እንደ መንደርደሪያ
በቅርቡ ዮሹዋ እስራኤል የተባለ አፍሪካ አሜሪካዊ ምሁርና የታሪክ ተመራማሪ በአምስቱ ዓመት የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ዓመታት ከአገሩ ከአሜሪካ መጥቶ የአየር ኃይልን በማቋቋምና ባልደረባ በመኾን ለአገራችን የነጻነት ጋድሎ ትልቅ መሥዋዕትነት ስለከፈለ አፍሪካ አሜሪካዊው ኮ/ል ጆን ሮቢንሰን በእንግሊዝኛ ቋንቋ አንድ ድንቅ የኾነ መጽሐፍ አበርክቶልናል፡፡ ይኸው ማጣቀሻዎቹንና መዘርዝሩን/ኢንዴክሱን ጨምሮ በ294 ገጾች የተቀነበበውና ታሪኩን በሚያጎለብቱ በርካታ ምስሎችና መረጃዎች የተካተቱበት ይህ መጽሐፍ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ለንባብ በቅቷል፡፡
መጽሐፉ በውጭ አገር ሲሆን የታተመው ባለኝ መረጃ መሠረት እስካሁን ድረስ አገራችን በሚገኙ መጻሕፍት መሸጫዎች አልተሰራጨም፡፡ በእርግጥ የመጽሐፉ ደራሲ የኾነው የታሪክ ተመራማሪው አሜሪካዊው ሚ/ር ዮሹዋ እስራኤል የኢትዮጵያ ባለውለታ የኾነውን የኮ/ል ሮቢንሰን የሕይወት ታሪክ የሚተርከውን መጽሐፍ በእዚሁ በአገራችን አሳትሞ በመጠነኛ ዋጋ ለአንባቢያን ለማድረስ አሳብ እንዳለው አውግቶኛል፡፡ እኔም ለዛሬ በዚህ የአገራችን ቁርጥ ቀን ወዳጅና ባለውለታ በኾነው በአሜሪካዊው አርበኛ በኮ/ል ጆን ሮቢንሰን የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ላይ አጭር ዳሰሳ ለማድረግ ወደድኹ፡፡
- ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በጥቁሩ ዓለም
የአገራችንን የኢትዮጵያ የረጅም ዘመናት ገናና ታሪክና ግዙፍ ሥልጣኔ፣ ነጻነትና የአባቶቻችን ተጋድሎ አኩሪ ታሪክ በአፍሪካ፣ በአፍሪካ አሜሪካውያን፣ በካረቢያንና በጃሜይካ በአጠቃላይ በጥቁሩ ዓለም ልዩ በኾነ ስስትና ናፍቆት የሚተርክና የሚታይ ነው፡፡ ከጥንት የታሪክ ድርሳናት እስከ ግሪካውያኑ የጥበብ መጻሕፍት፣ ከታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ቅዱስ ቁርአን ድረስ- የኢትዮጵያ ታሪክ የሰው ልጆች ታሪክ አንድ አካል ኾኖ በልዩ ስሜት በደማቁ ሲተርክ፣ ሲወሳ ኖሯል፡፡ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ታሪክ በተለይ በጥቁሩ ዓለም የኩራት ምንጭ፣ የነጻነት ተስፋ ቀንዲል ኾኖ ቆይቷል፡፡
በቅዱሳን መጽሐፍትና በታሪክ ድርሳናት ተመዝግቦ የሚገኘው የዚህ የአገራችን ታሪክና ሥልጣኔ፣ ታላቅ ስምና ዝና በተለይ ከዓድዋው ድል በኋላ እጅጉን ጎልቶና ደምቆ ነበር የወጣው፡፡ ለዘመናት በባርነትና በቅኝ ግዛት ስር ኾነው ሲማቅቁ የነበሩ፣ ታሪካቸውና ሥልጣኔያቸው፣ ማንነታቸውና ባህላቸው በአውሮፓውያን ቅኝ ገዢ ኃይሎች የተዘረፈባቸው አፍሪካውያንና መላው ጥቁር ሕዝብ ኢትዮጵያን የማንነታቸውና የታሪካቸው መሠረት አድርገው ማየት ጀመሩ፡፡
ጥቁር ሕዝብ እንደ ሸቀጥ ሲሸጥና ሲለወጥ በነበረበትና በቅኝ ግዛት ቀምበር ሥር ወድቆ ሲማቅቅና እንደ መርግ የከበደ የመከራ፣ ጨለማ ኑሮውን ሲገፋ በነበረበት ዘመን- በነጻነቷና በልዑላዊነቷ ትኖር የነበረችው ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ- ለመላው ጥቁር ዓለም በሩቅ ኾነው በተስፋ ይናፍቋት ይሳለሟት የነበረች እንደ ሕዝበ እስራኤል የተስፋ ምድራቸው- ከነዓናቸው ለመኾን በቃች፡፡
