Wednesday, 09 March 2016 13:39
“ኢትዮጵያዊያን ምሁራን. . . በአገር ቤት ያለነው የምንገኘው ማዕድ ቤታችን ውስጥ ሲሆን የተቀረው ተሰዷል”
ዶ/ር ፍሰሐ አስፋው
በይርጋ አበበ
በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ የስነ ማህበረሰብ ጥናት(Sociological science)የሶስተኛ ድግሪ ባለቤት ሲሆኑ በሙያቸውም አገራቸውን ከ40ዓመታት በላይ አገልግለዋል።የቀድሞው መንግስት ስርዓት የብሔረሰቦችን ማንነት በሚያጠናው“የብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት” ተዋቅረው የኢትዮጵያን ብሔረሰቦች ብዛት ማንነትና ምንነት በሚገልጸው የጥናት ቡድን ውስጥ ተሳትፈዋል። በቅርቡም ያንን የጥናት ውጤት በመጽሀፍ መልክ አዘጋጅተው ለንባብ አብቅተዋል።እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሙያቸው አዲስአበባ ዩኒቨርስሲቲ ያስተምሩ የቆዩት ዶክተር ፍሰሃ አስፋው ስለመጽሃፋቸው ስለቀድሞው የብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት ስለወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች እና ሌሎች ተያያዥ ነጥቦችን በማንሳት ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ሰፋ ያለ ቆይታ አድርገዋል። የቃለምልልሱን ሙሉ ክፍል ከዚህ በታች አቅርበነዋል።
ሰንደቅ፡- በሙያዎ የሶሾሎጂ ምሁር ቢሆኑም በቀድሞው መንግስት ተቋቁሞ በነበረው የብሔረሰቦች ጥናት ኢንስትትዩት ውስጥ ተሳትፈዋል። እንዴት ሊሳተፉ ቻሉ?
ዶክተር ፍሰሀ፡- እንዳልከው ትምህርቴ ሶሾሎጂ ነው፤ አዲስአበባ ዩኒቨርስቲ ነበር የማስተምረውም። በዚያን በነበረው መንግስት (የኢትዮጵያ ህዝባዊ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ) ምሁራን ለጥናቱ ይፈለጋሉ ብሎ ከየተቋሙ ሲመርጥ አንዱ ሆኜ ተመረጥኩ።በተማርኩበት የሶሾሎጂ ሙያ ላይ ተመድቤ በማህበራዊ ዘርፍ ነው የተሳተፍኩት።ይህን እድል በማግኘቴም እድለኛ ነኝ ብዬ ነው የማስበው። ምክንያቱም ኢትዮጵያን ዳር ድንበሯን በመዘዋወሬ ብሔረሰቧ መልክዓ ምድሯ እና ባህሏ ምን እንደሚመስል ማየት ችያለሁ።
ሰንደቅ፡- በወቅቱ በተጠናው የብሔረሰቦች ጥናት ውጤት ላይ ተመርኩዘው በቅርቡ መጽሀፉን አሳትመው ለገበያ አቅርበውታል። የጥናቱ ውጤት በህትመት ሳይወጣ መዘግየቱ ይታወቃልና በዚህ ወቅት ጥናቱን ለማሳተም ምን አነሳሳዎት?
