Wednesday, 23 March 2016 12:05
በውጭ ሀገር በሚኖሩ 200 ዲያስፖራዎች መነሻ የተመሰረተው “ኩራት በኢትዮጵያ” አግሮ-ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ አ/ማ ከመስራችነት መብት ጋር በተያያዘ ውዝግብ አስነስቷል። የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ዋና መስርያቤት 11 ሰዎችን በመስራችነት አውቃለሁ ሲል የአክሲዮኑ የቦርድ ሰብሳቢ 200 ዲያስፖራዎች የመስራችነት መብት በሕግ እንደተጠበቀ ነው ብሏል።
አንዳንድ የአክስዮን መሥራቾች መሆናቸውን ለሰንደቅ ጋዜጣ የተናገሩ ዲያስፖራዎች እንደሚሉት፤ በማኅበራዊ ድረ-ገጽ ግንኙነት ፈጥረን 200 ያህል ሰዎች ወደ አክሲዮን ምሥረታ ከገባን በኋላ ግን የአክስዮኑ መስራቾች 11 ሰዎች ብቻ ሆነው አግኝተናቸዋል ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ዋና መስርያቤት የሰነዶች ማረጋገጥ እና መመዝገብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ምናሴ ጌታሁን እንደገለጹት፣ ኩራት በኢትዮጵያ አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ አ/ማ የተመሰረተው በ 11 ሰዎች ሲሆን ከ 11 ባለ አክስዮኖች መካከል ዘጠኙ ራሳቸው ሲፈርሙ ሁለቱ በውክልና የተፈረሙ ናቸው” ብለዋል።
አያይዘውም ስለአክሲዮን ማሕበሩ ካፒታል ሲያብራሩ፣ “በ22 ሚሊየን ብር ካፒታል የተቋቋመ ነው። ከዚህ ውስጥ 5 ሚልየን 500 ሺህ ብር የተከፈለ ሲሆን ያልተከፈለው ካፒታል 16 ሚልየን 500 ሺ ብር ነው። የአንዱ አክሲዮን ዋጋ 5,000.00 ብር መሆኑን ገልጸዋል።
የኩራት በኢትዮጵያ አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ አ/ ማ በቦርድ አባልነት እንዲያስተዳድሩ የተመረጡት 11 አባለት በአክሲዮን ውስጥ ያላቸው ድርሻ 400 እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል። እስካሁን ባለው ሂደት ከቦርድ አባላት ውጪ በመስራችነት የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ዋና መስርያቤት የተመዘገበ የለም።
የኩራት በኢትዮጵያ አግሮ ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ አ/ማ አክሲዮን የቦርድ ሰብሳቢን አቶ አማኑኤል አለማየሁ ስለምስረተው ጠይቀናቸው በሰጡን ምላሽ፣ “ማሕበሩ የተመሰረተው በማሕበራዊ ድረገጽ በፓልቶክ በተደረገ ውይይት ነው። በቁጥር ሁለት መቶ በሚጠጉ ዲያስፓራ ኢትዮጵያዊን ውይይት ከተደረገ በኋላ ነው የተመሰረተው። ይህን ተከትሎ በውጭ የሚኖሩ ሁሉም ወደ ኢትዮጵያ በአንድ ጊዜ መምጣት ስለማይችሉ ተወካዮቻቸውን መርጠው ላኩ። አዲስ አበባ ከነበርነው ሰዎች ጋር አስራ አንድ ሆነን ተቀናጅተን ሁለት ተልዕኮ ይዘን ወደስራ ገባን። አንዱ ከመንግስት ጋር በጉዳዩ ላይ በመወያየት ተገቢውን ድጋፍ እንዲደረግልን መስራት፣ ሁለተኛው፣ ዲያስፖራው የሚሳተፍበትን የኢንቨስትመንት አክሲዮን ማቋቋም ነበር። አክሲዮኑን በተመለከተ መመስረቻና መተዳደሪያ ደንብ አዘጋጅተን ውልና ማስረጃ ሄደን አክሲዮን አቋቋምን። ምክንያቱም 200 ሰዎች በአንድ ጊዜ ቀርበው ለመፈረም አስቸጋሪ በመሆኑ ነው። ያደረግነውም አክሲዮን በተመዘገበ ካፒታል ካቋቋምን በኋላ ውክልና ለሰጡን ሰዎች በፓልቶክ የተሰራውን አሳወቅን። አክሲዮን እንዲገዙ፣ የገዘዙት አክሲዮን በስማቸው እንደሚዛወር ገለፅን። በተደረሰው ስምምነት ሰው ገንዘብ ማዋጣት ጀመረ። ገንዘቡ በዝግ ቋት ውስጥ መግባት ጀመረ። እስካሁን ድረስም በዝግ ቋት ውስጥ ነው ገንዘቡ ያለው። ሌሎች ወጪዎችን በራሳችን እየሸፈንን ነው ያለነው” ብለዋል።
“በውልና ማስረጃ ያለው ሰነድ 11 ሰዎች ብቻ መስራች መሆናቸውን ያሳያል። ማሕበሩን ለማቋቋም 200 የዲያስፖራ አባላት መወያየታቸውም ይታወቃል። ከዚህ አንፃር የመስራችነት መብትን እንዴት ይመለከቱታል?” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ “ኩባንያው ከተመሰረተ በኋላ የ11 አባላቶች የመስራችነት መብት እንዲነሳ በቃለ ጉባኤ ውሳኔ አሳልፈናል። ምክንያቱም በመመስረቻ ፅሁፍ ላይ የመስራቾች መብት ድንጋጌ ስለተቀመጠ ይህን የማስቀመጥ መብት ያለው በጠቅላላ ጉባኤው ስለሆነ እንዲሁም ሃሳቡ የተጠነሰሰው በ200 ሰዎች በመሆኑ የእነሱ ውሳኔ ስለሚፈለግ እንዲነሳ አድርገናል” ሲሉ አቶ አማኑኤል ገልጸዋል።
“ነገሮችን የበለጠ ግልፅ ለማድረግ 200 ዲያስፖራዎች የመስራችነት መብታቸው በዚህ አክሲዮን የተጠበቀ ነው የሚል ማረጋገጫ ይሰጡናል?” አቶ አማኑኤል በሰጡት ምላሽ “ሁሉም አባላት ተገቢውን ሰነድና ክፍያ ሲያሟሉ የአክሲዮን ድርሻቸው የሚተላለፍላቸው ከነመስራች መብታቸው ተጠብቆ ነው። ይህን የሚገልጽ ተጨማሪ ቃለጉባኤ ተዘጋጅቶ በውልና ማስረጃ ይገኛል። እኛ ፈርመናል። ሌሎችም እየመጡ እየፈረሙ ናቸው። ስለዚህም በዚህ የህግ አግባብ መሰረት አክሲዮኑ እንደሚቀጥል ማንም ጥርጣሬ ውስጥ ሊገባ አይገባም። እስካሁን ባለው ሂደት 89 ሰዎች ተገቢውን ክፍያና ሰነዶችን አሟልተው ተመዝግበዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
ስንደቅ