ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በ2007 ዓ.ም. ግንቦት ወር የተካሄደውን ምርጫ መቶ በመቶ በማሸነፍ መንግሥት ቢመሠርትም፣ ምርጫው ከተካሄደ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ራሱን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አግኝቶታል፡፡
የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ረቂቅ የጋራ ማስተር ፕላን በመቃወም ከምርጫው በፊት ተነስቶ የነበረው ተቃውሞ፣ ምርጫው ተጠናቆ መንግሥት ከተመሠረተ በኋላ በስፋት ደም አፋሳሽ ሆኖ በበርካታ የኦሮሚያ አካባቢዎች ቀጥሏል፡፡
በአማራ ክልል ከምርጫው በፊት ተነስቶ የነበረው የቅማንት የማንነት ጥያቄ ከምርጫው በኋላ በጦር መሣሪያ የታገዘ የደም መፋሰስ አስከትሏል፡፡ በአዲስ አበባ የትራፊክ ሥነ ሥርዓት ሕግ ፀድቆ ተግባራዊ መሆንን ተከትሎ፣ ታክሲ አሽከርካሪዎች አድማ በመምታት የሥነ ሥርዓት ሕጉ ተግባራዊነት እንዲዘገይ አስገድደዋል፡፡ በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በጋምቤላ፣ በትግራይና በሶማሊያ የተለያዩ ከማንነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ሥጋትን ፈጥረዋል፡፡
ለአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተመረጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን የመጀመርያ ስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለመረጣቸው ፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት፣ ‹‹ከትግራይ እስከ ደቡብ ጫፍ ሕዝብ ቅሬታ አንስቶብናል፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ ‹‹በእኛ ውስጥ ባለ መበላሸት ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ የሕዝቡን ጥያቄዎች ፈጥኖ ምላሽ ባለመስጠት ከሕዝብ ጋር ቅራኔ ውስጥ እየገባን መጥተናል፡፡ ሌላ አካል ላይ ጣት ከመቀሰር ይልቅ ችግሩ የራሳችን እንደሆነ አስምረን መሄድ አለብን፤›› ብለዋል፡፡ በዋናነትም ችግሩ የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ አንዳንድ ፀረ ሰላም ኃይሎች ደግሞ የተነሳውን ተቃውሞ በማፋፋም እየተጠቀሙበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ገዥው ፓርቲ በግንቦት ወር ምርጫውን ካሸነፈ በኋላ በነሐሴ ወር 2007 ዓ.ም. የድርጅቱን አሥረኛ ጠቅላላ ጉባዔ በመቐለ ከተማ አካሂዷል፡፡ በዚህ ጉባዔ ከተለዩ የፓርቲው ችግሮችና ጊዜ የማይሰጡ ጉዳዮች መካከል በአገሪቱ የተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር ችግር ዋነኛው ነው፡፡ ጉባዔው ሲጠናቀቅ ባለዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ ውስጥም መልካም አስተዳደርን የማስፈን ጉዳይ የሞት ሽረት መሆኑን ጠቅሶ ነበር፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ምርመራዊ ጋዜጠኝነት በማጎልበት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መዋጋት እንደሚያስፈልግ ሁሉ ተገልጾ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ገዥው ፓርቲ በለየው ችግር ላይ ተጨባጭ እንቅስቃሴ ውስጥ ሳይገባ የሕዝብ ቅራኔ ገንፍሎ ወጥቷል፡፡
ይህ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች እየተቀጣጠለ ባለበት ወቅት የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ከኢትዮጵያ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት ያስጠናው የመልካም አስተዳደር ጥናት ለከፍተኛ የመንግሥትና የፓርቲው አመራሮች ቀርቧል፡፡ በዚህም ሪፖርት እጅግ አስደንጋጭ የሆነ የመልካም አስተዳደር ችግር መለየቱ ተጠቁሟል፡፡ የሪፖርተር ምንጮች እንደሚሉት የጥናት ቡድኑ በተለያዩ የተመረጡ ክልሎች በተንቀሳቀሰበት ወቅት፣ በየክልሉ የፀጥታና የደኅንነት ኃይሎች ሳይቀር ክትትል ይካሄድባቸው ነበር፡፡ በኔትወርክ የተደራጀ የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነት ቡድኖች ሥር መስደዳቸውን የሚያሳይ በመሆኑ፣ ሪፖርቱ በከፍተኛው አመራር ላይ ድንጋጤን የፈጠረ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ችግሩ የመልካም አስተዳደር ነው?