ዶክተር ፍሰሀ፡- አሁን ከአዲስአበባ ዩኒቨርስቲ አስተማሪነት ወጥቼ በግሌ የምርምር እና የጥናት ስራዎችን እየሰራሁ ነው ያለሁት። ከምሰራቸው የጥናትና የምርምር ስራዎች አንዱ ደግሞ ይህ የብሔረሰቦች ጥናት መግለጫ የሚለው መጽሀፍ ነው። መጽሀፉን በዚህ ወቅት ለምን ለማሳተም ፈለጉ ላልከው ያ ጥናት ከፍተኛ ድካምና ጊዜ እንዲሁም ገንዘብ ወጥቶበት የተጠና ጥናት ነው። ግን ለምን ህዝብ እንዲያውቀው አይደረግም? የሚል ቁጭት ነበረኝ። ጥናቱን ካካሄዱት ጓደኞቼ መካከል አንዳንዶቹ በሞት ሲለዩ ቀሪዎቹ ከአገር ሲወጡ እና ሌሎቹም በተለያዩ የኑሮ ጉዳዮች ሲወጠሩ እኔ ታዲያ ለምን ይህንን ስራ ሰርቼ ለወጣቱ እንዲያውቀው አላደርግም ብዬ ነው የተነሳሁት።
ጥናቱ የተጠናው ከ30 ዓመታት በፊት ቢሆንም የጥናት ኢንስቲትዩቱ ስራውን 3/4ኛ እንዳከናወነ የመንግስት ለውጥ ተፈጠረና ባለሙያዎቹ (ጥናቱን ያካሄዱት) ተበታተኑ።በዚህ ምክንያትም ጥናቱ እዚያው ተዳፍኖ ቀረ። ህትመቱ የዘገየውም በዚህ ምክንያትም ነው።
ይህንን መጽሀፍ ለማዘጋጀት በጣም ቀላል ይሆን ነበር። ምክንያቱም በሰነድ በሰነድ ተጠርዞ የተዘጋጀ ነበር። ነገርግን ኢንስቲትዩቱ በመንግስት ለውጥ ምክንያት በሚፈርስበትና እኛ በምንለቅበት (የኢንስቲትዩቱ የጥናት ቡድን አባላትን) ጊዜ እኔ በግሌ መረጃው አልነበረኝም።ስለዚህ በቂ መረጃ አልነበረኝም። ካሰብኩ ከአምስት ዓመታት በላይ ቢሆነኝም በቁንጽሉ ማውጣት አልፈለኩም። ምክንያቱም እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች አሰፋፈር፣ማንነትና ምንነት በጣም ውስብስብ ስለሆነበ ጥንቃቄ መሰራት ያለበት መሆኑን አውቃለሁ። ያንን ጥንቃቄ ለመጠበቅ ስልነው የዘገየሁት።
ሰንደቅ፡- ለዘውዳዊው መንግስት መውደቅ ዋና ዋና ምክንያት ከነበሩት መካከል የብሔረሰብ ጥያቄ እና የመሬት ባለቤትነት የሚሉት ይገኙበታል። በወቅቱ ንጉሱን ተክቶ ስልጣኑን የተረከበው ወታደራዊው መንግስት የመሬት ጥያቄን መመለስ ችሎ ነበር። የብሔረሰቦችን የእኩልነት ጥያቄ እንዴት ነበር መፍታት የቻለው?
ዶክተር ፍሰሀ፡- የደርግ መንግስት የብሔረሰቦችን የእኩልነት ጥያቄ በደንብ ፈትቷል ለማለት የተጠናው ጥናት በስራ ላይ አልዋለም።ነገር ግን ጅምሩ ምን ነበር ያልን እንደሆን መሬት ላራሹ ለሚለው ጥያቄ ደርግ የወሰደው መፍትሔ ብዙ መሬት የያዙትን መሬታቸውን ቀምቶ ለሌለው ለማካፈል አዋጅ አውጥቶ በአዋጅ ተግባራዊ እንዲሆን አደረገ። በዚህ ጊዜ ግን ደርግ የተሳሳተውና በኋላም የገባው በርካቶች በጥረታቸው ሀብት ንብረት ያፈሩትንም የወረሰበትና የከተማ መሬት የቀማበት ስራው ነበር።
በብሔረሰብ ጥያቄ ለመመለስም ተመሳሳዩ ስህተት እንዳይደገም ደርግ ያደረገው ምንድን ነው ያልክ እንደሆን ጉዳዩ በጥንቃቄ እንዲጠና ተደረገ።ለመመለስ የታሰበው አንድ ብሔረሰብ ራሱን ማስተዳደር ይችላል ወይ በዚያ ብሔረሰብ ውስጥ ሌሎች ብሔረሰቦች አሉ ወይም የሉም ወይ የሚል መመዘኛ ወጥቶ ለትመሰራት ተጀመረ። ለዚህ ሀሳብ አንድምሳሌ ልስጥህ፤ ለምሳሌ አፋር ራሱን የቻለ አንድ ብሔረሰብ ነው ሌላ ድብልቅ ብሔረሰብ የለበትም። ማለቴ ቋንቋው፣ ሀይማኖቱ እና ባህሉ አንድ ነው። የአፋርን የብሔረሰብ ጥያቄ ለመፍታት የወሰድነው እርምጃ “የአፋር ራስ ገዝ አስተዳደር” በሚል ነበር።
