸው (ኢትዮሚዲያ፤ ኦክቶበር 30፣ 2015 ይመለከቷል)፡፡ ስለዚህም፣ እነኚህ መረጃዎች የመጨረሻና የማያሻሙ ናቸው ብሎ መደምደም አይቻልም፤ ፍንጭ-ሰጪ ናቸው ከማለት ሌላ፡፡ በመጨረሻም፣ ደራሲው ይህን መጽሐፍ በማዘጋጀቱ በትልቁ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ የተበታተኑ መረጃዎችን ከግል ምስክርነት ጋር አጣምሮ በአንድ ጥራዝ ማቅረብ ቀላል ሥራ አይደለምና! ይህ ገምጋሚ ኢትዮጵያውያን መጽሐፉን በማንበብ ቢያንስ እራሳቸውን ከሞሪንጋ ጋር እንዲያስተዋውቁ ያበረታታል።
Key References
Aberra Melese. Comparative assessment on chemical compositions and feeding values of Moringa stenopetalaand Moringa oleifera using in vitro gas production method. Ethiop J Appl Sci Technol. 2011; 2(2): 31-41.
Abera Lemma. “Shiferaw….Moringa. Te’amregnaw Ets (in Amargna)”; Addis Ababa, Ethiopia: MankusaAsatamie, Inc.; 2014 (2006 Eth Cal).
Anwar F, Latif S, Ashraf, M, et al. Moringa oleifera: A Food Plant with Multiple Medicinal Uses. Phyother Res. 2007; 21: 17-25.
Ashenafi Tadelle, Asfaw Debella. Proceedings of the Consultative Workshop on Moringa stenopetala to maximize its potential use; 22-23 May 2014. Available at:http://www.ephi.govt.et/images/pictures/proceedings%of_morings.pdf (accessed 26 October 2015).
Arora SB, Onsare J. Bioprospecting of Moringa (Moringaceae): Microbiological Perspective. J PharmacogPhytochem. 2013: 2 (2): 31-41.
Bennett RN, Mellon FA, Foidl N, et al. Profiling Glucosinolates and Phenolics in Vegetative and Reproductive Tissues of the Multi-Purpose Trees Moringa oleifera (Horseradish tree) and Moringa stenopetala. J Agric Food Chem. 2003; 51: 3546-3553.
Eyasu Seifu. Actual and Potential Applications of Moringa stenopetala, Underutilized Indigenous Vegetable of Southern Ethiopia: A Review. Int J Agric Food Res. 2014; 3(4): 8-19.
Getachew Addis, Dechasa Jiru, Yalemtsehay Mekonnen, et al. Moringa. [Moringa stenopetala (Bak.f.) Cufod.]. Guide to Use and Processing Practices. Addis Ababa, Ethiopia: HoA-REC&N; 2014.
Iwu MM. Handbook of African Medicinal Plants. Boca Raton, Fl: CRC Press, Inc. 1993, pp 210-210.
Yalemtsehay Mekonnen. The Multi-purpose Moringa tree: Ethiopia; 2003. Available at:http://www.tcdc.undp.org/sie/experiences/vol10/V 10_53_Moringa.pdf (accessed 26 October 2015).
The writer can be reached at FeFuBal@aol.com