የኢሕአዴግ ጠቅላላ ጉባዔ የመልካም አስተዳደር ችግር ህልውናውን እየተፈታተነው መሆኑን ከተስማማ በኋላ፣ የችግሩን መጠን ለማወቅ በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከልና በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር በአራት ክልሎችና በአዲስ አበባ በተካሄደው ጥናት የችግሩ መጠንና ስፋት አስደንጋጭ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ሕጋዊ ጨረታዎች፣ ታክስ፣ ኢንቨስትመንትና መሬት አቅርቦት የመሳሰሉ የአገልግሎት ዓይነቶች የሚመሩ ደላሎች፣ ባለሀብቶችና የተቋማት አመራሮች በፈጠሩት ኔትወርክ መሆኑን በቴሌቪዥን ከተላለፈው የባለሥልጣናቱ ውይይት መረዳት ተችሏል፡፡
በዚህ የባለሥልጣናቱ ውይይት ላይ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ ችግሩ የተፈጠረው ቢሮክራሲው በመተማመን ላይ ተመሥርቶ እንዲሠራ ስለተፈቀደ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
በየትኛውም አገር በአሜሪካም፣ በቻይናም ሆነ በኮሪያ ቢሮክራሲው በመተማመን ላይ የተመሠረተ ግንኙት እንደሌለው አቶ ዓባይ ፀሐዬ ያስረዳሉ፡፡ አሜሪካ ውስጥ የትራፊክ ፖሊስ የለበሰው ዩኒፎርም ደረት ላይ በተገጠመለት የድምፅ ማስተላለፊያ ካስቆመው ሾፌር ጋር ስለምን እያወራ እንደሆነ ማዕከል ላይ እንደሚታወቅ፣ ይህንን ድምፅ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ ሆኖ ያጠፋ የትራፊክ ፖሊስ በቀጥታ እንደሚባረር በምሳሌነት በመጥቀስ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር በዘመቻ ሳይሆን ተመሳሳይ ሥርዓቶችን በማበጀት መቅረፍ መጀመር እንዳለበት ይከራከራሉ፡፡ ‹‹በዘመቻ አመለካከት እስኪቀየር ስንጠብቅ እንበላለን፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡
በዚህ ውይይት ላይ ሌላው አስተያየት የሰነዘሩት የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በረከት ስምኦን የዘመቻ ሥራው በፍጥነት መጀመር እንዳለበት፣ ምክንያቱም ሲስተም እስኪበጅ ድረስ ጊዜ የሚሰጥ አለመሆኑን ተከራክረዋል፡፡
ውይይቱን የሰበሰቡት የፓርቲው ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒትር አቶ ኃይለ ማርያም፣ በአቶ በረከት በተነሳው ሐሳብ ላይ በመስማመት በፍጥነት የዘመቻ ሥራው መካሄድ እንዳለበት ከፍተኛ አመራሩን አሳምነዋል፡፡
ይሁን እንጂ አቶ ኃይለ ማርያም ሌላኛው በእኩል ፈተና የሆነባቸው ጉዳይ፣ ከተመሳሳይ የፖለቲካ ውይይት በኋላ አመራሩ ወደ ኔትወርኩ የመመለሱ ችግር ነው ብለዋል፡፡ ‹‹እዚህ እናወራለን እንጂ ከዚህ ስንወጣ የራሳችን ኔትወርክ እንዳይነካብን እንከላከላለን፤›› በማለት ከፍተኛ ትችት በመሰንዘር ከፍተኛ አመራሩ ለብቻው ፅዱ ሆኖ መቆም እንዳለበት መክረዋል፡፡
አቶ ኃይለ ማርያም ይህንን ሲሉ ከፍተኛ አመራሩ ራሱ በኪራይ ሰብሳቢነት ተዘፍቋል ማለታችው ይሁን ወይም ሌላ አይታወቅም፡፡ ይህ ከፍተኛ አመራር ራሱን ገምግሟል? ወይስ በደፈናው እየጮኸ ነው? የሚለው እስካሁን እንቆቅልሽ ነው፡፡
እሳቸው ግን በወቅቱ በድጋሚ ‹‹በብሔር፣ በአብሮ አደግነት፣ በጥቅም የምንከላከል ከሆነ ዋጋ የለውም፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡
በዚህ ሁኔታ የተጀመረው እንቅስቃሴ በአማራ ክልል 2,500 መካከለኛ ደረጃ አመራሮች ከሥራቸው ተሰናብተዋል፡፡ በትግራይ 1,500 እንዲሁም በአዲስ አበባ ከ600 በላይ መካከለኛ አመራሮች ከሥራቸው ተሰናብተዋል፡፡ አንዳንዶቹም በሕግ እንዲጠየቁ እየተደረገ ነው፡፡
የኢዴፓ የቀድሞ ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው ከሪፖርተር ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ችግሩ የመልካም አስተዳደር ገጽታ ቢኖረውም ከዚያ ላቅ ያለ ነው ይላሉ፡፡
‹‹በኢሕአዴግ አስተሳሰብ መልካም አስተዳደር የቢሮክራሲ ውጣ ውረድ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ወደ መንግሥት ቢሮዎች ሄዶ የሚገጥመው ውጣ ውረድና መጉላላት ተደርጎ ነው የሚታየው፡፡ በእርግጥም ይህ አንዱ የመልካም አስተዳደር መገለጫ ነው፤›› ይላሉ፡፡
ነገር ግን መልካም አስተዳደር የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት መገለጫ መሆኑን፣ መንግሥት በምርጫ አማካይነት ከሕዝቡ ጋር የገባውን ቃል በአግባቡ እየተወጣ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚቀርብ ጥያቄ ነው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በማለት ይገልጻሉ፡፡
ገዥው ፓርቲ የመልካም አስተዳደር ጥያቄን በዋናነት ከኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ጋር አስተሳስሮ ማየቱ ወደ ባሰ አዘቅት ውስጥ ይከተው እንደሆነ እንጂ መፍትሔ እንደማይሆነው ይከራከራሉ፡፡ ‹‹ለእኔ ምንጩ የፖለቲካ ሙስና ነው፡፡ ሥርዓቱ ለፖለቲካ ሥልጣን የበላይነት ብሎ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ ሙስና የሚፈጸም በመሆኑ ይኼን ተከትሎ የመጣ ነው፡፡ በቢሮክራሲው ውስጥ የሚቀጠሩት ሰዎች በሙያ ብቃታቸው፣ በትምህርት ደረጃቸውና በሥነ ምግባራቸው አይደለም በዋናነት የሚመለመሉት፡፡ በዋናነት የሚቀጠሩት ለሥርዓቱ ባላቸው ታማኝነት ነው፤›› በማለት ይከራከራሉ፡፡
ከ20 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ እያደረጉ ቢሆንም፣ አንድም ካድሬ የፖለቲካ ሙስና ፈጽሟል ተብሎ ዕርምጃ ሲወሰድበት ዓይተው እንደማያውቁ ይናገራሉ፡፡
ሌላው በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት መሥራችና የቀድሞው የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እንዲሁም የቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገብሩ አሥራት፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦት የተነሳው ተቃውሞ መገለጫ እንጂ ዋናው ምንጩ የዴሞክራሲ ዕጦት እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹ሕዝቡ በገዥው ፓርቲ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ሲያጣ የፈነዳ፤›› ነው ብለዋል፡፡
እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ የት ይደርሳል?
በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል የአቅም ግንባታና መልካም አስተዳደር ዲፓርትመንት ኃላፊ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ በተቋማቸው በተጠናው ጥናት መሠረት የችግሮቹ ዋነኛ ምክንያት ኪራይ ሰብሳቢነት ሲሆን ለዚሁ ደግሞ መነሻው በቂ ተጠያቂነት አለመረጋገጡ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የተወሰደው ዕርምጃ የጥናቱ ውጤትን ተከትሎ የመጣ መሆኑን፣ ትግራይ ላይም ሰፊ የማጣራት ሥራ እየተሠራ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከሚወሰደው ዕርምጃ በተጨማሪ ሙያዊ ብቃት ከዚህ በኋላ መፈተሽ እንደሚገባው ከስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የፖለቲካ ውግንና እንዳለ ሆኖ መሬት የሚያስተዳድር ስለመሬት አስተዳደር ዕውቀት ያለው መሆን አለበት፤›› ብለዋል፡፡
የፖለቲካ አመራሩም በተጨባጭ ውጤቱ መለካት እንዳበለትና ለዚህም ሥርዓት እንደሚበጅለት ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ በርካቶች መንግሥት የተያያዘውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ አመላለስ ግብታዊነት የተሞላበት እንዳይሆን እየጠየቁ ነው፡፡ በዚህ ሳምንት ምሁራን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ የተገኙት የሕግ ባለሙያው ዶ/ር መሐሪ ረዳኢ፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ በግምገማ ላይ የተመሠረተ መሆኑ እንደሚያሠጋቸው፣ ምክንያቱ ደግሞ ግምገማ በኔትወርክ ለተደራጁና ጉልበት ላላቸው ጉልበታቸውን በመጠቀም ታታሪና ሕግን የሚያስከብሩ ሠራተኞችን ለማጥቃት ምቹ ነው በማለት ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም እየተወሰደ ባለው ዕርምጃ እየተባረሩ ያሉት ሠራተኞች የሚጠቅሙና ታታሪዎች እንዳይሆኑ የሚል ጥያቄ አዘል አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በሰጡት ምላሽም ሥጋቱ ተገቢ ከመሆኑም አልፎ በተጨባጭ እንደተደረሰበት ገልጸዋል፡፡ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አሁንስ ችግሩ የመልካም አስተዳደር ነው? የሚለውን ጥያቄ እንዲያጎላው ያደርገዋል፡፡
ለገዥው ፓርቲ ውስጣዊ አሠራር ቅርብ የሆኑት አቶ ገብሩ አሥራት በበኩላቸው፣ ‹‹እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ ሕዝቡ በሚፈልገው መንገድ እየተወሰደ አይደለም፡፡ አካሄዱም ጥያቄውን ለመመለስ ሳይሆን ለማፈን በመሆኑ ችግሩ አንዴ ከእጅ ካመለጠ መመለስ የማይቻል በመሆኑ ቆም ብለው ያስቡበት፤›› ሲሉ ምክራቸውን ይለግሳሉ፡፡
አቶ ልደቱ የሥርዓቱ ቢሮክራሲ አብዛኛው ክፍል የታመመ በመሆኑ በሽተኛውን አካል ቆርጦ መጣል ፈተናው ዘርፈ ብዙ ቢሆንም፣ ያለው ብቸኛ አማራጭ ይኼው በመሆኑ መሠረታዊ የፖለቲካ ለውጥ ለማድረግ መንግሥት ቁርጠኝነቱን ነገ ዛሬ ሳይል መጀመር እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