ነገርግን ወደ ሌሎች ክልሎች ለምሳሌ አማራ ክልል ስትመጣ፤ የአማራ ብሔረሰብ ያለበትን ሁሉ ወደ አንድ አምጥቶ አንድ ለማድረግ በጣም ፈታኝ ነው።ምክንያቱም በአማራ ብሔረሰብ ውስጥ ጎንደርን ወስደህ ከሸዋ ጋር አንድ ሁን ብትለው ለአስተዳደር አይመችም።ስለዚህ የተደረገው ምንድንነው የአስተዳደር አመቺነትን በማየት ተካለለ።
ሌላው ደግሞ የፖለቲካ ችግር ያለባቸው ብሔረሰቦች ነበሩ። ለምሳሌ የትግራይ ብሔረሰብ (ኤርትራ እና ትግራ ይክልል) ፖለቲካዊ መፍትሔው ምንድንነው ብለን ስንወያይ የኤርትራ ራስገዝ እና የትግራይ ራስገዝ በሚል እንዲካለሉ ተደረገ። በአጠቃላይ የብሔረሰብ ጥያቄን ለመፍታት የብሔረሰብ ጥናት ኢንስቲትዩት ያካሄደው ጥረት ይህን ይመስል ነበር። እዚህ ላይ ግን ሊነሳ የሚገባው ትልቁ ነጥብ እነዚህ ብሔረሰቦች እርስ በእርሳቸው የሚያስተሳስራቸውን እንጂ ልዩነታቸውን የሚያጎላ አልነበረም። የሌለልዩነትም ለመፍጠር አልተሰራም ነበር።
ሰንደቅ፡- የጥናት ኢንስቲትዩቱ የተዋቀረው ከማንኛውም ፖለቲካዊ ተጽእኖ ነጻ በሆነ መልኩ እንደሆነ መጽሐፍዎ ላይ ገልጸዋል። ሆኖም ለስራችሁ መቀላጠፍ ልምድ ስትቀስሙ የነበረው ከሶሻሊስት አገሮች እንጂ ከካፒታሊስት አገሮች አልነበረም። በወቅቱ ኢትዮጵያን ያስተዳድር የነበረው የደርግ ስርዓትም የሶሻሊስት ሥርዓት እንደመከተሉ የእናንተ በተደጋጋሚ ወደሶሻሊስት አገር መሄዳችሁ አንዱ ተጽእኖ ነው ሊባል አይችልም?
ዶክተር ፍሰሀ፡- እኛ ለመፍታት የሞከርነው የብሔረሰቦችን ችግር ነው። ልምዳቸውን ለመካፈል የመረጥናቸው አገሮችም የብሔረሰብ ችግር ኖሮባቸው የፈቱትን አገሮች ነው። የምዕራባዊያኑ አገሮች የብሔረሰብ ችግር የለባቸውም። በብሔረሰብ ችግር ምክንያት የተጋጨ አገር የለም። ስለዚህ ከእነዚያ አገሮች የምናገኘው ልምድ የለም። ከምዕራባዊያኑ አገሮች የብሔረሰብ ጥያቄ የነበረባቸው ስዊዞች ብቻ ነበሩ። እነሱ ደግሞ ችግራቸውን የፈቱት “የጀርመኑ ስዊዝ ጀርመንኛ እንዲናገር የፈረንሳዩ ፈረንሳይኛ የጣሊያኑ ደግሞ ጣሊያንኛ እንዲናገር” በማለት ነበር። ያ ደግሞ ለእኛ ጥያቄ የሚሆን አልነበረም። ምክንያቱም የመልክ ዓምድራዊ አቀማመጥም ሆነ የኢኮኖሚ እድገታችን አመቺ አልነበረም።
ስለዚህ ትኩረታችንን ወደ ሶሻሊስት አገሮች እንዲሆን አደረግን። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው የሶሻሊስት አገሮችን ልም ድለመቅሰም የመረጥነው በአይዲዮሎጂ ተመሳሳይነት ሳይሆን መሬት ላይ ባለው ልምዳቸው (Actual practice) ነው።
ሰንደቅ፡- የእንግሊዝ መንግስት የኤርትራን ሁኔታ ለማወቅ የብሔረሰብ ጥናት አካሂዶ ነበር። ለምን ያንን እንደማጣቀሻ(reference) ለመጠቀም አልፈለጋችሁም?
