Wednesday, 23 March 2016 12:24
በይርጋ አበበ
የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጄንሲ ከአፋር እና ሶማሌ ክልል ውጭ እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ያላካተተ “የኢትዮጵያ የገጠር አቅርቦትና አገልግሎት አትላስ 2014” (Ethiopia’s Rural Facility and Services Atlas 2014” በሚል ያዘጋጀውን አትላስ (በርካታ ካርታዎችን የያዘ መጽሀፍ) ይፋ ያደረገው ባሳለፍነው ሰኞ መጋቢት 12 ቀን 2008 ዓ.ም ነበር።
አትላሱ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና ለሚመለከታቸው አካላት ይፋ በተደረገበት ወቅት የኤጄንሲው አመራሮችና የስራ ኃላፊዎች አትላሱን ለማዘጋጀት የዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል። አትላሱን ለማዘጋጀት ምን ያህል ገንዘብ እንደወሰደ ግን አልገለጹም። የሁሉም ክልል ፋይናንስ ቢሮዎች ተጨማሪ ድጋፍ ያደረጉ ባለድርሻዎች መሆናቸውም ጨምረው ገልፀዋል።
ስለ አትላሱ ማብራሪያ የሰጡት የኤጄንሲው ካርቶግራፍ ኤክስፐርቱ አቶ ሲሳይ ጉታ “ሁሉም ዳታዎች የተሰበሰቡት ከሁሉም ክልሎች ፋይናንስ ቢሮዎች ነው” ሲሉ ተናግረዋል። አያይዘውም “ሁሉም ዳታዎች የተሰበሰቡት በ2014 ነው” ብለዋል። በዚህም መሰረት አሁን ካለው እውነታ ጋር በመጠኑም ቢሆን አኃዛዊ ለውጦች ሊኖሩ እንደሚችሉ አሳስበዋል። አትላስ የተዘጋጀላቸው ክልሎች ዳታው የተሰበሰበው እንደ አውሮፓዊያን የዘመን ስሌት ከግንቦት 19 እስከ ሰኔ 17 ቀን 2014 ባሉት ጊዜያት መሆኑ ታውቋል።
የአትላሱ ጠቀሜታ እና የትኩረት ማዕከላት
ባለፈው ሰኞ ይፋ የሆነው የኢትዮጵያ የገጠር አቅርቦትና አገልግሎት አትላስ የተዘጋጀው በ2011 ተዘጋጅቶ የነበረውን አሻሽለው መሆኑን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል። ይህ አትላስም በሶስት መሰረታዊ አገልግሎቶች ላይ ማዕከል ያደረገ ሲሆን፤ እነሱም “ትምህርት፣ ጤና እና ውሃ” ናቸው።
የአትላሱ ቀዳሚ ዓላማ በወረዳ ደረጃ መረጃዎችን በትክክለኛ መንገድ ማድረስ ሲሆን በተለይም መሰረታዊ የሆኑ አቅርቦችን እና አገልግሎቶችን ተደራሽ የሚሆኑበትን መረጃ ማቅረብ መሆኑን የአትላሱ ሪፖርት ገልጿል። ለትምህርት ዘርፍ ማህበረሰብ የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን የገለጸው የአትላሱ መግለጫ “ለተማሪዎችና ለተመራማሪዎች ትክክለኛውን መረጃ በማቅረብ ለገጠሩ ማህበረሰብ አገልግሎቶችን እንዲያቀርቡ የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው” ይላል። ከዚህ በተጨማሪም ለአዳዲስ ተመራማሪዎች መገኘትና የፈጠራ ሰዎችን ለማፍራት ጥሩ የመወያያ እና የመከራከሪያ ሰነድ ሆኖ እንደሚያገለግልም ተነግሯል።
የአትላሱ መዘጋጀት የተፈጥሮ ሀብት ክምችቶችን በፍትሃዊነት ከመጠቀም ጀምሮ የህዝብን አሰፋፈር በሚገባ ለማወቅም የሚያስችል ጠቀሜታ ይሰጣል ተብሏል። በዚህም መሰረት በተለይ የአስፈጻሚ አካላት እና ፖሊሲ አውጭዎች እንዲሁም የፖሊሲ አማካሪዎች ይህንን አትላስ ተመርኩዘው ቀጣይ ስራዎቻቸውን መስራት እንደሚያስችላቸው ተነግሯል።
አትላሱን ተመርኩዞ ከክልል ተወካዮች የተነሱ ጥያቄዎች
“በአሁኑ ወቅት የኦሮሚያ ክልል በ18 ዞኖች የተዋቀረ ቢሆንም ይህ አትላስ ግን ክልሉ በ17 ዞኖች መዋቀሩን በመግለጽ ስህተት ሰርቷል። ከዚህ በተጨማሪም አሁን በተግባር የሌሉ ነገር ግን በ1997 ዓ.ም በነበረው የዞኖች አወቃቀር (ጂማ ልዩ ዞን፣ ቡራዩ ልዩ ዞን እና አዳማ ልዩ ዞን) በዚህ አትላስ መካተቱ ተገቢ አይደለም። ይህንን በዝግጅት ወቅት ተናግረን የነበረ ቢሆንም ሳይስተካከል ለህትመት በቅቷል።” ለምን? ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፋይናንስና ኢኮኖሚ ቢሮ ተወካዩ አቶ ዳኜ ለማ ጠይቀዋል።
