Wednesday, 16 March 2016 13:32

በፋኑኤል ክንፉ /ከጉባ/

 

 

በኪነ-ጥበባት ባለሙያዎች እና በጋዜጠኞች ቡድን መጋቢት 3 እና 4 ቀን 2008 ዓ.ም የሕዳሴ የኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ተጐብኝቷል። ቡድኑ በጉብኝቱ ፕሮጀክቱ ከዚህ በፊት ከነበረው ደረጃ ከፍ ማለቱን ከማስተዋሉም በተጨማሪ የአባይን የውሃ ፍሰት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመቆጣጠር በሚያስችል አቅም ላይ መደረሱን አይተናል።

የሕዳሴው ግድብ እስካሁን ድረስ ከ170 ሺህ በላይ ሕዝብ፣ ከ350 በላይ የዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ተጐብኝቷል። በአሁን ሰዓት 10,000 ሰራተኞች በሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። ከእነዚህም ውስጥ ከ30 የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሀገሮች የመጡ 350 የሚሆኑት የውጭ አገር ዜጐች ናቸው።

ዝግጅት ክፍላችን በዚህ ጉብኝት የሕዳሴው የኃይል ማመንጫ ግድብ ከነበረው ታሪካዊ ዳራ አንፃር አሁን የደረሰበትን ደረጃ በወፍበረር ለማየት ሞክሯል።

 

መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. የሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀከት መጀመሩን ይፋ ሲደረግ፣ ከግድቡ የሚገኘው የኃይል መጠን 5ሺ 250 ሜጋ ዋት ነበር። ሆኖም ግን የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በሕዳሴ ግድብ ላይ የዲዛይን እና ኦብቲማይዜሽን ሥራዎችን በመሥራት ተጨማሪ የ750 ሜጋ ዋት ኃይል እንዲገኝ አሻራውን አስቀምጧል። ይህም በመሆኑ ከሕዳሴ ግድብ የሚገኘው የኃይል መጠን ወደ 6ሺ ሜጋ ዋት ከፍ ተደርጓል።

ሌላው የሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጫ ይፋ በሆነበት ወቅት የተለያዩ ሃሳቦች በመገናኛ ብዙሃን እና በፖለቲከኞች ተንጸባርቀው ነበር። በጊዜው ከነበሩት የፖለቲካ ትንታኔዎች ጭብጥ አንፃር ትልቁን ስፍራ የሚወስዱት፣ ከሀገር ውስጥ የሁለት አሃዝ የዋጋ ግሽበት ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ ከሀገር ውጪ ደግሞ ከቱኒዚያ የተነሳው የአረቦች አብዮት (የአረቦች ጸደይ) ነበር። እነዚህን ሁለት ክስተቶች ከሕዳሴው ግድብ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ጋር በማያያዝ የተለያዩ የፖለቲካ ትንታኔዎች ሲቀርቡ እንደነበር የሚታወስ ነው።

አብዛኞቹ ትንታኔዎች ሲደመሩ ገዢው ፓርቲ የሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀከትን ይፋ ያደረገው፣ ሀገር ውስጥ ከተፈጠረው የሁለት አሃዝ የዋጋ ግሽበት እና የአረቦች አብዮትን ተከትሎ ከሚመጣ ሕዝባዊ ቁጣ ራሱን ለመከላከል ግድቡን የማስቀየሻ ፖለቲካዊ ስልት ለማድረግ አልሞ መሆኑን የሚያትቱ ነበሩ። እነዚህ ፖለቲካዊ ይዘት የነበራቸው ትንታኔዎች የተወሰነውን የሕብረተሰብ ክፍል ጉዳዩን በጥርጣሬ እንዲመለከተው ከማድረጋቸው ባሻገር፣ የግብፅ የፖለቲካ ተንታኞችም ተመሳሳይ ትንታኔዎችን እንዲሰጡ ተፅዕኖ ፈጥሮባቸው አልፏል።