ዶክተር ፍሰሀ፡- እንግሊዞች ያካሄዱት በተንኮል ላይ የተመሰረተ የራሳቸውን የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው። ምክንያቱም ህዝቡን አላሳተፉም እኛ አጥንተንልሃል፣ ይህን ተቀበል ነው ያሉት።
ወደ እኛ ጥናት ስትመጣ ግን በጥናት ቡድኑ ውስጥ ኤርትራዊያን ባለሙያዎች አሉ።እነዚያ የኤርትራ ተወላጅ ባለሙያዎች ስለኤርትራ ጥያቄ በሚነሳበት ጊዜ የጉዳዩ ቀጥተኛ ባለቤት የሆነው ኤርትራዊ ተወላጅ የሚያቀርባቸው ግብዓቶች አሉ። ከእንግሊዝ በተጨማሪም እኮ ጣሊያንም አጥንቶ ነበር። አሁንም በእኛ ላይ መርዝ ሆኖ የቆየን እንግሊዞች ጥናቱን ሲያካሂዱ መከፋፈልን ፈጥረው ጥለውት የሄዱት መርዝ ነው። የእንግሊዝን ጥናት አይተነው የተውነውም ለዚህነው። ጣሊያን ያጠናው ለአገዛዝ እንዲመቸው በአምስት ከፋፍሎ ነበር ያጠናው። የጣሊያንንም ያልወሰድነው በዚህ ምክንያት ነው።
ሰንደቅ፡- ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ከጥናት ኢንስቲትዩቱ ቡድን ጋር አብረው መስራት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል ይባላል። ምክንያታቸው ምን ነበር?
ዶክተር ፍሰሀ፡- ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ይህ የጥናት ኢንስቲትዩት ሲቋቋም ከተጠሩት ምሁራን አንዱ ነው። ከፍተኛ የጂኦግራፊ ምሁር ነው።ኢንስቲትዩቱን ተቀላቅሎ እንዲሰራ መንግስቱ ኃይለማሪያም ሲጠይቀው የመለሰለት መልስ “ሂድ ከዚህ እኔ ካንተጋር አልሰራም ወይም እሺ ጌታዬ አብሬ እሰራለሁ” አይደለም ያለው። መስፍን በወቅቱ የሰጠው መልስ “እኔ ልምከርህ የኢትዮጵያ ጥያቄ የብሔረሰብ ጥያቄ ሳይሆን የኢኮኖሚ ጥያቄ ነው። ለምን መጀመሪያ የኢኮኖሚ ኢንስቲትዩት አቋቁመህ በኢኮኖሚ ኢንስቲትዩቱ አታራምደውም አገሪቱ ትደግ” በማለት ነው የመለሰለት። ነገርግን የብሔረሰብ ጥናት ኢንስቲትዩት እንዲቋቋም በመወሰኑ ሀሳቡን ባለመቀበሉ ከኢንስቲትዩቱ ውስጥ ሳይገባ ቀረ።
ሰንደቅ፡- በብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት “የኢኮኖሚ እና መልክዓ ምድራዊ” ዘርፍ ውስጥ ሆነው ጥናቱን ካካሄዱት ምሁራን መካከል ፍሰሃ ጮሌ በ1968 ዓ.ም ተቋቁሞ በነበረው “የህዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤት” በሊቀመንበርነት እንዲመሩ የተመረጡ ቢሆንም ጽ/ቤቱን ለቀው መውጣታቸውን ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ እና ሌተናል ኮሎኔል ፍሰሀ ደስታ በመጽሀፎቻቸው ገልጸው ነበር። ዶክተር እሸቱ ጮሌ ከእናንተ ጋር ምን ያህል ጊዜ ነው የቆዩት?
ዶክተር ፍሰሀ፡- ዶክተር እሸቱ ጮሌ በጣም ሀቀኛ የሆነ እና ከራሱ ፍላጎት ይልቅ ለመርህ ፍላጎት ቅድሚያ የሚሰጥ ሰው ነው። በሙያውም እጅግ የተከበረ የኢኮኖሚክስ ምሁር ነው። በኢንስቲትዩቱ ውስጥ የኢኮኖሚ እና መልክዓ ምድራዊ ዘርፍ መሪ ሳይሆን በአባልነቱ ባደረገው ተሳትፎ ራሱን አንቱ ያሰኘ ጠንካራ ምሁር ነበር። ከእኛ ጋርም ኢህአዴግ መጥቶ ኢንስቲትዩቱን እስኪያፈርሰው ድረስ እስከመጨረሻው ተጉዟል። በኋላም የሚኒስትርነት ማዕረግ ይሰጥህ ሲባል እኔ አስተማሪ ስለሆንኩ የምፈልገው ወደአስተማሪነቴ መመለስ ነው የምፈልገው በማለቱ ወደዩኒቨርስቲ ሂዶ እንግሊዝ አገር ሰርቶ በመጨረሻም ዓለምአቀፍ ተቋማት ውስጥ ሰርቶ አገሩን ያስከበረ ምሁር ነው።
ሰንደቅ፡- በጥናት ኢንስቲትዩቱ ውስጥ ዶክተር ፋሲል ናሆም ተሳታፊ ነበሩ። የጥናት ኢንስቲትዩቱ አንዱ ተልዕኮም የአገሪቱን ህገመንግስት የማርቀቅ ስራ መስራት በመሆኑ ዶክተር ፋሲል ናሆምም ከህገመንግስት አርቃቂ ኮሚቴ ውስጥ ሆነው ያረቀቁ ቢሆንም በአሁኑ መንግስት ውስጥ እንደገና በሙያቸው እንዲሰሩ ሲጠየቁ ፈቃደኛ ሆነው የህገመንግስት አርቃቂ ኮሚቴ ውስጥ ተሳትፈዋል። በዚህ ተሳትፏቸውም ስለቀድሞው ህገመንግስት የተናገሩት ነገር አለ ይባላል። ምንድን ነው የተናገሩት?
