Wednesday, 23 March 2016 12:10

    የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ረቂቅ አዋጅ

ገመንግስታዊ ጥያቄ አስነሳ

 

የፌዴራል ፖሊስ ኮምሽን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያደርግ የህግ ረቂቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት በትላንትናው ዕለት ከመቅረቡ በተጨማሪም በተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት ሲሰጥ የነበረው የዐቃቤ ሕግ ሥራ ወደአንድ መጠቅለል እንዲያስችል የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ቀርቧል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮምሽን ተጠሪነቱ ለፌዴራልና አርብቶአደር ልማት ሚኒስቴር ሲሆን ይህንን ተጠሪነቱን አዲሱ ረቂቅ ሕግ በመለወጥ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን ይደነግጋል። ለዚህ የተሰጠው ምክንያት በተመለከተ አዋጁን ለማብራራት የተሰራጨው ሰነድ እንዲህ ይላል። «የፌዴራል ፖሊስ በዋናነት የወንጀል ድርጊቶችን እና ወንጀል ተፈጽሞ ሲገኝ የወንጀል ምርመራ በማድረግ ተጠርጣሪን በማስረጃ በመለየት ለሕግ እንዲቀርብ የማድረግ ኃላፊነት ያለበት ተቋም ነው። አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ሲታይ የፌዴራል ፖሊስ ኮምሽን ወንጀል መከላከል፣ የአገር ውስጥ ደህንነት ማስከበር፣ የሽብር ወንጀልን መከላከል እና ሌሎች በርካታ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ኃላፊነትን እየተወጣ በመሆኑ ለአንድ አስፈጻሚ ተቋም ብቻ ተጠሪ አድርጎ መቀጠል የአሠራር ክፍተት እንዳይፈጥር ታስቦ ወደፊት በጥናት ላይ ተመስርቶ እስኪወሰን ድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን ተወስኗል» ይላል።

የህግ ማስከበር ተግባር በዐቃቤ ሕግ ተቋም የሚከናወን ሲሆን ይህ የዐቃቤ ህግነት ሥራ በተለያዩ ተቋማት ተበታትኖ መሰራቱ የሕግ ማስከበር ሥራውን ውጤታማና ቀልጣፋ እንዳይሆን እንዳደረገው የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ይጠቅሳል። በፍትህ ሚኒስቴር፣ በገቢዎችና ጉምሩክ፣ በፌዴራል የስነምግባርና የጸረ ሙስና ኮምሽን፣ በሸማቾችና በክልሎች ተበታትኖ ሲከናወን የቆየውን የዐቃቤ ሕግ ሥራ በመሰብሰብ አንድ ጠንካራ እና ወቅቱ የሚጠይቀውን ተግባር መፈጸም የሚችል ተቋም መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን መንግሥት እንዳመነበት ያትታል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት የፍትህ ሚኒስቴር በህግ የተሰጡት ሥራዎች በአብዛኛው አዲስ ለሚቋቋመው የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሥልጣን ስር መውደቃቸውን በማስታወስ ፍትህ ሚኒስቴር ምን ሊሰራ ነው የሚል ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ፍትህ ሚኒስቴር ቴክኒካሊ ፈርሷል የሚል አስተያየትም ተደምጧል።

በዕለቱ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮምሽንን ማቋቋሚያ አዋጅ ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ኮምሽኑ ተጠሪነቱ ከፌዴራልና አርብቶአደር ልማት ሚኒስቴር በማውጣት አዲስ ወደሚቋቋመው የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መ/ቤት እንዲሆን ደንግጓል። በዚህም ምክንያት የኢፌዲሪ አስፈጻሚ አካላትን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ለም/ቤቱ ቀርቧል።

በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በአንቀጽ 16 ንዑስ አንቀጽ 3 ላይ ዐቃቢያነ ሕግ በሕግ መሠረት የተሰጣቸውን ሥልጣንና ተግባር በማከናወናቸው ምክያት ለሚደርስ ጉዳት የህግ ተጠያቂነት አይኖርባቸውም በሚል የተቀመጠው አንቀጽ አንዳንድ የም/ቤት አባላት ከሕገመንግስቱ ድንጋጌ ጋር ይጋጫል በማለት ጠንከር ያለ አስተያየቶችን አስደምጠዋል።

አዋጆቹ ለሕግ ለፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮምቴ የተመሩ ሲሆን ኮምቴው የሚመለከታቸውን ወገኖች በውይይት በማሳተፍ ካዳበረ በኋላ ለም/ቤቱ አቅርቦ ያስጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የኋላ ታሪክ

በመስከረም ወር 2008 መጨረሻ ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ አዲሱ ካቢኔያቸውን ሲያዋቅሩ የአስፈጻሚ አካላት አደረጃጀት ማሻሻያ የተወካዮች ም/ቤት አፅድቋል። በዚህ ማሻሻያ መሠረት ለጠ/ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆኑ ተቋማት 20 ገደማ ነበሩ። እነዚህም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮምሽን፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን፣ የመንግሥት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት፣ የብሔራዊ ፕላን ኮምሽን፣ የፌዴራል የሥነምግባርና የጸረ ሙስና ኮምሽን፣ የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን፣ የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል፣ የኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት፣ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ የቤተመንግሥት አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ም/ቤት ጽ/ቤት፣ የብሔራዊ አደጋ መከላከል ዝግጁነት ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለስልጣን፣ የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ፣ የመንግሥት ፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፣ የብረታብረት ኢንጂነሪንግ ሲሆን በረቂቅ ደረጃ ያሉት ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ እና የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ናቸው።

ስንደቅ

Leave a Reply