ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
እውነታው ከልብወለድ በላይ እንግዳ ነገር ነው!
እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 7/2014 “ድፍረት፡ የፊልም ጠለፋ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ባወጣሁት ትችት ድፍረት በሚለው ፊልም ላይ የኢትዮጵያ መሪ ተዋንያን ሆና በሰራችው የውርጃ ድርጊት ላይ የነበረኝን ቁጣ ገልጨ ነበር፡፡ በአበራሽ በቀለ እውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተሰራው ያ ፊልም በአሁኑ ጊዜ ጠለፋ እየተባለ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለአቅመ አዳም ባልደረሱ ልጃገረዶች ላይ የሚፈጸመውን እውነተኛ ኢሰብአዊ እና ኋላቀር ልምድ በማጋላጥ እየተሰራ ያለውን የትወና ታሪክ ይተርክልናል፡፡ ያ ፊልም እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 3/2014 በአዲስ አበባ ለመድረክ እይታ ለመቅረብ በሰከንዶች የሚቆጠር ጊዜ ሲቀረው እንዲቆም ተደርጓል፡፡ የድፍረት ፊልም ደራሲ የሆነው ዘረሰናይ ብርሀኔ መሀሪ መድረኩን በመቀበል በጭንቀት እና ሀዘን በተቀላቀለበት ሁኔታ ለታዳሚው የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጠ፡
የተከበራችሁ እንግዶች፣ አምባሳደሮች፣ ይህንን ፊልም እንድናቆም በፖሊስ ትዕዛዝ ተሰጥቶናል ምክንያቱም ከዚህ ጋር የተያዘ የፍርድ ቤት ጉዳይ አለ፡፡ ከዚህ በፊት የተነገረን ነገር የለም፡፡ የባህል ሚኒስቴር እናም መንግስት ስለዚህ ጉዳይ ያውቃል ማለት ነው፡፡ ይህንን ስንሰማ ለመጀመሪያ ጊዚያችን ነው፡፡ ግልጽ የሆነ ጥቃት ነው እተፈጸመብን ያለው፡፡ ይህ ሁኔታ በመፈጠሩ በእውነቱ ከልብ አዝናለሁ እናም በሌላ ጊዜ እንደምንገናኝ ተስፋ አደርጋለሁ…
“በድፍረት” ላይ በአገሪቱ ባለው ገዥ አካል የተሰነዘረው ይህ ጥቃት በኢትዮጵያ ላይ ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ላይ የተቃጣ የቅርብ ጊዜ አደጋ ብቻ ነው፡፡ አንድ ወር ቀደም ብሎ በነሀሴ ስድስት ታዋቂ የነበሩት የነጻው ፕሬስ የህትመት ውጤቶች ማለትም አፍሮ ታይምስ፣ አዲስ ጉዳይ፣ እንቁ፣ ፋክት፣ ጃኖ እና ሎሚ በገዥው አካል እንዲዘጉ ተደርጓል፡፡ እንደዚሁም በደርዘኖች የሚቆጠሩ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች እንዲታሰሩ ተደርገዋል ወይም ከአገር እንዲወጡ ተገደዋል፡፡ በሀምሌ ወር ውስጥ ገዥው አካል የዞን 9 ጦማሪያንን (ከርዕሰ ከተማዋ ከአዲስ አበባ ከመሀል ከተማው በስተደቡብ በኩል ትንሽ ወጣ ብሎ ከሚገኘው እና በተለምዶ ቃሊቲ እየተባለ ከሚጠራው የመለስ ዜናዊ የፖለቲካ እስረኞች የማጎሪያ እስር ቤት ከአንደኛው ብሎክ ቀጥሎ የተሰጠ ስያሜ) ህገወጥ በሆነ መልኩ ወደ 80 ለሚሆኑ ቀናት በቁጥጥር ስር አውሎ ካቆየ በኋላ አሁን በማጎሪያ እስር ቤቱ አስሯቸው ይገኛል፡፡ በተመሳሳይ ወር ገዥው አካል የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ቡድን አባል የሆነውን ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነጻነት እና የዴሞክራሲ ንቅናቄ እየተባለ የሚጠራውን ድርጅት ዋና ጸሐፊ የሆኑትን አንዳርጋቸው ጽጌን ወሮበላነትን በተላበሰ መልኩ የመን ላይ በመጥለፍ ወደ አዲስ አበባ በመውሰድ በማጎሪያ እስር ቤቱ ጨምሯቸዋል፡፡
ጋብቻ በጠለፋ (አስገድዶ መድፈር)፡ አደገኛው ተቋም በኢትዮጵያ፣
የጠለፋ ጋብቻ የሰው ልጅ ታሪክ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሲፈጸም የቆየ እጅግ በጣም ኋላቀር እና አስቀያሚ ከሆኑ ድርጊቶች መካከል አንደኛው መሆኑ የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም፡፡ በተለያዩ የሰብ ሰሀራ እና በደቡብ ኢስያ አገሮች በተለያየ መልኩ ሲተገበር ይታያል፡፡ በኢትዮጵያ በተለምዷዊው አተገባበሩ በግዳጅ በጠለፋ እንድታገባው የሚፈልገው ወጣት ጠላፊ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በግዳጅ ለማግባት የመረጣትን ልጃገረድ ተንኮል በተቀላቀለበት መልኩ ይከተሏታል፣ እናም እንደሚታደን አውሬ አባረው ለመያዝ እና በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ወጣት ወንዶች በፈረስ ጀርባ ላይ ተቀምጠው ሴቷ ከገበያ፣ ከትምህርት ቤት ወይም ደግሞ ሌሎች ስራዎችን ልትሰራ ሄዳ ስትመለስ ወይም ስትሄድ ከበስተኋላዋ ሳታስበው እንደ ዱብ እዳ ይከቧታል፡፡ ተጠላፊዋ ብቻዋን ወይም ደግሞ ከሌሎች ሰዎች ጋር አብራ ልትሆን ትችላለች፡፡ የሚጠልፋትን ወጣት በቁጥጥር ለማዋል ሊያግዙት አብረውት ከተገኙት ወጣቶች ጋር በመሆን ልጅቷን ጎትተው በመያዝ ተሸክመው ያገኛትን የሰው ሽልማት ከፈረሱ ላይ በማስቀመጥ ወደ ሰዋራ ቦታ ይዟት ይጋልባል፡፡ እዚያ ሰዋራ ቦታ ከደረሰች በኋላ ተጠላፊዋ እስከምታረግዝ ድረስ በጠላፊዋ ለቀናት ወይም ለሳምንታት በተደጋጋሚ የግዳጅ የግብረስጋ ግንኙነት ይፈጸምባታል፡፡ ተጠላፊዋ ጽንስ በጸነሰች ጊዜ የጠለፋት ሰው የእርሱን ልጅ ጽንስ ስለያዘች ሚስቴ ናት የሚል የባለቤትነት ስሜትን በእራሱ ላይ ያሳድራል፡፡ ከዚያ በኋላ ጠላፊው ወደ ተጠላፊዋ ወላጆች ዘንድ ሽማግሌዎችን መርጦ በመላክ ሽማግሌዎቹ እንዲያስታርቁ እና ለተጠላፊዋ ቤተሰቦች ካሳ ማለትም እንደ ገንዘብ እና ጥቂት ከብቶችን እንዲወስዱ በማድረግ ጋብቻው ህጋዊ እንዲሆን ጥረት ያደርጋሉ፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ ጠላፊው እና ተጠላፊዋ ልጃገረድ በሚስጥር እና በድብቅ ጋብቻ ለመፈጸም ስምምነት በማድረግ የማስመሰያ ጠለፋ እንዲካሄድ የሚያደርጉ ቢሆንም እንደዚህ ዓይነቱ የጠለፋ ዓይነት ብዙም የተለመደ አይደለም፡፡ ይሀ ኋላቀር የሆነ አስቀያሚ ልምድ በኢትዮጵያ ህግ የሚያስቀጣ ወንጀል ነው፣ ሆኖም ግን ይህ ኋላቀር ድርጊት በባለስልጣኖች መካከል የተለያየ እምነትን እያስያዘ በመምጣቱ በአሁኑ ወቅትም ጠለፋ በመተግበር ላይ ይገኛል::
በጠለፋ ጋብቻ ዙሪያ ስለሚነሱ በሽታዎች እና ስርጭታቸው የተካሄዱ ተጨባጭ የሆኑ ጥናቶች ባይገኙም በዚህ የአስነዋሪ ድርጊት ሰለባ በሚሆኑ ለአቅም አዳም ያልደረሱ ልጃገረዶች ላይ የስነ ልቦና እና አካላዊ ጉዳት በማድረስ በህይወት ዘመናቸው ላይ ከወሊድ ጋር በተያያዘ መልኩ የሚከሰቱ እንደ ፊስቱላ የመሳሰሉትን በሽታዎች ያስከትላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተጠላፊዋ የግዳጅ ግብረ ስጋ ግንኙነት በሚደረግባት ወቅት ገዳይ ከሆኑት በግብረ ስጋ ግንኙነት ከሚመጡ እንደ ኤች አይ ቪ ኤይድስ በመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎች ልትበከል ትችላለች፡፡
የአበራሽ በቀለ እውነተኛ አሰቃቂ ታሪክ
በኢትዮጵያ ለአቅመ አዳም ያልደረሰች እና የጠለፋ ጋብቻ ሰለባ የሆነችውን የአበራሽ በቀለ አሰቃቂ ታሪክ እ.ኤ.አ በ1999 “የትምህርት ቤት ልጃገረድ ገዳይ” በሚል ርዕስ ዘጋቢ ፊልም ተዘጋጅቶ ለዓለም አቀፍ ዓቀፍ ደረጃ ለእይታ እንዲቀርብ ተደርጓል (ሙሉ 50 ደቂቃ የሚፈጀውን ዘጋቢ ፊልም ከዚህ ጋ ጫና በማድረግ ይመልከቱ)፡፡ ቻርሎቴ ሜትካፍ የተባለችው የዘጋቢ ፊልሙ ዳይሬክተር ይህንን “የትምህርት ቤት ልጃገረድ ገዳይ” በውል ታስቦበት ሳይሆን በአጋጣሚ ነው ለመስራት ወደ ውሳኔ የመጣነው ብላለች፡፡ እ.ኤ.አ በ1996 ሜትካፍ አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኘው ከኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር/EWLA ከኦሪጂናል ጊዮርጊስ ጋር በመሆን ተቀራርበው በመስራት “የህጻናት ሙሽሮች በባህርዳር” [ኢትዮጵያ] በሚል ርዕስ ዘጋቢ ፊልም አዘጋጅታ አቅርባ ነበር፡፡ ሜትካፍ እንደምትግልጸው ከሆነ የ4 ዓመት ልጅ ሰርግን (የዚህችን ከቁጥጥር ውጭ በሆነ መልኩ ስታለቅስ የነበረች ህጻን ልጅ ሰርግ በታላቅ ሀዘን ውስጥ ሆኘ በፊልም ስቀርጸው ነበር) ንብረት ከተባለው የ11 ዓመት ልጅ ጋር ያደረገችውን የጋብቻ ስነስርዓት ተከታትያለሁ፡፡ ያ ዘጋቢ ፊልም “የህጻናት ሚስቶች ትረካ” በሚል ርዕስ በተባበሩት መንግስታት የህዝብ ፈንድ ድርጅት ገንዘብ ድጋፍ ሰጭነት ተዘጋጅቶ ከተጠናቀቀ በኋላ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅትን/ዩኒሴፍ ሽልማት አሸናፊ ሆኗል፡፡ ሜትካፍ አዲስ አበባ የአበራሽን ፎቶግራፍ በኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ጽ/ቤት ባየችው ጊዜ ስለአበራሽ የህግ ጉዳይ አስታወሰች፡፡ ሜትካፍ በተከታታይ ከአበራሽ ጋር ከተገናኘች በኋላ እና ለረዥም ጊዜ የወሰዱ ውይይቶችን ካደረጉ በኋላ ከእርሷ ጋር በመሆን ዘጋቢ ፊልም ለማዘጋጀት ፈቃደኛነቷን ገለጸች፡፡ በመቀጠልም ሜትካፍ እንዲህ ትላለች፣ “ከዚያ በኋላ ለስራው ማስፈጸሚያ የሚሆን ገንዘብ ለማሰባሰብ ወደ እንግሊዝ አገር ተመለስኩ፡፡ ለዚህ ስራ ተባባሪ ሆነው የቀረቡት በትክክለኛ እይታ/True Vision (በእንግሊዝ ቴሌቪዢን የፊልም እና የዘጋቢ ሰነዶች አምራች ካምፓኒ በመሆን ከሰብአዊ መብት እና ከዚህ ጋር ተዛማጅ በሆኑ ጉዳዮች ላይ እየሰራ በርካታ ዓለም አቀፋዊ ሽልማቶችን ያገኘ) እና የብዙ የፊልም ስራዎች አሸናፊ የሆነው የፊልም ባለሙያ ብሪያን ውድስ የፊልሙ አዘጋጅ እንዲሆን እንዲሁም ከፀሐይ በታች/Under the Sun ለሚለው ታዋቂ የቢቢሲ ፕሮግራም የኮሚሽን አርታኢ የሆነው ዳቪድ ፔርሰን ናቸው“ ብላች ሜትካፍ፡፡
