የአልቃይዳ ክንፍ የሆነው አልሸባብ በአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ከሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ከወጣበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ወዲህ፣ በሶማሊያም ሆነ በኬንያ የተለያዩ ጥቃቶችን እየሰነዘረ ይገኛል፡፡
በምዕራባውያን የሚደገፈውን የሶማሊያ መንግሥት በመቃወም በሶማሊያ ውጊያ የሚያካሂደው አልሸባብ፣ በፈራረሰችው ሶማሊያ ዓላማውን ማሳካት አልሆነለትም፡፡ ሆኖም በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጽመው የሽብር ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩትን ገድሏል፡፡ ከሶማሊያም ወጣ ብሎ በኬንያ በሚያደርገው ጥቃት ብዙዎችን ቀጥፏል፣ ንብረት አውድሟል፡፡
አልሸባብ ከኢትዮጵያም ሆነ ከአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል በሚደርስበት ተፅዕኖ ቢራቆትም፣ የተለያዩ ዘዴዎችን እየተጠቀመ ሶማሊያን ከማተራመስ አልተቆጠበም፡፡ ከሶማሊያም አልፎ በኬንያና በሌሎች አገሮች የሽብር ጥቃት ለመሰንዘር መጠነ ሰፊ ሥልጠና ይወስዳል፡፡ በኬንያም የሽብር ጥቃቱን በተደጋጋሚ ያደርሳል፡፡
ከሞቃዲሾ ለቆ ከወጣ ወዲህ ተዳክሟል ቢባልም በሶማሊያ ሰላም ሊሰፍን አልቻለም፡፡ ቡድኑን ጥቃቱን ከመፈጸም የገታውም የለም፡፡ ዘመናዊ መሣሪያ ታጥቋል፡፡ አባላቱም ፈታኝ በተባሉ ሁኔታዎች አልፈው ጥቃት ስለሚያደርሱበት ሥልት ይሠለጥናሉ፡፡ ለዚህም አልቃይዳ የጀርባ አጥንት ሆኖ ያገለግላል፡፡
የአልሸባብ አባላት በሶማሊያ በሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይልና በአሜሪካ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ልዩ ሥልጠና እየወሰዱ እንደነበር ቢቢሲ ፔንታጐንን ጠቅሶ ሰሞኑን ዘግቧል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች የአልሸባብ ልዩ የጦር አባላት ይሠለጥኑበት የነበረውን ካምፕ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ አውድመዋል፡፡
ፔንታጐን እንዳስታወቀው ከሞቃዲሾ በስተ ሰሜን 195 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የአልሸባብ የሥልጠና ካምፕ ላይ የአየር ድብደባ ከ150 በላይ ተዋጊዎች ተገድለዋል፡፡
የፔንታጐን ቃል አቀባይ ካፒቴን ጄፍ ዴቪስ እንደሚሉት፣ በካምፑ ይሠለጥኑ የነበሩት የአልሸባብ አባላት በአሜሪካና በአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ለማድረስ ነበር፡፡
‹‹የካምፑን ሥልጠና ጨርሰው ሊወጡ እንደነበር ደርሰንበታል፡፡ በመጀመሪያው ዙር ከ150 የሚበልጡ የአሸባሪ ተዋጊዎችን ገድለናል፤›› ብለዋል፡፡
የአየር ድብደባው የተካሄውም ቅዳሜ የካቲት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰው አልባ (ድሮን) እና በጦር አውሮፕላኖች ሲሆን፣ ድብደባውም በራሶ ካምፕ ውስጥ ይሠለጥኑ በነበሩት ልዩ የአልሸባብ ተዋጊዎች ላይ ያነጣጠረ እንደነበር ካፒታል ዴቪስ ገልጸዋል፡፡
የራሶ ካምፕ ለተወሰኑ ጊዜያት እየተሰለለና ቁጥጥር እየተደረገበት እንደነበር፣ የአልሸባብ አባላትም ሥልጠናውን ጨርሰው ወደ ማጥቃት ሊሸጋገሩ ጥቂት ሲቀራቸው ዕርምጃው እንደተወሰደም አክለዋል፡፡
የፔንታጐን ቃል አቀባይ አልሸባብ ሊፈጽም ስለነበረው የጥቃት ዓይነት ዝርዝር መግለጫ ከመስጠት ቢቆጠቡም፣ ቡድኑ መጠነ ሰፊ ጥቃት ለመፈጸም ተዘጋጅቶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ቡድኑ ባለፈው ወር በባይዳዋ በሚገኝ ምግብ ቤት ውስጥ ሁለት ፍንዳታዎችን መፈጸሙን አስታውቆ ነበር፡፡
