Wednesday, 16 March 2016 13:22

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በመንግሥት አስፈፃሚ፣ ሕግ ተርጓሚ አካላት ውስጥ የገጠሙትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ያስችለኛል ያለውን ንቅናቄ ከጀመረ ወራትን ቆጥሯል። በዚህ መሠረትም በዋነኝነት ከመሬት፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ፣ ከፍትህና ፀጥታ ጋር በተያያዘ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ፈጥረዋል የተባሉ ሹማምንትና በየደረጃው የሚገኙ ባለሙያዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል። ጠንከር ያለ እርምጃ ከወሰዱ ክልሎች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የአማራ እና የኦሮሚያ፣ የትግራይ ክልል ይገኙበታል። እነዚህ ክልሎች ጥፋት ተገኝቶባቸዋል የተባሉ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችን ከኃላፊነት የማንሳት፣ የማዘዋወር፣ ለሕግ የማቅረብ፣ የዲሲፕሊን እርምጃ የመውሰድ እና የመሳሰሉ እርምጃዎችን ወስደዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ዕለት የመንግሥትን የ6 ወራት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ለፓርላማው ባቀረቡበት ወቅት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የማጥራት ንቅናቄውን አስመልክቶ ካቀረቡት ሪፖርት፣ በፓርላማ አባላት ተጠይቀው ከሰጧቸው ምላሾች መካከል የሚከተሉት ተጠናቅረው ቀርበዋል።

·        እነሆ ፊሽካው ተነፍቷል፣ ግለቱ ሳይቀዘቅዝ ይቀጥላል፣

በዘንድሮ በጀት ዓመት መንግሥት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለማቃለል በደፈናውና በዘፈቀደ ከሚደረግ ይልቅ የጉዳዩን አሳሳቢነትና መንስኤዎች መሠረት በማድረግ ሊተገበሩ የሚችሉ መፍትሄዎችን በተለያዩ አካላት ቅንጅት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንዲጠና ተደርጓል። በዚህ መሠረት የፖለቲካ አመራሮች፣ የፌዴራልና የክልል ሌሎች አስፈፃሚ አካላት እንዲሁም የምልዐተ ሕዝቡ ተወካዮች በተለያዩ መድረኮች፣ በተለያዩ ጊዜያት ያነሱዋቸውን ጉዳዮች በማጠናቀር፣ ተጨማሪ ግብዐቶችንም በማከል በየደረጃው ግንዛቤ ለማስጨበጥ ተግባራዊ መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችሉ የንቅናቄ ሰነዶች እንዲዘጋጁ ተደርጓል። ከዚህ በመነሳት በተለይም በከተሞች በአዲስ አበባ እና በፌራል በተለያዩ አካላት እንዲሁም በክልል ቢሮዎችና በዋና ዋና ከተሞች በተጨማሪ በፍትህና ፍርድ አሰጣጥ ሥርዓት ውስጥ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ሥራዎች ተጀምረዋል። የመልካም አስተዳደር መርሆዎች አንዱ በሆነው የመንግሥትን አሰራር ግልፅ የማድረግ መርህ ላይ በመሥራት በጉዳዩ ላይ ግልጽነት እንዲሰፍን እና ችግሩ ከሕዝቡ የተደራጀና የነቃ ተሳትፎ ውጪ በጭራሽ እንደማይፈታ በማመን፣ የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማረጋገጥ የአሳታፊነት መርህን ተከትሎ መሥራት ተጀምሯል።

ሀገር አቀፍ ንቅናቄም እንዲፈጠር ችቦ ተለኩሷል። እስካሁን በተከናወነ ሀገራዊ ንቅናቄም ተስፋ ሰጪ ጅማሮው እየታየ ይገኛል። የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲባባስና ሕዝቡ ከመንግሥት የሚያገኘው አገልግሎት ከብልሹነትና ጉቦ እንዳይፀዳ ሲያደርጉ በነበሩ አካላት ላይ በየደረጃው የተጠያቂነት መርህ ተከትለን ተጠያቂ ማድረግም ተጀምሯል።

ሕዝቡ የተነቃቃ በመሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጣሪ በሆኑ አካላት አንድም በቀጥታ በመድረኮች በማጋለጥ፣ ሌላም በተለያዩ መንገዶች ያጋጠሙትን ችግሮች በማጋለጥ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ ጀምሯል። ይህም ሆኖ ከችግሩ ስፋትና ውስብስብነት አኳያ አሁን የተጀመረው ሥራ ሁኔታውን ለመለወጥ መሥራት እንደሚቻል ከመጠቆም አልፎ መሠረታዊ ለውጥ ከማምጣት አኳያ በጥልቀት መሠራት ስላለበት ግለቱ ሳይቀዘቅዝ፣ ሥራውን መቀጠልና ማስፋት ይጠይቀናል። ይህን ሥራ መቀጠሉ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የጥቅም መረቦች በተለያዩ ቦታዎች  እንደሚታየው መወራጨትን ማስከተሉ ስለማይቀር በምንም መልኩ ሳይቀለበስ እንዲቀጥል ማድረግ ይገባል።

ከዚያ አኳያ መንግሥት የጀመረውን መልካም አስተዳደር የማስፈን ሥራ ለልማታችን፣ ለዕድገታችን እንዲሁም ለመላው ሕዝባችን ተጠቃሚነትና ብቁ አገልግሎት የማግኘት መብቱ ላይ እንቅፋት የማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ በቁርጠኝነት የሚሠራና አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታችንን በዚህ አጋጣሚ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ።

·        ግንዱን ትቶ ቅርንጫፉን?!