“የትምህርት ቤት ልጃገረድ ገዳይ” በአንድ ወቅት መሳጭ እና የሚስብ፣ ስሜትን የሚገዛ አስድሳች፣ ቀልብን የሚስብ፣ ስሜትን የሚማርክ ኃይል ያለው፣ በውስጣዊ ግንፍልተኛነት ስሜት ያልተሞላ እና ሩህሩህነትን እና አፍቅሮትን በማሳየት እገዛ እንድናደርግ የሚገፋፋ መሳጭ ፊልም ነበር፡፡ ሜትካፍ “ጋብቻ በጠለፋ” የሚለውን አሳዛኝ ታሪክ በአጥጋቢ ሁኔታ ልትተርክልን የምትችል ጠንቃቃ፣ ጎበዝ፣ ብልህ እና ሩህሩህ የተዋጣላት የዘጋቢ ፊልም ባለሙያ ናት፡፡ ሜትካፍ እንደ ጎበዝ የዘጋቢ ፊልም ተራኪ የተለያዩ የፊልም ተዋንያን ገጸ ባህሪዎችን ማለትም– አበራሽ፣ የእርሷ ወላጆች፣ እህት እና ወንድሞች፣ የአበራሽ ጠላፊ ወላጆች፣ የአካባቢ ማህበረሰብ ሽማግሌዎች፣ የህግ ባለሙያዎች፣ ዳኞች– በማካተት እነዚህ ተዋንያን ታሪካቸውን በቀጥታ ለተመልካቹ እንዲነግሩ በማድረግ የተዋጣላት የጥበቡ ባለሙያ መሆኗን በተግባር አስመስክራለች፡፡ አሰቃቂው የጠለፋ ጋብቻ ተቋም ትረካ ከተለያዩ ዕይታዎች አንጸር ሲነገር ስትሰማ ሜትካፍ ካሜራዋን ወደዚሁ እውነታ ላይ አዞረች፡፡ በእርግጥ ሜትካፍ ካሜራውን ወደ እነርሱ አነጣጥራ መቅረጽ እንዲችል ባዘጋጀችው ጊዜ በትረካው ውስጥ የሚሳተፉት በርካታዎቹ ተዋንያን ገጸ ባህሪያት በፊልሙ ላይ መሳተፍ ጀመሩ፡፡ ሜትካፍ በፊልም ቀረጻ ውጤቱ ላይ ምንም ዓይነት የመጨመር ወይም የመቀነስ እና የማስተካከል ስራ አላደረችም፣ ስብከትም አላካሄደችም፣ እንዲያውም በጉዳዩ ውስጥ ሆኖ እውነታውን እንደወረደ ያለምንም ጣልቃገብነት ማየት እና መቅረጽ እጅግ በጣም ትዕግስትን እና ጽናት ያለው የሙያ ስነምግባርን የሚጠይቅ ከመሆኑ አንጻር እርሷም ለዚህ ክቡር የሆነ የሙያ ስነምግባር ተገዥ በመሆን ምንም ዓይነት የእርሷን ውሳኔ የመስጠት እንቅስቃሴ እና ሙከራም አላደረገችም፡፡ የዚያ ዓይነቱ የፊልም ቀረጻ አካሄድ ነው በተመልካቾቹ ዘንድ የአንድን የፊልም የተቀባይነት አሳማኝነት፣ ቀስቃሽነት እና ለህሊናም አስደንጋጭ ሆኖ ጠንካራ መሰረት በመያዝ ጎልቶ እንዲወጣ የሚያደርገው፡፡
ፊልሙን ከተመለከተ በኋላ ተመልካቹ የእራሱን አስተያየት እንዲሰጥ በእራሱ ህሊናም ሆነ በሌላ ውጫዊ አካል ይጠየቃል፡፡ ሆኖም ግን ውስጣዊ ባህሪው እንዳይታወቅ በታሪክ እና በልማድ ጉም ውስጥ እንዲጠፋ የተደረገን እና ቫይረሱን ሳይረጭ እና መጭውን የኢትዮጵያ ወጣት ልጃገረዶች እና ሴቶች ትውልድ ሳያጠፋ እየተባለ መሰናክል እና ጋሬጣ በመጣል ለዕይታ እንዳይበቃ ጭፍን እና አምባገነናዊ ትዕዛዝ እና ክልከላ እየተላለፈበት ባለ አሰቃቂ ተውኔት ላይ እንዴት አድርጎ አስተያየት ለመስጠት ይቻላል? እንደ ባለሙያ “የትምህርት ቤት ልጃገረድ ገዳይ” በሚለው ዘጋቢ ፊልም ላይ ያለኝ አስተያየት እንደዚያ ዓይነት አረመኒያዊ እና ግዙፍ የሆነ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ በዜጎቻችን ላይ እንዲያካሂድ የተፈቀደለትን ተቋማዊ ስርዓት ማውገዝ እና በቀጣይነትም ዛሬ እና ነገ ሳይባል እንደዚያ ዓይነቱ አስከፊ እና አስነዋሪ ድርጊት ከምድረገጽ እንዲጠፋ የተጠናከረ ዘመቻ መጀመር አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህንን ስናገር እራሴን ከፍ ከፍ እያደረግሁ አይደለም፡፡ የህጻናት መከላከያ ፈንድ/Children’s Defense Fund መስራች የሆኑት ማሪያን ራይት ኤድልማን አንድን የተጠላ መጥፎ ነገር በተቀነባበረ መልኩ ለማስወገድ የጥንካሬን አስፋለጊነት፣ ኃያልነት እና ጽናት በማስመልከት እንዲህ የሚል ንግግር አሰምተው ነበር፣ “በኢፍትሐዊነት ላይ ቁንጫ መሆን አለባችሁ፡፡ በቂ የሆኑ እንዲሁም በአግባቡ የተደራጁ እና ስትራቴጂካዊ በሆነ መልኩ ስስ ብልትን እየለዩ የሚቆነጥጡ ቁንጫዎች ታላቁን ውሻ እንኳ እንዳይመቸው ማድረግ ይችላሉ፡፡ እንደዚሁም ሁሉ በሀገር ላይ ታላቅ እና ዘለቄታ ያለው ሽግግር ማድረግ ይቻላል፡፡“
የአበራሽ ታሪክ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ላይ ታላቅ ትኩረትን በማግኘቱ እና ታላቅ ፊልም ተብሎ በሰንዳንስ እና በበርሊን የፊልም በዓል/Sundance and Berlin Film Festivals ላይ ቀርቦ አሸናፊ በመሆኑ እና በታላቅ አድናቆት እና ጭብጨባ ሽልማት እንዲያገኝ በመደረጉ ሜትካፍ ታላቅ ደስታ ተሰምቷታል፡፡ ሆኖም ግን የታሪኩ ባለቤት ማን መሆን ይኖርበታል የሚል እርባናየለሽ አጨቃጫቂ ክርክር ሊነሳ ይችላል የሚል እሳቤ በአዕምሮዋ ላይ የስጋት ደመና አጥሎቶባታል፡፡ ድፍረት በሚለው ዘጋቢ ፊልም ላይ የተተረከው ታሪክ በዋናነት የአበራሽ ታሪክ ነው፡፡ እናም ማንኛውም ለእርሷ የሚደረግ የገንዘብ ቃል ኪዳን እና ካሳ የሚያስገኝ ነገር ሁሉ መከበር አለበት፡፡ “ከሁሉም በላይ በዚህ የህጻንነት ለጋ እድሜዋ የእርሷ ድፍረት፣ ወኔ እና አስገራሚ ጽናት ታክሎበት ነው ይህን ፊልም የተዋጣለት እና ተወዳጅ እንዲሆን ያደረገው” ነበር ያለችው ሜትካፍ፡፡
በተጨማሪም ሜትካፍ እንዲህ የሚል አስተያየቷን ሰጥታለች፣ “ከ15 ዓመታት በፊት የአበራሽን ታሪክ ለህዝብ ዕይታ እንዲበቃ ያደረገውን “የትምህርት ቤትልጃገረድ ገዳይ” የሚለውን ፊልም በማቀነባበር ያዘጋጀውን የባለሙያዎች ቡድን ሳያመሰግኑ ማለፍ ታላቅ ስህተት ነው… የፊልም አቀነባባሪ ቡድኑ እና እኔ ይህንን ታሪክ ወደ ፊልምነት ለመቀየር ጠንካራ እና እልህ አስጨራሽ ስራ ሰርተናል፡፡ በዚህም ታላቅ ስራ ኩራት ይሰማናል፣ እናም ድፍረት የተመሰረተበት ታሪካዊ ዳህራ ጎልቶ እንዲወጣ በማድረጋችን የተሰጠንን ምስጋና እናደንቃለን፡፡“
“የትምህርት ቤት ልጃገረድ ገዳይ” የሚለው በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተው ዘጋቢ ፊልም በኢትዮጵያ እና በመላው አፍሪካ የሚገባውን ቦታ እንዲይዝ ባለመደረጉ እና አድናቆትም ሳይቸረው በመቅረቱ በጣም ያሳዝናል፡፡ በእኔ አመለካከት ይህ ዘጋቢ ፊልም በአፍሪካ እና በሌሎችም የዓለም ክፍሎች ለሴቶች የሰብአዊ መብት መከበር በጽናት በመቆም ታላቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ እና በዓለም ላይ ያሉትን በተለይም የአፍሪካን ሴቶች ለለውጥ የሚያነሳሳ አስፈላጊ ገጸበረከት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
የትምህርት ቤት ልጃገረድ ገዳይ፡ የአበራሽ ታሪክ፣
የአበራሽ ታሪክ የተሰራው ከአገሪቱ መናገሻ ከተማ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምስራቅ በ165 ኪ/ሜ ርቀት ላይ የአርሲ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው በአሰላ ከተማ ነው፡፡ (ሆኖም ግን የዚህ ዓይነት ተመሳሳይ ታሪክ በዚህች የአሰላ ከተማ ከመካሄዱ በፊት በሌሎች የኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች እንዲሁም ከአገሪቱ መናገሻ ከተማ ከአዲስ አበባ በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በሚገኙት ሳይቀር በቀላሉ እና በተንሰራፋ መልኩ ሲፈጸም የቆየ ክስተት ነበር፡፡)
ከዕለታት አንድ ቀን ገመቹ ከበደ በሚባል የ29 ዓመት እድሜ ባለው ጎልማሳ ሚስት ፈላጊ በሚመራ ሰባት አባላት ባሉት በአንድ የፈረሰኞች ቡድን በድንገት እስከተከበበችባት ቅጽበታዊ ጊዜ ድረስ አበራሽ ከጓደኞቿ ጋር በመሆን ከትምህርት ቤት በመመለስ ወደ ቤቷ በመሄድ ላይ ነበረች፡፡ ገመቹ እና ግብረአበር ጓደኞቹ አበራሽን በኃይል በመጥለፍ እና በማስገደድ በሚስጥር ምርኮኛ አድርገው ወደሚያቆዩባት ከመንደሩ ወጣ ብላ ወደምትገኘው ወደ ገመቹ ቤተሰቦች የሳር ጎጆ ቤት በፍጥነት ይዘዋት በረሩ፡፡ ይህንን ጉዳይ አበራሽ እንደምትገልጸው ከሆነ ከሰባቱ ፈረሰኞች ጋር ፊት ለፊት የተገኛኘችባት ያች ቀን እጅግ በጣም አስቸጋሪ እና የመጽዓት ቀን ነበረች፡፡ በእርሷ ስብዕና ላይ የተጋረጠው አደጋ የሌሊት ቅዠት እና በጥንት ጊዜ የሰው ልጅ ስልጣኔ ባልዳበረበት እና የህይወት እንቅስቃሴም ከእንስሳት ብዙም ባልተለየበት ዘመን እንደነበረው እና በታሪክ እንደምናውቀው ሁሉ አንድ የዋሻ ሰው የፈለጋትን እና የመረጣትን ሴት አናቷን በዱላ ይመታ እና ጸጉሯን ጨምድዶ በመያዝ ወደ ዋሻው ይጎትታታል፡፡ ከዚያም አውሬያዊ የሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነት በማድረግ የፍትወተ ስጋ ሀራራውን ከፈጸመ በኋላ በድል አድራጊነት መንፈስ ከዋሻው ውስጥ በመውጣት ደረቱን በእጆቹ እየደለቀ እና በእጆቹ እያጨበጨበ ለዋሻ ጓደኞቹ የእራሱ የግል ንብረት የሆነች ወይዘሪት የዋሻ ሴት እንዳገኘ አድርጎ ይገልጻል የሚለውን አንድ ሰው የሚያስበውን ያስታውሳል፡፡ በትምህርት ቤት ልጃገረድ ገዳይ ዘጋቢ ፊልም ላይ አበራሽ የተፈጸመባትን የጠለፋ ጥቃት ፍርኃት በተቀላቀለበት መልኩ በዝርዝር እንደዚህ በማለት ገልጻዋለች፡
ሰባት ባለፈረሶች ወደ እኔ እየጋለቡ መጡ እና በኃይል አስገድደው ጠለፋ ፈጸሙብኝ፡፡ በአለንጋ ገረፉኝ፡፡ እኔ እና ጓደኞቼ በከፍተኛ ሁኔታ እንጮህ እና እናለቅስ ነበር፡፡ ከያዙት ፈረስ ጀርባ ላይ እንድወጣ አስገደዱኝ፡፡ ከፈረሱ ሶስት ጊዜ ወደቅሁ፡፡ ከዚህም ከዚያ እያሉ እጆቼን ይዘው እየጎተቱ ከጠለፈኝ ቤተሶቦች ቤት ደረስኩ….
