Wednesday, 23 March 2016 12:02
ከኤል ኒኖ የአየር ለውጥ ጋር በተያያዘ የተከሰተው ድርቅ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። የድርቁ ሁኔታ በዜጎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ መንግስት አሁንም ቢሆን የድረሱልኝ ጥሪ በማቅረብ ላይ ነው። 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ወይንም ከጠቅላላው ህዝብ ውስጥ አንድ አስረኛ የሚሆነው ህዝብ በከፋ የረሃብ አደጋ ውስጥ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት የተረጂው ቁጥር አሁን ባለበት ደረጃ ባልጨመረበት ሁኔታ ለምግብ እህል አቅርቦት እስከ 380 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ካደረገ በኋላ ጉዳዩ ከአቅሙ በላይ እየሆነ መሄዱን ተከትሎ የድረሱልኝ ጥሪ አሰምቷል።መንግስት ቀደም ብሎ በ2007 አጋማሽ ባስታወቀው መረጃ መሰረት በድርቅ ተጠቅተው የእለት እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብለው የነበሩት የዜጎች ቁጥር 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ነበር። ይህ አሃዝ በዚያው ዓመት ክረምት ወር ላይ ወደ 8 ነጥብ 9 ሚሊዮን አሻቅቧል። ቁጥሩ እየጨመረ ሄዶ በአሁኑ ሰዓት ወደ 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ደርሷል።
የዝናቡ ሁኔታ በቀጣዩ ክረምት የማይሰተካከል ከሆነ የተረጂው ቁጥር ከዚህም በላይ ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ መንግስት ከሌሎች ረድኤት ድርጅቶች ጋር በመተባበር በ2016 ያለውን አጠቃላይ የተረጂዎች ሁኔታ አሃዝ የሚሰራ ሲሆን በአዲሱ ጥናት መሰረት በሁሉም አቅጣጫ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር አሁን ካለውም በላይ ይጨምራል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን የሰሞኑ የዩኤስኤድ መረጃ ያመለክታል። ለምሳሌ የድርቅ ተጎጂ የሆኑትን አርሶ አደሮችን ለመጪው የዘር ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ የዘር እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብለው የተያዙት የአርሶ አደሮች ቁጥር 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን ሆኖም በቀጣይ ይህ ቁጥር ወደ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ያድጋል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑን የኤጀንሲው መረጃ ጨምሮ ያመለክታል። በዚህ ዙሪያ በግንባር ቀደምትነት እገዛ ከሚያደርጉት የረድኤት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID)፤ ከሰሞኑ መግለጫ ሰጥቷል።
ባለፈው ቅዳሜ በማርዮት ሆቴል ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት በኤጀንሲው የአሜሪካ የውጭ አደጋ ጉዳዮች ቢሮ ዋና ዳይሬክተር ጀርሚ ኮኒካንዲክ ናቸው። በእለቱ በተለቀቀው መረጃ መሰረት በአሁኑ ሰዓት የእለት እርዳታ የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር 10 ነጥብ 2 ሚሊዮን ደርሷል። ንፁህ ውሃ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር 