16 March 2016

በይርጋ አበበ

 

መጋቢት 5 ቀን 2008 ዓ.ም ከረፋዱ 3፡30 ጀምሮ የቀድሞው “የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ የአሁኑ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ” በዋናው ጽ/ቤት ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር መገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ ለአውሮፓ ህብረት ዲፕሎማቶች፣ ለተለያዩ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ሲቪክ ማህበራት ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ለጉዳዩ ቅርብ ለሆኑ ድርጅቶች ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የሰመጉ መግለጫ ትኩረት ያደረገው በቅርቡ በምዕራብ ሸዋ ዞን ጊንጪ ከተማ ተከስቶ በአሁኑ ወቅት በመላው ኦሮሚያ በሚያስብል መልኩ በተቀጣጠለው ህዝባዊ ተቃውሞ ዙሪያ የሰብአዊና የህግ ጥሰቶችን በማጥናት ባዘጋጀው 140ኛ ልዩ መግለጫው ላይ ነበር።

ባሳለፍነው ሀሙስ (መጋቢት 1 ቀን 2008 ዓ.ም) ደግሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የመንግስታቸውን የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸም በአንድ ፓርቲ አባላት ብቻ ተዋቀረው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርታቸውን ባቀረቡበት ወቅት በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ “መንግስታቸው ተጎጂዎችን ይቅርታ” እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

ከዚህ በታች የሰመጉን መግለጫ እና ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የቀረቡላቸውን ጥያቄዎች ከእነ መልሶቻቸው እና የአቶ ኃይለማሪያምን የፓርላማ ንግግር አያይዘን እናቀርበዋለን።

የሰመጉ መግለጫ ጥቅል ሀሳብ

ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) 140ኛውን ልዩ መግለጫውን ይፋ ያደረገው “በመንግስት የጸጥታ እና ታጣቂ ሀይሎች በዜጎች ላይ የሚፈጸም አሰቃቂ ግድያ፣ ህገ ወጥ እስር፣ ድብደባ፣ ማስፈራራት እና ማዋከብ በአስቸኳይ ይቁም” በሚል ርዕስ ነው። በዚህ መግለጫ ላይ በኦሮሚያ ክልል የተነሳው ተቃውሞ ከሚያዝያ 2006 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑን የገለጸው ሰመጉ በዚያ ወቅትም ለተነሳው የህዝብ ጥያቄ መንግስት አፋጣኝና ሰላማዊ መልስ እንዲሰጥ መግለጫ አውጥቶ እንደነበረ ገልጾ በ132ኛ ልዩ መግለጫ) ሆኖም መንግስት የወሰደው እርምጃ ተቃራኒውን መሆኑን አስታውሷል። ይህም በመሆኑ ችግሮች ውለው ባደሩ ቁጥር ይዘታቸውን እየጨመሩ እና እየተወሳሰቡ መጥተው አሁን ላይ ለደረሰው የከፋ ችግር መብቃቱን ገልጿል። “ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለችውና ፍጹም አስገዳጅ የሆነው የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን በአንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ 9 እያንዳንዱ ሰው በህይወት የመኖር ተፈጥሯዊ መብት እንዳለው ይደነግጋል። የኢፌዴሪ ህገ መንግስትም በአንቀጽ 15 ማንኛውም ሰው በህይወት የመኖር መብት አለው። በህግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ህይወቱን አያጣም ሲል ያረጋግጣል። ይሁን እንጂ ይህንን ህገ መንግስታዊና ዓለም አቀፍ ድንጋጌ በመተላለፍ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች ግድያ ተፈጽሟል” ሲል ገልጿል።

ሰመጉ በመግለጫው አክሎም “የመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ለተቃውሞ በወጡ ዜጎች ላይ በወሰዷቸው ከመጠን ያለፉ የሀይል እርምጃዎች የበርካታ ዜጎች ህይወት ጠፍቷል። በርካታ ሰዎች በጥይት ተደብድበው የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በርካታ ሰዎች ታስረዋል። ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች የደረሱበት አይታወቅም” ሲል ገልጿል። (ሰመጉ ሪፖርቱን ያቀረበው በ33 ወረዳዎች ብቻ ከኅዳር 2 ቀን 2008 ዓ.ም እስከ የካቲት 12 ቀን 2008 ዓ.ም ብቻ ሲሆን 103 ሰዎች በመንግስት ታጣቂ ሀይሎች እና በአጋዚ ሰራዊት መሞታቸውን፣ 84 ሰዎች መታሰራቸውን፣ 57 ሰዎች በጠና የተጎዱ መሆናቸውን አስታውቋል)