ገመቹ ማታ ወደ ቤቱ ሲመለስ አበራሽን ያሰቃያታል፡
ፊቴን በጥፊ ይመታኛል፣ እናም ለተወሰነ ጊዜ እራሴን እስታለሁ፡፡ ግዙፍ እና ትልቅ ሰው ስለሆነ ልገፋው ወይም ልገዳደረው አልችልም ነበር፡፡ እግሮቼን ኃይሉን እና ጉልበቱን በመጠቀም ይለያያቸዋል፣ ይፈለቅቃቸዋል፡፡ ከዚያም ስሜተቢስ በሆነ መልኩ ደበደበኝ እና ክብረ ንጽህናዬን ወሰደ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወንዶቹ ተመለሱ፡፡ ደምታለች ብለው ተናገሩ፣ እናም እንድቀመጥ ንጹህ ቦታ አሳዩኝ፡፡ ከዚያ በኋላ የደፈረኝ ሰው የእኔ ባልተብዬ መሆኑን ተረዳሁ፡፡
ክብረ ንጽህናዋን በወሰደ በማግስቱ ገመቹ ለአበራሽ አንድ ሲኒ ቡና ሰጣት፣ እናም የአገሩ ልጅ እንደሆነች እና የእርሱ ጓደኞች እርሷን ለመጠበቅ እዚህ እንዳሉ በመንገር ቀለደባት፡፡ አበራሽ የእርሷ ጠባቂ ዘበኞች ወደ ውጭ ወጣ ብለው ሲንሾካሾኩ ከቤቱ ማዕዘን ላይ አንድ ጠባቂ የሌለው ጠብመንጃ አየች፡፡ ቀስ ብላ ጠብመንጃውን በመያዝ ሳትታይ ወደ በቆሎው ሰብል ውስጥ ገባች፡፡ ገመቹ በድንገት ደረሰ እና ወዲያውኑ ተከታትሏት ወደ በቆሎው ሰብል ውስጥ ገባ:: አደገኛ በሆነ መልኩ እየቀረባት መጣ፡፡ አበራሽም ወደ እርሷ እንዳይጠጋ አስጠነቀቀችው፡፡ ገመቹ ግን የእርሷን ማስጠንቀቂያ ከምንም ባለመቁጠር ወደ እርሷ መጠጋት ጀመር፡፡ ድምጿን ከፍ አድርጋ “እንደገና ደግሜ ልነግርህ አልችልም” በማለት አስጠነቀቀችው፡፡ ልትተኩስ እንደምትችል አላመነም ነበር፡፡ አበራሽ የAK-47 መሳሪያን በመጠቀም ወደ አየር ሁለት ጊዜ ተኮሰች፡፡ ገመቹ ግን ወደ እርሷ እየቀረበ ከመሄድ አልተቆጠበም ነበር፡፡ ወደ እርሷ እየቀረበ መጣ፡፡ ጠብመንጃውን አወረደች እና ተኮሰች፡፡ ገመቹ ወደቀ እና መታችኝ በማለት የመጨረሻ ቃሉን ተናገረ፡፡ የአካባቢ ሚሊሻዎች ተኩሱን ሰሙና አካባቢውን ወረሩት፡፡ የገመቹ ጓደኞች የአበራሽን ጉሮሮ በማነቅ የጓደኛቸውን ደም ለመበቀል ሙከራ አደረጉ፡፡ አበራሽም በሚሊሻዎች በቀጥጥር ስር ውላ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰደች እና በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተከሰሰች፡፡ እርሷ ግን ራሷን ለመከላከል ያደረገችው ስለሆነ ትክክለኛ መሆኑን እንዲህ በማለት አስረዳች፡፡
የደረሰብኝን ስቃይ ሳስታውሰው እኔ ሰው ገድያለሁ ብዬ አላስብም፡፡ እኔ ይህንን የማየው አንድ ደመኛ የሆነ ጠላቴን እንደገደልኩ ነው፡፡ እኔ ለሌላ ሰው እንደማዝነው ሁሉ ለእርሱ ግን ምንም ዓይነት ሀዘን አይሰማኝም፡፡ እራሴን መግደል መቻል ነበረብኝ፡፡
የገመቹ ቤተሰቦች ታሪክ፤
የተዋረዱት የገመቹ ቤተሰቦች በአበራሽ ላይ የተደረገው ጠለፋ እና አስገድዶ መድፈር ምንም ስህተት እንዳላዩበት ተናገሩ፡፡ እራሳቸው ቤተሰቦቹ የዚህ ሰይጣናዊ ባህላዊ ልምድ ሰለባ ናቸውና፡፡ የእነርሱ ልጅ በአበራሽ ላይ የፈጸመው ተግባር ትክክል እና የተለመደ እንዲሁም ከትውልድ ትውልድ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ማህበረሰቡ የተቀበለው ባህል ነው፡፡ አበራሽ የመጠለፏን እና የመደፈሯን ጉዳይ ከእርሷ በፊት የነበሩት በሺዎች የሚቆጠሩ ልጃገረዶች ሲያደርጉት እንደነበረው ለምን በትህትና እንዳልተቀበለችው ሊገባን አልቻለም፡፡ የገመቹ አባት ልጃቸውን በገደለችው በአበራሽ ላይ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ እንደሚፈልጉ እንዲህ በማለት ተናገሩ፡
ለእኔ ጥሩ የነበረው ልጄ ነፍሰ ገዳይ ናት፡፡ የእኛን ህልውና ነው የዘረፈች፡፡ እርሷን ለጋብቻ ነበር የጠለፋት… በእርሷ ለመገደል አልነበረም… በእኛ ላይ ጥሩ ነገር አልሰራችም፡፡ ለዘላለሙ ሀዘን አውርሳናለች…እርሷ የእኔ ልጅ ነፍሰ ገዳይ ናት፡፡ የእኔ ምራት መሆን ትችል ነበር ወይም ደግሞ የእኔ የልጅ ልጆች እናት መሆን ትችል ነበር፡፡ እንደዚያ ነበር ልትሆን የምትችለው… ሆኖም ግን አሁን በእርግጠኝነት የእኔ ልጅ ገዳይ ናት፡፡ ሚስት ባሏን ስትገድል ታይቶም ተሰምቶም አያውቅ፡፡
ምንም እንኳ በተፈጠረው ክስተት በጣም ያዘኑ ቢሆንም ያለውን የማህበረሰብ ባህል ተከትሎ ልጃቸው በሰራው ስራ የገመቹ እናት ምንም ዓይነት ስህተት ያላዩበት መሆናቸውን እንዲህ በማለት ተናግረዋል፡
የእኔ ልጅ ምንም ዓይነት ተደርጎ የማያውቅ አዲስ ነገር አልሰራም፡፡ ብዙ ሰዎች በጠለፋ ጋብቻ ይፈጽማሉ…ብዙ ሴቶች በጠለፋ ጋብቻ ከፈጸሙ በኋላ የተሻለ ህይወት እንደሚኖሩ እና በርካታ ልጆችንም አፍርተው እንደሚኖሩ ይታወቃል… በሬ በጥሎሽ መልክ ሰጥቼ ልጀን ልድረው እቅድ ይዠ ነበር፣ ሆኖም ግን ከአዲስ አበባ የሚወዳቸውን ጓደኞች በመያዝ 3 በሬዎች ታርደው ማግባት እንደሚፈልግ ይነግረኝ ነበር፡፡ እጅግ በጣም ቆንጆ ህይወት ይኖረው ነበር፣ ነገር ግን እዚህ ያሉት ጓደኞቹ አሳሳቱት፡፡ ይህች ገዳይ ልጃገረድ እርሱን ትውደደው አትውደደው የማውቀው ነገር የለም፡፡ እኔ እንዲህ ዓይነቱ ነገር እንዲደረግ አልፈልግም ነበር፡፡ አጠቃላይ ህይወታችንን ነው ያጠፋችው፡፡
የአበራሽ ወላጆች ታሪክ፤
የአበራሽ ወላጆች ለሁለተኛ ጊዜ የጠለፋ ጋብቻ ተውኔትን አስተናግደዋል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት የመጀመሪያ ልጃቸው የሆነችው መስታወት የጠለፋ ጋብቻ ሰለባ ነበረች፡፡ ተስፋ የቆረጡት እና በሀሳብ የተብሰለሰሉት የአበራሽ አባት ስለልጃቸው ዕጣፈንታ አንዲህ በማለት ተናዝዘዋል፡
በእኛ አገር አካባቢ አንዲት ሴት አንድን ወንድ በምትገድልበት ጊዜ ወዲያ ወንዝ አቋርጣ ከአካባቢው በጣም ርቃ መኖር አለባት፡፡ ያለፈው ትውልድ የደነገገውን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን በማክበር መኖር አለባት፡፡ እኛ በሀዘን እንድዋጥ አድርጋናለች፣ ሆኖም ግን በህይወት መኖሯ በጣም ያስደስተናል…
በልጃቸው መጠለፍ ምክንያት ቤተሰቡ የደረሰበትን ስቃይ የአበራሽ እናት እንዲህ በማለት ገልጸዋል፡
ከብቶቻችንን በመሸጥ የደም ካሳ በመክፈል ለጉዳዩ እልባት መስጠት አለብን፡፡ ከዘመዶቻችን ገንዘብ መበደር አለብን… መስታወት በተጠለፈችበት ጊዜ አባቷ ቢላዋ ይዘው በመውጣት ልጃቸውን ከጠላፊዎች ለማዳን ጥረት አድርገው ነበር፡፡ የአበራሽ እናትም ጠላፊዎች ባለቤቴን ይገድሉብኛል በሚል ስጋት አብሬ ወጣሁ ብለዋል፡፡ በክስተቱ ላይ ቢገኝ ኖሮ ወይ ይገድሉት ነበር አለዚያም እርሱ ይገድላቸው ነበር፡፡ የሰው ህይወት ከሚያልፍ በሚል መስታዋትን ጠላፊዎች እንዲወስዷት ፈቀድን ምክንያቱም ምንም ዓይነት ሰው እንዲሞት አልፈለግንምና፡፡
የአስታራቂ ሽማግሌዎች ታሪክ፤
በቤተሰቦች መካከል ያለውን ጉዳይ ያስታረቁት የማህበረሰቡ አስታራቂ ሽማግሌዎች ጉዳዩ የተበላ እቁብ ነው፣ አስቀድሞ ተጠናቅቋልና፡፡ ለጉዳዩ የመጨረሻ እልባት በመስጠት ጉዳዩ ተዘግቶ ነበር፡፡ ከሽማግሌዎቹ መካከል አንደኛው እንዲህ በማለት ገለጻ አድርገው ነበር፤
ጠላፊው ከተገደለ በኋላ እኛ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ገብተናል፡፡ ለቤተሰቦች እንዲህ ብለን ነገርናቸው፣ “እርሱ ሞቷል፣ ስለሆነም እናንተ መታረቅ አለባችሁ፡፡ የሟቹን ቤተሰቦች እርቅ ማውረድ እንዳለባቸው ነግረናቸው ነበር፡፡ ፍርድ ቤት እርሷን (አበራሽን) በነጻ እንዲለቃት እንፈልጋለን፡፡ ከመጀመሪያውም ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት መሄድ አልነበረበትም፡፡ ጉዳዩን ዘግተነዋል፡፡ይህ ነገር አልቋል… አልቋል፡፡
የመስታወት ታሪክ (የአበራሽ ታላቅ እህት)፣
መስታወት ለኢትዮጵያ አሎምፒክ እንድትሮጥ የገንዘብ ጉርሻ ተሰጥታ ነበር፡፡ መስታወት የመጀመሪያዋ ጥቁር አፍሪካዊ እና በ10 ሺህ ሜትሮች የወርቅ ሜዳሊያ እ.ኤ.አ በ1992 በባርሴሎና ኦሎምፒክ ውድድር አሸናፊ የሆነችው የደራርቱ ቱሉ ጓደኛ የመጀመሪያ ልጅ ናት፡፡ መስታወት በሀገር ውስጥ በሚደረግ የመንገድ ላይ ሩጫ ኮከብ ሯጭ ስትሆን በርካታ ሜዳሊያዎችን ወስዳለች፡፡ መስታወት በጠለፋ ከተወሰደች በኋላ ከጠላፊዋ 4 ልጆችን የወለደችለት ሲሆን አጠቃላይ ህልሟን ሁሉ አጨልማ በአንድ ሊወድቅ በተንጋደደ ደሳሳ ቤት ውስጥ ጠላ በመሸጥ ኑሮን በመግፋት ላይ ትገኛለች፡፡ የጠላፊ ባሏ አባት የአበራሽን ጉዳይ ለማስታረቅ ከተመረጡት ሽማግሌዎች አንዱ ናቸው፡፡ መስታወት ስላለፈው ነገር እንዲህ በማለት ትናገራለች፡
ሻምፒዮን ለመሆን እመኝ ነበር፡፡ ብዙውን ጊዜ አንደኛ እየወጣሁ በማሸነፍ ሜዳሊያ እሸለም ነበር፡፡ የረዥም ርቀት ሩጫዬን ለማሻሻል ስልጠና ወስጀ ነበር፡፡ ስፖርትን በጣም እወድ ነበር ሆኖም ግን ባልታሰበ ሁኔታ በተጠለፍኩ ጊዜ እርግፍ አድርጌ ተውኩት…በዚህ አካባቢ ያሉትን ወንዶች በምመለከትበት ጊዜ አብዛኞቹ የእራሳቸውን ህይወት ለማሻሻል ደንታ የላቸውም፡፡ ሁሉንም የሚያስደስታቸው ነገር ቢኖር የአንድን ሰው ልጅ ጠልፈው በመውሰድ ሚስቶቻቸው ተብለው እንዲጠሩላቸው ይፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ወንዶች የሚሰሩት ነገር በጣም ያበሳጨኛል፡፡
በመጨረሻም መስታወት አራቱን ልጆቿን እና ባልተብዮውን እርግፍ አድርጋ በመተው ተሰወረች!
