ጋይም (ገብረእግዚኣብሄር ኃይለሚካኤል) ማን ነው?
ገብረእግዚኣብሄር (ጋይም) ከአቶ ኃይለሚካኤል ገብረማሪያምና ወይዘሮ ሓዳስ ደስታ ሕዳር 1 ቀን 1941 ዓ.ም. ሞኖክሶይቶ በምትባል መንደር ተወለደ። ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ እዛው ሞኖክሶይቶ እስከ 4ኛ ክፍል ተማረ። በወቅቱ በሞኖክሶይቶ ከ4ኛ ክፍል በላይ ትምህርት ስላልነበረ ወደ ዓዲግራት በመሄድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በዓዲግራት በሚገኘው ጽንሰታ ለማርያም የካቶሊክ አዳሪ ትምህርት ቤት ኣጠናቀቀ።
በ1958 ዓ.ም. የፍልስፍናና ቲዮሎጂ ትምህርታቸውን በቫቲካን እንዲከታተሉና የካቶሊክ ካህናት እንዲሆኑ ከተላኩት በርከት ያሉ ተማሪዎች ጋራ ወደ ጣሊያን (ቫቲካን) ለከፍተኛ ትምህርት ተላከ። በቫቲካን ለሶስት ዓመት የፍልስፍና ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ ላጭር ጊዜ ዕረፍት ወደ ኢትዮጵያ ከጓደኞቹ ጋራ ተመለሰ። ከዕረፍት በኋላ ጓደኞቹ የቲዮሎጂ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ወደ ቫቲካን ሲመለሱ ገብረእግዚኣብሄር (ከንግዲህ ጓድ ጋይም በሚለው በትግል ስሙ እቀጥላለሁ) የቲዮሎጂን ትምህርት በመከታተል የካቶሊክ ካህን ሆኖ ህይወቱን መቀጠል ስላልፈለገ ወደ ቫቲካን ሳይመለስ ቀረ። በምትኩ በቀን እየስራ ማታ ማታ ፖለቲካል ሳይንስ በወቅቱ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ መቀጥሉን መርጦ ኑሮዉን አዲስ አበባ አድርጎ ቀን እየሰራ ማታ እየተማረ እስከ 1963 ዓ.ም. ቀጠለ። በ1963 እስኮላርሽፕ አግኝቶ ሙሉ ጊዜውን ለትምህርት ሰጥቶ ለመማር ወደ ያኔው ሶቬት ህብረት ሂዶ ትምህርቱን እስከ 1966ዓ.ም. ተከታተለ።
ከ1960ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ከፈተኛ ሚና ከነበራቸውና በኋላም ኢህ አፓን ከመሰረቱት ዋናዎቹ እንደነ ዶክተር ተስፋይ ደበሳይ፣ ዘርኡ ክሕሸን፣ ጸሎተ ህዝቂያስ ዓነቶቹ ጋራ ገና አዲስ አበባ ከገባ ጊዜ ጀምሮ ግኑኝነት ስለነበረው ጓድ ጋይም ገና ከምስረታው በፊት በኢህ አፓ መስራቾች በአባልነት ከታጩት አንዱ ስለነበረ ገና ድርጂቱ በ1964 ዓ.