Wednesday, 09 March 2016 13:39
በሳምሶን ደሳለኝ
ገዢው ፓርቲ የመልካም አስተዳደር ችግሮ ፈጣሪዎች እና የኪራይ ሰብሳቢዎችን ዋሻ ለማጥራት የጀመረው እንቅስቃሴ በማንኛውም መመዘኛ በበጎ ጎኑ የሚወሰድ ነው። ሥርዓቱን ብልሹ አሠራርን ከሚከተሉ ሌቦችና ምግባረ ብልሹ አመራሮቹን ለመታደግ የተጀመረው ዘመቻ ቀላል እንደማይሆን የሚጠበቅ ብቻ ሳይሆን ሥርዓቱንም አደጋ ውስጥ ሊጥለው የሚችልበት እድልም በዋዛ የሚታይ አይደለም። አሁን ላይ ግን አማራጭ የሌለው በመሆኑ ወደኋላ ለመሄድ የሚታሰብ እርምጃ ካለ አደጋው ከሚፈራው የሚበልጥ ነው የሚሆነው።
ከዚህ በፊት የህዝብን ንብረት ወይም ህዝብ የሚጠብቀውን የመልካም አስተዳደር ፍላጎት ለሟሟላት የሚደረግ ትግል ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑ የሚታወስ ነው። ዛሬ ላይ ግን ገዢው ፓርቲ ህልውናውን የሚታደግበት እንጂ የህዝብን ሃብት ማስመለስ ወይም የመልካም አስተዳደር ዕጦትን የማስፈን እርምጃ ተደርጎ በቀላሉ የሚገለጽ ፖለቲካዊ ትግል አይደለም። የትኛም ፓርቲ ከራሱ ህልውና በላይ ሊያመልከው ወይም ዋጋ ሊከፍልበት የሚችል ጓድ ይኖረዋል ተብሎ አይገመትም። ሆኖም ከተገኘ ፖለቲካ ፓርቲው እንደጅብ ቁስል እራሱን እየበላ ለመጨረስ የመረጠ መሆን አለበት። በርግጥ ምርጫው የፖለቲካ ፓርቲዎች እና አባሎቻቸው እንደሆነ አከራካሪ አይደለም።
የመልካም አስተዳደር ችግሮ ፈጣሪዎች እና የኪራይ ሰብሳቢዎችን ዋሻ ማጥራት በበጎነቱ የሚታይ ቢሆንም አሁን እየተወሰደ ባለው ጅምር እርምጃ ላይ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ሙሉ ለሙሉ አለ ብሎ ለመውሰድ አዳጋች ነው። ምክንያቱም የተወሰደው አብዛኛው እርምጃ በመካከለኛ አመራሮች እና በባለሙያዎች ላይ ያተኮረ በመሆኑ ነው። ከአንዳንድ የገዢው ፓርቲ አባሎች እየሰማነው ያለው ነገር፣ መካከለኛ አመራሮች ለፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች እና ሥራ አስፈፃሚዎች የጦስ ዶሮ እየሆኑ ነው የሚል ነው። ቅሬታው የተወሰነ መልዕክት ያለው ቢሆንም ሙሉ መልዕክት የሚኖረው፣ የበላይ፣ የበታች አመራር የሚል ይዘት የሌለው ሥርዓቱን መታደግ ብቻ መመዘኛ ያደረገ ዘመቻ መከናወን አለበት የሚል መርህ ሲነሳ ወይም ሲቀመጥ ነው።
ለአብነት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በትግራይ ክልል፣ በአማራ ክልል ባለፉት አንድ ወራት ጊዜ ውስጥ የተደረጉትን የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ ዘመቻዎችን ስንመለከት የሚሰጠን ስዕል አለ። ይህ ስዕል የንቅናቄው ዘመቻ ተገቢነቱን ከውጤት ጋር አያይዞ የሚያመላክት ቢሆንም የአስተዳደር ሰንሰለቶችን ሙሉ ለሙሉ የቃኘ አይደለም። በተለይ በከፍተኛ ደረጃ በፈፃሚነት ላይ የተቀመጡ ጉምቱ የሥርዓቱ ኃላፊዎችን የዳሰሰ አይደለም። ወይም በቀላል ቋንቋ የአንድ ዛፍ ግንድን ቅርጫፎች መመልመል ነው የሚመስለው። በሳይንሱ ቅርንጫፎች ሲገረዙ ተመልሰው ይበቅላሉ። ጥሩ አትክልተኛ ግን ሲኖር አለቦታቸው የበቀሉ ዛፎችን ከስራቸው እየነቀለ ለቦታው ተስማሚ የሆኑ ዛፎችን ይተክልባቸዋል። ለማንኛውም ከሰሞኑ ወደ ተደረጉት ዘመቻዎች ናሙና እንግባ።