የሙላቷ ታሪክ (የአበራሽ ታናሽ እህት)፣
ሙላቷ የእህቶቿ እጣ ፈንታ በእኔም ይደርስብኛል በማለት በጣም ትፈራ ነበር፡፡ ለዚህም ከመፍራቷ የተነሳ እጅ በመስጠት እንዲህ ብላ ነበር፡
በአበራሽ ላይ የተፈጸመው ድርጊት በእኔም ላይ በቅርቡ ይፈጸማል የሚል እምነት አለኝ፡፡ አበራሽ በጠለፋ ከተወሰደች ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ሁልጊዜ በፍርሀት ቆፈን ውስጥ ተውጨ ነው ያለሁት፡፡ እራሴ ብቻዬን ወደ ገጠር አካባቢ መሄድ እንኳን አልችልም፡፡ ወደ ትምህርት ቤት ወይም ወደ ገበያ በምሄድበት ጊዜ ሁልጊዜ በፍርሀት ቆፈን ውስጥ ተሸብቤ ነው…ምንም ዓይነት ተስፋ የለኝም…ላደርግ የምችለው ነገር ቢኖር እቤት ውስጥ መደበቅ ብቻ ነው… እናም ትምህርቴን ለማጠናቀቅ የሚሆንልኝ አይሆንም… የትም ቦታ መሄድ እና መንቀሳቀስ አልችልም… ስለሆነም ላደርግ የምችለው ነገር ቢኖር የጠለፋ ጥቃት እስከሚፈጸምብኝ ድረስ ተቀምጨ መጠበቅ ነው…
የመስታወት ጠላፊ – ባል ታሪክ፤
የመስታወት ጠላፊ-ባል በጠለፋ ጋብቻ መፈጸም እስከዚህም ድረስ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብሎ አያስብም ነበር፡፡ ሁሉም ወንድ የሆኑ ወጣቶች በየማህበረሰቡ ሁልጊዜ ጠለፋ እንደሚያደርጉት ሁሉ እንደዚሁም ወደፊትም ይደረጋል፣ ይቀጥላል፡፡ ጠለፋ በሴቶች ላይ የሚደረግ ለእነርሱ የተዘጋጀ መልካም ነገር ነው፡፡ እንዲህ በማለትም ገለጻ አድርጓል፡
ወንዶች ሴቶችን የሚጠልፉት በፍቅር ሲወድቁ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል መስታወትን ጠለፍኳት፡፡ አንድ ነገር ብናገር ብተፈቅዱልኝ በእውነት እወዳታለሁ፣ የእርሷ ወላጆች ሙሉ በሙሉ ስምምነት በማድረጋቸው ምክንያት አይደለም፡፡ የእኔ ወላጆች ከሌላ አካባቢ እንዳገባ ነግረውኝ ነበር፣ እናም ለዚያ ዝግጅት እቅድ ተይዞ ነበር ሆኖም ግን ወጣት ነበርኩና ተገፋፋሁ፡፡ ማን ጌታ እና አለቃ እንደሆነ ለማሳየት ወሰንኩ፡፡ ሌላ ሰው ጠልፏት ይሆናል በማለት ፈራሁ፡፡ ይኸ ነገር እንዲያመልጠኝ አልፈለግሁም፡፡ አፈንኳት እና ክብረ ንጽህናዋን ወሰድኩት፡፡ በማግስቱ ለእርሷ ወላጆች ገንዘብ ተላከ እና የሰርጉ ቀን እንዲቆረጥ እና ዝግጅት እንዲጀመር ለማድረግ ሽማገሌዎች ተላኩ፡፡ በመካከሉ እርሷ አረገዘች፡፡ በአሁኑ ጊዜ አራት ልጆች አሉን እናም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡
የህግ ባሙያው ታሪክ፣
የአበራሽ ጠበቃ የሆነችው መዓዛ አሸናፊ የሴቶችን ጥቃት እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ለመከላከል በማሰብ ከጥቂት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበርን መሰረተች፡፡ መዓዛም ስለጉዳዩ እንዲህ በማለት አስረዳች፡
ስለአበራሽ ጉዳይ ቀደም ሲል አውቀናል ምክንያቱም ይፋ ተደርጎ ነበርና…እናም የአበራሽን ጉዳይ በመያዝ በፍርድ ቤት ለመቆም ወሰንን ምክንያቱም በእንደዚህ አይነቱ ኋላቀር ባህል መዝመቱ በጣም አዲስ እና ስርነቀል እርምጃ ነበርና እንዲሁም ጠለፋ አስቀያሚ የሆነ እና ጋብቻን ለመፈጸም የሚያገለግል መጥፎ ባህል ነበርና፡፡ ስለሆነም ይህንን አስቀያሚ የሆነ ጠለፋ የሚባል መጥፎ ባህል ለመገዳደር አበራሽ የመጀመሪያ ሆነች…ምስክሮችን ለማግኘት አልጋ በአልጋ እና ቀላል ነገር አልነበረም ምክንያቱም ማህበረሰቡ ለእንደዚህ ዓይነት ወንጀል ምስክርነት ለመስጠት ተባባሪ አይደለምና፡፡ ሆኖም ግን ህጉ ስላለን በጉዳዩ ላይ ለመቀጠል ሙከራችንን ጀመርን…ለፖሊስ የተናገርኩት አንድ ነገር ቢኖር ግዴታችሁን መወጣ ባትችሉ… እና ህጉ ተግባራዊ ባይደረግ እናንተ ከስራ ትወገዳላችሁ፡፡ ስለሆነም ስራቸውን ላለመስራት ማመንታታቸውን አቆሙ፡፡
ዳንኤል በቀለ የሚባል ወጣት የህግ ባለሙያ የጠለፋ ጋብቻ ጉዳዮችን ለመመርመር እና ወደ ህግ ፊት ለማቅረብ ከኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ጋር አብሮ ለመስራት ፈቃደኛ ሆነ፡፡ ዳንኤል የአበራሽ ጉዳይ በቀረበበት ወቅት ሌላ የጠለፋ ወንጀል የተፈጸመባትን ሰውነት የምትባል ወጣት ሴት ጉዳይ በመያዝ ከቤተሰቦቿ መንደር ድረስ በመሄድ ተቀራርቦ በመስራት ላይ ነበር፡፡ ዳንኤል በአሁኑ ወቅት የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ጉዳዮች ክፍል ኃላፊ ሆኖ በመስራት ላይ የሚገኝ ሲሆን ዓለም አቀፋዊ የሆኑ ጉዳዮችን በማየት የክትትል ስራዎችን ያካሄዳል እንዲሁም ከዚህ ጋር በተያያዙ ተዛማጅ ነገሮች ላይ ምርምር ያደርጋል፣ ለሰብአዊ መብቶች መከበርም የውትወታ ተግባራትን ያከናውናል፡፡ (እ.ኤ.አ በ2007 ዳንኤል እና ነጻነት በኢትዮጵያ ባለው ገዥ አካል እራሳቸው ተጠልፈው “መንግስትን የመገልበጥ ሙከራ” የሚል የሸፍጥ ክስ ተመስርቶባቸው በነበረበት ጊዜ እነርሱን የሚያበረታታ ጽሁፍ አውጥቸ የነበረ በመሆኑ ታላቅ ደስታ ተሰምቶኛል (“የዝንጀሮ የፍርድ ቤትውሎ በይስሙላው ፍርድ ቤት” በሚል ርዕስ አዘጋጅቸ አቅርቤው የነበረውን ትችት ይመልከቱ… እንደ ዳንኤል ያለ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ ጥረት ማድረግ ይችል የነበረን ሰው ከዚያች አገር ማጣት ቀላል ጉዳት አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያን መጎዳት በአፍሪካ መካስ እያየሁት ስለሆነ ቢያንስ በዚህ እንኳ እራሴን አጽናናለሁ፡፡)
ዳንኤል እንዲህ በማለት ገለጻ አድርጎ ነበር፡
በሰውነት ጉዳይ ላይ ፖሊስ በጣም ውሱን የሆነ ነገር ነበር ያደረገው፡፡ አንድ ጊዜ እንደዚህ ያለ የጠለፋ ወንጀል ከተፈጸመ በኋላ ከእንደዚህ ያለው ድርጊት ባህላዊ በሆነ መልኩ እዚያው በመስማማት እና በማስታረቅ የተጠለፈችዋ ሴትም በዚያው ሚስት እንድትሆን በማግባባት የሚጨርሱት ጉዳይ ስለሆነ በህግ አስፈጻሚ ኃላፊዎች በኩል ህጉን ከማስፈጸም አንጻር እራሳቸውን ወደ ጉዳዩ ላለማስገባት ቸልተኝነት ጎልቶ ይታይ ነበር፡፡ እንደ አበራሽ ጉዳይ በጠለፋ ወንጀል ጉዳያቸው በመታየት ላይ የሚገኙ እስከ አሁን ድረስ እልባት ያላገኘውን የሰውነትን ጉዳይ ጨምሮ አምስት የክስ ጉዳዮች አሉ፡፡
የዳኛው ታሪክ፣
አደጋው ከተፈጸመ ሁለት ዓመት በኋላ ሶስት ዳኞችን ያካተተ ችሎት ላይ ተሰየመ፡፡ አበራሽ ከወንጀል ነጻ በሆነ ስሜት ላይ ሆና ቆማች፡፡ በመቀመጫ ወንበሩ ላይ ከተሰየሙት ዳኞች መካከል አንደኛው እንዲህ የሚል ንባብ ማሰማት ጀመረ፡
እ.ኤ.አ በ1996 ገመቹ ከበደ ከጥቂት ግብረ አበሮቹ ጋር ሆኖ የጠለፋ ወንጀል እስከፈጸሙባት ድረስ የአሁኗ ተከላካይ ወደ ቤቷ በመመለስ ላይ ነበረች… በዚያው ዕለት ምሽት ላይ ከቤቱ በመውሰድ በኃይል አስገድዶ ክብረ ንጽህናዋን ወስዷል… ህይወቷን ለማትረፍ ስትል በመተኮስ ህይወቱን አጥፍታለች…
…የመከላከያ ማስረጃው እና የተወሰደው እርምጃ የሚጣጣም ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ሟች ተከላካይን ለመጉዳት ኃይል ተጠቅሟል፡፡ የሟች ድርጊቶች የሀገሪቱን ህግ የጣሱ ናቸው፡፡ ተከላካይ የወሰድሽው እርምጃ እራስን ከመከላከል አንጻር ብቸኛው አማራጭ ነበር፡፡ ስለሆነም የሰራሽው ስራ ጥፋተኛ አያሰኝሽም፡፡ ፍርድ ቤቱ በነጻ አሰናብቶሻል፡፡
ስለጠለፋ ጋብቻ ያልተነገረው ታሪክ፣
አስቀያሚው የጠለፋ ጋብቻ ተቋማዊ ህይወት ለምንድን ነው በመቀጠል ላይ ያለው እና በኢትዮጵያ እያደገ የመጣው? ያ በሚሊዮኖች ዶላር የሚያስወጣ ጥያቄ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል የጠለፋ ጋብቻን፣ የህጻናት ሙሽራነትን እና በሌሎችም ችግሮች ላይ ግንዛቤ ወስዷል፡፡ ገዥው አካል የእንደዚያ ዓይነቱ ድርጊት መተግበር በጠቅላላ በሴቶች ላይ አዋራጅ፣ አስደንጋጭ እና ከሰብአዊነት በታች የወረደ ችግር ብቻ አይደለም የሚያስከትለው ሆኖም ግን ለአደጋው በጣም ተጋላጭ በሆኑት የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ክፍሎች እና እድሜአቸው ለአካለ መጠን ያልደረሱ የገጠር ልጃገረዶች ላይ የከፋ ይሆናል ከሚል እሳቤም ጭምር ነው፡፡ ይህ ህገወጥ ድርጊት በዓለም አቀፉ የሰብአዊነት ህግ የተወገዘ መሆኑን አሳምሮ ያውቃል፡፡ ገዥው አካል ከዚህ ጋር በሚጻረር መልኩ ግን ሴቶች የፖለቲካው የጀርባ አጥንት ናቸው በማለት ሲያውጅ ይደመጣል፡፡ እ.ኤ.አ በ2010 አሁን በህይወት የሌለው መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ ሜይ 2010 በተደረገው አገር አቀፍ ምርጫ 99.6 በመቶ የድምጽ ውጤት በማምጣት በዝረራ አሸንፊያለሁ በማለት ለፓርቲው ድል መቀዳጀት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉለት ሴቶች ከመጠን ያለፈ ምስጋና እና ውደሳ በማድረግ የድል በዓሉን ለማክበር መስቀል አደባባይ በመገኘት የሚከተለውን ዲስኩር በማሰማት እንዲህ ብሎ ነበር፣ “…የድርጀታችን የጀርባ አጥንት የሆኑት እና በሴቶች እኩልነት ዙሪያ ያለንን የድርጅታችንን መልካም አካሄድ የተገነዘቡት እና ለትግሉ በቆራጥነት ለተሰለፉት፣ እንዲሁም በዚህ የሰላም፣ የልማት እና የዴሞክራሲ ግንባታ ጉዙ በጽናት ከጎናችን ለተሰለፉት የኢትዮጵያ ሴቶች ያለንን ከፍተኛ አክብሮት እና ምስጋና እናቀርባለን፡፡ ለኢትዮጵያ ሴቶች ያለን አድናቆት ወሰን የለውም!“ እንደዚህ ያለ ኋላቀር እና እንስሳዊ ድርጊት የህብረተሰቡ ግማሽ አካል በሆኑት ሴቶች ላይ በመፈጸም ላይ ያለ አስቀያሚ ወንጀል የእርሱ የጀርባ አጥንት በሆኑት ሴቶች ላይ እየተፈጸመ እና ቀጣይ ሆኖም በመተግበር ላይ መሆኑን እያየ ያለ ገዥ አካል እንዴት እንዲህ ያለ ንግግር ሊያሰማ ይችላል? ይህንን እርስ በእርሱ የሚጣረስ አራምባ እና ቆቦ የሆነ ዝባዝንኪ ንግግር ለማድረግ የሚያስችል የሞራል ብቃትስ አለውን?
