በቅርቡ ለኤርትራ አዋሳኝ ከሆነ ነው ከትግራይ ክልል በተለይ ፅርዓያ ግርማይ ተብሎ ከሚታወቀው አካባቢ በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን በኤርትራ ታጣቂ ኃይሎች ተጠልፈው ተወስደው ነበር፡፡

በባህላዊ መንገድ ወርቅ ከሚወጣበት ካፍታ ሁመራ ወረዳ ወርቅ በማውጣት ላይ ከነበሩ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን ከንጋቱ 12 ሰዓት ላይ ድንበር ዘልቀው በገቡ የኤርትራ ታጣቂ ኃይሎች ታፍነው ተወስደዋል፡፡ መጀመርያ አካባቢ ቁጥራቸው 85 መሆኑ የተነገረው እነዚህ የሻዕቢያ ሰለባ የሆኑት ኢትዮጵያውያን 32 እንደሆኑ በሱዳን አደራዳሪነት ከተመለሱ ዜጎች ቁጥር አንፃር ተመልክቷል፡፡

ኢትዮጵያውያኑ ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ ጉዳዩ ይፋ የወጣው በማኅበራዊ ሚዲያ ሲሆን፣ ከዚያም ከጠለፋው አመለጡ የተባሉትን ወጣቶች አነጋግሮ የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ዜናውን ማሠራጨቱ ይታወሳል፡፡

እነዚህ ዜጎች በሌላ አገር ለዚያውም በጠላት አገር ታጣቂ ኃይሎች ሲወሰዱ ለሁለት ሳምንታት ያህል የኢትዮጵያ መንግሥት ያወጣው መግለጫ አልነበረም፡፡ የመንግሥት ሚዲያም ስለጉዳዩ ትንፍሽ ያለው ነገር አልነበረም፡፡ የግሉ ሚዲያም ቢሆን አጀንዳ ሲያደርገው አልተስተዋለም፡፡

ታፍነው የተወሰዱትን ዜጎች በተመለከተ የተለያዩ ሚዲያዎች የተለያየና አንዳንዶቹም ተቃራኒ የሆኑ ዜናዎች እያወጡ መንግሥት በጉዳዩ ላይ ዝምታን መምረጡ፣ ከብዙዎች ዘንድ ወቀሳ የደረሰበት ሲሆን፣ ከገዛ አገራቸው በኃይል ታፍነው ስለተወሰዱት ዜጎች ሁኔታ የሕዝቡን የማወቅ መብት፣ መረጃን የማግኘትና ስለአገሩ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ የማወቅ መብት የጣሰ ሲሉም አስተያየት ሰጪዎች ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ለዜጎች ያለው ተቆርቋሪነትም ጥያቄ ውስጥ የከተተ ነው ያሉም አልጠፉ፡፡

ስለጠለፋው

ጠለፋው የተከናወነው ጥር 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ሲሆን ከንጋቱ 12 ሰዓት ላይ መሆኑ፣ ታጋቾቹ ለኢትዮጵያ ፈርስት ኦንላይን ሚዲያ ባለቤት ቢንያም ከበደ ተናግረዋል፡፡ ከተመለሱት ጋር ቅርበት ያላቸው ሪፖርተር ያነጋገራቸው ምንጮች እንደሚሉት፣ የተጠለፉት ኢትዮጵያውያን በባህላዊ መንገድ ወርቅ ከሚወጣበት ቦታ ከተወሰዱ በኋላ በግድ የተከዜን ወንዝ እንዲሻገሩ በማድረግ ለስምንት ሰዓታት በእግር ተጉዘው፣ ጉሊት በተባለ ቦታ ሻምበል ዳዊት የተባለና ሌሎች የኤርትራ መከላከያ ኃይል ወታደራዊ መኰንኖች አግኝተዋቸዋል፡፡

አንዳንድ ዘገባዎች ጠለፋውን ያከናወኑት ግንቦት ሰባት አርበኞች ግንባር በመባል የሚታወቀው ድርጅት አባላት እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡ ሆኖም ከተመላሾቹ መካከል አንዳንዶቹ ለኢትዮጵያ ፈርስት እንደገለጹት፣ ከስድስቱ ታጣቂዎች መካከል የኤርትራ ሚሊሻና ትግርኛ ተናጋሪ የኤርትራ ወታደሮች ነበሩባቸው፡፡