ዶክተር ፍሰሀ፡- እኔ ስለዶክተር ፋሲል የማውቀው በየኒቨርስቲ ቆይታው ጥሩ የህግ መምህር እንደነበረ ነው። ዲሰርቴሽኑን(ለማስትሬት እና ለሶስተኛ ዲግሪ መመረቂያ የሚዘጋጅ ጽሁፍ) የሰራውም በኢትዮጵያ ህገመንግስት ላይ ነው።በዚህ ምክንያትም ከአጥኚው ቡድን እንዲካተት ተደርጓል።
በጥናት ኢንስቲትዩቱ ውስጥ ቅድም እንደነገርኩህ የሀሳብ ልዩነቶች ነበሩ። ለምሳሌ ህገመንግስቱን በተመለከተ ኮሌክቲቭ ሊደርሺፕ ይሁን ሲል ሌላው ይህ ስርዓት ሶሻሊስት ስለሆነ ኮሌክቲቭ ሊደርሺፕ አይሆንም ብሎ ይከራከራል።ሌላው ደግሞ እኛ ይህ ስርዓት ምንአገባን የምንሰራው ዘለቄታዊ የሆነ ህገመንግስት ነው የሚል ሁሉ ክርክር ነበር። በዚህ ወቅት ዶክተር ፋሲል “ምንቸገራችሁ አሁን ባለው የመንግስት ሁኔታ እንቅረጸው” ሲል ተናግሮ ነበር። ይህ ማለት ከኮሌክቲቭ ሊደርሺፕ ይልቅ የአንድ ሰው አመራርነትን በሚደግፍ መልኩ ማለት ነው። በዚህጊዜ ብዙዎች ቁጣቸውን አሰምተው ነበር። እንዲያውም አንዳንዶቹ ዶክተር ፋሲልን እስከ መዝለፍም የደረሱ ነበሩ።
ጥናት ኢንስቲትዩቱ ውስጥ እስከመጨረሻው ጊዜ ድረስ የገፋበት ሰው በኋላም ደግሞ በስራቸው ተመስግነው የሚንስትርነት ማዕረግ ይሰጣችሁ ተብለው ከተጠየቁት መካከል አንዱ እርሱ ነበር። ሌሎቹ የሚንስትርነት ማዕረጉን ሳይቀበሉ ሲቀሩ ዶክተር ፋሲል ግን ጥያቄው ተቀብሎ የፕሬዚዳንቱ የህግ አማካሪ ሆኖ ሰርቷል። ኢህአዴግ ከመጣ በኋላም እዚያው ነው ያለው። (ዶክተር ፋሲል ናሆም በአሁኑ ወቅት የጠላይሚኒስትሩ የህግ አማካሪ ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ)
የአሁኑ ህገመንግስት በሚረቀቅበት ጊዜ “ያለፈው ህገመንግስት እና ይህ የአሁኑ ህገመንግስት በምንም መልኩ ሊነጻጸሩ አይችሉም። ይህ ህዝባዊ ነው” ሲል አስተያየት ሰጠ ሲባል ሰምቻለሁ። ለእሱ ካለኝ የትምህርት እና ከዛኛው ህገመንግስት ቀረጻ ባለው ድካም ጋር ሳየው አሁን የተናገረው በፍጹም የማይመጣጠን ሆኖ ነው ያገኘሁት።
ሰንደቅ፡- የብሔረሰቦች ኢንስቲትዩት በህገመንግስት ማርቀቅ ስራ መሳተፉን ነግረውናል። ህግመንግስት ስታረቁ መካተት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎችና መስፈርቶች ናቸው ብላችሁ የተወያያችሁባቸው ነጥቦች ምንድን ናቸው?