ም. በበርሊን (ጀርመን) ላይ ባደረገው የመጀመሪያ ጉባኤው ሲመሰረት በአባልነት በግልጽ ከታቀፉት አንዱ ነበር። ስለሆነም በ1966 አቢዮቱ ሲፈነዳና ድርጅቱ ለተለያየ ስራ አባላት ሲመድብ ጓድ ጋይምም ትምህርቱን አቋርጦ ለድርጅታዊ ስራ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ተደረገ። ለድርጅታዊ ስራ ምደባውም ዓዲግራትን ማእከል በማድረግ በትግራይ ለድርጅቱ አባላት እንዲመለምልና የኢህ አፓ ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድን መጀመሪያ እንዲገባበት በድርጅቱ ተውስኖ የነበረውን የዓዲ ኢሮብ አከባቢ እንዲያጠናና አስፈላጊ የስንቅ ዝግጅት እዛው እንዲያደርግ ተመድቦ ከነበረው ከጓድ ተስፋይ ኃይለማሪያም (ቀያፋ) (ነብሱን ይማር እሱም ዛሬ በህይወት የለም) ጋራ አብሮ እንዲሰራ ነበር።
እስከ 1968 በዓዲግራት ከተማ ድርጅታዊ ስራውን ሲሰራና አልፎ አልፎ ወደ ዓሲምባም ብቅ እያለ ዓሲምባ ያኔ ገብቶ ከነበረው ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድን ጋራ እየተገናኘ በከተማ ከነበረው አመራር ጋራ እያገናኘ ቆይቶ በ1968 ሓምሌ አከባቢ 8 የሚሆኑ የትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድን አባላት ከቡድኑ ከድተው ወደ ዓዲግራት ሲገቡ ጓድ ጋይም ከከተማ ወደ ዓዲ ኢሮብ እየዘለቀ ከትጥቅ ትግል ጀማሪዎች ጋራ ሲያደርገው የነበረ ግኑኝነት ያውቁ ስለነበረ ከተማውን ለቆ ወደ ሜዳ እንዲወጣና ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድኑን እንዲቀላቀል ተገደደ። ወደ ሜዳ እንደወጣ ወዲያውኑ ከትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድን ተለይተው ለአንድ ተልእኮ ወደ ዓዲግራት አከባቢ ወደ ዓዲ አውሊዕ ከሌላ አባል ጋራ ተልከው አንድ ቤት ውስጥ እያሉ በአከባቢው አርሶ አደሮች ተከበው ተያዙና አርሶ አደሮቹ ወዲያውኑ ወደ ዓዲግራት በመውሰድ ለደርግ አሳልፈው ሰጡዋቸው።
ዓዲግራት ላይ ሲመረመሩ የኢህ አፓ ትጥቅ ትግል ጀማሪዎች አባላት መሆናቸውን ከድተው የጀብሃ አባላት ነን ብለው፣ ቃላቸውን ስለሰጡ በጅብሃ አባልነታቸው ወደ ኤርትራ አስመራ እንዲላኩና ጉዳያቸው እዛ እንዲወሰ ተደረገ። በጀብሃ አባልነታቸው የ7 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸው አስመራ ሰምበል እየተባለ ሲታወቅ ወደነበረው ወህኒ ቤት እንዲወርዱ ተደረገ። በ1969 ዓ.ም. ሻዕቢያ ሰምበል ወህኒ ቤት የነበሩ አባላቱን ለማስፈታ በወህኒ ቤቱ ላይ በወሰደው እርምጃ እነ ጓድ ጋይምም አብረው በሻዕቢያ አባላት ከወህኒ ቤቱ ተፈተው ወደ ዳግም ወደ ድርጅታቸው ኢህ አፓ በዓሲምባ ላይ ተቀላቀሉ።