የጠለፋ ጋብቻ እና ያለእድሜ ጋብቻ በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች በየዕለቱ ይካሄዳል፡፡ የእንደዚህ ያለው ልምድ መተግበር ባለፉት ጥቂት ሳምንቶች ብቻ ጠቅላላ የሆነ ማስረጃ ማግኘት ይቻላል፡፡ የችግሩን ስፋት እና ጥልቀት የሚያመላክቱ በጣም ጥቂት የሆኑ ተጨባጭነት ያላቸው እና ስልታዊ የሆኑ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ ሆኖም ግን ይህንን አደገኛ የሆነ ኋላቀር ባህል ለማስቀረት ወይም ደግሞ ቢያንስ ለመቀነስ የሚያስችሉ ፈጣን የፖሊሲ እርምጃዎች እና ወሳኝ የሆነ አስፈጻሚ አካል እንደሚያስፈልግ ከበቂ በላይ መረጃዎች አሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2004 የህዝብ ምክር ቤት/Population Council ትንተና እንዲህ የሚል ጥቆማ ሰጥቶ ነበር፣ “ኢትዮጵያ ጥቂት በጣም መብትን የሚጥሱ የጋብቻ ልምዶች ማለትም እንደ የጠለፋ ጋብቻ፣ ወንድም ወይም አጎት ሲሞት ወንድም በግድ ሚስቱን እንዲወርስ መደረግ የመሳሰሉት መፈጸሚያ አገር ናት፡፡“ እ.ኤ.አ በ2005 “ጎጅ ልማዳዊ ተሞክሮዎች በኢትዮጵያ/Harmful Practices in Ethiopia” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ተመሳሳይ ዘገባ እንዲህ በሚል መልኩ ቀርቦ ነበር፣ “የጠለፋ ጋብቻ በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ ይገኛል፡፡ በአንድ የመነሻ መረጃ ለማግኘት በተደረገ ጥናት መሰረት በህብረተሰቡ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑ የልጃገረዶች ጋብቻዎች የሚፈጸሙት በጠለፋ መሆኑን ያመላክታል፡፡ የመተግበር ስፋቱ እና ጥልቀቱ ደግሞ እንደ ኦሮሚያ እና ደቡብ በመሳሰሉት ክልሎች ላይ የጠነከረ ሆኗል“ ይላል፡፡ እንደ የተባበሩት መንግስታት የ2009 ጥናት “በኢትዮጵያ የጠለፋ ጋብቻ ተደጋግሞ የመከሰት መጠኑ ከፍተኛ ሲሆን የአገሪቱ አማካይ 69 በመቶ ሲሆን በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ደግሞ 92 በመቶ” መሆኑን ያመላክታል፡፡ እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው አብይ ጉዳይ የጠለፋ ጋብቻ እና ያለእድሜ ጋብቻ ችግሮች በአንድ በተወሰነ አካባቢ ወይም ደግሞ በአንድ ክልል ብቻ የሚወሰኑ ሳይሆን በመላ ኢትዮጵያ በበርካታ የገጠሪቱ ማህበረሰብ አካባቢዎች የሚፈጸሙ መሆናቸው ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ግንዛቤ ለመውሰድ በጣም አስቻጋሪ ሆኖ የሚቀርበው ነገር ገዥው አካል የጠለፋ ጋብቻ ሰለባዎችን መብት ለማስከበር የሚያስችል አስፈላጊ እና በቂ ሀብት ያለው የመሆኑ እውነታነት ነው፡፡ በአስገድዶ መድፈር እና በመጽሐፍ የባለቤትነት መብት ወንጀል ላይ ግልጽ እና የማያሻሙ ህጎች አሉ፡፡ ገዥው አካል ጠላፊዎችን እና ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ልጃገረዶችን አስገድደው የሚደፍሩ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ የሚያቀርቡ እና ህጉን ለማስፈጸም የሚያስችሉ በመላ ሀገሪቱ ተሰራጭተው የሚገኙ ከበቂ በላይ የሆኑ በርካታ ፖሊሶች፣ ሚሊሻዎች፣ ዳኞች እና አቃብያነ ህጎች አሉት፡፡ በእርግጥ እነዚህ የሚባሉት ፖሊሶች፣ ሚሊሻዎች፣ አቃብያነ ህጎች እና ዳኞች በኒዮርክ እንደተደረገው ሁሉ ወደ ዝርዝር ጉዳይ ጠልቀው በመግባት የተቃዋሚ የፖለቲካ አመራሮችን እና አባላትን አስገድደው ለገዥው አካል በማስረከብ የተካኑ አፈ ጮሌዎች ናቸው፡፡ ሲነሽጣቸው ሽጉጥ ወይም ደግሞ AK-47 አያወጡም አይባልም፡፡ ሆኖም ግን ህጻናት የሚደፍሩትን እና የሚጠልፉትን ወንጀለኞች በቁጥጥር ስር ለማቅረብ በአጠቃላይ ኃይልየለሽ ደካሞች ሆነው ይገኛሉ!
በጣም እንቆቅልሽ የሆነው ሌላው ነገር ደግሞ አበራሽን በነፍሰ ገዳይነት በቁጥጥር ስር አውለው ለህግ ያቀረቧት ፖሊሶች ገመቹ እንዲዚያ ያለ የጠለፋ ወንጀል ሲሰራ አንዲት ነገር አላደረጉም ነበር፡፡ የአበራሽ ጉዳይ በተንጠልጠል በነበረበት ጊዜ እና ጠበቃ ዳንኤል በቀለ የሰውነትን የጠለፋ ጋብቻ ጉዳይ እያጣራ ባለበት ጊዜ የአካባቢ ፖሊሶችን በማዘዝ የምርመራ ስራውን እንዲጀምሩ እና እንዲያጣሩ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ ፖሊሶች ግን ያንን ለማድረግ ቸልተኞች ነበር የሆኑት እናም ምናልባትም ለሜትካፍ ለማይታጠፈው የቀረጻ ካሜራም ቢሆን፡፡ እውነታው ግን ገዥው አካል የነጻው ፕሬስ አባላት እና ጦማሪያንን ቅጽበታዊ በሆነ መልኩ እየያዘ በማጎሪያ እስር ቤቶች በማሰቃየት ላይ ይገኛል፣ ሆኖም ግን እንደዚህ ባለ ሁኔታ የተደራጁ እና ለአቅመ አዳም ባልደረሱ ልጃገረዶች ላይ ጭካኔ የተሞላበት አውሬአዊ እና ጭራቃዊ ድርጊት የሚፈጽሙባቸውን ወሮበላ ወንጀለኞችን በቄጥጥር ስር በማዋል ወደ ህግ በማቅረብ ለማስቀጣት ጥረት ሲያደርግ አይታይም፡፡ ገዥው አካል የኢንተርኔት አገልግሎትን፣ ሬዲዮን ለማፈን እና የሳቴላይት ግንኙነቶችን በአገር ውስጥ እንዳይደርሱ ለማገድ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ያፈስሳል፡፡ ሆኖም ግን የጠለፋ ጋብቻን አዙሪት በመስበር ከሀገሪቱ ለማስወገድ እንዲቻል አስፈላጊውን የሆነ የቅስቀሳ ትምህርት በመስጠት የህዝቡን ግንዛቤ ከፍ በማድረግ ለውጥ ማምጣት እንዲቻል የሚያስፈልገውን ጥቂት ዶላሮች እንኳ አይመድብም፡፡ ገዥው አካል ጎጅ ማህበራዊ መልማዶችን ለማስወገድ በሚል ከምዕራቡ ዓለም በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር እርዳታን ይቀበላል፡፡ በዚያ ገንዘብ ምን እየተሰራበት ነው? በግልጽ ለመነጋገር ገዥው አካል የጠለፋ ጋብቻን ተቋማዊ አሰራር ለማስወገድ የአሰራር ዘዴው እና የማስፈጸሚያ ገንዘቡ እንዲሁም ሌሎች ግብዓቶችን አጥቶ አይደለም ተግባራዊ ማድረግ ያልቻለው፡፡
ታዲያ ችግሩ ምንድን ነው? ገዥው አካል እንደዚህ ያለ ኋላቀር እና ህገወጥ ወንጀል እየተሰራ እያየ ለምንድን ነው እጆቹን አጣጥፎ በደረቱ ላይ በማድረግ አላየሁም አልሰማሁም የሚለው? ገዥው አካል ዝም ብሎ በዘፈቀደ ለችግሩ ምንም ዓይነት ትኩረት ባለመስጠት የተወው ነገር ሊሆን ይችል እንዴ? ምንም ለማድረግ ካለመቻል ደካማነት የመነጨ ይሆን? በአካባቢ ማህበረሰቦች ላይ እንደዚህ ያለ አስቀያሚ እና አቅምን የሚፈታተን ድርጊት እየተፈጸመ እያየ ገዥው አካል ምንም ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ የማይፈልገው የህበረተሰቡን አቅም በማዳሸቅ በረዥም ጊዜ ዕቅዱ ህዝቡን በቁጥጥሩ ስር አድርጎ እንደፈለገው ለመግዛት እንዲመቸው በማሰብ ነውን? ወይስ ደግሞ የፖለቲካ ቁርጠኝት ከማጣት የመነጨ ነው? ነው ወይስ እርምጃ ለመውሰድ የማይፈለገው እንደዚህ ያለ ድርጊት የሚፈጸምባቸውን አካባቢዎች የአካባቢ አመራሮች ላለማስቀየም ቸልተኝነት ማሳየቱ መልካም ነው ከሚል እሳቤ? ነው ወይስ ደግሞ ገዥው አካል እንደዚህ ዓይነቱ ህገወጥ ድርጊት በአቅመ አዳም ባልደረሱ ልጃገረዶች ላይ ሲፈጸም የሚመለከተውን ጭካኔ እና አረመኒያዊ ድርጊት ዝም ብሎ የሚያየው ከዚህ ቀደምም የነበረ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የተጠናከረ ባህል እና ተቋማዊ ስርዓት ስለሆነ ቀጣይነት ቢኖረው ችግር የለውም ከሚል የየዋህነት አስተሳሰብ ነው? ወይስ ደግሞ በሴቶች ላይ የሚደረግ ንቀት ነው? ለሴቶች ዋጋ አልተሰጣቸውም ማለት ነው? ወይም ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ልጃገረዶች እንደ ሶስተኛ ዜጋ ይቆጠራሉ? ወይም ደግሞ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ልጃገረዶች ለምርጫ ማደናገሪያ ጉዳይ ድምጽ ለመስጠት አይችሉም በሚል ምክንት? ነው ወይስ ደግሞ የግብዓት እጥረት ችግር ስላለ? ነው ወይስ የአካባቢውን ተቃውሞ በመፍራት? እነዚህ ከዚህ በላይ በቀረቡት ጥያቄዎች ምክንያት ነው ወይስ ደግሞ በሌላ ከእነዚህ ውጭ በሆኑ ምክንያቶች? ምንድን ነው ያለው ችግር?