ጥቁር ሕዝብ ከሰው ተርታ ሊያስመድበው የሚችል አእምሮአዊና ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማንነትን አላዳበረም በሚል ዘረኛ ስብከታቸው ጥቁር ሕዝብን ከሰው ተርታ፣ ክብርና ልእልና አውርደው እንደ እንሰሳ ሲነዱትና ሲገዙት በነበሩበት ወቅት ከኢትዮጵያ ምድር የተሰማው የዓድዋው ድል የነጻነት ጮራ፣ የድል ብስራት መላው ጥቁር ሕዝብን አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲራመድና ከዳር እስከ ዳር ለነጻነቱ፣ ለመብቱና ለክብሩ እንዲታገል ያነቀሳቀሰው አንጸባራቂ ድል ነበር፡፡
እንደእነ አፍሪካ አሜሪካዊው ማርከስ ጋርቬይ ያሉ የጥቁር መብት ታጋዮችም ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴያቸው ባሻገርም በወንጌል ስም የተሰበኩትን ነጭ አምላክ/የአውሮፓውያንን አምላክ አናመልክም ሲሉ በግልፅ አውጀው ነበር፡፡ ጋርቬይ እ.ኤ.አ. በ1989 በጻፈው መጽሐፉ፣ We as Negros have found a new ideal. Whilst our God has no color … We Negros believe in the God of Ethiopia, the everlasting God … we shall worship him through the spectacles of Ethiopia. እስከማለት ደርሶ ነበር፡፡
በአውሮፓውያኑ በወንጌል ወይም በክርስትና ሃይማኖት ስብከት ዘመቻ ስም በባርነትና በቅኝ ግዛት ወድቀው የነበሩ በርካታ አፍሪካውያንና አፍሪካ አሜሪካውያን ጥቁር ሕዝቦች በተለይ ከዓድዋው ድል በኋላ ራሳቸውን ከአውሮፓውኑ ቁጥጥር ሥር በማውጣት- አቢሲኒያ፣ ኢትዮጵያ በሚል ስም የቤተ እምነታቸውን ስም ቀየሩ፡፡ ይህ ወደቀደመው አባቶቻቸው እምነት፣ ታሪክና ማንነት የመመለስ ‹Back to the Root› ዘመቻም ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ጃማይካና ካረቢያን ድረስ የተደረገ ነበር፡፡
ይህ በአፍሪካውያን፣ በአፍሪካ አሜሪካውያን ጥቁር ሕዝቦች መካከል የተቀነቀነውና የገነነው የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የኋላ ኋላ ለጥቁር ሕዝቦች ነጻነትና ልዑላዊነት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ይህን ታሪካዊ እውነታ አስመልክቶም የደቡብ አፍሪካው የቀድሞ ፕ/ት የነበሩት ታቦ እምቤኪ፣ እ.ኤ.አ. በ2010የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ የክብር ዶክትሬት በተሰጣቸው ጊዜ ባደረጉት ንግግራቸው፣ የኢትዮጵያዊነት መንፈስና እንቅስቃሴ በፓርቲያቸው በአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ/ANC ምስረታ ሂደት እንዴት የገዘፈ፣ ጥልቅና ረቂቅ፣ አስተዋጽኦውም ታላቅ መኾኑን እንዲህ ገልጸውት ነበር፣
The African National Congress Party/ANC believes that Ethiopianism is a symptom of progress, brought about by the contact of the natives of Africa with European civilization, making itself felt in all departments of the social, religious and economic structure.