ሕዝቡ ከሚያነሳቸው ጥያቄዎች መካከል መስማት አቅቷቹሃል፣ እየሰማችሁ አይደለም የሚለው ይገኝበት ነበር። በመካከሉ ትሰማላችሁ ግን ተግባራዊ እያደረጋችሁ አይደለም ተባልን፣ አሁን በደረስንበት ደረጃ ሕዝቡ እያለን ያለው ወደተግባር ገብታችኋል፣ ግን አስፉት፣ ጥልቀት እንዲኖው አድርጉ ነው። ለመሆኑ ይህ ሥራ ይቀጥላል ወይ? ብሎም ይጠይቃል።

የሕዝቡን አስተሳሰብ፣ አስተያየት በየጊዜው እየወሰድን፣ እየገመገምን፣ ራሳችንን እያጎለበትን መጥተናል። ከዚህ አኳያ መስማት አቁማችኋል ከሚባለው ተነስተን፣ መስማት ጀምራችኋል ግን አትተገብሩም ወደሚል ሄደናል፣ አሁን ደግሞ መስማት ጀምራቹሃል፣ መተግበርም ጀምራቹሃል ተብለናል። ይሄ ሁሉ የሕዝቡ ትክክለኛ አስተያየት ነው። መጨረሻ ላይ ማስቀጠል ትችላላችሁ ወይ፣ ቅርንጫፉን ብቻ ነው፣ ግንዱንም መልክ ታስይዛላችሁ የሚል ጥያቄ አለ። በእኛ እምነት ይህን ሥራ የምንሠራበት መነሻ የተወሰነ ማባበያ ሳይሆን መሠረታዊ ለውጥ ካላመጣ በስተቀር የሕልውና ችግርም ስለሆነ ነው። ስለዚህ ቅርንጫፍ ሄደም፣ አልሄደ መሠረታዊ ለውጥ ካልመጣ፣ ችግሩን ከሥር መሠረቱ የሚያቃልል ካልሆነ በስተቀር ሥራችን የሚፈለገውን ውጤት አያመጣም። ለምሳሌ አዲስ አበባ ላይ የአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር የጀመራቸው ጥሩ፣ ጥሩ ሥራዎች አሉ። እስከ ኃላፊዎች ድረስ እርምጃ ወስዷል። በፌዴራል መንግሥት ባስቀመጥነው ሥርዓት በምናይበት ጊዜ በቂ ስላልሆነ የፌዴራል መንግሥት ደግሞ በቀጥታ መጥቶ የሚወስዳቸው እርምጃዎች ይኖራሉ። ይህን በማድረግ የተጀመሩ ሥራዎችን የበለጠ እያጠለቅን እንሄዳለን። ስለዚህ ቅርንጫፍም፣ ግንድም ሳይባል በችግሩ የተሳተፉ አካላት ለችግሩ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት በሚችል ደረጃ፣ የሕዝቡን እርካታ ሊያረጋግጥ በሚችል ደረጃ በሕዝቡ በራሱ ተሳትፎም ጭምር እየሰራን ነው። የአዲስአበባ አስተዳደር ሆነ የፌዴራል መንግሥት እነኚህ መረጃዎች የሚያገኘው ከሕዝቡ እንደመሆኑ መጠን ሕዝቡ የሚሰጠውን መረጃ ወስደን የሚስተካከሉ ነገሮችን ለማስተካከል ዝግጅት አለ። እስካሁን የተጀመሩ ሥራዎች አበረታች ናቸው። በእኔ እምነት የአዲስአበባ አስተዳደር ችግሩን ለማስተካከል የሄደባቸው ርቀቶች ጥሩ ጅምሮች ናቸው። ሥራው በአንድ ጊዜ ተጀምሮ በአንድ ጊዜ የሚያልቅ ሳይሆን በየጊዜው እያጠራን፣ ጥልቀት እየሰጠነው የምንሄድበት ሥራ ነው። ስለዚህ በትግስት፣ በጋራ በመሥራት እያጠራን እንሄዳለን።

ከዚህ አኳያ ጥያቄው ትክክል ነው፣ አስተያየቱም ትክክል ነው፣ ይህንን ይዘን እንቀጥላለን። ለዚህ እንደ ግብዐት ተደርጎ የሚወሰደው የፓርላማው የሱፐርቪዥን ውጤት ነው። ም/ቤቱ ያደረጋቸው ጥልቀት ያላቸው ሱፐርቪዥኖች አሉ፣ ለእኔም ጽ/ቤት ደርሰዋል። እነዚህን ሱፐርቭዥኖች ይዘን ዘመቻው ጥልቀት እንዲኖረው ሥራ ጀምረናል። ስለዚህ ይህ ሥራ የተጀመረውን የልማት፣ የዕድገት፣ የህዳሴ ጉዞ መልካም አስተዳደርን በማስፈን የምናመጣቸው ውጤቶች የምናረጋግጥ እንደመሆኑ መጠን አጠናክረን የምንቀጥልበት ይሆናል።

ስነደቅ

Leave a Reply