አሁን ላይ ሆነን ትንታኔዎቹን ስንመዝናቸው በሁለት ማሳያዎች ውሃ የሚያነሱ ሆነው አናገኛቸውም። አንደኛው፣ ፕሬዝደነት ኢሳያስ አፈወርቂ ከኤርትራ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት የቀጥታ ቃለ ምልልስ ፕሮግራም ላይ ያሉትን ማንሳት ተገቢ ይሆናል። ይኽውም፣ በ80ዎቹ መለስ የናይል ወንዝን ለመጠቀም የግብፅ መንግስት ባለስልጣኖች ማናገር እንደሚፈልግ አማክሮኝ ነበር። በወቅቱ መጠየቁ አስፈላጊ አለመሆኑን ምክር ሰጥቼው ነበር። መለስ ግን እራት ስንበላ ሚስተር ዑመር ሱሌማንን በናይል ጉዳይ ሊያወያያቸው ሞክሮ፤ ሱሌይማን (የሆስኒ ሙባረክ ምክትል ፕሬዝደንት የነበሩ) ግን “አንተ ማነህ እና ስለናይል ትጠይቀናለህ” ብሎ እንደመለሰለት መለስ እራሱ ነግሮኛል ብለዋል። ከዚህ መረዳት የሚቻለው በናይል ወንዝ ለመጠቀም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በ80ዎቹም እቅድ እንደነበራቸው ነው።

ሌላው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የጊዜ አመራረጣቸው ከአረቦች አብዮት መቀጣጠል ጋር ለማያያዝ የታለመ ቢሆንም፤ ጠቀሜታውን ስንመለከተው ገዢው ፓርቲን ከማዳን በበለጠ ሀገራዊ ጥቅም ለማስከበር የነበረው አመቺ ሁኔታ የሚያመዝን ነበር። ይህም ሲባል፣ ወቅቱ ግብፅ በአረቡ ዓለም አብዮት መወጠሯ ብቻ ሳይሆን የነበራት ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ /Soft Power/ ከአጠገቧ አልነበረም። እነዚህ ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት ስናስገባ ለአንድ ተራ ፖለቲከኛ ሰው እንኳን ፍላጎቱን ለማሳካት ተመራጭ ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው። ሆኖም ግን ተደጋግሞ እንደተነገረው በናይል ወንዝ ላይ ለመጠቀም ዋስትና የሚሆነው፣ በኢኮኖሚ የዳበረች እና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት የተገነባች ግብፅን ማግኘት ሲቻል ብቻ ነው።

በተጨማሪም የሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ይፋ ከሆነ ሰዓት ጀምሮ ስንዘግብ፣ ስንከታተል ለነበርነው አብዛኛዎቹ ጋዜጠኞች ደግሞ የሚሰጠን ትርጉም ለየት የሚል ነው። የነበረውን ሂደት ሙሉ በዚህ ጽሁፍ መዘገብ አይቻልም። በእጃችን ያለውን እውነት ለማስቀመጥ ያህል መሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ሰዓት ጀምሮ በየአመቱ ግንባታው እያደገ የኃይል ማመንጫውም እውን እየሆነ መምጣቱን ለማረጋገጥ ከዚህ በፊት የሰራናቸው ሪፖርቶች እና ዛሬ ላይ የምናቀርበው ሃተታ ምስክር ተደርገው መወሰድ ይችላሉ።

ኢንጅነር ስመኘው በቀለ የፕሮጀክቱ ዋና ሥራአስኪያጅ በበኩላቸው ባደረጉት ገለፃ፣ “አባይ ለዘመናት ሲፈስ የነበረ ወንዝ ነው። በጥንታዊ ወይም በዘመናዊ መንገድ ሲያስተዳድሩ የነበሩ የኢትዮጵያ መንግስታት አባይ ወንዝ ለመጠቀም ያላደረጉት ሙከራ አልነበረም። የአባይን ወንዝ ለመጠቀምና ወደስራ ውስጥ ለማስገባት የቻለው ግን የእኛ ትውልድ ነው። ይህን እድለኛነታችን ማመን፣ ማስተጋባት ይጠበቅብናል። ከእድለኛነታችን ባሻገር ስርዓት ያለው አካሄድ እና አቅጣጫ በማስቀመጣችን ለስኬታችን የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። የሕዳሴው ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ መሳካት ቁልፉ ነጥብ መንግስታችን በኃይል አቅርቦት ዘርፍ የነደፈው የፖሊሲና የስትራቴጂ ውጤት ነው” ብለዋል።