የመለስ ዜናዊ ሚስት የነበረችው አዜብ መስፍን እ.ኤ.አ ፌብሯሪ 2010 በዩኤስ የመንግስት መምሪያ ውስጥ ለሚሰሩት ለማሪያ ኦቴሮ በዊኪሊክስ አማካይነት የቀረበው ዘገባ እንዲህ ይል ነበር፣ “በአፋር ክልል ከማህበረሰብ እና ከኃይማኖት መሪዎች ጋር በመሆን ለአራት ተከታታይ ዓመታት በወይዘሮዋ በኢትዮጵያ መንግስት ስም በተደረገ ጥረት የሴቶች ግርዛት አመርቂ በሆነ መልኩ ሊቀንስ ችሏል…አዜብ እንደገለጸችው ባለፉት አራት ዓመታት የአካባቢውን ማህበረሰብ ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ ጥረት ሲደረግ የቆየ መሆኑን ተናግራለች፡፡ በእርሷ ያላሰለሰ ጥረት፣ በማህበረሰቡ ውይይቶች፣ ክርክሮች እና የስብከት ስራዎች ምክንያት የአፋር ክልል አመራሮች በአሁኑ ጊዜ የሴት ልጅ ግርዛት “ሀራም/የተወገዘ” ወይም ደግሞ የተከለከለ ተግባር ነው ብለው ነበር በማለት ዘገባ አቅርባ ነበር፡፡“ “ለጠለፋ ጋብቻም” እንደዚህ አድርጋ ብትሰራ ጥሩ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡
በኢኪኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊ እና በዲፕሎማሲው መስክ አቅም ፈጥሪያሁ የሚል ገዥ አካል የእራሱን ህገ መንግስት እና አዋጅ መሰረት በማድረግ ይህን ኋላ ቀር እና አስነዋሪ የሆነ የማህበራዊ ጠንቅ ልምድ ለምን ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ሽባ እንደሚሆን ለመገንዘብ አስቸጋሪ ሆኖብኛል፡፡ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ታላቅ ግድብ በጥቁር አባይ ወንዝ ዳርቻ ላይ የሚገነባ ገዥ አካል እንዴት ከጠለፋ ጋብቻ የማህበራዊ ተቋማዊ ቀውስ ላይ ሊከላከል የሚችል መከላከያ ግድብ መስራት ይሳነዋል?
በአንዳንድ ውሱን አጋጣሚዎች ገዥው አካል በጎጅ የጋብቻ ልምዶች ላይ እርምጃ የመውሰድ ሙከራዎች ቢታዩም ቅሉ እነዚህ እርምጃዎች ከልብ ታምኖባቸው በሙሉ ልብ እና ቅንነትን በተላበሰ መልኩ ችግሩን ከመሰረቱ ጠራርጎ ለማጥፋት ሳይሆን ለይስሙላ እና በማስመሰል ከለጋሽ እና አበዳሪ ድርጅቶች ድጋፍ ለማግኘት የሚደረግ የሸፍጥ ስራ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለእድሜ ጋብቻን እና ተዛማጅ ተግባራትን ማስወገድ/Combate Early Marriages and Related Practices in Ethiopia በሚል ርዕስ መኮንን እና ሀራልድ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፋቸው እንዲህ የሚል የመከራከሪያ ጭብጥ አስፍረዋል፣ “ህዝቡ አዳዲስ ህጎች ከወጡ በኋላ ለተግባራዊነታቸው አሉታዊ የሆነ ምላሽ ከሚሰጥባቸው ምክንያቶች አንዱ በመንግስት እየተወሰዱ ያሉት አስትራቴጅዎች እና እርምጃዎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡“ በመጀመሪያ ደረጃ ያለእድሜ ጋብቻን ለማስቀረት የሚደረገው የቅስቀሳ ዘመቻ ግልጽነት ያንሰዋል… ትክክለኛ የሆነ የእቅድ አነዳደፍ እና የማስፈጸሚያ እስትራቴጅ ይጎድለዋል፡፡ ከተለያዩ የፖለቲካ እና የሲቪክ ቡድኖች ከሚደረግ ግፊት የተነሳ መንግስት አንድ ጊዜ ያለእድሜ ጋብቻን ጉዳይ በቤተሰብ ህጉ ውስጥ እንዲካተት ማድረጉን ማስተዋል ይቻላል…”
ጠላፊዎችን እና አስገድዶ ደፋሪዎችን የመቅጣት አስፈላጊነት፣
የኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ 35 የሚከተሉትን መብቶች ያጎናጽፋል፣ “በዚህ ህገመንግስት ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ሴቶች ከወንዶች እኩል የጋብቻ መብት አላቸው፡፡“ አንቀጽ 34 የሚከተለውን መብት ይሰጣል…”ጋብቻ በሁለቱ ተጋቢዎች ሙሉ ስምምነት ብቻ ነጻ በሆነ መልክ ይፈጸማል፡፡“ እ.ኤ.አ በ2000 ተሻሽሎ የወጣው የቤተሰብ ህግ አንቀጽ 6 እንዲህ በማለት ያውጃል፣ “ህጋዊ ጋብቻ ሁለቱ ተጋቢዎች ነጻ በሆነ መልኩ ስምምነት ሲያደርጉ ብቻ ይፈጸማል፡፡“ እንደዚሁም አንቀጽ 7 እንዲህ ይላል፣ “ማንኛውም ወንድም ሆነ ሴት እድሚያቸው 18 እና ከዚያ በላይ ካልሆነ ጋብቻ መፈጸም አይችሉም፡፡“በኢትዮጵያ ህጻናትን አስገድዶ ለመድፈር የሚፈቅድ ህገመንግስታዊም ሆነ ህጋዊ መሰረት የለውም፡፡ ሆኖም ግን የገዥው አካል አመራሮች ጆሮ ዳባ ልበስ ሲሉት የጠለፋ ጋብቻ እና የህጻናት ሙሽራነት (የቀድሞ የህጻናት መደፈር ትክክለኛ ገጽታ) እየተጠናከረ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡.
ጠላፊዎችን እና አስገድዶ ደፋሪዎችን ለመቅጣት የወጡት ህጎች ግልጽ እና ቀጥተኛ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ (አዋጅ ቁጥር 414/2004) አስገድዶ መድፈር የሚለው ቃል ከ19 ጊዜ እና ጠለፋ ከ15 ጊዜ ባላነሰ መልኩ በተናጠል መጠቀስ ብቻ ሳይሆን እንደ የወንጀል ድርጊት አባባሽ ጭምር ሆነው ቀርበዋል፡፡ አንቀጽ 587 (የሴት ጠለፋ) የሚለው የሚከተለውን ይላል፣ “(1) አንዲትን ሴት በጠለፋ በኃይል በማስገደድ ለማግባት ዓላማ አድርጎ የተንቀሳቀሰ ሰው ወይም ደግሞ ቀደም ሲል በማስፈራራት፣ በመዛት፣ በማታለል ወይም በማሳሳት እንደዚህ ያለ ወንጀል የፈጸመ ሰው ከ3 እስከ 10 ዓመታት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ (2) የጠለፋ ድርጊት ወንጀሉ የተፈጸመው በአስገድዶ መድፈር ከሆነ ወንጀል ፈጻሚው በዚህ ህግ አስገድዶ መድፈር የሚለው የህግ ቅጣት ተፈጻሚ ይሆናል፡፡ (3) የጠለፋ ድርጊት ወንጀል ከተፈጸመ በኋላ በጠላፊው እና በተጠላፊዋ መካከል በተደረገ ስምምነት ጋብቻ ተፈጽሟል የሚል ስምምነት ቢፈጽሙም በወንጀል ህጉ ከመጠየቅ አይድንም…
አንቀጽ 620 (አስገድዶ መድፈር) የሚከተለውን መብት ያጎናጽፋል፣ ”(1)ማንም ቢሆን አንዲትን ሴት ከጋብቻ ውጭ በማስገደድ ወይም በግድያ በማስፈራራት የግብረ ስጋ ግንኙነት የፈጸመ ከሆን ከ5 እስከ 15 ዓመታት በሚሆን ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ (2) እድሜዋ ከ13 እስከ 18 ዓመት በሆነች ወጣት ልጃገረድ ላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የተፈጸመ ከሆነ፣ … ወይም ደግሞ… d) በብዙ ወንዶች በህብረት ወይም ደግሞ በጥቃት ሰለባዋ ላይ ጭካኔ ወይም የእራስን ስግብግብ ፍላጎት ለማሟላት ሲባል የሚደረግ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ከ5 እስከ 20 ዓመታት በሚሆን ጽኑ እስራት ያስቀጣል፡፡ (3) አስገድዶ መድፈሩ በጥቃት ሰለባዋ ላይ አስከፊ የሆነ የአካል ወይም መንፈሳዊ ጉዳት ያደረሰ ወይም ሞትን ያስከተለ ከሆነ በእድሜ ልክ እስራት የሚያስቀጣ ይሆናል፡፡ (4) አስገድዶ መድፈሩ በጥቃት ሰለባዋ ላይ ህገወጥ ድርጊትን ወይም ደግሞ ጠለፋን በማካሄድ ለተላላፊ በሽታ አጋልጧት ከሆነ በዚህ ህግ በአስፈላጊው ቦታ የተጠቀሰው አንቀጽ ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡“
ገዥው አካል ለሚያወጣቸው ህጎቹ ህገመንግስታዊ ተጠያቂነት የማይኖረው ለምንድን ነው? ገዥው አካል የእራሱን ዜጎች ሰብአዊ መብት የማስጠበቅ አስገዳጅ የሆነ ዓለም አቀፋዊ የህግ ግዴታ እንዳለበት ያውቃልን? ወይም ደግሞ እስከ አሁንም ድረስ የዋሻውን ሰው ዓይነት ኑሮ ለመኖር የጫካውን ህግ ይተገብራሉ? ላለፉት ስምንት ዓመታት ስለ የህግ የበላይነት ጠንካራ ትችቶችን እያነሳሁ ስናገር እንደቆየሁ እገነዘባለሁ፡፡ ምናልባትም እኔ የማቀርባቸው ውይይቶች እና ትችቶች ስለአስገድዶ መድፈር እና ጠለፋ የሚያትቱትን እና የሚደነግጉትን ህጎች ለማስፈጸም ኃላፊነቱ ካላቸው ሰዎች የግንዛቤ አቅም በላይ ሆነው ሊሆን ይችላል፡፡ መገንዘብ ያለባቸው ቀላሉ እውነታ ግን የእራሱን ህጎች ለማስፈጸም ቸል የሚል፣ የሚጥስ እና ንቀትን የሚያሳይ መንግስት በህዝቡ ላይ ስሜታዊ የሆኑ ንቀቶች እንዲፈለፈሉ በማድረግ የህግ አልባነት ስርዓት አንዲንሰራፋ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ መንግስት እራሱ ምሳሌ በመሆን ለህጎቹ ተግባራዊነት በተግባር ማሳየት አለበት፡፡ በእርግጥ ሁሉም ከዚህ በላይ የተባሉት ነገሮች ሁሉ የመንግስትን መኖር ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡ ታማዕኒነትን እና ቅቡልነትን ማግኘት!?
ጀግንነት፣ ጭራቅነት እና ፍትህ፣
አበራሽ የእርሷን ጠላፊ ለመከላከል ባደረገችው ተጋድሎ እራሷን “ጀግና” አድርጋ አላቀረበችም፡፡ ጠላቷን የገደለች ዓይነት ስሜት ይሰማታል፡፡ ሌሎች ሰዎች የእርሷ ዓይነት አደጋ ሲወድቅባቸው እራሳቸውን ከአደጋ ለመከላከል ሲሉ እንደሚያደርጉት ዓይነት የሞት ሽረት ትግል አድርጋለች፡፡ ገመቹ ግን “ጠላት” አልነበረም፡፡ ይልቁንም እጅግ በጣም ኋላቀር እና እንስሳዊ የሆነ የባህላዊ ስርዓት ተቋም አሰቃቂ ሰለባ የነበረ ምስኪን እንጅ፡፡ ምንም ዓይነት የተሻለ ነገር አያውቅም ነበር፡፡ ይልቁንም በእርሱ የእድሜ እኩያ የሆኑት በየጊዜው የሚያደርጉትን ነገር ነው የፈጸመው፡፡ ሆኖም ግን አበራሽ የእርሷን መብት በመጣስ በህይወቷ ላይ አደጋን ደቅኖባት በነበረው ሰው ላይ ጠብመንጃ በማንሳቷ ወይም ደግሞ ተኩሳ በመግደሏ አይደለም ጀግና መባሏ ሆኖም ግን የሰብአዊ መብት እንዳይገሰስ እና ይልቁንም በትክክለኛው መንገድ እንዲከበር ቋሚ የሆነ ትምህርት ለሰው ልጆች ሁሉ በመስጠቷ እንጅ፡፡ እርሷ የእኔ ጀግናዬ ነች ምክንያቱም አበራሽ ለእራሷ ጥቅም እና ክብር ብቻ አልነበረም የቆመችው፣ ሆኖም ግን እርሷ በጽናት የቆመችው ለሁሉም ኢትዮጵያውያት ልጃገረዶች እና ሴቶች ሁሉ ስለነበረ ነው፡፡ በጣም ጥቂቶች እጅግም በጣም ጥቂቶች የሚያደርጉትን አድርጋለች፡፡ በአንዲት ሀገር የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በሙሉ ለሰብአዊ መብቶቻቸው እና ክብሮቻቸው ምንም ነገር ባለማድረግ ሁልጊዜ ከዳር ቆመው የሚመለከቱ ከሆነ እነዚህ ዜጎች የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ሰለባ ሆነዋል ማለት እውነትነት የለውምን?