የጉዳት አይነቶች እና የጉዳቱ መጠን

በሰመጉ 140ኛ ልዩ መግለጫ እንደተገለጸው በኦሮሚያ ክልል በተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ከእስር እና የአካል ጉዳት በተጨማሪ ማሰቃየት (torture) እንደሚገኝበት ገልጿል። በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 18 ንዑስ አንቀጽ 1 “ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት ኢ-ሰብአዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው” ሲል ይደነግጋል። ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለችው የሰብአዊ መብቶች መግለጫ በአንቀጽ አምስት ላይ “ማንም ሰው የማሰቃየት ድርጊት ሊፈጸምበት ወይም በጭካኔ እና ኢ ሰብአዊ በሆነ መንገድ ሊጉላላ ወይም ሊቀጣ አይችልም” ሲል ይገልጻል። ሆኖም በኦሮሚያ ክልል በተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ የመንግስት ታጣቂ ሀይሎች ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ድብደባ እና ማሰቃየት መፈጸሙን የሰመጉ መግለጫ አስታውቋል። በዚህ ሁኔታም  ከ18 ዓመት ወጣት ጀምሮ እስከ 55 ዓመት ጎልማሳ ያሉ ሴት እና ወንድ ዜጎች ማሰቃየት እንደተፈጸመባቸው አስታውቋል።

ከማሰቃየት በተጨማሪ ደግሞ በክልሉ የተለያዩ የገጠር ቀበሌዎች የበርካታ ዜጎች መኖሪያ ቤት መቃጠሉን፤ በቤቱ መቃጠል ምክንያትም መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ንብረት መውደሙን ገልጿል። “የተቃውሞ እንቅስቃሴውን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አመያ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች ከ30 ዓመታት በላይ ሲኖሩ የነበሩ ነዋሪዎችን ታህሳስ 2 ቀን 2008 ዓ.ም ሌሊት ጀምሮ የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን በመቃወም ሰልፍ ከወጡ ሰላማዊ ሰልፈኞች መካከል የአማራ ብሔር ተወላጆችን መኖሪያ ቤቶች ከእነሙሉ ንብረታቸው አቃጥለውባቸዋል። በዚህ ምክንያት ብዙ ሰዎች ተፈናቅለው በአጎራባች ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ለመጠለል ተገድደዋል። (በአጠቃላይ ከ800 በላይ ቤቶች ተቃጥለዋል)ምግብና አልባሳትም በቀይ መስቀል አማካኝነት ሲቀርብላቸው ቆይቷል” በማለት አስታውቋል።

ሰመጉ ከኦሮሚያ ክልል መስተዳድር በአገኘሁት መረጃ ብሎ የገበሬ ማህበር ጽ/ቤቶች፣ ንዑስ ፖሊስ ጣቢያዎች (ኮምዩኒቲ ፖሊስ ጣቢያዎች) እና የገበሬዎች ማሰልጠኛ አዳራሾች ጉዳት እንደደረሰባቸው የገለጸ ሲሆን ከአስር በላይ የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ንብረት የሆኑ ተሽከርካሪዎችና ግምቱ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የከተማ አውቶብስ መቃጠሉን አስታውቋል። በአምቦ በጀልዱ እና ግንደ በረት በተባሉ ከተሞችና አካባቢዎች ደግሞ የመንግስት ታጣቂ ሀይሎች ሴቶችን አስገድደው መድፈራቸውን አረጋግጫለሁ ሲል የገለጸ ሲሆን እነዚሁ ታጣቂዎች ደግሞ የነዋሪዎችን ቤት በህገ ወጥ መንገድ እየፈተሹ በፍተሻ ወቅት የሚያገኙትን ንብረትም ይወስዳሉ፤ በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ድብደባም ይፈጽማሉ፤ ዛቻ፣ ማስፈራሪያ እና ስድብም ይሰነዝራሉ ሲል ገልጿል።