ዶክተር ፍሰሀ፡- ህገመንግስት ስትቀርጽ ከመሬት ተነስተህ “እኛ ወይም እኔ” ብለህ የምትሰራው ነገር አይደለም። ብዙ ግብዓቶች አሉ።አንድ መሰረታዊ የሆነ ህገመንግስት ሲቀረጽ በህዝቡ ስነልቦናዊ አመለካከት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። ብሔረሰቦችን በምታጠናበት ጊዜ ቋንቋው፣ ባህሉ፣ ቁጥሩ፣ አካባቢው፣ ልምዱ፣ ማህበራዊ እና ኢኖሚያዊ ሁኔታዎችታጠናለህ። ይህንን ካደረግህ በኋላ ህገመንግስት ትቀርጻለህ። እነዚህን ካጠናህ በኋላ ህገመንግስት በምትቀርጽበት ጊዜ ያህገመንግስት በአገሪቱ ህዝቦች ባህል፣ቋንቋ እና ኢኮኖሚ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት።
ብዙ ጊዜ የምንሳሳተው የሌሎችን ገልብጠን በማምጣት በቀጥታ ለመተርጎም በመሞከራችን ነው። ያለፈው ወጣት ትልቁ ስህተቱ “ሶሻሊዝምን አንብቦ ሶሻሊዝምን ኢትዮጵያ ውስጥ ለመተግበር መሞከሩ ነው”። ስለዚህ ያእንዳይሆን ህገመንግስቱን ስንቀረጽ እነዚህን ሁሉ መሰረታዊ ነጥቦች አድርገናል። ከዚህ በኋላ ህዝቡ እንዲወያይበት ወደህዝቡ ተመርቶ በትውይይትና ትችት ተካሂዶበት ነበር የጸደቀው።
ሰንደቅ፡- የጥናት ኢንስቲትዩቱ ዓላማው ሳያሳካ መበተኑን በመጽሐፍዎ ገልጸዋል።ከፖለቲካ ተጽእኖ ነጻ ከነበረ በአሁኑ መንግስት ምክንያት እንዲፈርስ መደረጉ ለምን አስፈለገ?
ዶክተር ፍሰሀ፡- በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አንዱ ትልቁ ችግራችን ከዘውዱ ጀምሮ ማለቴ ነው አንዱ ንጉስ ተነስቶ ሌላውን ንጉስ በሚማርክበት ጊዜ የተማረከው የሰራውን ማጥፋት ወይም ራሱ የሰራው አድርጎ ለስራው እውቅና (ክሬዲት) በመቀማት ማቅረብ ነው።ደርግ ለምሳሌ ንጉሱ የሰሩትን ብዙዎችን አጥፍቷል። በኢህአዴግ የተፈጸመውም ተመሳሳዩ ነው። ደርግ በመንግስትነቱ ያቋቁመው እንጂ ይህ የብሔረሰብ ጥናት ኢንስቲትዩት ግን የደርግ አልነበረም። የጥናት ኢንስቲትዩቱ በአዋጅ ሲቋቋም አንድም የፓርቲአባል የሆነ ወይም የመንግስት ካድሬ ጫናእ ንዳይፈጥርበት ከለላ ተሰጥቶት የተሰራ ስራ ነው።ይህ ስራ የተሰራው በኢትዮጵያ ልጆች እንጂ በካድሬ አልነበረም የተሰራው።በኢትዮጵያ ምሁራን የተቋቋመው ያኢንስቲትዩት መቀጠል ሲገባው አልቀጠለም። መፍረሱ ለአገሪቱ ውድመት(Disaster) ነው።ምናልባት ኢህአዴግ ከጦር ሜዳ የመጣ በመሆኑ የአስተዳደር ልምድ አልነበረውም፤ ብዙም ችግር ስላለ ሳይረዳው የፈረሰ ይመስለኛል። ምናልባት አሁን ቢጠየቁ (ኢህአዴጎችን) መፍረስ እንዳልነበረበት ይናገራሉ ባይ ነኝ።
ሰንደቅ፡- የአሁኑ የኢትዮጵያ ህገመንግስት ከግለሰብ መብት ይልቅ ለቡድን መብት ትኩረት የሰጠ ለመሆኑ የህገመንግስቱ መግቢያ ያሳያል። ሆኖም ግን በብሔረሰቦች ማንነትና በክልል አወቃወቀር ምክንያት አሁንም ድረስ የብሔር ጥያቄ እንዳልተፈታ ምልክቶች እየታዩ ነው። ይህ ለምን ሆነ? መፍትሔውስ ምንድንነው ይላሉ?