ታጋቾቹ ከኤርትራ ወታደራዊ መኰንኖች ጋር ከተገናኙ በኋላ ልብሳቸውን አውልቀው ወታደራዊ ልብስ እንዲለብሱ የተደረገ መሆኑን፣ ‹‹ከአሁን በኋላ ወታደሮች ናችሁ፣ ትሠለጥናላችሁ፤›› ተብለው በእጃቸው የነበረውን ንብረት በሙሉ እንዲያስረክቡ መደረጋቸው ተሰምቷል፡፡ ከዚያም ወደ ጀርድን (የመስኖ እርሻ የሚከናወንበት ቦታ) ተወስደው ለአሥር ቀናት ያህል የጉልበት ሥራ እንዲሠሩ መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡

ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 40 የሚሆናቸው እነዚህ ከታገቱ በኋላ የተመለሱት ዜጎች በኤርትራ ቆይታቸው አንዳንድ ነገሮች የተመለከቱ ሲሆን፣ በተለይ ከወታደሮቹ ውጪ ሲቪል ኤርትራዊያን እነሱን ዓይተው ተደብቀው ሲያለቅሱና ሐዘናቸውን ሲገልጹላቸው እንደነበሩ ታዝበዋል፡፡ ያለ ክፍያ ተገደው የእርሻ ሥራ በሚሠሩበት አካባቢ እንደነሱ ተጠልፈው የተወሰዱ ቁጥራቸው ከ30 በላይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ቀን ቀን በዚሁ ተመሳሳይ የጉልበት ሥራ ተገደው ሲሠሩ፣ ሌሊት ሌሊት ደግሞ በአሰቃቂ ሁኔታ ታስረው እንደሚያድሩ መመልከታቸውንም ተናግረዋል፡፡

አብዛኞቹ ለማምለጥ ሲሞክሩ በጥይት የተገደሉ፣ ተመትተው አካላቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸው በሕይወት የተረፉ መኖራቸውን፣ እንዲሁም በርካቶች ተገደው ወታደራዊ ሥልጠና ወስደው በተለይ ግንቦት ሰባት አርበኞች ግንባር የተባለውን ድርጅት እንዲቀላቀሉ መደረጋቸውንም ከዕገታው የተመለሱት ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው በኤርትራ አዋሳኝ አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንደሚናገሩት፣ የኤርትራ ወታደሮችና በኤርትራ የሚገኙ የኢትዮጵያ አማፂ ኃይሎች በተደጋጋሚ ኢትዮጵያውያንን እያፈኑ ይወስዳሉ፡፡ ይህንን በተመለከተ በቅርቡ ጥያቄ የቀረበላቸው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ‹‹እያንዳንዱን የድንበር ወሰን ወታደር አስቁሞ መጠበቅ አይቻልም፤›› ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የኤርትራ መንግሥት ኃላፊነት የጎደለው የሽፍትነት ተግባር ላይ የተሰማራ በመሆኑ በተፈጸመው ጠለፋ እምብዛም አለመገረማቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ተመጣጣኝ አንዳንዴም ‹‹የማያዳግም›› ዕርምጃ በመውሰድ አፀፋ ምላሽ እንደሚሰጥ ዝቶ የነበረ ሲሆን፣ በቅርቡ የተጠለፉት ዜጎች በሱዳን አማካይነት በመመለሳቸው ዕርምጃ ከመውሰድ የተቆጠበ ይመስላል፡፡

በባድመ አካባቢ በ1990 ዓ.ም. በኤርትራ በተቀሰቀሰው ጦርነት ከሁለቱም አገሮች 70 ሺሕ ያህል ዜጎች ማለቃቸው ይታወሳል፡፡ የድንበሩ ጉዳይ እስካሁንም ዕልባት አላገኘም፡፡

ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ በድንበር አካባቢ የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን እየታፈኑ የሚወሰዱ ሲሆን፣ መንግሥት ግልጽ የሆነ የማጣራት ሥራና ዕርምጃ ሲወስድ ባለመታየቱ ወቀሳ ይቀርብበታል፡፡