እነ ጓድ ጋይም ከኤርትራ በተመለሱበት ማግስት በ1969 መጨረሻ አጋማሽ በኢህ አሰ ውስጥ በትግራይ በተደረገው የእርማት እንቅስቃሴና አዲስ አወቃቀር መሰረት የሰራዊቱ ጠቅላይ ፓርቲ ኮሚቴ አባል አባል ሆኖ ተመረጠ። በ1970 ከህወሓት ጋራ በትግራይ በተደረገው ጦርነት ኢህ አሰ ተሸንፎ በኤርትራ በኩል ወደ ጎንደር ሲያፈገፍግ ጓድ ጋይምም አብሮ አፈግፍጎ ጎንደር (ጸለምት) ገባ። በ1971 ዓ.ም. ጸለምት የተሰባሰበው ኢህ አሰ ወደ 4 ሪጅን ሲከፋፈል ጓድ ጋይም በዛው በጠፓኮ ሃላፊነቱ የጠፓኮ ተወካይ በሪጅን 4 (ወልቃይት) ሆኖ ተመድቦ ህወሓት በድጋሚ ወደ ወልቃይት በመሻገር በሪጅን 4 የነበረ ኢህ አሰን በጦርነት አሸንፎ እስከሚያለቅቅ እዛው ሪጅን 4 ቆየ። በ1972 ህዳር አከባቢ ሪጅን 4 በህወሓት ተሽንፎ ወደ ሪጂን 1 ጸለምት ሲያፈገፍግ ጓድ ጋይምም አብሮ ወደ ጸለምት አፈገፈገ።
በ1972 በኢህ አሰ ውስጥ በተከሰተው ብተና በርካታ አባላት ወደየ አቅጣጨው በመበታተን ምክንያት ከፍተኛ ጨልምተኝነት በትግሉ መቀጠል ላይ በተፈጠረበት ወቅት ብዙዎቻችን ትግሉን የቀጠልን ሲኒየር አባላት ከዛ ጨለምተኝነት ወጥተን ትግሉን ለመቀጠል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱት አመራር ጓዶች ጓድ ጋይም አንዱ ነበር። ብተናው ተጠናቆ፣ የሚሄደው ወደየምሄድበት ሂዶ፣ ትግሉን እንቀጥላልን ያልን አባላት ተነጥለን ጸለምት ከቀረን በኋላ በተግባር ራሳቸው አርአያ በመሆን አመራር ሲሰጡ ከነበሩት መሪዎች አንዱ የነበረው ጓድ ጋይም ሰራዊቱ ትግሉን ለመቀጠል ጊዜ ወስዶ በጥልቀት ለመወያየት ወደ ኤርትራ በሄደበት ወቅት ጸለምት በመቅረት ሰራዊቱ ተወያይቶ እስከሚመለስ አከባቢውን እያጠኑ እንዲቆዩ በፈቃደኝነት በአካቢው ከቀሩት ወደ 10 የሚሆኑ ሲኒየር አባላት አንዱ በመሆን እዛው ጸለመት ቀረ።
በ1972 ለስራ ተልእኮ ከአንድ ሌላ ጓድ ጋራ ሆነው ማይሓርገጽ ካለው የሞኖኮሳን ሰፈር አጠግብ ሲደርሱ በድንገት ከአንድ ጸረህዝብ ጋራ ተገናኝተ በተከፈተው ቶክስ እጁ ላይ ቆሰለ። ቁስሉ ለጊዜው ከላይ የደርቀ ቢምስልም ክውስጡ አልዳነም ነበርና ተምልሶ ማበጥና መግል መፍጠር ጅመረ፣ ቀስ በቀስም እየሰፋና ጋንግሪን እየፈጠረ መሄድ ቀጠለ። በውቅቱ በቦታው የነበርን አባላት እንኳን ወደ ጋንግሪን ያደገ ቁስል ማከሚያ መድሃኒትና ባለሙያ ስላልነበረን የጓዱ እጣፋንታ ቀስ እያለ በእጁ የጅመረው ጋንግሪን ሞላው ሰውነቱን በክሎ መሞት እየሆነ መጣ። ገና የእጁ ቁስል እየባሰበት በነበረብት ወቅት ብረቱን እንዲያወርድ ተደርጎ ስለነበረ እንጂ ብረት ይዞ ቢሆን ኖሮ ራሱን ለመጨረስ ወደሚፈልግበት ደራጃ ደረሰና እባካችሁ ከዚህ ስቃይ ገላግሉኝ ማለት ጀመረ። ህይወቱ በራሱ ቁጥጥር