የተነሱ ጥያቄዎች

የመገናኛ ብዙሃን ለሰመጉ የስራ ኃላፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበው ነበር። ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከልም የሚከተሉት ይገኙበታል።

ጥያቄ:-  በአንዳንድ አካባቢዎች በተቃውሞው ምክንያት ጉዳት ከደረሰባቸው ዜጎች መካከል የጸጥታ ሀይሎችን ቅድሚያ እንዲያክሙ የሚገደዱ የጤና ባለሙያዎች ወከባ እና ጫና እየደረሰባቸው መሆኑ ይነገራል። የተገደሉም አሉ ይባላል፡፡ እናንተ ግን በሪፖርታችሁ ይህንን አላካተታችሁትም።  ለምን?

መልስ:- የሙያ ስነ ምግባራቸውን በመጣስ ቅድሚያ መታከም ያለባቸው የጸጥታ ሀይሎች ናቸው ተብለው የተጎዱ ወይም የተገደሉ ነርሶችና ዶክተሮች መኖራቸውን በመረጃ ደረጃ ደርሶናል ሆኖም ማስረጃውን ባለማግኘታችን ይህን ያህል ዶክተሮችና ነርሶች ተጎዱ ብለን ማቀረብ አንችልም። ምክንያቱም የእኛ አሰራር እና መመዘኛ በሚፈቅደው መሰረት መረጃውን በማስረጃ አስደግፈን ትክክለኛውን ነገር በመግለጫ ማቅረብ አንችልም።

ጥያቄ:-  በኦሮሚያ ክልል የተነሳውን ተቃውሞ በተመለከተ የመንግስት ኃላፊዎች መግለጫ ሲሰጡ ከተቃዋሚዎች መሀል አሸባሪዎችና የታጠቁ ሀይሎች አሉ ሲሉ ይገልጻሉ። በተለይ የመንግስት ኮምዩኑኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትሩ ትግላችን ከታጣቁ ሀይሎች ጋር ነው ሲሉ ተናግረዋል። እናንተ ባደረጋችሁት ምርመራ በፓርላማ አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ ድርጅቶችም ሆኑ ጦር የታጠቁ ሀይሎችን አግኝታችኋል?

መልስ:- ቀደም ብለን እንደገለጽነው ጥናቱን ያካሄድነው በ33 ወረዳዎች እና ከኅዳር 2 እስከ የካቲት 12 ቀን ያሉትን ብቻ ነው። በእነዚህ ጊዜያትና አካባቢዎች ባደረግናቸው ማጣራቶች በዓለም አቀፍ መግለጫ አሸባሪ የሆኑ ድርጅቶችም ሆኑ የታጠቁ ሀይሎች ከመንግስት ታጣቂ ሀይሎች ጋር ተኩስ ሲፈጽሙም ሆነ በንብረትና በህይወት ላይ ጉዳት ሲፈጽሙ አላየንም። ተቃውሞ ያነሱት ዜጎች እንደመሆናቸው ሁሉ በድርጊቱ የተበሳጩና ቁጣ ያደረባቸው ዜጎች ባልተደራጀ መልኩ ከመንግስት ታጣቂዎች ጋር ተዋግተው ይሆናል እንጂ የተደራጀ ቡድን ግን አላየንም።

ጥያቄ:-  ሪፖርታችሁን በምታዘጋጁበት ወቅት የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን ረቂቅ እንዳያችሁት ገልጻችኋል። በእናንተ አስተሳሰብና ከነዋሪዎች ባገኛችሁት መረጃ ማስተር ፕላኑ ችግር ያለበት ከይዘቱ ወይስ ከውይይቱ ሂደት ላይ ሆኖ ነው ያገኛችሁት?

