Wednesday, 09 March 2016 13:12
የህዳሴ ግድብ የቦንድ ሽያጭ እየቀነሰ መሄዱን የተለያዩ ምሁራን ጥናቶች አመልክተዋል። ማክሰኞ የካቲት 29/ 2008 በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመተባባር “የታላቁ ህዳሴ ግንባታ የኢትዮጵያን ህዳሴና ቁጠባ ከማሳደግ አንፃር ያመጣው ፋይዳ” በሚል ርዕስ በቀረቡት የተለያዩ ጥናቶች በቦንድ የሚሰበሰበው የገንዘብ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መሄዱን ተመልክቷል። በዚሁ ዙሪያ ጥናት በማድረግና በማቅረብ ተሳትፎ ያደረጉት የባህር ዳር፣ የጂማና የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲዎች ናቸው።
በቀረቡት ጥናቶች መሰረት ባለፉት አራት አመት ከግማሽ ጊዜያት ውስጥ በአጠቃላይ ከህብረተሰቡ 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡ ታውቋል። ይህ የገንዘብ መጠን በየወቅቱ የዶላር የምንዛሪ መጠን ሲሰላ 410 ሚሊዮን ዶላር መሆኑ ታውቋል።
በ2011/2012 በአጠቃላይ በአራት አመታት ከግማሽ ባለው ጊዜ በህዝቡ ከተዋጣው አጠቃላይ 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገንዘብ ውስጥ 37 ነጥብ 62 በመቶ ገንዘብን ማሰባሰብ የተቻለ ሲሆን፤ ይህ የገንዘብ መጠን እ.ኤ.አ. በ2012/2013 በ20 ነጥብ 05 በመቶ ወርዶ ታይቷል። በተመሳሳይ መልኩ እ.ኤ.አ. በ2013/2014 በ15 ነጥብ 71 በመቶ የቀነሰ መሆኑን በጂማ ዩኒቨርስቲ የቀረበው ይሄው ጥናት አመልክቷል።
የህዳሴው ግድብ የቦንድ ቁጠባ መጠን ከአጠቃላይ ለሀገሪቱ ቁጠባ ያበረከተው የቁጠባ መጠን በ2003/2004 ዓ.ም 3 ነጥብ 2 በመቶ የነበረ ሲሆን በ2004/2005 ወደ 2 ነጥብ 2 ወርዷል። ይኸው መጠን በ2005/2006 ወደ 1 ነጥብ1 በመቶ የወረደ መሆኑን በጂማ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ወንድይፍራው ሙሉጌታ ገልፀውልናል። ለግድቡ ግንባታ ከህብረተሰቡ በተለያየ መልኩ ገንዘብ የሚሰባሰብ ሲሆን ካለው የቦንድ ሽያጭ በተጨማሪ የ8100A ሞባይል አጭር መልዕክት በኩል የሚደረግ የእድል ጨዋታና ሎተሪ ይጠቀሳሉ።
በቦንድ ሽያጭ ረገድ በአጠቃላይ በሃገር ውስጥና በውጪ ሀገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያንና ትውልደ ኢትዮጵያን የተሰባሰበ ገቢ ሲሆን ከአጠቃላይ ገንዘብ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆነው የገንዘብ መጠን ከሀገር ውስጥ የተሰበሰበ መሆኑን ጥናቶቹ አመልክተዋል። ይህም ከአጠቃላዩ 7 ነጥብ 6 ቢሊዮን ውስጥ 6 ነጥብ 96 ቢሊዮን ብር ነው። በሀገር ውስጥ ቦንድ ሽያጭ ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ደመወዝተኛ ሰራተኛው ሲሆን ይህም ከአጠቃላዩ የቦንድ ግዢ ውስጥ 46 በመቶውን ይይዛል ተብሏል። ከሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የተሰበሰበው የገንዘብ መጠን በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠ ሲሆን በዚህ በኩል ቃል የተገባውና የተሰበሰበው የገንዘብ መጠን ልዩነት ያለው መሆኑ ተመልክቷል። በቦንድ ግዢ በኩል አነስተኛ ተሳትፎን ያስመዘገበው ዲያስፖራው ነው። በአፍሪካ፤ በመካከለኛው ምስራቅ፤ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ የቦንድ ሽያጭ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የተሻለ እንቅቃሴ እየታየበት ያለው የመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ መሆኑ ታውቋል።
በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ የመቀነስ አዝማሚያዎች ያሉ መሆኑ ታውቋል። በአጠቃላይ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ሀገራት እንደሚኖሩ መረጃዎች የሚያመለክቱ ሲሆን እስከዛሬ በተደረገው እንቅስቃሴ ከዲያስፖራው ማሰባሰብ የተቻለው የገንዘብ መጠን በአጠቃላይ ለግድቡ ከህዝብ ከተሰባሰበው ገንዘብ ውስጥ ከ 7 በመቶ የሚበልጥ ሆኖ አልታየም።
በቀጣይ ለግድቡ ገንዘብ በማሰባሰቡ ረገድ እስካሁን ከተሄደባቸው መንገዶች ሌሎች አማራጮችም እንዲታዩ በጥናቶቹ ላይ ተመልክተዋል። በተለይ ሰራተኞችና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ቦንድ ከገዙ በኋላ የቦንድ ግዢው ሰርተፍኬት እየተሠጠ ባለመሆኑም ይህ ጉዳይ መስተካከል ያለበት መሆኑን ዶክተር ወንድይፍራው ገልፀውልናል።
ስንደቅ