5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሲሆን ለድርቅ የተጋለጡ ዜጎችን ለመርዳት በያዝነው የፈረንጆች አመት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል። እስካሁን ባለው ሁኔታ መንግስት ከካዝናው 381 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያደረገ መሆኑን የአሜሪካ ኢምባሲ መግለጫ ያመለክታል። ይኸው መግለጫ የኤልኒኖ ተፅዕኖ፤ በ2016 ጭምር የሚቀጥል መሆኑን አስታውቆ፤ ተፅዕኖውም ባልተስተካከለ ዝናብና በጎርፍ ጭምር የሚገለፅ መሆኑን አስታውቋል።
አንዳንድ ጊዜ የእርዳታ እህል መዘግየት እንደዚሁም ያልተሟላ እርዳታ አሰጣጥ ሁኔታ መኖሩም የተመለከተ ሲሆን በድርቅ በተጎዱት አካባቢዎች በቂ ውሃ አለመኖርና የንፅህና አጠባበቁም ጉዳይ በጣም አናሳ በመሆኑ የተላላፊ በሽታ የመከሰት እድሉ ሰፊ መሆኑን የዩኤስኤይድ መግለጫ ጨምሮ ያመለክታል። ይሄንኑ ችግር ለመከላከልም በድርቅ በተጠቁ 5 መቶ ወረዳዎች 25 ሚሊዮን የሚሆኑ ህፃናትን የፀረ ሚዝል ክትባትን ለመከተብ እቅድ የተያዘ መሆኑ ታውቋል። በኢትዮጵያ የተረጂው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
ያም ሆኖ መጪው የዝናብ ወቅት ተስተካክሎ ለድርቅ የተጋለጡት አርሶ አደሮችና ከፊል አርሶ አደሮች ወደ ግብርና ስራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ ከተፈጠረ በሚል ዩኤስኤይድ እና ሌሎች ተባባሪ የረድኤት ድርጅቶች ለ360 ሺህ ተረጂዎች የሚውል የዘር እርዳታ ማቅረባቸውን የዩኤስአይድ ሰሞኑን የሰጠው መረጃ ጨምሮ ያመለክታል።ይህም በአሁኑ ሰዓት ያስፈልጋል ተብሎ የሚጠበቀውን 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ከፍ የሚያደርገው ይሆናል። የአሜሪካ መንግስት በዩኤስኤይድ በኩል ከተለያዩ መንግስታዊ ካልሆኑ የረድኤት ድርጅቶችና የአለም ምግብ ፕሮግራም ጋር በመተባበር 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ተረጂዎችን በማገዝ ላይ መሆኑን በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ መረጃ ያመለክታል። በአሁኑ ሰዓት ዩኤስ ኤይድ ዘርፈ ብዙ ድጋፍ እያደረገ እያደረገ ሲሆን የኤጀንሲው እገዛ ቀጥተኛ የምግብ እህል እርዳታን ለተረጂዎች ማቅረብ፣ በምግብ የተጎዱ ሰዎችን የህክምና አገልግሎትን መስጠትና የእርዳታ አሰጣጡን ከሌሎች የረድኤት ድርጅቶች ጋር ማቀናጀት መሆኑን የራሱ የኤጀንሲው መረጃ ያመለክታል።
የዩኤስኤይድ መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ የድርቁ ሁኔታ የበለጠ ከከፋባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደሮች የሚገኙበት አፋር ክልል ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በክልሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተረጂዎች የሚገኙ መሆኑ ታውቋል። በአካባቢውም ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ እንስሳትም የመኖ እጥረት ገጥሟቸዋል። መረጃው እንደሚያመለክተው ከሆነ በክልሉ የተከሰተው ድርቅ በእንስሳቱ ላይ የሞት አደጋን ማስከተል ጀምሯል። እስከአሁን ድረስም በክልሉ 105 ሺህ የቀንድ ከብቶች፣ ከ440 ሺህ በላይ በጎችና ፍየሎች፣ ወደ 15 ሺህ የሚጠጉ ግመሎች 4 ሺህ 5 መቶ የሚሆኑ አህዮች ሞተዋል። የድርቁን መከሰት ተከትሎ በክልሉ የእህል ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ የጨመረ ሲሆን የከብቶች ዋጋ በአንፃሩ ክፉና ያሽቆለቆለ መሆኑን ይኸው መረጃ ያመለክታል። በአፋር ያለውን የከፋ የድርቅ ሁኔታ ለመቋቋም ዩኤስአይድን ጨምሮ የተባበሩት መንግስታት የምግብና የእርሻ ደርጅት (FAO) እና ኢንተርናሽናል ሬስኪው ኮሚቴ (IRC) ሌሎች የረድኤት ድርጅቶች በመረባረብ ላይ ናቸው።