አበራሽ የተሟላ ፍትህ ተገኝቷል የሚል እምነት አልነበራትም፡፡ በእርግጥ በእርሷ ታናሽ እህት በሙላቷ እና በጠቅላላው በሀገሪቱ ውስጥ በሚገኙ በሌሎች ልጃገረዶች ዘንድ እንደዚህ ያለ ተመሳሳይ ስቃይ እና ኢፍትሀዊነት በቀላሉ ሊደርስ ይችላል በማለት ተናግራለች፡፡ የእርሷ ታላቅ እህት መስታወት የዚህ አስቀያሚ ድርጊት የጥቃት ሰለባ ነበረች፡፡ አበራሽ እንዲህ በማለት አስጠንቅቃለች፣ “በወንጀለኞች ላይ ምንም ዓይነት እርምጃ አልተወሰደም፡፡ ስለሆነም አሁንም ቢሆን ተመሳሳይ የሆነ ወንጀል በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡ በእኔ ላይ እንደደረሰው ሁሉ ልጃገረዶች ወደ ትምህርት ቤት ወይም ወደ ገበያ በሚሄዱበት ጊዜ ሊጠለፉ ይችላሉ፡፡ እነርሱን ሊያቆም የሚያስችል ተጨባጫነት ያለው ስራ እስከ አሁን ድረስ አልተሰራም፡፡ ስለሆነም አሁንም ቢሆን በጠለፋ የዕኩይ ምግባራቸው ለመቀጠል ድፍረቱን አግኝተዋል፡፡“ የአበራሽ የመጨረሻው ፍትህ ማለት በእድሜዋ እና በቤተሰቧ ታስራ ከኖረችበት ከዚያ ውጉዝ ከማሪዮ ከሆነ ቀያጅ እና አሰቀያሚ ባህል እራሷን መንጫቃ በማውጣት ለእራሷ እና ለሌላውም የማህበረሰብ አባላት አዲስ ህይወትን ማስተማር መቻሏ ነው፡፡ ህጉ እና አስፈጻሚዎቹ ከዳር ቆመው ምንም ባለማድረግ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ሲመለከቱ ስታይ አሁንም እንደገና የጥቃቱ ሰለባ የመሆን ያህል ይሰማታል፡፡ የፍትህ ዓይን በየትኛውም ቦታ እንዳታይ ሆና በጨርቅ ተሸፍናለች፣ ሆኖም ግን በኢትዮጵያ ዓይኖቿ ተደንቁለው እና ተመንግለው እንዲወጡ ተደርጎ ሙሉ በሙሉ ዓይነ ስውር ሆናለች፡፡
የህግ ባሙያ ጓደኞቼ መዓዛ አሸናፊ እና ዳንኤል በቀለ ጀግኖች ናቸው፡፡ እኔ መዓዛን እና የእርሷን ማህበር አውቃለሁ፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 ገዥው አካል “የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር” እና የቀድሞ “የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ” በአሁኑ በወያኔ የግዳጅ ስያሜ ኢትዮጵያ የምትለዋን የምንነት መገለጫው የሆነችውን ቃል በማውጣት “ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ” ተብሎ እንዲጠራ የወሰነበትን ሁለቱን በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ ጠንካራ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት ድርጅቶች 90 በመቶ የሚሆነውን የማስፈጸሚያ በጀታቸውን ከውጭ ያመጣሉ በማለት ፈቃዶቻቸውን አላድስም በሚል ችግር ፈጥሮ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ለበርካታ ዓመታት ማስፈራሪያ ሲደርሰው ቆይቷል፡፡ መዓዛ እና የእርሷ የህግ ባሉሙያ የስራ ባልደረቦቿ በኢትዮጵያ የሴቶች መብቶች እንዲከበሩ በጽናት በመቆም ሲታገሉ ቆይተዋል፡፡ ስለሆነም አሁንም ቢሆን አዲሱ የወጣት ሴቶች እና ወንዶች ትውልድ የእርሷን ዱካ በመከተል ከግብ ያደርሰዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ስለዳንኤል የምለው ነገር ቢኖር “የኢትዮጵያ ማጣት ለአፍሪካ ማግኘት ነው፡፡”
የአበራሽ ጠላፊ እና አስገድዶ ደፋሪ የነበረው ገመቹ በእርግጠኝነት ጭራቅ አይደለም፡፡ የእርሱ ወላጆች እና እርሱ የጠለፋ ተግባሩን እንዲሳካ ሲያግዙት የነበሩት ጓደኞቹም እንደዚሁ ጭራቆች አይደሉም፡፡ ሁሉም ቢሆኑ የድንቁርና እና የኋላቀርነት ልምዶች ሰለባዎች ናቸው፡፡ የእነርሱ ልምዶች ጎጅ ለመሆናቸው ትምህርት እና የግንዛቤ ማበልጸጊያ ስልጠና ድጋፍ ቢደረግላቸው ኖሮ እራሳቸውን በመለወጥ አካሄዳቸውንም በማሳመር ከእንዲህ ዓይነት ተግባር ይቆጠቡ ነበር፡፡ በእኔ አመለካከት በጠለፋው ምክንያት ወደ ጉዳዩ በአስታራቂነት የተቀላቀሉት ሽማግሌዎች የጋብቻ ጠለፋን በሁለቱ ተፋላሚ ቡድኖች መካከል በመገኘት አንዴ የሆነውን ነገር መመለስ ስለማይቻል በሚል እምነት በመካከላቸው ዕርቀሰላም በማውረድ ማህበራዊ ቅቡልነት እንዲኖር እና እንደገና መግባባት እንዲፈጠር የሚያደርጉት ጥረት እንጅ በእውነቱ ሆን ብለው ሰዎችን ለመጉዳት አምነውበት የሚያደርጉት ድርጊት ነው ብዬ ለመቀበል ያጠራጥረኛል፡፡
ሜትካፍ ይህንን ዘጋቢ ፊልም አውጥታ ለዕይታ ባበቃችበት ጊዜ አንዳንዶች ምዕራባዊ ስለሆነች (“ነጭ” ብላችሁ አንብቡት) አፍሪካዉያን/ት እንዴት እንደሚኖሩ ለማሳየት ነው የሚል ትችት ሰንዝረው ነበር፡፡ የመልዕክት አስተላላፊዎች ስትራቴጅ የተለመደው የሁልጊዜው ቅጥፈት ነው፡፡ ደግሞስ የአፍሪካውያንን አኗኗር ማሳየቷ በምን መስፈርት ነው ስህተት የሚሆነው? ተራ የበታችነት ስሜትን ለመግለጽ ካልሆነ በስተቀር እርባና የለውም ወገኖቼ! ሜትካፍ በአበራሽ ታሪክ ላይ ጸጥተኛ ጀግና ሆናለች የሚል እምነት አለኝ፡፡ ተጨባጭ ታሪኩን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለህሊና ፍርድ ካደረሰች በኋላ ሜትካፍ ከአንድ ምዕተ ዓመት በፊት ከምድረገ ገጽ መጥፋት የነበረባቸው ለምሳሌም ያህል ህይወትን መገበር እና ባላቸው የሞቱባቸውን ጋለሞታ ሴቶች የባላቸው እሬሳ ወደ አመድነት እስኪቀየር ድረስ በሚቃጠልበት ነበልባል እሳት ውስጥ ጋለሞታዎችንም አስገብቶ በማንደድ (በህንድ አገር ሱቲ ተብሎ ይጠራል) የሚደረገውን ከንቱ የሆነ ክብረ በዓል ፍጹም በሆነ መልኩ እንዲወገድ መልዕክት ለማስተላለፍ ነው፡፡
በዚህ እጅግ አስደንጋጭ በሆነው ባህላዊ ልምዳችን ላይ የተለየ ትኩረት እንዲያገኝ የሚያደርገውን ፊልም በመስራት ዓለም አቀፋዊ አሸናፊ በመሆን ሽልማት ያስገኘውን ፊልም በሰራው በኢትዮጵያዊው ፊልም ሰሪ በዘረሰናይ ብርኃኔ መሀሪ በጣም ኩራት ይሰማኛል፡፡ የእራሱን ሙያዊ ችሎታ ተጠቅሞ ለአዲሱ የኢትዮጵያ ትውልድ እንደዚህ ያለ በጣም ኋላቀር የሆነ ባህላዊ ልምድን ማካፈል በመቻሉ ጀግና ነው፡፡ ይኸ ፊልም የሚመለከታቸው የገዥው አካል ክፍሎች ወደዚህ ችግር ፊታቸውን መለስ በማድረግ የሴቶችን ሰብአዊ መብት በማስከበር በኩል እና የምስኪን እህቶቻችንን ዕድል የተሻለ ለማድረግ የእራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
“የጠለፋ ጋብቻን” ተቋማዊ የሚያደርጉ የአስታራቂ ሽማግሌዎች ተቋማትን ኢተቋማዊ ለማድረግየቀረበ ጥሪ፣
በኢትዮጵያ የጠለፋ ጋብቻ ታሪክ ውስጥ ሶስት ዓይነት ጭራቆች አሉ፡ ተቋሙ እራሱ፣ ጭራቃዊውን ተቋም ኢተቋማዊ ለማድረግ ስልጣኑ ያላቸው ሆኖም ግን በማይታወቅ ምክንያት ኢተቋማዊ ለማድረግ ሙሉ ተነሳሽነት የሌላቸው እና የእውነተኛ ተግባር አልባዎች፣ በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ ለእንደዚህ ያለው አሰቃቂ ወንጀል በአስታራቂነት የሚቀርቡት ሽማግሌዎች እየተባሉ የሚጠሩት ናቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ሆን ብሎ የስራ ኃላፊነቱን የዘነጋውን እና እጅግ በጣም ኋላቀር እና ጭካኔ የተሞላባቸው ባህላዊ ልምዶችን በመተግበር ሕገመንግስቱ እና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ህጋዊ መብቶቻቸው በሰፊው ሲጣሱ ዝም ብሎ የሚመለከትን ጭራቃዊ ገዥ አካል ለምን ኃካፊነቱን አልተወጣም በሚል የምጨምረው ነገር የለኝም፡፡
በጠለፋ ጋብቻ ላይ ጸጥ በማለት እና ድብቅ የሆነ ጭራቃዊ ወንጀልን እያስፈጸመ ያለው እራሱ የአስታራቂ ሽማግሌዎች ተቋም እንደሆነ አምናለሁ፡፡ አስታራቂ ሽማግሌዎች በጠለፋ ጋብቻ ጊዜ በአካባቢው ማህበረሰብ ውስጥ ስምምነትን እና እርቅን በማስፈን እንዲሁም ሚዛንን በማስጠበቅ በኩል የአድራጊ ፈጣሪነት ተግባራትን በመስራት ታላቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ምንም ነገር ከእውነታው ውጭ ጋት ያህል ፈቀቅ ሊል አይችልም፡፡ በእኔ አስተያየት እነዚህ አስታራቂ ሽማግሌዎች ጋብቻ በጠለፋ የሚፈጽሙ ወንጀለኞች በጥፋት ተጠያቂ እንዳይሆኑ ተባባሪ በመሆን በድብቅ ሆነው ደባ የሚሸርቡ፣ ለጠላፊዎች የሚከላከሉ እና በጸጥታ ሳይታወቅባቸው ለወንጀለኞች ግበረ አበር ናቸው የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ የአስታርቂ ሽማግሌዎች አስቀድሞ የታወጀው ዓላማቸው የጠላፊውን እና ያለእድሜ ጋብቻ የሚፈጸምባትን ልጃገረድ ወላጆች በማስታረቅ ነገሮች ሁሉ ከቁጥጥር ውጭ በመሆን ከእጅ እንዳይወጡ ያደርጋሉ፡፡ በእርግጥ አስታራቂ ሽማግሌዎች የጠለፋ ጋብቻን ህጋዊ እና ተቋማዊ መልክ እንዲኖረው በማድረግ ጠላፊው ወንጀለኛ ለህግ እንዳይቀርብ ጥፋቱ ተሸፋፍኖ እንዲቀር ከለላ በመሆን ጉዳዩ በእነርሱው እንዲያልቅ ያደርጋሉ፡፡ በጠለፋ ጋብቻ ጊዜ አስታራቂ ሽማግሌዎች ስለሚያደርጓቸው ነገሮች ሊሰመሩባቸው የሚገቡ ጥቂት ነገሮች አሉ፡ በመጀመሪያ ደረጃ ገና ከወጣትነታቸው ጀምረው ሲለማመዱ የቆዩ እና አሁን በእድሜ ሽማግሌ የሆኑ ሁሉም ወንዶች ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የጠለፋ ጋብቻ ወንጀሎች ሁልጊዜ እና ቀን በቀን የሚፈጸሙ ስለሆነ እነዚህ ሽማግሌዎች ለእንደዚህ ያሉ ልምዶች እና ጉዳዮች ደንታ የሌላቸው እና በአዕምሯቸው ውስጥ ምንም የሚኮሰኩስ ነገር ሊፈጠሩባቸው የማይችሉ ፍጹም ጸረ ለውጥ ፍጡሮች ናቸው፡፡ በሶስተኛ ደረጃ እንደ ባህሉ እምነት እና እንደ ግል እምነታቸው አስታራቂ ሽማግሌዎች የጠለፋ ጋብቻን ምንም ዓይነት ስህተት የሌለበት እንደሆነ አድርገው ነው የሚመለከቱት፡፡