በተለይ የኢሮብ ሕዝብ የመብት ተቆርቋሪ (IRAA) የተባለ ቡድን እንደሚለውኧ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የኢሮብ አካባቢ ንፁኃን ነዋሪዎች ከቤታቸው ታፍነው ተወስደዋል፡፡ ስማቸውንና ማንነታቸውን በውል የዘረዘራቸው 97 አርሶ አደሮችን በግልጽ በመዝገብ አስፍሮ የገቡበት አለመታወቁን ቀደም ሲል አሳውቋል፡፡ ሌላ የአካባቢው ሕዝብ ተቆርቋሪ የሆነውና በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ የሚኖረው ዓለም ተስፋዬ የተባለው ታዋቂ ጸሐፊ፣ ‹‹Neglected Irob Abductees›› (የተዘነጉት የተጠለፉ የኢሮብ ሕዝብ ተወላጆች) በሚል መጣጥፍ ተመሳሳይ ቅሬታ አሰምቷል፡፡

‹‹ቁጥራቸው ከ100 በላይ የሚሆኑ የኢሮብ ተወላጆች ሻዕቢያ አፍኖ ወስዶአቸው እስከዛሬ ምን እያደረጋቸው ይሆን?›› በማለት የሚጠይቀው አቶ ዓለም፣ ‹‹የሚገርመው የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለእነዚህ ንፁኃን ዜጎች ዝም ማለቱ ነው፤›› ይላል፡፡

‹‹በሌሎች አገሮች አንድ ዜጋ በጠላት ከተወሰደ ምን እንደሚሠራ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ዜጎቹ ተጠልፈው ለዘመናት እየማቀቁ ቁጭ ብሎ የሚመለከት ብቸኛ መንግሥት ነው፤›› ሲልም ጸሐፊው ይወቅሳል፡፡

ሪፖርተር ባደረገው ማጣራት ቀደም ሲል የገቡበት ስላልታወቀ እነዚህ ዜጎች የትግራይ ክልል መንግሥትና የፌደራል መንግሥት ከነዝርዝር ስማቸው የተገለጹላቸው ቢሆንም ምንም የሰጡት ምላሽ የለም፡፡

የኤርትራ መንግሥት ነፍጥ ያነገቡ የኢትዮጵያ የአማፂ ኃይሎች ወደ ኢትዮጵያ በማስረግ የተለያዩ ጥቃቶች ሲፈጽም ይስተዋላል፡፡ ቀደም ሲል የአውሮፓ ቱሪስቶችና ኢትዮጵያውያን ከአፋር ክልል አፍኖ መውሰዱ የሚታወስ ሲሆን፣ በፈረንጆቹ ምክንያት ይመስላል ጉዳዩ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ሆኖ ነበር፡፡ መንግሥትም ሦስት ወታደራዊ የሻዕቢያ ካምፖች ማጥቃቱን ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት ሻዕቢያ ለፈጸመው ትንኮሳ አንዳንድ ወሳኝ ሥፍራዎች ላይ የአውሮፕላን ጥቃት በኢትዮጵያ መንግሥት ተፈጽሞ ነበር፡፡ እንዲሁም በ2004 ዓ.ም. በተመሳሳይ በባህላዊ መንገድ ወርቅ በማውጣት ላይ ከነበሩት መካከል እንደ አሁኑ 140 ኢትዮጵያውያን ተጠልፈው የተወሰዱ ሲሆን፣ እስከ ዛሬ የገቡበት አልታወቀም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሻዕቢያ ትንኮሳ የማይቆም ከሆነ፣ ኢትዮጵያ ለአንዴና ለመጨረሻ ዕርምጃ ለመውሰድ እንደምትገደድ ባለፈው ዓመት ገልጸው ነበር፡፡

በኤርትራ እየተሰቃዩ ስለሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የመንግሥት ባለሥልጣን፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት እጅና እግሩን አጣጥፎ አልተቀመጠም፡፡ ጉዳዩን እያጠናው ይገኛል፡፡ የሚወስደውም ዕርምጃ እየተጠና ነው፤›› ብለው፣ ዝርዝር መግለጫ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ በ1990 ዓ.ም. በድንበር ሰበብ ወደ ጦርነት ከገቡ ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 18 ዓመታት ሰላምም ጦርነትም በሌለበት ሁኔታ ይገኛሉ፡፡