የአባይ ወንዝ በሰው ሰራሽ ማስተላለፊያ ፍሰቱን ቀጥሏል

የአባይ ወንዝ ለረጅም ዘመናት ሀገራችን ለቆ ሲወጣ ተፈጥሮ በቀደደችለት የመፍሰሻ  ጉድጓዶች ነበር። ፍሰቱን መቆጣጠር በማይቻልበት ሁኔታ በአደባባይ ደረቱን ለፀሃይ ከፍቶ አለከልካይ ሀገር ለቆ ይወጣል። ዛሬ ላይ ግን አባይ ኢትዮጵያን ለቆ ከመውጣቱ በፊት በሰው ሰራሽ ቱቦ  (culvert boxes) እንዲፈስ ተደርጓል።

ከዚህ በፊት የአባይን ወንዝ ተፈጥሮያዊ ፍስት በተወሰነ ደረጃ በማስቀየስ እና ወደተፈጥሮያዊ ፍሰቱ በመመለስ አቅጣጫውን ይዞ ወደታችኞቹ ሀገሮች እንዲፈስ ማድረግ በትልቁ ስኬት የምናስታውሰው ነው። ዛሬ ላይ ደግሞ የአባይ ወንዝን የውሃ ፍስትን ሳይንሳዊ በሆነ ቀመር መቆጣጠር እና መጠቀም ወደሚያስችልን ደረጃ ተሸጋግረናል። የማይቻል ይመስለን የነበረውን የአባይ ወንዝ ፍሰትን መቆጣጠር፣ ተችሎ ስናየው ብሔራዊ ኩራት ከማላበሱም በላይ በተፈጠረው አቅም ለመደሰት በቅተናል።

በተለይ የብረታ ብረት እና የኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ወጣት ኢንጅነሮች በውሃ ማስተላለፊያው ቱቦዎችን ማዘጋጀት እና የኤልክትሮ ሜካኒካል ክፍሎችን ለመስራት የደረሱበት በራስ መተማመን እና ብቃት አስገራሚ ነው። በተለይ በእድሜያቸው ወጣት በመሆናቸው በቀጣይ በሀገር ደረጃ የሚኖራቸው ፋይዳ በጣም ግዙፉ ይሆናል።

ቀጣይ ስራዎች

በሰው ሰራሽ ቱቦ የአባይ ወንዝ መፍሰስ ከጀመረ በኋላ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የውሃ ፍሰቱን መክፈት እና መዝጋት ስለሚቻል ቀጣዩ ስራ የሚሆነው የግድቡን ውሃ መሙላት ነው። በውሃ መሙላቱ ሂደት የሚፈጠረው ሰው ሰራሽ ሃይቅ ርዝመቱ 246 ኪሎ ሜትር (ከአዲስ አበባ እስከ ሻሸመኔ) ወደኋላ በመንሸራተት ይተኛል። 1ሺ 874 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ወይም 87ሺ 400 መቶ ሄክታር ይሸፍናል። በዚህ የቆዳ ስፋት ውስጥ የሚገኙ ወረዳዎች በውሃ ይሸፈናሉ። እነሱም ጉባ፣ ሰዳል፣ ሾርከሌ እና ኦዳ ቡል ጊል ናቸው። በከፊል የሚነካቸው ወረዳዎች ደግሞ አጋሎ መቺ እና ወንበራ ወረዳዎችን ነው። በአሁን ሰዓት ለተነሺ ወረዳዎች አስፈላጊውን የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ከገለፃዎች ለመረዳት ተችሏል።

ስንደቅ

Leave a Reply