ከዚህም በተጨማሪ አስታራቂ ሽማግሌዎች ስለምቾት፣ ደህና መሆን ወይም ደግሞ የጥቃት ሰለባ ስለሆነቸው ልጃገረድ የሰብአዊ መብት ጥሰት የተለዬ ትኩረት የሌላቸው መሆናቸውን መገንዘብ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ ወንጀል ለተፈጸመባት ልጃገረድ የቁሳቁስ እርዳታ ወይም ደግሞ ፍትህን በማስገኘት እረገድ ጣልቃ አይገቡም፣ ሆኖም ግን የጥቃት ሰለባዋን ወላጆች አፍ አስይዘው ጸጥ በማድረግ የልጅቷን ልሳን እንዲሸበብ ያደርጋሉ፡፡ ጥቃት የደረሰባትን ልጃገረድ በመቅረብ ምን ዓይነት ካሳ (ቁሳቁስ፣ ገንዘብ፣ እንስሳት፣ ወዘተ) ወይም ደግሞ ጥቃት ያደረሰባት ጠላፊ በህግ ፊት ቀርቦ አስፈላጊውን ፍትህ ማግኘት ያለበት መሆን አለመሆኑን እንደምትፈልግ አይጠይቋትም፡፡ አስታራቂ ሽማግሌዎች ለልጃገረዷ አንዳች ነገር አይሰጧትም፣ ተስፋም ቢሆን፡፡ ይልቁንም የጥቃት ሰለባዋ ልጃገረድ ለወንጀለኛ ጠላፊው የግብረ ስጋ መፈጸሚያ ባሪያ፣ ቤት ጠባቂ እና ህጻን ቀፍቃፊ በመሆን የተፈጠረ ዕድል አድርገው ይቆጥሯታል፡፡ በአስታራቂ ሽማግሌዎች ሊሰጥ የታሰበው ካሳ ለጥቃት ሰለባዋ ልጃገረድ ቤተሰቦች እንጅ ለእርሷ አይደለም፡፡ ምን ያህል ዋጋ እንደምታወጣ እንኳ ያላትን ስሜት እንድትገልጽ ዕድል አይሰጣትም፡፡ የእርሷን ህይወት ሰብአዊ መብት በሁለት በሬዎች ወይም በአምስት በጎች እና ሁለት ፍየሎች ልትሸጥ ትችላለችን? ለመሆኑ ከዚህ ስምምነት እርሷ የምታገኘው ደስታ ምንድን ነው? ያም ሆነ ይህ በመጨረሻ የወላጆቿ ንበረት ናት፡፡
አስታራቂ ሽማግዎች የጥቃት ሰለባ የሆነችውን ልጃገረድ ሰብአዊ መብት እንዳላት ፍጡር አድርገው አይቆጥሯትም፣ ለእነርሱ እርሷ በዋናነት ወላጆቿ ከሌላ አካል ጋር ለሚያደርጉት ስምምነት በንብረትነት መተላለፍ የምትችል ዕቃ አድርገው ይቆጥሯታል፡፡ አስታራቂ ሽማግሌዎቹ በማስታርቅ የጊዜ ሂደታቸው በእርግጠኝነት የጥቃት ሰለባ የሆነችውን ልጃገረድ እንደ ዕቃ መለወጫ ሸቀጥ አድርገው ይቆጥሯታል፡፡ የእነርሱ እውነተኛ ስራቸው ማስታረቅ አይደለም፣ ሆኖም የእነርሱ ዋነኛ ተግባር በልጃገረዷ ላይ ዋጋ መጣል እና ትክክለኛ የጊዜው የገበያ ዋጋን እንድታወጣ መወሰን ነው፡፡ ለአስታራቂ ሽማግሌዎች የልጃገረዷ ዋጋ ሁልጊዜ የተወሰነ ቁጥር ካላቸው ከብቶች ወይም ገንዘብ ጋር እኩል የመሆን ጉዳይ ነው፡፡ በጠለፋ ጋብቻ የሚፈጸምባት ልጃገረድ እንግዲህ ዋጋዋ ይህንን ያህል ነው፡፡ የአካባቢው ማህበረሰብ ልጃገረዷን እንደ ሰብአዊ ፍጡር ሳይሆን የሚመለከቷት እንደአልወለደች ጥጃ ነው፡፡
በእኔ አስተያየት በአጠቃላይ የአስታራቂ ሽማግሌዎች ተቋም የማያቋርጠውን የጠለፋ ጋብቻ አዙሪት በአለበት እንዲቀጥል ማመቻቸት እና ህጋዊ ሽፋን በመስጠት የጥቃቱ ሰለባ የሆነችው ልጃገረድ ወደ ፍትህ አደባባይ ለመድረስ ምንም ዓይነት ምርጫ እንዳይኖራት እና ከህግ ከለላ ውጭ ሆና ምርጫየለሽ በመሆን የኢፍትሀዊነት መናሀሪያ ሆና እንድትቀር ማድረግ ነው፡፡ የአስታራቂ ሽማግሌዎች ተቋም የጠለፋ ወይም ደግሞ የአስገድዶ መደፈር ጥቃት የደረሰባትን ልጃገረድ ህጋዊ ሽፋን በማስያዝ ጉዳዩ ለፍትህ አካላት እንዳይደርስ ለማድረግ ብቻ አይደለም ዋናው ተግባሩ፣ ሆኖም ግን በእርሷ ላይ የተፈጸመውን ወንጀል ያለምንም ቅሬታ እና በሙሉ የጨዋነት መንፈስ እንድትቀበል ማስገደድ ነው፡፡ የተቋሙ አስታራቂ ሽማግሌዎች እራሱን ህጉን እና ፍትህን የጥቃት ሰለባ አድርገዋል፡፡ ፖሊሶች በጠለፋ የተደረገ ጋብቻ ላይ አስታራቂ ሽማግሌዎችም የተሳተፉ መሆናቸውን ከተገነዘቡ ከዚያ በኋላ ጉዳዩን ቸል በማለት ጆሮ ዳባ ልበስ ይላሉ፡፡ (አንዳንድ ጊዜ ፖሊሶቹ እራሳቸውም በጠለፋ ጋብቻ ላይ የሚሳተፉባቸው አጋጣሚዎችም አሉ)፡፡ የጠላፊው ወላጆች ወይም ደግሞ አስታራቂ ሽማግሌዎች ጉዳዩ እነርሱ በሚፈልጉት መልክ እንዲሆንላቸው የጠለፋ ወንጀሉን ለሚያጣሩት ፖሊሶች ጉቦ የሚሰጡበት ሁኔታም የተለመደ ነው፡፡ የጠለፋ ጋብቻ በሚፈጸምበት አጋጣሚ የአስታራቂ ሽማግሌዎች ተቋማትም ህገወጥ መሆን አለባቸው፡፡
የአስታራቂ ሽማግሌዎች ጣልቃገብነት በማይኖርበት ጊዜ ምን ሊሆን ይችላል? የአስታራቂ ሽማግሌዎች ተቋማት ባይኖሩ ኖሮ የጠለፋ ጋብቻ ምን ሊሆን ይችላል? የአለእድሜ ጋብቻ ተጠላፊዋ ወላጆች ምንም ዓይነት ምርጫ አይኖራቸውም ነበር፣ ሆኖም ግን የወንጀሉን ጉዳይ ወደ ፖሊስ በመውሰድ ወንጀሉ እንዲጣራ እና ፍትህ እንዲያገኝ ያደርጉ ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ ልጃቸውን ሳይሆን አንድ ዘራፊ ንብረታቸውን ቢዘርፍባቸው ኖሮ እንደሚያደርጉት ነገር ማለት ነው ፡፡ በህጉ መሰረት የወንጀል ክሱ እንዲያምን የማድረግ እና ረዥም የሆነ የእስራት ቅጣትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮችን በማስረጃ ማረጋገጥ ከባድ አይደለም፡፡ የጥቃት ሰለባዋ እራሷ ጠላፊዋ እና አሰገድዶ የደፈራት ማን እንደሆነ መመስከር ትችላለች፡፡ የወንጀል ድርጊቱ ለፍትህ አካል ከደረሰም በኋላ አስታራቂ ሽማግሌዎቹ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ በመግባት መሰናክል በመፍጠር የፍርድ ሂደቱን ሊያጨናግፉ ይችላሉ፡፡
ባጭሩ የአስታራቂ ሽማግሌዎች ተቋማት ለግዳጅ ጋብቻ ችግር ዋናዎቹ ሲሆኑ እነርሱም እንደሚታሰበው መፍትሄ ሰጭ አይደሉም፡፡ የአበራሽ ታላቅ እህት የሆነችው መስታወት ካለችው እውነታ ጎን እስማማለሁ፡፡ ይኸውም “በጠለፋ ጋብቻ ላይ የወጣው ህግ ተፈጻሚነት የሚኖረው ከሆነ ወንዶች ይለወጣሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ህጉ የላላ ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ ወንዶች ለዘላለሙ ከቁጥጥር ውጭ ይሆናሉ፡፡“ አስታራቂ ሽማግሌዎቹ ምንም ይስሩ ምን የጠለፋ ጋብቻ የፈጸሙ ወንጀለኞች ያለምንም ምህረት ጉዳያቸው በፍትህ አካላት ታይቶ በአንቀጽ 587 (3) በተደነገገው መሰረት የሚከተለው የጥፋተኝነት ቅጣት ሊጣልባቸው ይገባል፣ “የጠለፋ ጋብቻ መፈጸሙን ተከትሎ በጠላፊው እና የጠለፋ ጥቃቱ ሰለባ በሆነችው መካከል የጋብቻ ስምምነት የፈጸሙ ቢሆንም ጠለፋው በወንጀል ከመጠየቅ ነጻ ሊሆን አይችልም…“
የጠለፋ ጋብቻ ለኢትዮጵያ ብቻ የተተወ ልዩ ችግር አይደለም፡፡ በሌሎች በርካታ የሰብ ሰሀራ አገሮች እና በደቡብ ኢስያ አገሮችም የሚካሄድ ተግባር ነው፡፡ የእርሱን መጥፎ ገጽታዎች ባሳየባቸው አገሮች እና ቦታዎች ሁሉ ሙልጭ ብሎ እስከሚጠፋ ድረስ መወጋት አለበት፡፡ በሴቶች ሰብአዊነት ላይ ያነጣጠረ አሳፋሪ ወንጀል ስለሆነ ሁሉም የሰው ዘሮች ሁሉ በአንድነት ቆመን በጋራ ልናወግዘው ይገባል፡፡ ዓለም በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሰው ግብርን በኃይማኖታዊ በዓል ስምም ሆነ ባሏ የሞተባትን ምስኪን ሴት በሞተው ባሏ የአጽም ማቃጠያ ምድጃ ውሰጥ ገብታ በምንም ዓይነት መልኩ አትቃጠልም፡፡ ከደኃ የገጠር ቤተሰቦች የሚወለዱ ህጻናትን መግደል በጽናት ሊወገዝ ይገባል፡፡ ስለግብረ ስጋ ግንኙነት ባርነት ዓለም አቀፍ ዘመቻዎች አሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለውን በ10፣ በ12፣ በ14፣ እና በ16 ዓመት እድሚያቸው ህጻናት ልጃገረዶች የጠለፋ ጋብቻ ሲፈጸምባቸው ዓለም እየተመለከተ ለምንድን ነው የሚቀበለው? በኢፍትሀዊነት ላይ የሚደረግ ትዕግስት በፍትህ ላይ የሚደረግ የጠለፋ እና የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ነው፡፡
ሜትካፍ የትምህርት ቤት ልጃገረድ ገዳይ የሚለውን ፊልም እ፣ኤ.አ በ1999 በኢትዮጵያ አዘጋጅታለች፣ ሆኖም ግን የጠለፋ ጋብቻ ያለምንም የወንጀል ተጠያቂነት በአሁኑ ጊዜም ቢሆን በከፍተኛ ደረጃ በመስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡ የጠለፋ ጋብቻ እና የህጻናት ሙሽራነት ችግሮች ዘለቄታዊ እና ትክክለኛ መፍትሄ የሚመነጨው ከመንግስት አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ትክክለኛው መፍትሄ የሚገኘው ህብረተሰቡን የሲቪክ ትምህርት እና የተግባር ተሞክሮን ከሚያስተምሩ ከሲቪል ማህበረሰብ ተቋማት ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ቀጣዩ የጠለፋ ጋብቻ የመስቀል ጦርነት ርዕሴ ይሆናል፡፡
“በጠለፋ ጋብቻ ላይ የወጣው ህግ ተፈጻሚነት የሚኖረው ከሆነ ወንዶች ይለወጣሉ ብዬአስባለሁ፡፡ ህጉ የላላ ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ ግን ወንዶች ለዘላለሙከቁጥጥር ውጭይሆናሉ፡፡“ መስታወት በቀለ (የአበራሽ በቀለ ታላቅ እህት)
በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እንዲቆሙ የበኩልዎን እገዛ ያድርጉ!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
ጥቅምት 21 ቀን 2007 ዓ.ም