Wednesday, 09 March 2016 13:15

  • በ  ፀጋው መላኩ

መንግስት በኢትዮጵያ መጠነ ሰፊ ድርቅ መከሰቱን ከገለፀበት ወቅት ጀምሮ የተለያዩ እርዳታ ሰጪ አካላት እገዛ እንዲያደርጉለት ጥሪ ማቅረብ ከጀመረ ዋል አደር ብሏል። ለእርዳታ ጥያቄው ምላሽ በመስጠቱ ረገድ አለም አቀፉ ማህበረሰብ የሰጠው ምላሽ ያን ያህል በመሆኑ መንግስት በግሉ የተወሰነ እርዳታ ለማቅረብ ተገዶ ቆይቷል። በመንግስት በኩል ያለው እርዳታን የማቅረብ አቅም ውስን መሆንና የችግሩ ስፋትና የእርዳታ አቅርቦት ጊዜው ሰፊ መሆን የሌሎች አካላትን የረድኤት ጣልቃ ገብነት የሚጠይቅ ሆኖ ተገኝቷል።  ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ ባንኪሙን የኢትዮጵያ የድርቅ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ገልፀው ለጋሽ አካላት የረድኤት እጃቸውን እንዲዘረጉ የተማፅዕኖ ጥሪ አቅርበዋል።

 

በተመሳሳይ መልኩ የአለም አቀፉ የምግብ ፕሮግራም ኤግዚኪዩቲቭ ዳይሬክተር ኤርታሪን ኮዚን ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ከመሆኑ በፊት አለም አቀፉ ማህበረሰብ በእርዳታው አቅርቦቱ በኩል አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል። በኢትዮጵያ ድርቅ ዙሪያ ተፈላጊውን የእርዳታ መጠን ለማሰባበሰብ ጥረት ያደረገው አለም አቀፉ የምግብ ፕሮግራም፤ “ይህንን ቀውስ ወደ ከፋ ደረጃ ከመድረሱ በፊት ማስወገድ የምንችለው በድርቅ ለተጎዱት ቤሰቦች በመድረስ ነው” በማለት ኤግዚኪዩቲቭ ዳይሬክተሩ ጠንከር ያለ ጥሪያቸውን ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

 

የምግብ ፕሮግራሙ ላቀረበው የእርዳታ ጥሪ ምላሽ ማግኘት የቻለው 26 በመቶውን ብቻ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህም የእርዳታ መጠን እስከመጪው ሚያዚያ ወር ብቻ የሚያገለግል መሆኑን ቀደም ባለው ጊዜ  ተመልክቷል። የኢትዮጵያ መንግስት ካለው የመጠባበበቂያ ክምችት፣ በቀጥታ የእህል ግዢ በማከንወንና ከአለም አቀፉ ባገኘው የተወሰነ እርዳታ በድርቅ ተጎጂዎች ናቸው ተብለው ለተለዩት 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች አፋጣኝ የእህል እርዳታ ሲያቀርብ ቆይቷል። ከተከሰተው ሰፊ የድርቅ መጠን አንፃር  የኢትዮጵያ መንግስት እርዳታ የማቅረብ አቅም ውስን መሆኑን በመግለፅ አለም አቀፉ ማህበረሰብ የረድኤት እጁን እንዲዘረጋ በግሉ የተለያዩ ጥሪዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል።

 

ለዚህ ጥሪ የተሰጠው ምላሽ ያን ያህል አመርቂ ነው ተብሎ የሚነገር  አልነበረም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው የችግሩን ስፋት ለማሳየት በመንግስት በኩል ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከል አንዱ የእርደታ ጥሪው በተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሀፊ ባንኪ ሙን በኩል ጥሪው እንዲተላለፍ ማድረግ ነበር። ባለፈው ጥር ወር በአፍሪካ ህብረት 26ኛው የመሪዎች ጉባኤ ላይ በአዲስ አበባ የተገኙት ሚስተር ባንኪሙን  የድርቁን መጠንና ክብደት በተመለከተ በኢትዮጵያ ባለስልጣናት በኩል ገለፃ ከተደረገላቸው በኋላ በአዲስ አበባ በተካሄደው የረድኤት ድርጅቶች ስብሰባ ላይ ኦፊሴላዊ የእርዳታ ጥሪን አስተላልፈዋል።

 

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሰፋ ያለ ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን የድርቅ ተጎጂ የሆኑትን ወገኖች ለመታደግ መንግስት ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ ቢያደርግም ያገኘው ምላሽ ውስን መሆኑን ገልፀው ተጨማሪ ጥሪን ያቀረቡበት ሁኔታም ነበር። ባንኪሙን በኦሮሚያ አንዳንድ በድርቁ የተጎዱ አካባቢዎችን ከጎበኙ በኋላ አለም አቀፉ ማህበረሰብ የእርዳታ እጁን ለኢትዮጵያ እንዲዘረጋ ጥሪያቸውን ያስተላለፉት በዚያው ሰሞን ነበር።

 