ዶክተር ፍሰሀ፡- እኔ በዜግነቴ የምመልሰው መልስ ምናልባት ኢህኤዴግ መጀመሪያ ይህንን ሲያቅድ የጊዜውን የፖለቲካ ሁኔታ ለማስተንፈስ እንጂ ረጅም ርቀት ችግሩን አልተገነዘበውም ባይ ነኝ። በወቅቱ (ኢህአዴግ አዲሱን ህገመንግስት ባረቀቀበት ወቅት)ብሔረሰቦች ተነስተው ደስታቸውን ገልጸዋል ጨፍረዋል። ነገርግን እያደር ያንነገር እንዳለው ለመተግበር ሲነሳ አገርን የሚበታትን እና በአገር ላይ ችግር የሚያመጣ መሆኑን ሲረዳ ተግባራዊ ከማድረግ ተቆጠበ።ቃል እንደገባው ቢያደርግ ኖሮ አሁን ኢህአዴግ የሚገዛው አገር ሊኖርም አይችልም ነበር።
እነዛ ቃል የተገባላቸው ደግሞ “የተገባልንቃል የትገባ?” ሲሉ በመጠየቅ ላይ ናቸው።ይህን ችግር በምን ያበርደዋል ለሚለው ራሱን የቻለ ጥናት የሚጠይቅ ነው የሚሆነው። በሰከነ መንፈስ ቁጭ ብሎ ችግሩን አጥንቶ የሚያቀርብ ገለልተኛ የሆነ የህዝብ ድምጽ ያላቸው ለህዝብ ማቅረብ ይሻላል ባይ ነኝ።
ሰንደቅ፡- የአገሪቱን ወቅታዊ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ቀውስ የሚከታተሉ የተለያዩ አስተያየት ሰጪዎች እጣታቸውን ከሚቀስሩባቸው አካላት መካከል የምሁራን ዝምታ በዝቷል እያሉ ነው።ለመሆኑ ምሁራኑ የትገቡ?
ዶክተር ፍሰሀ፡- ኢትዮጵያዊያን ምሁራን የትገቡ የሚለው ጥያቄ ወሳኝ ጥያቄ ነው። በአገር ቤት ያለነው ማድቤታችን ውስጥ ስንሆን ብዙ ቁጥር ያለው የተሰደደው ምሁር ደግሞ ያውበስደት እየኖረ ነው። ለምን ተሰደደ ካልከኝ ብዙ ምክንያቶች ልታነሳ ትችላለህ። ነገርግን አንድ ምሳሌ ልንገርህ። ቨርጂኒያ በሚባል አንድ የአሜሪካ ንዑስ አገር (ስቴት) አንድ አካባቢ ብቻ 36 አንቱ የተባሉ የኢትዮጵያ ዶክተሮች አሉ። ዶክተር ስልህ የህክምና ባለሙያዎቹን ብቻ ነው።ከዚህ ውጭ አሜሪካ ውስጥ በእያንዳንዱ ዩኒቨርስቲ ቢያንስ ሁለት ሁለት ፕሮፌሰሮችን ታገኛለህ። እነዚህ ለኢትዮጵያ ይጠቅማሉ የምላቸው ምሁራን አሜሪካን እያገለገሉ ይገኛሉ። እዚህ ያለው ደግሞ በየኩሽና የተኛው ነው።
ሰንደቅ፡- ኢትዮጵያዊያን ምሁራን በአገራቸው ጉዳይ ላይ አደባባይ ወጥተው ሀሳባቸውን ከመግለጽ ይልቅ “እኔ ባለሙያ እንጂ ፖለቲካ ውስጥ አልገባም” በማለት ምሁራዊና አገራዊ ግዴታቸውን እየተወጡ አይደለም ተብለው ይተቻሉ። ለመሆኑ አገሪቱ ውስጥ የአደባባይ ምሁር የጠፋበት ምክንያት ምንድን ነው?