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጡት አቶ ደሳለኝ ታደሰ በበኩላቸው “በእኛ ክልል አምስት ዞኖች መኖራቸውን አትላሱ መግለጹ ስህተት ነው። ምክንያቱም ክልላችን በሶስት ዞኖችና አንድ ልዩ ዞን ብቻ ነው ያለው። እንዲሁም በመተከል ዞን ስር የሚገኘውን ፓዊ ወረዳን “ፓዊ ልዩ ወረዳ” ተብሎ መቅረቡም ትክክል አይደለም። ፓዊ ወረዳ ተብሎ ሊስተካከል ይገባል። ሲርባበይ ወረዳ ስሙ ተቀይሮ ሰላል ወረዳ ከተባለ አራት ዓመታት ያለፉት ቢሆንም በዚህ አትላስ ላይ ግን ሲርባበይ ወረዳ ተብሎ መጠቀሱ ተገቢ አይደለም በዝግጅቱ ወቅትም ተናግረን የነበረ ቢሆንም አልተስተካከለም። ከዚህ በተጨማሪም የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ተከትሎ ከሰላል ወረዳ ስድስት ቀበሌዎች ውሃው ስለሚያርፍባቸው ነዋሪዎቹ ወደ ሌላ አካባቢ ሂደው እንዲሰፍሩ የተደረገ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ግን አትላሱን ሲያዘጋጅ ይህንን ሁሉ ታሳቢ ሳያደርግ አዘጋጅል። ይህ ሊስተካከል ይገባል” ሲሉ ጠይቀዋል።
ከደቡብ ክልል የተወከሉት በበኩላቸው ደግሞ “በአንዳንድ ዞኖች እና ወረዳዎች የግዛት ወሰን ላይ ጥያቄ ይነሳል። ይህንን ጥያቄ መመለስ ያለበት የኢትዮጵያ ካርታ ስራሮች ኤጄንሲ ቢሆንም ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጄንሲ አትላሱን ሲያዘጋጅ መረጃዎችን ደበላልቋል። ይህ እንዴት ሊስተካከል ይችላል” ሲሉ ጠይቀዋል።
ለእነዚህ ጥያቄዎች የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ዋና ዳይሬክተር ቢራቱ ይገዙ እና ካቶግራፍ ኤክስፐርቱ አቶ ሲሳይ ጉታ መልስ ሰጥተውባቸዋል። አቶ ቢራቱ ከድንበር ጋር በተያያየ ለተነሱ ጥያቄዎች ወደ ፊት ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጄንሲ ከክልሎች ጋር በጋራ በመሆን ችግሮቹን ለመቅረፍ እንደሚሰራ እና ይህ አትላስም መስተካከል እንደሚችል ተናግረዋል።
አቶ ቢራቱ “ድሮ የነበሩ ቀበሌዎችና ወረዳዎች ቁጥራቸው በአሁኑ ሰዓት በከፍተኛ ፍጥነት ጨምሯል። ይህ ሲሆን ደግሞ አንዱ ከሁለት ይከፈላል ወይም የአንደኛው አንድ ክፍል ለሌላኛው ወረዳ ወይም ቀበሌ ጋር ተካልሏል። ይህ ደግም እኛ ስራውን በምንሰራበት ወቅት ፈታኝ እንደሚሆን ግልጽ ነው። እያንዳንዱን ቦታ በአካል ተገኝተን ካላየን በጣም ፈታኝ ሆኖብን ነበር። ሁለተኛ ደግሞ አንድ አዲስ ወረዳ ሲመሰረት ከሌሎች የተለያዩ ወረዳዎች ቀበሌዎችን በማሰባሰብ በመሆኑ አሁንም ለእኛ ስራ ፈታኝ ሆኖ አግኝተነዋል። ይህ በመሆኑ በየጊዜው ከክልል መስተዳደሮች ሳይቀር ጥያቄ ቢቀርብልንም ለቆጠራ ስራ በምንሰራበት ጊዜ ሊስተካከል የሚችል ባለመሆኑ ሳናስተካክለው ቀርተናል” ብለዋል። ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተነሳው የፓዊ ልዩ ወረዳ አለመሆን ጥያቄ ምክንያቱ የ2007 ዓ.ም የህዝብና ቤት ቆጠራ ሲሰራ ፓዊ ልዩ ወረዳ ስለነበረ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ቢራቱ አያይዘውም ስራው የተሰራው በ2007 እ.ኤ.አ ተካሂዶ በነበረው የህዝና ቤት ቆጠራ ዳታ ላይ በመነሳት መሆኑን ተናግረው አሁን የተነሱት ጥያቄዎች (ከክልል ተወካዮች የቀረቡት የስያሜ እና የአከላለል ጥያቄ) ሊነሱ የቻሉት ማዕከላዊው ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ለአትላሱ ሥራ የቆየ ዳታ መጠቀሙ እንደሆነ ገልጸዋል። “ግብአቶችን ተቀብለን ችግር ያለባቸውን ቦታዎች እንደገና ማየት እንችላለን። ዌብሳይታችን ላይ ስናስቀምጥም የተስተካከለውን መረጃ ይሆናል” ሲሉ ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል።