አዲስ አበባ
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተደረገው የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ የተገኙት ውጤቶች ይህን ይመስላሉ። ይኽውም፣ በአዲስ አበባ ባለፉት 6 ወራት መሬት ነክ በሆኑ ጉዳዮች የመልካም አስተዳደር ችግር በፈጠሩ 119 ባለሙያ እና በ30 አመራሮች ላይ እርምጃ መወሰዱን የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ማስታወቁ ይታወሳል። የዚህ እርምጃ ጠንካራ ጎን እንደቀድሞው “ተሽከርካሪ የሙስና ወንበር” ላይ ከመዳጥ አጥፊዎቹ በሕግ መጠየቅ፣ ከሥራ ማገድ እንዲሁም በሥነምግባር ክስ ማየት ያካተተ እርምጃ መወሰዱ ላይ ነው።
ለተወሰደው እርምጃ ሌላው ማረጋገጫ የሶስተኛ ወገን ምስክርነት ማግኘታችን ነው። ይህም ሲባል፣ የፌዴራል የሥነምግባር እና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 85 የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት አስተዳደር ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ይፋ በማድረጉ ነው።
ጠቅላይ የሆነ ጥፋታቸው አስተዳደሩ እንዳስቀመጠው፣ ከ10ሩም ክፍለ ከተሞች በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች የነበራቸውን የመሬት አስተዳደር ኃላፊነት እና የሥራ ድርሻ በመጠቀም የመንግሥት መሬት በሕገወጥ መንገድ ካርታ አዘጋጅቶ በመስጠት ለልማት ጥቅም ሊውሉ የሚችሉ ቦታዎችን በግለሰብ ይዞታ በማካተት እና በፍርድ ቤት እግድ የወጣባቸውን መሬቶች ያልታገዱ አድርጎ መረጃ በመስጠት በመጠርጠራቸው ነው። እንዲሁም ተጠርጣሪዎቹ በሐሰተኛ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ስም ቦታ እንዲይዙ በማድረግና በመሣሠሉት ወንጀሎች መሳተፋቸውን አስተዳደሩ ይፋ አድርጓል።
አስተዳደሩ ይህን ይፋ ማድረጉ ያስከብረዋል። አያይዞም መመለስ ያለባቸው ጥያቄዎችም ግን አሉ። መልስ ከሚሹ ጥያቄዎች መካከል፣ ለእነዚህ አጥፊዎች ከለላ ሰጪው ማን ነበር? ከሕግ ውጪ የሚሰበስቡትን ኪራይ ለብቻቸው ይጠቀሙበት ነበር? ወይንስ የአስተዳደሩ ተቀራማች ቢሮክራሲ ይካፈላቸው ነበር? የመቀሌ የኢህአዴግ ጉባኤ ውሳኔ አስተዳደሩን አጣብቂኝ ውስጥ ባይከተው፣ በራሱ ተነሳሽነት እነዚህ አጥፊዎች አሳልፎ ለሕግ ይሰጣቸው ነበር? የአስተዳደሩ ከፍተኛ ኃላፊዎች ንፅህናቸውን በአደባባይ ለማስመስከር ምን ያህል ዝግጁ ናቸው?
ሌላው እርምጃ ከመወሰዱ ጥቂት ቀናት በፊት፣ የቦሌ ክፍለ ከተማው አቶ ጊዮን ከሀገር ወጥተው ለምን ኮበለሉ? የካናዳ የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት መያዛቸው አይታወቅም ነበር? በየትኛው ሰንሰለት ውስጥ ተሳታፊ ነበሩ?
