እርቃን ሲቀሩ ከሕዝብ ለመታረቅ ? በቅድሚያ እስረኞችን መፍታት የጎሳ ፖለቲካ ፖሊሲና ዜጎችን ሽብርተኛ እያሉ መፈረጅ መቆም አለበት:: ስልጣን ለሕዝብ ማስረከብን ይጨምራል:: የኢትዮጵያውያን ጥያቄዎች እጅግ ብዙ ናቸው::የሕዝብን ጥያቄ ሳይመልሱ ኖሮ አሁን እመልሳለሁ ማለት በሕዝብ ላይ መቀለድ ነው::ሕወሓት የሚረግመው የሰው ደም መጣጩ ደርግ በ17 አመቱ ቆይታው እንኳን ባለፉት 25 አመታት የተፈጠሩ ችግሮችን አልፈጠረም:: በዲሞክራሲ ስም አልነገደም በግልጽ አፋኝ ነኝ ብሎ በግልጽ ነበር የዜጎችን ደም የሚጠጣው ይህ ብቻ አይደለም ዜጎችን ጸረ አብዮተኛ ብሎ ቢፈርጅም አምልጠው ስደት የሄዱትን እንኳን በፖለቲካ እምነት እንደወጡ አምኖ የተቀበለ ወታደራዊ ጁንታ ነበር::ደርግን ማንሳት በኔ ባያምርም ሕወሓቶች ራሳቸው የሚያወዳድሩት ወደፊት ከሚኬደው ሳይሆን ከተቀበረ ሬሳ ጋር ስለሆነ ምክንያቱ ይህ ነው::

ወደ ሰሞነኛው ጉዳያችን ስንገባ ሕወሓት መራሹ አገዛዝ ከትግራይ እስከ ደቡብ ጫፍ ሕዝቡ ተመሳሳይ ተቃውሞ አንስቷል በተለይ በኦሮሚያ በተግባር ዞር በሉ ብሎናል ችግሩን በመፍታት ከሕዝቡ መታረቅ አለብን:: የሚል ዲስኩር አያሰማ ነው::አገዛዙ ከሕዝብ ጋር ቅራኔ የገባው የጎሳ ፖለቲካውን በአገሪቱ ላይ ካወጀ ጀምሮ እንዲሁም ሃሳባቸውን በነጻነት በገልጹ መብታቸውን የጠየቁ ምንም ያልታጠቁ ሰላማዊ እና ደሃ ዜጎችን አሸባሪ ብለኦ ሲፈርጅ ሲያስር ሲገድል እና ተመሳሳይ ጸረ ሕዝብ እርምጃዎችን ሲወስድ መሆኑን ባለፈው 20 አማእታት አልተረዳውም:: ወያኔ ምንም ጊዜ የሚነቃው ሕዝብ ነቅቶ ከጨረሰ በኋላ ነው::ነቅቻለሁ ብሎ ፖሊሲ ቢለውጥ ጥሩ ነው ሆነኦም እያወቀ በሕዝብ እና አገር ላይ ጥፋት በተደጋጋሚ እየፈጸመ ይገኛል::ከሕዝብ ለመታረቅ በቅድሚያ እስር ቤቶች ማጽዳት(በሽብር እና በተመሳሳይ ወንጀል በሃሰት ተፈርጀው የታሰሩትን መፍታት) የጎሳ ፖለቲካ ፖሊሲና ዜጎችን ሽብርተኛ እያሉ መፈረጅ መቆም አለበት::ከዚህ በመቀጠል ስልታን በመልቀቅ ወርዶ ሕዝባዊ መንግስት መመስረት ብቸኛ መፍትሄ ነው::

በሃገራችን ጉዳይ ሁላችንም ዜጎች ይመለከተናል::ሃገር የጥቂቶች መፈንጫ ልትሆን አይገባም::በሃሰት እና በፕሮፓጋንዳ አገር ማስተዳደር ውጤት አልባ ያደርጋል ይህን ደግሞ ካለፉት 25 አመታት ሂደት መማር ግድ ይላል:: አገሪቱ ላለፉት 50 ዓመታት አይታው በማታውቀው ድርቅ ምክንያት ችግር ውስጥ የገቡ ከአሥር ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያንን መታደግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በኦሮሚያ በርካታ አካባቢዎች ከአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በመቃወም የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ፣ በአማራ ክልል የቅማንት ማኅበረሰብ የማንነት ጥያቄ ተከትሎ የተቀሰቀሰ በጦር መሣሪያ የታጀበ ግጭት፣ በኦሮሚያ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለመመለስ የክልሉ መንግሥትና ፓርቲ የጋራ ማስተር ፕላኑ እንዲታጠፍ መደረጉን ቢገልጹም፣ ተቃውሞው መልኩን ቀይሮ በሌሎች አካባቢዎች ቀጥሎ ይገኛል::እንዲሁም የወልቃይት ጠገዴ በሃይል ከትግራይ ክልል መጠቃለሉ ተቃውሞ አስነስቷል::የቁጫ ሕዝብ የኮንሶ ሕዝብ የመዠንገር እና የሱርማ ሕዝብ ጥያቄዎች የጋምቤላ ግጭት በተጨማሪም በመላው ሃገሪቱ ተስፋፍቶ የሚገኙ በርካታ ጥያቄዎች እና ተቃውሞዎች የፈጠራቸው የሕወሓት አገዛዝ የሚከተለው እና ስህተት ነው ብሎ ያመነበት የፖለቲካ የኢኮኖሚ እና የማህበረሰባዊ ፖሊሲዎች መሆናቸው እሙን ነው::

በአገሪቱ የተንሰራፋው የጎሳ ፖለቲካ ሕዝቦች በሃገሪት እንደ ዜጋ ተዘዋውረው የመስራት መብታቸውን ገፏል::በአንድ ብሄር የበላይነት ኢኮኖሚውን ለመቆታጠር የሚደረገው ሩጫ ሌሎች ዜጎች ደሃ እንዲሆኑ አድርጓል::ለዚህ ሁሉ ግን መፍትሄው ይቅርታ ሳይሆን ስልጣን መልቀቅ ነው::በኦሮሚያ ክልል ለተደረገው ግድያ ተጠያቂው ማነው? ከፌዴራሉም ይሁን ከክልሉ ግድያውን ያዘዘው ተጠያቂው ክፍል በአለም አቀፍ ሕግ መሰረት ለፍርድ መቅረብ አለበት::እንዲሁ መላቀቅ የለም:: እያንዳንዱዋ ጉዳይ ወደ ተግባር እንድትቀየር በተግባር መታገላችን እንቀጥላለን:: ‪#‎ምንሊክሳልሳዊ‬  Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ)

Leave a Reply