ባለፈው ሳምንት ደግሞ የአውስትራሊያ ባህር ኃይል በዓሳ ማጥመጃ ጀልባ ውስጥ የተጫነና ከኦማን ወደብ ተነስቶ ወደ ሶማሊያ ሲጓጓዝ የነበረ የጦር መሣሪያ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል፡፡ ጀልባው ላውንቸሮችና ከ2,000 በላይ ከባድ መትረየሶችን ይዞ እንደነበርም የባህር ኃይሉ ቃል አቀባይ አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ ጦር ኃይል በሶማሊያ፣ በሊቢያና በናይጄሪያ የሚገኙ የሽብር ቡድኖችን ለመምታት እንቅስቃሴ ከጀመረ ከርሟል፡፡ በጂቡቲ ከሚገኘው የጦር ኃይሉ ካምፕ በመነሳትም፣ በአልሸባብ ላይ በሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ውጤታማ መሆኑን የአፍሪካ ሴኪዩሪቲ ኮሮስፖንዳንት ቶሚ ኦላዲፖ ዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2014 በአሜሪካ ድሮን ጥቃት የተገደለውን የጀሃዲስት ቡድኖቹ መሪ አህመድ ጎዳኔንም በመጥቀስ፣ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ቡድኑ እየተሰለለ እንደሆነ ደርሶበታል፡፡ ሆኖም ከኤሌክትሮኒክስ የስለላና የቁጥጥር መሣሪያዎች ዓይን ሊሰወር አልቻለም ብሏል፡፡
አልሸባብ የመሪውን መገደል ተከትሎ ጥቃት ውስብስብ ለማድረግ ሥልጠና ይወስዳል፡፡ በተግባር ደግሞ እዚያው ሶማሊያና ኬንያ ውስጥ ያሳያል፡፡ አሜሪካ እንደምትለው አልሸባብ አሁን ለመፈጸም አቅዶት የነበረው ጥቃት መጠነ ሰፊ ነበር፡፡ ለጥቃቱም ከ150 በላይ የሚሆኑ አባላቱን አሠልጥኗል፡፡ ቡድኑ በአሜሪካ የጦር አውሮፕላኖች ከመመታቱ በፊትም ሥልጠናውን አጠናቅቆ ከካምፑ የሚወጣበት ጊዜ ደርሶ ነበር፡፡ ሆኖም አሜሪካ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት አስቁሜያለሁ የምትልበትን ምት በአልሸባብ ላይ አሳርፋለች፡፡
እ.ኤ.አ. 2016 ከገባ ወዲህ በባይዶዋ 30፣ በሞቃዲሾ ኤስዋይኤል ሆቴል ዘጠኝ፣ በሞቃዲሾ ሊዶ ወደብ 20 ዜጎችን፣ እንዲሁም የኬንያ የጦር ካምፕ በሚገኝበት ኤልአዲ 180 ወታደሮችን የገደለው አልሸባብ ከአይኤስ ጋር ግንኙነት የለውም ይባላል፡፡
ቶሚ ኦላዲፖ እንደሚለው፣ አይኤስ በምሥራቅ አፍሪካ ይዞታውን ለማስፋፋት ቢሠራም፣ የአልሸባብ ድጋፍ የለውም፡፡ የአልሸባብ ጥያቄ ሶማሊያ በምዕራባውያን በሚደገፉ ዜጎች አትመራም የሚል ሲሆን፣ ታማኝነቱም ለአልቃይዳ ነው፡፡
በናይጄሪያ የሚገኘው ቦኮ ሐራም መነሻው በናይጄሪያ ያለው አገዛዝ ፍትሐዊ አይደለም፣ መንግሥት መለወጥ አለበት የሚል ቢሆንም፣ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት የአይኤስ አጋር መሆን እንደሚፈልግ አስታውቆ በአይኤስ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
በጦርነትና በሽብር ጥቃት ረዥም ዓመታትን ባሳለፈችው ምሥራቅ አፍሪካ የሚገኘው አልሸባብ እስካሁን የአይኤስ አጋር መሆኑን ባይገልጽም፣ ለአልሸባብ አባላትን ከፑንትላንድ ወጣቶችን የሚመለምለው ሼክ አብዱልቃድር ሙሚ፣ ለአይኤስ አጋር ነን ሲል አሳውቋል፡፡
ሆኖም በሶማሊያ የሚገኘው አልሸባብ አባላት በአይኤስ ጉዳይ ላይ እንዳይወያዩ ገደብ ጥሏል፡፡ የአይኤስ ዓይነት አመለካከት ያንፀባረቁ ሁለት ከፍተኛ ኮማንደሮችን ጨምሮ የውጭ ዜግነት ያላቸው አባላቱን ማሰሩን የአልሸባብ ደጋፊ የሆነ ሚዲያ ዘግቧል፡፡ አባላቱም ወደ አይኤስ ለመቀላቀል ብለው ክህደት እንዳይፈጽሙም አስጠንቅቋል፡፡
የአልሸባብ አባላት በአይኤስ ፕሮፓጋንዳ ተስበው ወደ ቡድኑ የሚቀላቀሉ ከሆነ፣ በሶማሊያ ያለው አለመረጋጋት ወደ ከፋ ደረጃ ይሸጋገራል የሚሉ አሉ፡፡ ጦርነቱም በአይኤስ፣ በአልሸባብና በሶማሊያ መንግሥት መካከል ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ለሶማሊያ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያና ኬንያም ትልቅ ሥጋት ነው፡፡
- በጋዜጣው ሪፖርተር’s blog
- 1498 reads