- የኢትዮጵ ባለውለታ አርበኛው ኮ/ል ጆን ሮቢንሰን ማን ነው?!
ኮ/ል ጆን ሮቢንሰን አፍሪካዊ ዝርያ ያለው ጥቁር አሜሪካዊ ነው፡፡ ይኸው ሰው የልጅነት ብርቱ ምኞቱ የነበረውን አውሮፕላን የማብረር ትምህርት መማር እንዳይችል በቆዳው መጥቆር ምክንያት ዕገዳ ተጥሎበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሮቢንሰን በአቬዬሽን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤቱ የጽዳት ሠራተኛ አድርገው እንዲቀጥሩት ጠየቀ፡፡ በዚህ ሥራ ላይም እያለ ለበረራ ትምህርት ብርቱ ናፍቆት የነበረው ወጣቱ ሮቢንሰን በክፍሉ ውስጥ ሌክቸር ሲሰጥ እየተደበቀ መከታተል፣ ከትምህርት በኋላም በማስተማሪየ ሰሌዳው ላይ የቀረውን ኖት እየገለበጠና ተማሪዎች የሚጥሉትን የማስተማሪያ ኖቶች በማሰባሰብ የበረራ ትምህርት በራሱ መማር ጀመረ፡፡
የበረራ ማስተማሪያ መጻሕፍትንና ማኑዋሎችን በማንበብ እውቀቱን ያጠናከረው ሮቢንሰን በአንድ አጋጣሚ ከጓደኛው ጋር ለበረራ ሥልጠና የምትሆን አወውሮፕላን ገጣጥሞ ያቀረበበት ኢግዚቢሽን ትልቅ የመነጋገሪ ርእስ እንዲኾን አደረገው፡፡ በሮቢንሰን ልዩ ችሎታ የተደነቀው የበረራ ትምህርት ቤቱ ነጭ ዳይሬክተር ሮቢንሰን የበረራ ማስልጠኛ ትምህርት ቤት እንዲገባ ፈቀደለት፡፡ ጆን ሮቢንሰን በዚህ የበረራ ትምህርት ቤት ገብቶ ለመሰልጠንም የመጀመሪያ ጥቁር አሜሪካዊ ኾነ፡፡ ትምህርቱን ካጠናቀቅም በኋላ ያለ ምንም ቀለም ልዩነት የበረራረ ትምህርትን የሚሰጥ ተቋም በዘሜሪካ በማቋቋም ብዙዎችን በበረራና በአቬዬሽን ሙያ አሰልጥኖ ለመርቃት እንዲበቁ አደረገ፡፡
- የፋሽስት ወረራና የጥቁር አሜሪካውያን ቁጣ
ለአፍሪካ አሜሪካውያንና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ቀንደሊል ብርሃን ኾና የምትታየው ኢትዮጵያ በኢጣሊያ ፋሽስት መወረሯ በአሜሪካ በተሰማ ጊዜ በርካታ ጥቁር አሜሪካውያን ከኢትዮጵያውየን ጎን ኾነው ለመዋጋት ጠየቁ፡፡ ግና በአሜሪካ ሕግ መሠረት አሜሪካ በምታደርገው ጦርነት ካልኾነ በስተቀር አሜሪካዊ ዜጋ ኾኖ ሌላ አገር መዋጋት አይቻልም፡፡ ይሁን እንጂ አፍሪካ አሜሪካውያን የአሜሪካን አደባባዮች በተቃውሞ ሰልፍ ማናወጥ ያዙ፡፡
ከጣሊያን ወረራ በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው ኮ/ል ሮቢንሰን የኢምፔሪያል ኢትዮጵያን አየር ኃይልን፣ ኦርማ ጋራዥንና እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊትን የኤሌክትሪክና የመካኒካል ኢንጂነሪንግ ክፍል በማቋቋም ከፍተኛ የኾነ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከዚህ በኋላ ወደ አሜሪካ የተመለሰው ሮቢንሰን የኢትዮጵያ በፋሽስት ኢጣሊያ መወረሯን በሰማ ጊዜ አፍሪካ አሜሪካውያንና ሌሎች በአሜሪካ ያሉ ኢትዮጵያኖች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ለመርዳት እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ፡፡
የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ቀንዲልና ብቸኛ ተስፋ የኾነችው ኢትዮጵያ በፋሽሽት ኢጣሊያ መወረር ዕረፍት የነሣው ሮቢንሰን እ.ኤ.አ. በ1936 አሜሪካን ለቆ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የኢትዮጵያን አየር ኃይልንና አርበኞችን በመቀላለቀል በተለያዩ ግንባሮች የኢትዮጵያውያንን የነጻነት ተጋድሎ ዋና አጋር ለመኾን በቃ፡፡ ኮ/ል ሮቢንሰን በኦጋዴን ግንባር ከጥቁር አንበሳ ኃይሎች ከእነ መላኩ በያን ጋር በመኾን የላቀ አስተዋጽኦ ማድረጉን ዮሹዋ እስራኤልThe Lion and the Condor: The Untold Story of Col. John Robinson and the Crippling of Ethiopia መጽሐፉ በሰፊው ተርኮታል፡፡
- የዮሹዋ እስራኤል ቁጭት የወለደው የኮ/ል ሮቢንሰን ታሪካዊ መጽሐፍ
ለኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክና የነጻነት ተጋድሎ ልዩ አክብሮት ያለው አፍሪካ አሜሪካዊው የታሪክ ተመራማሪ ዮሹዋ እስራኤል ይህን የኢትዮጵያ ባለውለታና የኢትዮጵያውያን የቁርጥ ቀን ወዳጅ የኾነውን የኮ/ል ጆን ሮቢንሰን ታሪክ እንዲጽፍ ያስገደደውን ምክንያቱን እንዲህ ሲል በአጭር ቃል ይገልጸዋል፡፡ ‹‹My quest was to find out why Col. Robinson’s legacy had been forgotten and had gone unrecorded in Ethiopian history …››
በእርግጥም ዛሬ በኩራት ስለምንናገርለት የአገራችንና የሕዝባችን ነጻነትና ሉዓላዊነት መከበር ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ ከአውሮፓ እስከ ኤዥያ፣ ኩባ፣ ጃማይካና ካረቢያ ድረስ ትልቅ መሥዋዕትነትን የከፈሉና የዘነጋናቸው የኢትዮጵያውያን የቁርጥ ቀን ወዳጆችና ባለውለታዎች አሉ፡፡ አሜሪካዊው ዮሹዋ እስራኤል ከእነዚህ የአገራችን ነጻነት ባለውለታዎች መካከል በሚወዳት ኢትዮጵያ በአውሮፕላን አደጋ ስላረፈውና መካነ መቃብሩ በአዲስ አበባ ጉለሌ ስለሚገኘው ስለ አርበኛው ኮ/ል ሮቢንሰን ለበርካታ ዓመታት ምርምርና ጥናት አድርጎ የጻፈውን መጽሐፍ አበርክቶልናል፡፡
ዮሹዋ ይህን መጽሐፍ ሲያዘጋጅ መረጃ በማሰባሰብና ሮቢንሰንን የሚያውቁ እድሜ ባለጠጋ የኾኑ ኢትዮጵውያንና አፍሪካ አሜሪካውያንን በማነጋገር በርካታ ዓመታትን አሳልፏል፡፡ በዚህ ምርምርና ጥናት ለኢትዮጵያ ታሪክና ቅርስ ልዩ ክብር ያላቸው እንደእነ ኢንጂነር ታደለ ብጡል፣ ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስትና ሪታ ፓንክረስት፣ ካፒቴን አለማየሁ አበበ፣ ካርዲናል ብፁዕ ብርሃን ኢየሱስ፣ ሀጂ ሀምዛ፣ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር፣ የቀድሞ ኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፕሬዝዳንት መ/አ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ … እና ሌሎችም የዚህን የኢትዮጵያ ባለውለታ የኮ/ል ሮቢንሰን ታሪክ ትንሣኤ እንዲያገኝ ያደረጉትን አስተዋጽኦና እገዛ ዮሹዋ በመጽሐፉ ውስጥ ከምስጋና እና ከልዩ አድናቆት ጋር ገልጾአል፡፡
ባሳለፍነው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ኢትዮጵያን የጎበኙት የመጀመሪያ ጥቁር አሜሪካዊ ፕ/ት ባራክ ሑሴን ኦባማ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በተደረገላቸው የእራት ግብዣ ላይ፣ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ወዳጅና ባልደረባ የኾነውን ኮ/ል ጆን ሮቢንሰን በተመለከተ ባደረጉት ንግግራቸው እንዲህ ነበር ያሉት፣ ‹‹Colonel John Robinson, an American who was one of the fathers of the Tuskegee Airmen, nicknamed the Brown Condor, came to Ethiopia and trained Ethiopian pilots to tame their heavens and helped to set up the Ethiopian air Force.››
በዚሁ ታሪካዊ የእራት ግብዣ ላይ ጠቅላይ ሚ/ር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም በዚሁ የእራት ግብዣ ላይ ስለዚህ ጀግና የኢትዮጵያ ወዳጅ እንዲህ አስታውሰውታል፣
I feel this an appropriate moment to mention one African-American hero who came to Ethiopia in 1935 to help us in our struggle against Fascism and colonial aggression. Colonel John Robinson was the first American to take up arms against Fascism. Colonel Robinson was responsible for founding the Ethiopian Air Force during the Italian Invasion. Called the Brown Condor of Ethiopia, he became the first Commander of the Air Force. He was a wonderful example of those Americans who actively supported Ethiopia in time of both peace and conflict.
በመጨረሻም አንድ ነገር ለማለት እወዳለኹ፡፡ የኢትዮጵያ ጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ጀግኖች አርበኞች- አባቶቻችንና እናቶቻችን በዱር በገደሉ ከፋሽስት ኢጣሊያ ወራሪ ጋር ተፋልመውና ክቡር የሕይወታቸውን ሠውተው በዓል አቀፍ መድረክ ዳግመኛ የአገራችንን የኢትዮጵያን ነጻነትና ሉዓላዊነትን ያበሰሩበትን 70ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ መታሰቢያ በዓል ለማክብር በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደኾነ ይታወቃል፡፡
ስለሆነም መንግሥትም ኾነ የኢትዮጵያ ጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማኅበር እንደእነ ኮ/ል ጆን ሮቢንሰን ያሉ የዘነጋናቸውን የአገራችንና የሕዝባችን ባለውለታና የቁርጥ ቀን ወዳጅ የኾኑ ጀግኖች፣ አርበኞቻችንን በዚህ የነጻነት/ድል በዓላችን የ70ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ መታሰቢያ በዓል ላይ በሚገባ የሚዘከሩበት ታሪካቸውና ገድላቸው የሚነገርበት እንዲሆን እንደሚገባው በማስታወስ በአፍሪካ አሜሪካዊው አርበኛው፣ በኮ/ል ጆን ሮቢንሰን ታሪክ መጽሐፍ ላይ ያደረኩትን አጭር ዳሰሳ ላብቃ፡፡
ሰላም!!