የብሄር ፖለቲካ ትርኢት በዩኒቨርስቲዎቻችን
=======================
የኢህኣዴግ መንግሰት መንበረ መንግስት ከመቆጣጠሩ በፊት በኢትዮጵያ ከሁለት ያልበለጡ ዩኒቨርስቲዎች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ በነዚህ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ተማሪዎችም የሚማሩት ትምህርት ጥራት ያለው ስለነበር ብቁ እና ተወዳዳሪ እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ቁጥራቸው ትንሽ ቢሆንም ተማሪዎቹ በዘር ፣ በብሄር፣ በጎሳና፣ በነገድ ያልተከፋፈሉ በኢትዮጵያ አንድነት ጥላ ስር ፀንተው ዘውዳዊውና ወታደራዊው ጭቆና ለማስወገድ በጋራ ተዋድቀዋል፡፡
ለምሳሌ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የነበሩ ተማሪዎች ትላልቅና ጥልቅ ፖለቲካዊ ክርክሮች በማድረግ፤ ታገል(struggle) የሚባል ጋዜጣ በማሳተም ፀረ ፊውዳሊዝም፣ፀረ ኢመፐርያሊዝም እና ፀረ ቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ብርቱ ትግል አድርገዋል፡፡ የተማሪዎቹ ማህበርም መጠርያው የአዲስ አበባ ተማሪዎች ማህበር እንጂ የዚህና የዚያ ብሄር ተዎላጆች ማህበር የሚል አይደለም ፡፡ ያኔ አአዩ አሁን ካለው አአዩ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡
A. ዛሬ በየብሄረሰቡ መደራጀት(የአማራ ብሄር ተዎላጆች ፣የትግራይ ብሄር ተዎላጆች ፣ የኦሮምያ ብሄር ተዎላጆች ፣ የሶማልየ ብሄር ተዎላጆች ፣ የአፋር ብሄር ተዎላጆች ማህበር … ወዘተ በሚል ስንጥቅጥቅ ብለዋል)፡፡ በብሄር መደራጀቱ ለጥሩ ቢሆንና ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ቢሆን ባልከፋ ነበር፡፡ አስከፊነቱ ውደብሄር ፍጥጫና ጠብ በፀሓይ ብርሀን ፍጥነት እየተቀየረ ለአገር አንድነት ፀር መሆኑ ነው፡፡
B. በየ ብሄረሰቡ የፖለቲካ ማህበር መሳተፍ( የህወሓት፡የዲህዴን፡የኦህዴድ፡የብአዴን)፡፡ በቃ ዩኒቨርስቲዎቹ የጥናትና የምርምር ተቋሞች ሞሆናቸው ቀርቶ የፖለቲካ ማጥመቅያ፤ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መናሃርያ ሆኖዋል፡፡ አህአዴግ የሚባል ገዢ ፓርቲ ላፀደቀው ህግ መቼም ተገዢ እንደማይሆን ያሳያል፡፡ ልክ በኣለም አቀፍ ደረጃ ኣንድ ህግ ሲፀድቅ ልእለ ሃያል አገሮች ሳያከብሩ ድሃዎቹ እና አፍሪካውያን ብቻ በህጉ እንዲታጠሩ እንደሚደረገው ሁሉ የኢትዮጵያ ህገመንግስትም ተቃዋሚዎች እንጂ ኢህአዴግ እንዲያከብረው አይፈለግም፡፡ ኢህኣዴግን የሚገዛ ህግ እስከአሁን የለም፡፡ የዩኒቨርስቲዎቻችን የትምህርት ጥራትም የወደቀው የትምህርት ነፃነት በኮሚኒቲ ፖሊሲንግ ታጥሮ በየዲፓርትመንቱ የፖለቲካ መሪዎች ተሹመው ተቋሙ የፖለቲካ እውድማ ስለሆነ ነው፡፡
C. ዛሬ እንደትናንቱ አዲስ አበባ የተለያዩ ሀሳቦች በነፃ የሚንሸራሸሩበት እድል የለም፡፡ ትላንት በሃፄ ሃይለስላሴ የነበረ የተማሪዎች ነፃነት ዛሬ ፍፁም የለም፡፡ በዩኒቨርስቲ ደረጃ በሃፄ ሃይለስላሴ የነበረ የመከራከርና ሃሳብን በነፃ የማንሸራሸር ነፃነት በኢህኣዴግ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ተዘግቶ በምትኩ በብሄር ፖለቲካ ተተክቶዋል፡፡
ወዘተርፈ…
በድምሩ ሲታይ ዩኒቨርስቲዎቻችን የዘር ፖለቲካ ትርኢት የሚንፀባረቅባቸው፤ተማሪው በየዘር ከረጢቱ ገብቶ እንዲደራጅ በማድረግ ብሄርተኛ ሆኖ እንዲወጣ ምቹ ሁኔታ የፈጠሩበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ሄደን ሄደን መጨረሻ ላይ መደማመጥ ጠፍቶ(አቅቶን) የባቢሎን ግንብ ሰራቶኞች እንዳንሆን ያሰጋል፡፡
በሰላማዊ መንገድ ተደራጅተን ፀረ ጥይት ፖለቲካ ፤ፀረ ብኄርተኝነት እንዲሁም ፀረ ከፋፍለ ግዛ ፖለሲ የሆነ ትግል የምናደርግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህንን አደገኛ አካሄድ ማከም ይጠበቅብናል፡፡ ከገዢው ቡዱን በተቃራኒ አቅጣጫ የኢትዮጵያ አንድነት በሚያፀናና የሃገር ፍቅር በሚጨምር መልኩ ሁነኛ አቅጣጫ በመቀየስ አገራችን ሁላችን በፍቅር አንድ ሁነን የምንኖርባት ለማድረግ መጣር ብሄራዊ ግዴታችን ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!

Leave a Reply