በደርቅ ለተጠቁት ወገኖች በ2016 እርዳታ ለማቅረብ እስከ 1ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ መሆኑ ቢረጋገጥም ባለፈው የካቲት ወር መጀመሪያ ድረስ 272 የአሜሪካን ዶላር ወጪ ተደርጓል። ከዚህም ውስጥ መንግስት እርዳታን በማሰባሰብና ከካዝናው 381 ሚሊዮን ዶላር ቢያወጣም ከሚያስፈልገው አጠቃላይ ገንዘብ አንፃር የ714 ሚሊዮን ዶላር ክፍተት ይታያል። መንግስት በተለያየ መልኩ ገንዘብ በማሰባሰብና ከካዝናው በማውጣት ለእርዳታ ካዋለው ገንዘብ ውስጥ 272 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው የገንዘብ መጠን በፈረንጆቹ 2015 ለቀረበው እርዳታ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ቀሪው 109 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ ካለፈው ጥር ወር በኋላ ወጪ የተደረገ ነው።

 

ከ109 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነው በውጪ ሀገራት በጎ አድራጎት ድርጅቶች የተለገሰ መሆኑን በቅርቡ በዚሁ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የመንግስት ኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ አመልክተዋል። የተባበሩት መንግስታት እንደዚሁም የኢትዮጵያ መንግስት በተናጠል እያደረጉት ያለውን የእርዳታ ጥሪ ተከትሎ በተባበሩት መንግስታት በኩል እየተደረገ ካለው ድጋፍ በተጨማሪ አንዳንድ መንግስታት ቀጥተኛ ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው።

 

በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር ቆይታ ያደረጉት የኦስትሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰባስቲያን ኩሩዝ ኢትዮጵያ በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት ያስችላት ዘንድ መንግስታቸው የሰባት ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ እርዳታ ቃል የገባ መሆኑን አስታውቀዋል። በተመሳሳይ መልኩ የግብፅ መንግስት በአለም አቀፉ የምግብ ፕሮግራም (WFP) በኩል ለኢትዮጵያ ድረቅ ተጎጆዎች የሚውል የአንድ ሚሊዮን ዶላር እርዳታ የለገሰ መሆኑን ከሰሞኑ አስታውቋል። በዚህ በግብፅ መንግስት በኩል በተደረገው የገንዘብ እገዛ የአለም አቀፉ የምግብ ፕሮግራም አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሜትሪክ ቶን ልዩ ልዩ የእርዳታ እህሎችንና ዘይትን ገዝቶ ለተረጂዎች የሚያርቀብ መሆኑ በፕሮግራሙ የኢትዮጵያ ወኪልና ካንትሪ ዳይሬክተር ሚስተር ጆን አይሊፍ  አመልክተዋል።

 

ከዚህም በተጨማሪ የአሜሪካ አለም አለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ(USAID) 97 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ያመለከተ ሲሆን አሜሪካ በኢትዮጵያ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የተቀናጀ ድጋፍ ለማድረግ የአደጋ ጊዜ የእርዳታ ምላሽ ሰጪ ቡድን (Disaster Assistance Response Team) እንዲቋቋም አድረጋለች። ይህም አካል በቀጣይ በተቀናጀ መልኩ እርዳታ በማቅረቡ ረገድ ከኢትዮጵያ መንግስት፣ከተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ከሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች ጋር በጋራ የሚሰራ መሆኑን በድረገፁ በለቀቀው መረጃ  አስታውቋል።

 

ይህ የተቋቋመው ቡድን በኢትዮጵያ በድርቅ የተጎዱ አካባባዎችን በመጎብኘትና የችግሩን ስፋት በመፈተሸ በቀጣይ ከእለት ምግብ እርዳታ ጀምሮ እስከ ዘር እህል ድረስ ለተጎጂዎች ለማቅረብ የራሱን የመስክ ጥናት ያደርጋል ተብሏል።

በሀገሪቱ የተከሰተው ድርቅ ያካለለው ዮቀዳ ስፋትና የተጠቃው የህዝብ መጠን ሰፊ ነው። እስካሁን ባለው ሁኔታ 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዜጎች በድርቅ ተጠቂዎች መሆናቸው የተረጋገጠ ሲሆን በቀጣይ የበልግ ዝናብ በተጠናከረ መልኩ የማይቀጥል ከሆነ የተረጂው ቁጥር ከዚህም በላይ ሊጨምር ይችላል የሚሉ ስጋቶች አሉ።

 

ብሄራዊ ሜትሮሎጂ አጀንሲ የበልግ ዝናቡን አስመልከቶ ሰሞኑን የለቀቀው የትንበያ መረጃ በቀጣዩ ወር የሀገሪቱን ሰፊ ሰብል አብቃይ አካባቢዎች ባካለለ መልኩ ሰፊ የዝናብ ስርጭት የሚኖር መሆኑን አመልክቷል። ይህ የዝናብ ስርጭት በስፋት የሚቀጥል ከሆነ በድርቅ የተጠቁ አካባቢዎች የግጦሽ ሳርን፣ የመጠጥ ውሃንና የተወሰነ የሰብል ምርትን እንዲያመርቱ እገዛ ስለሚያደርግላቸው የሚያስፈልገው የእርዳታ ፍላጎት መጠን እንዲቀንስ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል። ይሄው የዚህ ሳምንት የብሄራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ትንበያ በተወሰኑ የሀገሪቱ በልግ እህል አምራች አካባቢዎች አሁን ያለው ፀሃያማ የአየር ሁኔታ የሚቀጥልበት ሁኔታ መኖሩንም  ያመለክታል። የተረጂው መጠን ባለበት ይቀጥል ወይንም የሚቀንስና የሚጨምር የመሆኑ ጉዳይ በተወሰነ ደረጃ የሚወሰነው በቅርቡ ከጀመረው የበልግ ዝናብ ስርጭትና መጠን ጋር የሚያያዝ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

Leave a Reply