ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ባለፈው ሳምንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር መንግስት በኦሮሚያ ለተከሰተውን ችግር ተከትሎ ለደረሰው ጉዳት ይቅርታ እንደሚጠይቅ በይፋ ገልጸዋል። ይህ ጉዳይ የብዙዎች መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖም ሰንብቷል። መንግሥት በዚህ ደረጃ ህዝብን አክብሮ ይቅርታ መጠየቁን ማድነቅና ማበረታታት ያስፈልጋል። እንዲህ አይነቱ ኃላፊነት የመውሰድ ባህል እንዲዳብርም የሁላችንም ምኞት ይመስለኛል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ጀርባ ግን ሁለት አብይ ጉዳዮች ጥያቄ ያጭራሉ። የመጀመሪያው እና ዋናው ነገር የጠፋው የሰው ህይወት በይቅርታ ሊታለፍ የሚችል ነው ወይ? የሚለው ነው። ሁላችንም ራሳችንን በዚህ ችግር ሳቢያ የቤተሰብ አባሉን በተነጠቀ ቤተሰብ ቦታ አድርገን እናስበው። ለዚያውም መንግስት ጥፋቱ የኔ ነው ባለው ግጭትና ሁከት ሳቢያ ቤተሰቡን ለተነጠቀ ሰው ይሄ ይቅርታ ምን አይነት ስሜት ሊፈጥርበት እንደሚችል መገመት የሚከብድ አይመስለኝም። መንግሥትም ይሄ ይጠፋዋል ብዬ አላስብም። አሁንም ቢሆን መንግስት ከይቅርታው በተጨማሪ በሰው ህይወት የደረሰውን ጉዳት በሚመለከት አጣርቶ ተገቢውን እርምጃ ሊወስድ ይገባል። ቤተሰባቸውን የተነጠቁ ሰዎችም ምንም እንኳን ህይወት መመለስ ባይቻልም የሞራል ካሳ እና ማጽናኛ ማግኘት ይኖርባቸዋል። ያን ጊዜ ይቅርታው የተሟላ ይሆናል።

ሌላው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ተድበስብሶ የቀረው የዜጎች የማንነት ጥያቄ ነው። ካልተሳሳትኩ ግጭቶቹ የተቀሰቀሱት መጀመሪያ ላይ ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ነው። መንግስት ግን አሁን እየነገረን ያለው የግጭቱ መንስኤ የመልካም አስተዳደር እጦት እንደሆነ ነው። የመልካም አስተዳደር እጦት ችግር አንዱ ሆኖ የሚቀድመው ግን የማንነት ጥያቄ ነው። ነገሩ የተገጣጠመለት መንግስት ግን ጥያቄውን የወቅቱ ንቅናቄ በሆነው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ላይ አላኮ ለማለፍ ጥረት እያደረገ ነው። በዚያም ሆነ በዚህ ግጭትን እና ሁከትን ማስቆሙ ትክክለኛ ውሳኔ እና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ውሳኔ በመሆኑ መከበር አለበት። ነገር ግን ትክክለኛ መንስኤውን አጣርቶ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት አማራጭ የማይገኝለት ተግባር ነው። አሁንም በተለይ ከማንነት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎችን በጥልቀት መርምሮ ተገቢውን ምላሽ በመስጠት የተረጋጋ ህዝብ መፍጠር ትልቁ የመንግስት የቤት ስራ ነው የሚሆነው።

በስልክ የተሰጠ አስተያየት 

Last modified on Wednesday, 16 March 2016 13:22

Leave a Reply