መልስ:- ንብረታችንን እናጣለን፣ ተመጣጣኝ ካሳ አይከፈለንም እና ከአዲስ አበባ ሰፋ ያለ ቦታ ይወጣል የሚሉ መልሶችን ነው የሚሰጡን። ከዚህ በተረፈ ግን ትልቁ እና መሰረታዊው ችግር መንግስት ዜጎቹን በሚመለከታቸው የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ አለማወያየቱ ነው። አብዛኞቹ የተቃውሞው አስተባባሪዎችና ተቃዋሚዎች ረቂቅ ማስተር ፕላኑ እጃቸው ላይ የለም። ለምን እጃቸው ላይ የለም ካልን በድብቅ ነው የተሰራው። መንግስት አንስቸዋለሁ እስካለበት ድረስ እንኳ ማስተር ፕላኑ ይዘቱ ይህን ነው የሚመስለው ጥቅሙ ይህ ነው ብሎ ህዝቡን ያወያየበት ጊዜ የለም። ይህ ነገር የሚያሳየው በህዝብ ጉዳዮች ላይ ለመወያየትና ለመከራከር ያለው እድል በመጥበቡ ምክንያት ዜጎች መረጃ በጊዜ ባለማግኘታቸውና ባለመግለጻቸው፣ በልማቱም አጀንዳዎች ላይ ባለመሳተፋቸው እንደዚህ አይነት ተቃውሞዎች እየተከሰቱ እና አንዳንዴም ከቁጥጥር ውጭ እየሆኑ እንደሆነ አመላካች ነው።

ቀደም ሲል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማህበራት አዋጅ ከመውጣቱ በፊት በርካታ ድርጅቶች ነበሩ በፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ውይይትና ጥናት እንዲሁም ምርምር የሚያካሂዱ። አሁን ያሉት የመንግስት እቅዶች ግን ህዝብ አይወያይባቸውም፣ የሲቪል ማህበረሰብ ተቋማትም የፋይናንስ አቅም ስሌለላቸውና አንዳንዶቹም እንዳይሰሩ ስለተደረጉ እንደዚህ አይነት ውይይቶች ማካሄድ አልቻሉም።

ጥያቄ:- ድርጅታችሁ ስራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የምታወጡትን ሪፖርት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጀምሮ ለጠቅላይ ሚኒስትር እና ለፕሬዚዳንት ጽ/ቤቶች እና ሌሎች ለሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት እንደምታቀርቡ ገልጻችኋል። በእነዚህ ሪፖርቶች ላይ ከመንግስት በኩል ግብረ መልስ (feedback) ቀርቦላችሁ እስቲ እንየው ብለዋችሁ ያውቃሉ?

መልስ:- ከመንግስት በኩል አሉታዊ ግብረ መልሶችን በተደጋጋሚ ጊዜ እናገኛለን። የምርመራ ውጤታችሁን ከዚህ በኋላ አትላኩልን ተብሎ ከሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ቢሮ የተላከልን ጊዜ አለ። እንደዚህ ቢሉንም እኛ ግን አሁንም ሪፖርቶቻችንን ከመላክ አልተቆጠብንም። አንድ ቀን ምናልባት የእኛን የምርመራ ውጤት ተመርኩዞ ተጨማሪ ምርመራ እንደሚደርጉና እርምጃዎች እንደሚወስዱ ተስፋ እናደርጋለን። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ተቀራርበን ብንወያይ መልካም ነው እንላለን።

ጥያቄ:- በሪፖርታችሁ (በ140ኛ ልዩ መግለጫ) ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች (የሞቱ፣ የታሰሩ፣ የተፈናቀሉ እና የቆሰሉትን) ስም ዝርዝር ይፋ አድርጋችኋል። ነገር ግን የጉዳት ፈጻሚዎችን ማንነትና ስም ያልገለጻችሁት በመረጃ ማጣት ነው ወይስ በሌላ ምክንያት?