ስር ሳትሆን በኛ በጓዶቹ እጅ ቁጥጥር ስር ሆነችና ምን እናድርገው የሚለውም እኛ በቦታው የነበርን ሲንየር አባላት ወሰንለት። ውሳኔያችን ደግሞ ጓድ ጋይም ለህወሓት እጁን እንዲሰጥ የሚል ሆኖ ይህንን ውሳኔያችን ጓዱ እንዲቀበለው ማሳመን ኣለብን የሚል ነበረ። ውሳኔያችን ሲነገረው ጓድ ጋይም ፈጽሞ አለ። ከብዙ ውይይት በኋላ ግን ውሳኔያን ተቀብሎ ጓዱን ወስደን ቤት ሙሉ (ወልቃይት) በሚባል ሰፈር የህወሓት አባላት ከነበሩበት ቦታ አጠገብ አድርሰን በቦታው ለነበሩ የህወሓት ታጋዮች እጁን እንዲሰጥ ተደረገ።
ህወሓትም እንደገምትነው ከጓዱ ማግኘት የምትፈልገውን ለማግኘት መጀመሪያ ጓዱን ማሳከም አስፈላጊ መሆኑ አምናበት በቀጥታ ወደ ህክምና በመውሰድ አሳከመቸው። ከዛም 06 እየተባለ በሚታወቀው የህወሓት ምርመራና እስራት ክፍል ወስዳ ከመረመረችው በኋላ እዛው 06 ሆኖ የተለያየ የትርጉም ስራ እንዲሰራላቸው አደረገች። ብ1972 መጨረሻ አከባቢ ህወሓት ማይጸምሪን ለመምታት ስትዘጋጅ ጓድ ጋይም አከባቢውን ያውቅ እንደነበረ የህወሓት አመራር ስላወቀ ለጓዱ ስለ አከባቢው የምያውቀውን ሁሉ እንዲነግራቸው ጠየቁትና ጓዱ በነበረው ችሎታ ጥሩ የሆነ በካርታ የተደገፈ የማይጸምሪና አከባቢዋ አስፈላጊ መረጃ ሁሉ በሚገባ ሰጣቸው። የህወሓት መሪዎች በአቀራረቡና የመረጃው ጥልቀት በጣም ተደስቱና ማይጸምሪን ለመምታት ከሚንቀሳቀሰው ሀይል ጋራ በመንገድ መሪነት የዘዉት ወደ ማይጸምሪ ወሰዱት። ጓዱ የመንገድ መሪነቱን ተልእኮዉን በሚገባ ተውጥቶ ኦፐረሽኑም የተሳካ ስለሆነ በአመራሩም በአባላቱም እሱ ላይ የነበረ የጠበቀ ጥበቃ ከኦፐረሽኑ በኋላ በተወሰነ ደራጃ ላላ ማላቱን በሚገባ ተመለከተ። ከኦፐረሽኑ በኋላ ሀይሎች በአከባቢው ገጂ ቦታውችንና ወደ ማይጸብሪ የሚያገቡ መንገዶች በሙሉ በሀወሓት ታጋዮች ተይዘው ጥበቃ እየተደርገ በከተማውና በአክባቢው አንዳንድ ስራዎችን ለመስራት የህወሓት ጦር እዛው በቆየበት ቀናት ጓድ ጋይም ስትጠብቀው ከነበርችው ጋንታ ወደ አመራሩ ሲጠራ በቀን ጊዜ ያለ ጠባቂ ሁሉ መመላለስ የምችልበት ሁኔታ ተፈጠረና የጥበቃው ሁኔታ መላላቱን በሚገባ ተገነዘበ። እሱን የምትጠብቅ የነበረች ጋንታ ሰፈሯ የዋርዲያ ጠረር እየተባለ ሲጠራ ከነበረው ከማይጸምሪ ከተማ ወደ ዓዲወሰኔ ማውጫ መንገድ አጠገብ ከነበረው ጉብታ ስለነበረ በከተማዋ የሚደረግ እንቅስቃሴና የከተማዋ መውጫና መግቢያ መንገዶች ሁሉም በሚገባ ለማየትና ለመቆጣጠር አመች ነበር። የህወሓት አባላት ምንም የማያውቁዋት፣ ከተወሰነ ሰው ውጭ የከተማዋ ነዋሪዎችም ብዙ የማይውቁዋት ከከተማው ወደ ብራ የምታወርድ ገደላማ መንገድ መኖሯን ጓድ ጋይም ያውቅ ስለነበረ፣ በዚች መሽሎኪያ መንገድ ለምሽሎክ ጅግጅቱን ጀመረ። ከማይጸብሪ ድል በኋላ በሁለተኛው ቀን ማምሻ ላይ በድሉ የተደሰተው የህወሓት ሰራዊት በየአከባቢው ተሰባስቦ በጭፈራ ላይ እያለ ለማምለጥ አመች ሰዓት ያኔ መሆኑ ያውቀ ጓድ ጋይም ለማምለጥ ዝግጅቱን ሆዴን እየቆረጠኝ ነውና ሊጸዳዳ እፈልጋለሁ በማለት ጀመረ። ተፈቅዶለት ዋርዲያ ተስጥቶ ወደ መጸዳጃ ቦታ እንደሄደ ጠባቂው ትንሽ ራቅ ብሎ እየጠበቀው እያለ አንደሚጸዳዳ ሰው ሱሪውን ሳይፈታ ቁጭ ብሎ ትንሽ ከቆየ በኋላ ተንስቶ ከጉብታዋ ወደ ከተማው በኩል ሮጠ። ጨለማ ስለነበረ ጠባቂው ቢተኩስበትም ሊመታው አልቻልምና ጓዱ አምልጦ ወደ ከተማው በመውረድ በቀጥታ ወደ ገደሏ መንገድ ሮጦ በመሄድ ገደሉን ወርዶ ወደ ብራ ወረደ። ከብራ ወደላይ ወደ ደጋ በኩል በማቅናት ማይጸምሪ ዓዲ ኣርቃይ የሚወስደውን የመኪና መንገድ አቋርጦ ወደ ሃዋዛ አቅጣጫ ወጥቶ ተሸሸገ።
ህወሓቶች ማምለጡን እንዳወቁ እሱ እንደገመተው ፍለጋውን ወደ ታች ወደ ብራና ዋልድባ በረሃ በኩል አደረጉና ሌሊቱና ቀኑን ሙሉ ፈልገው ሊያገኙት ስይችሉ ቀሩ። ህወሓቶች ከሁለት ቀን ፍለጋ በኋላ ተስፋ ቆርጠው ፍለጋውን አቁመው፣ በማይጸምሪ የነበራቸው ቆይታም ጨርሰው፣ አከባቢውን ለቀው እስከሚሄዱ ከቅርብ ርቀት እዛው ዋሲያ አከባቢ ሆኖ ሲከታተል ከቆየ በኋላ፣ አከባቢውን ሙሉ በሙሉ ለቀው መውጣታቸውን ከተረዳ በኋላ ከዋሲያ በብራ በኩል አቋርጦ በደምብ ወደሚያውቀው የነበረ ዋልድባ በርሃ ገብቶ ከኢህአሰ ጋራ ለመገናኘት የምችለበት የራሱ መላ መዘየድ ጀመረ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላም በወቅቱ በወልቃይት አከባቢ ስትንቀሳቅሰ ከነበረችው አንዲት የኢህ አሰ እስኳድ ጋራ በራሱ መንገድ ግኑኝነት መስርቶም ከእስኳዱዋ ጋራ ተገናኝቶ ዳግም ከኢህአሰ ጋራ ተገናኘ። ኢህአሰ ግጨው በረሃን ማእከሉ አድርጎ በጸገዴና አርማጭሆ በቆየበት የሁለት ዓመት ጊዜ በሰራዊቱ ኢንተልጀንስ ክፍል ተመድቦ ተግባሩን በሚገባ ሲያከናወነ ቆየና በ1974 ሰራዊቱ የተወሰኑ ከሃዲዎች በቢትወደድ አዳነና ሰዎቻቸው ላይ በፈጸሙት አስነዋሪ ግድያ ምክንያት ከጸገዴና አርማጭሆ ህዝብ ጋራ ባደረገው አስከፊ ጦርነት ምክንያት ኢህ አሰ አክባቢዉን እንዲለቅ ተገዶ፣ በጭልጋ በኩል ወደ ቋራ ሲያፈገፍግ፣ ጓድ ጋይምም አብሮ ቋራ ገባ። በ1974 አጋማሽ አከባቢ ሰራዊቱ ቋራ ከገባ በኋላ በሰራዊት አመራር ደረጃ ተመድቦ እስከ የኢህ አፓ ሁለተኛ ጉባኤ በሰራዊት አመራር ደረጃ ከሰራ በኋላ በ1976 በቋራ በተደረገው የፓርቲው ሁለተኛ ጉባኤ የፓርቲው ማእከላዊ ኮሚቴ አባል ሆኖ ተመርጦ ማገልገል ጀመረ። 