አቶ ሲሳይ ጉታ በበኩላቸው “ይህ አትላስ የተሰራው ከአስር ዓመት በፊት በተሰበሰበ ዳታ እንጂ አዲስ በ2014 የተሰራ ስላልሆነ ማፑ ላይ የሚታየው እና መሬት ላይ ያለው እንደሚለያይ ግልጽ ነው። ነገር ግን እጃችን ላይ ባለው መረጃ እንሰራና ለእናንተ (ለክልሎች) ጥሬ ዳታዎችን እንሰጣችሁና የራሳችሁን አትላስ መስራት ትችላላችሁ” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል። አቶ ሲሳይ አክለውም “ከዚህ በተጨማሪ ኤዲቲንግ ላይ ክፍተት አለ የተባለው ችግሩን አይተነዋል አስተካክለን ዌብሳይቱ ላይ እንጭነዋለን” ብለዋል።
ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና
ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት የተነሱ ጥያቄዎች
ከክልል ተወካዮች በተጨማሪ ሌሎች በመድረኩ የተገኙ አስተያየት ሰጭዎችና ጥያቄ አቅርበው ነበር። መረጃዎቻችሁን በማዘመን (update በማድረግ) በኩል ለምን አስር ዓመት ትጠብቃላችሁ በየጊዜው ለምን አይስተካከልም? የሚል ጥያቄ ከብሔራዊ መረጃ ደህንነት ኤጄንሲ (INSA) የቀረበ ጥያቄ ነበር። ለዚህ ጥያቄ መልስ የሰጡት አቶ ሲሳይ ጉታ “የቆጠራ ስራ እጅግ በጣም ከፍተኛ ገንዘብ መጠን ያለው ገንዘብ ይጠይቃል። በየሁለት ዓመቱ ወይም በየዓመቱ እና በየአምስት ዓመቱ ቆጠራ ለማካሄድ የአገሪቱ ኢኮኖሚ አቅም የሚፈቅድ አይደለም። የመንግስትን አቅም የሚፈታተን ነው” ብለዋል።
የዚህ አትላስ ስያሜ የገጠር አገልቅሎት ሰጪ የተባለው ለምንድን ነው ከተሞችን ለምን አላካተተም? በዚህ አትላስ ላይ የአዲስ አበባ አልተሰራም ምክንያቱ ምንድን ነው? ሲል ከዓለም ባንክ ተወካይ የቀረበውን ጥያቄ ሲመልሱም “የከተሞችን ሙሉ በሙሉ አላከተትንም። በዚህ አትላስ መረጃዎችን የሰበሰብነና ለማካተት የሞከርነው በከተማ አስተዳደር ደረጃና በክልል ደረጃ ከተዋቀሩት አነስተኛ መጠን ያላቸውን ሀረሪንና ድሬዳዋ ከተማን ነው” ብለዋል አቶ ሲሳይ፡፡ አያይዘውም “አዲስ አበባ ለምን አልተካተተም ለተባለው አዲስ አበባ በእኛ (በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ) ባይሰራም አዲስ አበባ አስተዳደር በ2012 አሰርቶታል። ለዚህ ነው በእኛ ተሰርቶ ያልቀረበው ብለዋል።
በአማራ ክልል ሶስት ልዩ ዞኖች (ኦሮሞ ብሔረሰብ፣ ዋግህምራ ብሔረሰብና አዊ ብሔረሰብ ዞኖች) እንዳሉ የሚታወቅ ቢሆንም በዚህ አትላስ ላይ ግን “የአርጎባ ብሔረሰብ ዞን” ብላችሁ ከልላችኋል። ድንበር የማካለል ስልጣን ኣላችሁ ወይ? የሚል ጥያቄ ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያ ቀርቦ ነበር። ለዚህ ጥያቄም መልስ የሰጡት አቶ ሲሳይ “ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጄንሲ ድንበር የማካለል ስልጣን የለውም። ይህ ስልጣን ለብሔራዊ ካርታ ስራ ኤጄንሲ ነው የተሰጠው። እኛ ግን ህዝብና ቤት ቆጠራ ለማካሄድ የቆጠራ ካርታ ስራ ለመስራት ስልጣን አለን። ይህን ስልጣናችንን ተጠቅመን ህዝብና ቤት ለመቁጠር የሚያስችል ካርታ እንሰራለን እንጂ ድንበር ያካለለ ስራ አልሰራንም” ብለዋል።
ስንደቅ