ዶክተር ፍሰሀ፡- በእኔ እድሜ ክልል ያለው ባለፉት 40 ዓመታት ዘውዱ መውረድ አለበት ብሎ ዘውዱን አወረደ፣ ደርግ መውረድ አለበት ብሎ ጮኸ ደርግ ወረደ፣ አሁንም እሱ የሚፈልገው መንግስት ሲሆንለት ባለማየቱ ማለትም እንደጎረቤቶቻችን አምስት ዓመቱን ጠብቆ ስልጣኑን የሚያስረክብ፣ ፓርላማ ለመግባትም ህዝብ መርጦት ፓርላማ በመግባት የህዝብን ድምጽ የሚያሰማ እንዲሆንና አመራሩ እንደህዝቡ አይነት የሚኖር ነበር። ይህ ባለመሆኑ ደግሞ በድጋሚ ሲናገር እንደገና ሲደበደብ ኖሯል።እኔ ተናግሬ ለውጥ ካላመጣሁ፣ ተናግሬ ወደምሰማበት እሄዳለሁ ወይም ለኑሮዬ እኖራለሁ ብሎ የተቀመጠ ነው።
የሚያሳዝነው ግን የወጣቱ ነው። አገር የሚገነባው በወጣት ነው።ወጣቱ ግን አንደኛ ነገር እየደነቆረ ነው ያለው። ለምንድንነው እየደነቆረ ያለው ለሚለው የግድ መናገር ስላለብኝ እናገራለሁ “ትምህርቱ ጥራት የለውም።” ዛሬ እኛ የምናስበው ይህን ያህል ዩኒቨርስቲ ከፍተናል የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱ ይህን ያህል ደርሷል ወዘተ…. እያልን ነው። ግን እዛ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚያስተምሩት ምንአይነት መምህራን ናቸው ብለህ ከጠየቅህ አንድ የአንደኛ ደረጃ መምህር ከተማሪው ጋር ጫት ሲቅም ታየዋለህ።በዚያ መንገድ የመጣ ተማሪ ነው ዩኒቨርስቲ ገብቶ የሚወጣውና ወደስራ የሚገባው። በዚህ መልኩ አገርን ልትገነባ አትችልም። ለዚህ ደግሞ የትምህርት ጥራቱን በሚገባ ልትፈትሸው የሚገባነው።
ሰንደቅ፡- በአንድ ወቅት ዶክተር ኃይሉ ዓርአያ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያምን በብሔራዊ ሸንጎ ቀርበው “አሁን አገሪቱ ላለችበት ቀውስ ተጠያቂው አንተ ነህ” ብለው ሲናገሩት ተሰምተዋል። አሁን እንደዛ አይነት ምሁራን ለምን ጠፉ ነው? ጥያቄው?
ዶክተር ፍሰሀ፡- ኃይሉ ዓርአያን በሚገባ የማውቀው ወዳጄ ነው። አሁን አንተ ያልከው ንንግግር ሲናገርም እንደታዛቢ ተጋብዤ ከእሱ ጎን ነበርኩ አስታውሳለሁ። ኃይሉ ዓርአያ አገሩን የሚወድ ይህንን ህገመንግስት (የኢህዴሪን) ቀን ከሌት ከሰሩት እና ከለፉት ምሁራን አንዱ በመሆኑ እና ያ ድካም ከንቱ መቅረቱ አናዶት ነው መንግስቱ ኃይለማሪያምን የተናገረው። ሊመጣበት የሚችለውን መዘዝ ቢያውቅም የመጣው ይምጣ ብሎ ቆርጦ ነው እንደዛ የተናገረው። ኃይሉ ራስ ወዳድ ያልሆነ ምሁር ነው። እንደሌሎቹ ውጭ አገር ቢሄድ ተንደላቆ የሚኖር ሰው ቢሆንም አገሬን ብሎ በመቅረቱ ለእሱ አድናቆት አለኝ።
አንተ አሁን የጠየከኝ እንደ ኃይሉ አይነት ተናጋሪዎች አሉ ወይ? እያልከኝው።መልሴ አሉም፣ የሉምም የሚል ነው። አሁን የዩኒቨርስቲ መምህር ለመሆን መመዘኛው የፓርቲ አባል መሆን ነው። ልክ አንተ የጋዜጣችሁን ገመና በሌላጋዜጣ እንደማትተቸው ሁሉ ፓርቲህንም በአደባባይ አትተችም። ሀሳብህን የምትገልጸው በዚያው በመሰረታዊ ድርጅትህ ውስጥ ብቻ ነው የሚሆነው።
በሌላ በኩል ደግሞ አንተ እንደምትለው የአደባባይ ምሁሮችም አሉ። ለዚህ አንድምሳሌ ላንሳልህ።ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም እኔ እሰከማውቀው ድረስ መንግስቱ ኃይለማሪያምን “ወረድ እና ህዝባዊ መንግስት ይቋቋም” ያለ ሰው ነው። አሁንም ቢሆን ደግሞ በኢህአዴግ ጊዜ በግልጽ የሚናገር ራስ ወዳድ ያልሆነሰው ነው።
ምንጭ ስንደቅ