1983 ደርግ ወድቆ ኢህ አዴግ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ህወሓት በቀጥታ ከሱዳንና ከማሀል አገር ኢህ አሰንና ብሎም ኢህ አፓን ከትግሉ ሜዳ ፈጽሞ ለማጥፋት በከፈተው ጦርነት ወቅት በቋራ ሰራዊቱን እያስተባበረ ሲያዋጋ ቆይቶ፣ ሰራዊቱ ባብዛኛው በህወሓት ተመቶ የሚክደ ክዶ የሚማረከው ተማርኮ፣ የሚሞተ ሙቶ የሰራዊቱ ቁጥር እጅግ በተመናመነበት ጊዜ ካሞፍላጅ አድርጎ ከ1983 ግንቦት እስከ 1984 ለአንድ ዓመት ያህል ተቋርጦ የነበርውን የሜዳ ከሱዳን ግኑኝነት እንደገና ለመፍጠርና ሜዳና ሱዳን የነረውን የድርጅቱ መዋቅር ለማገናኘት ብሎም ሱዳን ከነበርን አባላት ጋራ ስለ ትግሉ እንዴት እንቀጥል የሚለውን ለመምከር በ1984 ሰኔ ላይ ወደ ሱዳን (ገዳሪፍ) ገባ።
ሱዳን ላይ ከነበሩ ሲኒየር አባላትና በወቅቱ ሱዳን የነበረ ብቸኛ የማእከላዊ ኮሚቴ አባል ዖስማን ጠዊል (ሳሙኤል አለማይርሁ) ጋራ ስለ ሰራዊቱ ሁኔታና ከንግዲህ ትግሉን እንዴት እንቀጥል በሚለው ከመከረ በኋላ ሳይቆይ በመጣበት መንገድ ወደ ቋራ የተዋቸው ጥቂት ጓዶቹ ተመልሶ ስለ አጠቃላይ ሁኔታ ከነሱ ጋራ መክሮ፣ በቋራ የነበረው ትጥቅ ትግል የመቀጠል ሁኔታ እየደበዘዘ መሆኑ ተርድቶ ከጓዱ ጋራ በመመካከር፣ እሱና ውሱን ጓዶች ካሞፍላጅ አደርገው በ1984 መጨረሻ አከባቢ ሜዳን ትተው ወደ ከተማ ትግሉን በህቡዕ ለመስቀጠ ገቡ። በ1985 መጀመሪያ ላይ ጓድ ጋይም አዲስ አበባ ገብቶ አዲስ አበባን ከተለየዩ ከተሞች የሚያገናኝ መዋቅረ ዘርግቶ በህቡእ አዲስ አበባ እየኖረና እየሰራ እያለ ጓድ ጋይም አዲስ አበባ መገባቱና አዲስ አበባ ሆኖ የኢህ አፓን ድርጀታዊ የስራ መሆኑ ለህወሓት ደህንነቶች መረጃ ደረሳቸው። የህወሓት ደህንነቶች ደግሞ ከዛች ዕለት ጀምረው ያድኑት ጀመር። ከብዙ አደና በኋላ ግንቦት 11 ቀን 1985 ዓ.ም. አዲስ አበባ የነበረበት ቤት ታውቆ፣ ቤቱ ተክቦ እጁን እንዲሰጥ ተጠየቀ። ለህወሓት ደህንነቶች እጁን ቢስጥ የሚከተለውን እርምጃ ጠንቅቆ የሚያውቅ የነበረው ጓድ ጋይም እጁን ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረና ቶክስ ተከፈተ። በቶክሱም እሱም ገድሎ በመጨረሻ በበርካታ ጥይቶች ተመቶ ተሰዋ።
በክፍል 22 የኢህ አሰ የ1973 ግጨው በርሃን ማእከል ያደረገ እንቅስቃሴ ምን ይመስል ነበር ይጄላችሁ እቀርባለሁ። እስከዛው በቸር ሰንብቱ፣ ላልደረሰው ማዳረሱን ኣትርሱ፣ የነገ ሰው ይበለን።
ክብርና ሞገስ ለሁሉም ለዓላማቸው ውድ ህይወታቸውን ለከፈሉ ሰማዕታት!!!
በየነ ገብራይ፣ ከደንማርክ
ምንጭ ዕረና ትግራይ