ትግራይ
በትግራይ ክልል የተደረገው የመልካም አስተዳደር የንቅናቄ መድረኮች በሥራ አስፈፃሚዎች በኩል ብዙም ለውጥ የሚጠበቅ አልነበረም። ለዚህም ዋናው ምክንያት ሕወሓት መቀሌ ላይ ባደረገው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ በቁጥር በዛ ያሉ ከፍተኛ አመራሮችን ከኃላፊነታቸው በማንሳቱ ነው። ሆኖም አቶ አባይ ወልዱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ለክልሉ ምክር ቤት የስድሰት ወር ሪፖርት ሰሞኑን ባቀረቡበት ወቅት እንዳስቀመጡት በክልሉ የመልካም አስተዳደር ችግር በፈጠሩ 398 አመራሮች በሕግ እንዲጠየቁ ተወስኗል።
ህወሓት በክልሉ ውስጥ ካለው መልካም አስተዳደር አንፃር ብቻ የመልካም አስተዳደር ንቅናቄውን ከሚቃኘው እንዳንድ የፓርቲው ካድሬዎች ዋጋ በተከፈለበት መስመር ውስጥ መኖራቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል። ህወሓት ለሥርዓቱ የከፈለውን ምትክ አልባ ዋጋ ለራሳቸው ብልጽግና የሚያውሉ አንዳንድ ካድሬዎችን በንቃት ሊከታተላቸውና አጥፊ ሆነው ሲገኙም ለፍርድ ሊያቀርባቸው ይገባል። በተለይ ከትግራይ ሕዝብ ዕሴቶች ውጪ የሚንቀሳቀሱ እንዲሁም ህወሓትን ምርኩዝ አድርገው ከሚያምታቱ የከተማ ካድሬዎች፣ ፓርቲው ራሱን መነጠል ይጠበቅበታል።
አማራ ክልል
በአማራ ክልል ም/ቤት የቀረበው ሪፖርት የመልካም አስተዳደር ችግር በፈጠሩ አካላት ላይ እርምጃ መውሰዱን የሚገልጹ ናቸው። ይኽውም፣ በፍትህና ፀጥታ አካላት ላይ ከተወሰዱት መካከል 50 አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ፣ 2 የዞን መምሪያ ኃላፊዎች እንዲታሠሩ፣ 6 አመራሮች በሕግ እንዲጠየቁ ውሳኔ ተላልፏል። በኅብረተሰቡ አመኔታ የሌላቸው በቂ ማስረጃ በሌላቸው የፍትህ አካላት ላይ ደግሞ ከቦታ ቦታ እንዲዛወሩ ተደርጓል።
በአስተዳደርና የፀጥታ ጉዳዮች መዋቅሮች በኩል ከፖሊስ አካላት መካከል፤ 16 ወደ ሌላ ቦታ ተዛውረዋል፣ 18 ከሥራ ታግደዋል፣ 113 ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፣ 15 ለዲስፒሊን እንዲቀርቡ አድርጓል። እንዲሁም፣ 232 ከሥራ ተሰናብተዋል፣ 121 ትጥቅ አውርደዋል፣ 27 ከኃላፊነታቸው እንዲወርዱ ተደርጓል። በሌሎች ብሔረሰብ አስተዳደር ሕገመንግሥቱን በኃይል ለመናድ በሞከሩ 76 ሰዎች ላይ ክስ መስርተዋል። በመንገድ ትራንስፖርት ዘርፍ የሥነምግባር ችግር በታየባቸው 35 ሙያተኞች ላይ እርምጃ መውሰዳቸውንም አያይዘው ገልጸዋል።
በአማራ ክልል የተደረገው የመልካም አስተዳደር መድረክ ንቅናቄ በጥልቀትም በስፋትም ጥሩ የሚባል ነው። ሆኖም ግን የመልካም አስተዳደር ጥያቄው በይፋ ያላወጣው ለዝግጅት ክፍላችን በችግርነት የሚደርሱን በወንዜነት የመተዛዘል ጉዳይ ነው። ይህም ሲባል ምስራቅ እንትን፣ ደቡብ እንትን፣ ሰሜን እንትን፣ ምዕራብ እንትን እየተባለ የተዘረጉ የቢሮክራሲ ሰንሰለቶች መበጠስ እና መፐወዝ አለባቸው። በሁሉም የአማራ ክፍል ተመጣጣይ የሆነ የእድገት ሥራዎች መከናወን አለባቸው። በተለይ የአማራ ቆላ ቦታዎች ብዙ የተደረጉ ጥረቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ አሁንም በመልካም አስተዳደር ንቅናቄ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
ኦሮሚያ
የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ማዕከላዊ ኮሚቴ የካቲት 25 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ቀናት በአዳማ ከተማ ባካሄደው ጉባኤ ሁለት የፓርቲውን ከፍተኛ አመራሮች ማንሳቱን አስታውቋል። ሁለቱም ከፍተኛ አመራሮች የኦሕዴድ እና የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚዎች ናቸው። እስካሁን በተደረገው የመልካም አስተዳደር ንቅናቄ መድረክ በሥራ አስፈፃሚ ደረጃ የተነሱ ከፍተኛ የፓርቲ አመራሮች ናቸው።
የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት በሰጠው መግለጫ የስራ ኃላፊዎቹ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረገው በአመራር ችግር ነው ይላል። የኦህዴድ እና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባል እንዲሁም የኦህዴድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ዳባ ደበሌ ከተነሱት አንዱ ናቸው። አቶ ዳባ በታየባቸው የአመራር ችግር ምክንያት ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ እንዲሁም ከኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባልነት ተነስተዋል። ሆኖም ግን የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው እንዲቀጥሉ መወሰኑን መግለጫው ያትታል።
ሌላው የኦህዴድ እና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባል እና የኦሮሚያ ክልል የእርሻ እና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ጀማነህ መነሳታቸውን በመግለጫው ተገልጻል። መግለጫው አያይዞም፣ አቶ ዘላለም እስከ ቀጣዩ የድርጀቱ ጉባኤ ድረስ ከማንኛውም የድርጅት እንቅስቃሴ መታገዳቸውን የድርጅቱ ውሳኔ ያሳያል። ሆኖም ግን በሁለቱ ከፍተኛ አመራሮች መካከል ያለውን የጥፋተኝነት ደረጃ አያብራራም። አንዱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ሆኖ ሲቀጥል ሌላው ከፖለቲካ እንቅስቃሴ ይታገዳል። ለምን? ማብራሪያ የለም።
ማዕከላዊ ኮሚቴው በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠሩ ሁከቶች የሰው ህይወት ማለፉን እና ንብረት መውደሙን የተመለከተ ሲሆን፥ ለደረሰው የሰው ህይወት መጥፋት እና ንብረት ውድመት የተሰማውን ሀዘን ከመግለጽ ውጪ ተጠያቂ አካል አላስቀመጠም። ለተጎዱ ወገኖችም የታሰበ ነገር እንዳለ የተገለጸ ነገር የለም። በድፍኑ ብቻ የክልሉ ነዋሪ ከጸጥታ ሀይሎች ጎን በመቆም ክልሉ ወደ ነበረበት ሰላም እና መረጋጋት እንዲመለስ ላደረገው አስተወጽኦም ኦህዴድ አድናቆት እና ምስጋናውን አስተላልፏል ይላል መግለጫው።
ማዕከላዊ ኮሚቴው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋትን የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም በመግለጫው ከገለጸ በኋላ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ፈጥረዋል ተብለው በተያዙ እና ኪራይ ሰብሳቢዎች ላይም የክልሉ መንግስት ምህረት የለሽ እርምጃን እንደሚወስድም ማስገንዘቡን ያሰፍራል። የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ እየተሰራ ባለው ስራ ላይም ህብረተሰቡ ከመንግስት ጎን በመሆን ትብበር እንዲያደርግም ማዕከላዊ ኮሚቴው ጥሪው አቅርቧል።
በማዕከላዊ ኮሚቴው መግለጫ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ። በተለይ በክልሉ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን እና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋትም ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ በመሆን እንደሚሰራ ከማስታወቁ ጋር የሚያያዙ ናቸው። ምክንያቱም አሁን በማዕከላዊ ኮሚቴው የተወሰዱ እርምጃዎች ሥር ነቀል ባለመሆናቸው ነው። እርምጃው ሰንሰለት ለመበጠስ ያለመ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም፣ ሰንሰለቱን ሙሉ ለሙሉ መበጠስ አለመቻሉ ነው። ሰንሰለቱ ሙሉ ለሙሉ ሳይበጠስ ሙሉ ድጋፍ ከሕብረተሰቡ ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ ነው። ይህ ማለት ግን አሁን በማዕከላዊ ኮሚቴው የተወሰደው እርምጃ ትንሽ ነው ማለት ግን አይደለም።
ስንደቅ