Wednesday, 23 March 2016 12:19

  • በ 
  • የአዲስ አበባ ከተማ አየር ግለት አዘል ሆኗል። ይሞቃል ሳይሆን አናት ይበሳል ይላሉ በርካታ ነዋሪዎቿ። የአየሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሞቀ መምጣት ከአየር ጠባይ ለውጥ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። የአየር ጠባይ ለውጥ አንዱ መገለጫ የከባቢ አየር መሞቅ ብሎም ለኑሮ እጅግ አስቸጋሪ መሆን ነው። የአየሩ መሞቅ የሰዎችን ጤና ከመፈታተኑና ምቾትን ከመንሳቱ በተጨማሪም ቀስ በቀስ የውሃ ትነትንም በማሳደግ የመጠጥ ውሃን ችግር ያስከትላል። አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታም በአዲስ አበባ ከተማ እየሆነ ያለው ይኸው ነው።

የአየር ጠባይ ለውጥ ዓለም አቀፍ ችግር እንደመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚመጣ ቀውስ በቀጥታ ተጎጂ መሆናችን እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃም የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የከተሞች መስፋፋትን ተከትሎ የተሽከርካሪዎች፣ የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎች መጨመር እንዲሁም የኢንደስትሪ ብክለቶች መኖር የራሳቸው የላቀ ድርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ የአካባቢ ደንና የአየር ጠባይ ለውጥ ሚኒስቴር የከተሞችን ብክለት አስቀድሞ ለመታደግ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ (Road Map) ረቂቅ ሕግ እያዘጋጀ ሲሆን፤ በዚህ ሕግ ላይ ባለድርሻ አካላት ሰሞኑን በአዲስ አበባ ሐርመኒ ሆቴል ተገናኝተው ተወያይተዋል። ስለፍኖተ ካርታው ምንነትና አስፈላጊነት ጉዳይ በሚኒስቴሩ የሕግ ተከባሪነት ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ መሐሪ ወንድማገኝን አነጋግረናል።

ጥያቄ፡- የዚህን ዓውደ-ጥናት ዓላማ በአጭሩ ቢገልፁልን?

አቶ መሐሪ፡- የዓውደ-ጥናቱ ዋና ዓላማ፤ የኢኮኖሚ ዕድገትን ተከትሎ የከተሞች መስፋፋት አለ። የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት፣ የተሽከርካሪዎች ቁጥር መበራከት አለ። የሕዝብ ቁጥር በጨመረ ቁጥር የደረቅ ቆሻሻ ይጨምራል። ይህ ተደማምሮ በከተሞች አካባቢ የአየር ብክለትን ያስከትላል። ስለዚህ ይህ የአየር ብክለት የከፋ ደረጃ ደርሶ ከዚያ በኋላ ከምንንቀሳቀስ ከወዲሁ የአየር ብክለትን ለመቀነስ የሚያስችለንን ፍኖተ-ካርታ (ሮድ ማፕ) እያዘጋጀን ነው ያለነው።

Ø  ፍኖተ ካርታው ትኩረቱ ምንድን ነው?

·  ፍኖተ ካርታው የሚያወራው በኢትዮጵያ የትኞቹ ከተሞች ናቸው፣ ለአየር ብክለት ሊጋለጡ የሚችሉት። የትኞቹ የኅብረተሰብ ክፍሎች ናቸው። ችግሩን ለማስቀረት ምን ማድረግ አለብን የሚለውን ለማወቅ ነው። ከዚህ ዓውደ ጥናት የምንጠብቀው በረቂቅ ደረጃ ያለው ሕግ ለማዳበር ነው። ይህ ፍኖተ ካርታ ወደ ተግባር ሲሸጋገር የባለድርሻ አካላት በትግበራው ላይ ምን ድርሻ አላቸው። ድርሻቸው ከታወቀ በኋላ ይህንን ሊያስተባብር የሚችል አንድ ኮሚቴ ለማቋቋም ነው። ከአየር ብክለት ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችሉ ችግሮችን መቅረፍ ነው።

Ø  የፍኖተ ካርታ አለመኖር ያስከተለው ጉዳት ምንድን ነው?

·   የፍኖተ ካርታ አለመኖር ሊያስከትል የሚችለው ቅርፅ የያዘና የተቀናጀ የችግር አፈታት ዘዴ እንዳይኖር ያደርጋል። የችግሩ ምንጮቻችን የትኞቹ ናቸው፣ ምንጮቹን ከለየን ደግሞ የጎላ ድርሻ ያለው የትኛው ነው? ለዚህ የሚጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች የትኞቹ ናቸው? የሚለውን በውል ለመለየት ስለሚጠቅም ነው። የፍኖተ ካርታ መኖር የተበታተነ ሥራ እንዳይሠራ ይረዳል። የአየር ብክለት ችግር ሊከላከል የሚችል ትክክለኛ መሣሪያ ካላስቀመጥን ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑ የማይቀር ነው። የከተሞች መስፋፋትም የማይቀር በመሆኑ ከወዲሁ መዘጋጀቱ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው።

Ø  እስካሁን ያደረጋችሁት ጥናት ምንን ያሳያል?

· በእኛ መ/ቤት የተጠና ጥናት የለም፣ በዩኒቨርሲቲዎች ግን አለ። አሁን ካለንበት የዕድገት ደረጃ፣ የከተሞች መስፋፋት፣ የተሽከርካሪዎች መጨመርን ስናነፃፅረው ከበድ ያለ የአየር ንብረት ብክለት ሊከሰት ይችላል የሚል ድምዳሜ ስላለን ነው።

Ø  ፍኖተ ካርታው ለከተሞች ብቻ ለምን?

·    ሁሉም በአንድ ጊዜ ሲሠራ ዝብርቅርቁ ስለሚወጣ እንጂ የገጠሩን ቢካተት ችግር የለውም። ግን በከተሞች አካባቢ ሰዎች ሰብሰብ ብለው ስለሚኖሩ፣ የብክለቱ ተቀባይ አየር ከተሞች አካባቢ ስላለ ነው ትኩረት ያስፈለገው። በዋናነት ከአየር ብክለት ጋር ከወሰድን የኢትዮጵያ ችግር የቤት ውስጥ የአየር ብክለት ችግር ነው፣ ምግብ ስናዘጋጅ፣ ቡናና ሻይ ስናፈላ ወዘተ… አለ። ይሄ ደግሞ ችግሩ ተከስቶ የከፋ ደረጃ ከመድረሡ በፊት ብንከላከል በሚል ነው።

Ø  ፍኖተ ካርታው መቼ ወደ ሥራ ይገባል?

·  በያዝነው ሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሸን ዕቅድ ተይዟል። ይኸኛው ዓመት በዝግጅት ምዕራፍ ብንወስደው በቀጣዩ ዓመት ግን ወደ ተግባር ይገባል የሚል ሃሳብ አለን።

Ø  እስካሁን ባለው ጥናት በከተሞች አካባቢ ከፍተኛ ብክለት የሚያሳዩት ተሽከርካሪዎች ናቸው፣ ፋብሪካዎች ናቸው ወይስ?

·    ብክለቱ ከብዙ ነገሮች ጋር ይገናኛል፣ ከተሽከርካሪዎች ጋር፣ ከደረቅ ቆሻሻ ጋር ይገናኛል። የብዙ ችግሮች ድምር ውጤት ነው።n

Leave a Reply