መልስ:- በርካታ ጊዜ መረጃዎቹ እና ማስረጃዎቹ ይደርሱናል። ሪፖርቱን የምናቀርበው ለመንግስት ነው ይህ ጥሰት ተፈጥሯል በዳዮቹን ለህግ አቅርቡ ተበዳዮቹን ደግሞ ካሳ ስጡ እያልን ነው የምናቀርበው። አሁንም የፈጻሚዎቹን ማንነት በተመለከተ የመንግስት አካላት መረጃውን ከፈለጉ ልንሰጣቸው ዝግጁዎች ነን። ከዚህ በተረፈ ግን የዜጎች እንደወንጀለኛ ያለመቆጠር መብታቸውን ተጋፍተን ስማቸውን ማቅረብ አንችልም።

ጥያቄ:- በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በኦሮሚያ ክልል በደረሰው ተቃውሞ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ይቅርታ እንጠይቃለን ብለዋል። የአቶ ኃይለማሪያምን ይቅርታ ሰመጉ እንዴት ያየዋል?

መልስ:- የአቶ ኃይለማሪያምን ይቅርታ እንደሁላችሁም ነው የሰማነው። ስለዚህ የተለየ ነገር መናገር አንችልም። ነገር ግን ይቅርታው በቅንነት ታስቦ በግልጽ ችግሮችን ለመፍታት ከሆነ በመልካም ጎኑ ነው የምናየው። ይቅርታው ወደ መሬት ሲወርድ ደግሞ እነዚህ ሞቱ የተባሉትም ሆኑ እኛ አጣርተን መሞታቸውን ላረጋገጥናቸው ወገኖች መንግስት መሞታቸውን በትክክል አምኖ እውቅና ሰጥቶ የእነዚህን ገዳዮች ደግሞ ወደ ፍትህ አቅርቦ ተገቢውን የህግ እርምጃ የሚወሰድበት፣ ካሳ የሚከፈልበት፣ የታሰሩ ሰዎች የሚፈቱበት አይነት መፍትሔ የሚያመጣ ከሆነ ይቅርታው ጥሩ ነው። እነዚህን የማይመልስ ከሆነ ግን ምን ትርጉም ሊሰጥ እንደሚችል አናውቅም። ከዚህ በተረፈ ግን አቶ ኃይለማሪያም ከይቅርታቸው በዘለለ ዛቻም ያዘለ መልስ ነው የሰጡት።

የአቶ ኃይለማሪያም መግለጫ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በፓርላማ ቀርበው የመንግስታቸውን የስድስት ወራት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት በኦሮሚያ ክልል ስለተከሰተው ተቃውሞ ሲመልሱ “በኦሮሚያ ክልል ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት ዙሪያ አሁን ደጋግመን የምንለው ሌላ አካል ላይ ጣት ከመቀሰር ይልቅ ችግሩ የራሳችን እንደሆነ አውቀን መሄድ አለብን” ያሉ ሲሆን አያይዘውም “በእኛ ውስጥ ባለ ብልሽት ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ የህዝቡን ጥያቄዎች ፈጥኖ ምላሽ ባለመስጠት ምክንያት ከህዝብ ጋር ቅራኔ ውስጥ እየገባን መጥተናል። ይህ ቅራኔ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ወደ ግጭት አምርቷል። ይህ ማለት ግን ኦሮሚያ ውስጥ ግጭት ስላለ ሌላ ቦታ ችግሩ የለም ማለት አይደለም። ከትግራይ ጀምሮ እስከ ደቡብ ጫፍ ድረስ ይህ ችግር ተመሳሳይ ነው ልዩነቱ የግጭትና ያለመጋጨት ነው” ብለዋል።

አቶ ኃይለማሪያም የተፈጠረው ችግር የራሱ የመንግስት መሆኑን በገለጹበት ንግግራቸው ደግሞ “ችግሩ የራሳችን እንደሆነ በመውሰድ መፍታት አለብን። ሌላ ምክንያት መፍጠር ሌላ ቀዳሚ የውድቀት መንገድ ነው” ሲሉ ገልጸው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም “ህዝቡ ከፊት ለፊቱ ቆመን ደንቀራ ስንሆንበት ዘወር በሉ ብሎ መግፋቱ አይቀርም። ዘወር በሉ ሲል አንዳንዴ በቃሉ ሌላ ጊዜ ደግሞ በእጁ ይላል። አሁን በአንዳንድ ቦታ በእጁ ዘወር በሉ እያለን ነው” ብለዋል።

ስንደቅ

Leave a Reply