መንግስት በተለየዩ አጋጣሚዎች ችግሩ እየተባባሰ መሆኑን በተደጋጋሚ ቢገለፅም የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ምላሽ ግን የተፈለገውን ያህል አለመሆኑ እየተነገረ ነው። ለለጋሽ ድርጅቶችና በኢትዮጵያ መንግስት በኩል እየተደረገላቸው ላለው ጥሪ እየሰጡት ያለው ምላሽ የተቀዛቀዘ መሆኑን በኢትዮጵያ በኩል በተደጋጋሚ ሲገለፅ ቆይቷል። የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ባገኟቸው አጋጣሚዎች ሁሉ የችግሩ አድማስ እየሰፋ መሆኑን በመግለፅ ድርቁ ከቁጥጥር ውጪ ከመሆኑ በፊት አለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲረባረብ ጥሪ በማቅረብ ላይ ናቸው።
ሌላው ከዚሁ ጋር ተያይዞ እየተነሳ ያለው ስጋት ድርቁ አጠቃላይ የኢኮኖሚውን እንቅስቃሴ ሊጎዳው ይችላል የሚለው ጉዳይ ነው። ሀገሪቱ የግብርና ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ መውረዱ የማይታበል ሀቅ ነው። በካሽ ቢተመኑ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያወጡ እንስሳት በድርቅ በመሞት ላይ ናቸው። መንግስት አብዛኛውን ትኩረቱና ርብርቡን ድርቁን በመከላከል ላይ ማሳረፍ ግድ ሆኖበታል። ቀደም ሲል በውጭ ምንዛሪ ከውጪ እየተገዛ ለከተማ ነዋሪዎች ሲቀርብ ከነበረው የድጎማ ስንዴ በተጨማሪ ለድርቅ ለተጋለጡ ወገኖች የእለት ቀለብን ለማቅረብ መንግስት ተጨማሪ እህልን በግዢ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ተገዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ከኦል አፍሪካን ዶት ኮም ጋር ባደረጉት ቆይታ በድርቁ ወቅታዊ ሁኔታ ላይም የተወሰነ ማብራሪያን ሰጥተው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ማብራሪያቸው በድርቅ የተጠቁ ወገኖች በረሃብ እንዳይጠቁ መንግስት የተቻለውን ሁሉ እያደረገ መሆኑን አመልክተው፤ ይሁንና መንግስት እርዳታ የማቅረቡ ሂደት የሀገሪቱን አድገት በማይገታ መልኩ እንዲሆን የማጣጣም ስራን አብሮ እየሰራ የሚሄድ መሆኑን ጨምረው አመልክተዋል።
ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑ ዜጎችን የመርዳቱ ስራ ኢኮኖሚውን በማይጎዳ መልኩ እንዲከናወን ለማድረግ ግን የእርዳታ ሰጪዎች ለጋስነት የሚያስፈልግ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተው፤ በዚህ ረገድ ያለው ምላሽ ግን የተቀዛቀዘ መሆኑን አልሸሸጉም። ያም ሆኖ በእርዳታ ሰጪዎች ያለው መቀዛቀዝ የሚቀጥል ከሆነ ሊከተል የሚችለውን ከባድ አደጋ ለመከላከል በመንግስት በበኩል የልማት በጀቱን ሳይቀር ወደ እርዳታ ለማዞር የሚገደድ መሆኑን ጨምረው አመልክተዋል። ሚስተር ጀርሚ ኮኒንዲክ ድርቁ በሃምሳ አመት ታሪክ ውስጥ ያልታየ መሆኑን አመልክተው በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ከበጀቱ ጭምር በመቀነስ ያደረገውን እገዘና ችግሩንም ለመቋቋም ያሳየውንም ቁርጠኝነት አድቀዋል። ችግሩ ሰፊ ቢሆንም ዩኤስአይድ ካለው የካበተ ልምድ አኳያ በሁሉም ዘርፍ የሚታዩትን ችግሮች ለመቋቋም የሚሰራ መሆኑን ጨምረው አመልክተዋል።
ስንደቅ